ማን ነው አሸባሪ?!
በበርማ አገር በዛ በሜዳ — ንጹህ ሙስሊም ሲንገላታ
እልፍኝ ጓዳቸው ሲታመስ — በሴት በልጆች እሪታ
ባውሬ ዱላ ሲቀጧቸው — ሲጨርሳቸው በተርታ
ጦሩን ሰብቆ የቡድሃ ቄስ — ደካሞች ላይ ሲበረታ
ያንን ንጹህ የልጆች ደም ጎርፍ አድርጎት በሱ ’ሩምታ
ይሄ ሚስኪን የበርማ ሰው —በሰይጣን ጦር ሲንገላታ
“አንድ አምላኬ” ብሎ ባለ በግፍ በስለት ሲመታ
የናት አንገት ሲቀነጠስ — ልጅ ሲናወጥ ባዘን ዋይታ
“ላንተ ነፍስማ ቁብ የለን” — አለው አለም በዝምታ!
"ማን ሊተክዝ በሙስሊም ሞት ?! ማን በሃዘን ሊንገላታ?!"
“ቀጥልበት !በል አቃጥለው” — ሲል ደገፈው በጸጥታ
ጨቅላ ሤቱ ተዘምቶበት — ሲቆራረጥ በሊባኖስ
ሰይጣናዊው የአይሁድ ዱላ በሌት ቀን ሲመላለስ
ሰማይ ጠቀሱ ህንጻቸው — በላያቸው ሲደረመስ
በጭራቆች አውሮፕላን — አገር ክብራቸው ሲገሰስ
ሚስኪኑ ህዝብ እያማጠ— ሰሜን ምስራቁ ሲታመስ
ካሸባሪ አልተመደበም — ያይሁዶቹ ጦር መትረየስ
የፊሊስጤሙ ተበዳይ — አገር ምድሩ ተወሮበት!
እድሜ ልኩን ግፍ ላይ ሆኖ — አባት ልጁን ሲገሉበት
እንኳን እሱን ሊደግፉ —ምዕራቦቹ አላገጡበት!
አሸባሪ ብለው ፈርደው — በምጡ ላይ ምጥ ጫኑበት
ይህ ነው ወገን የዚህ አለም ትልቅ ጉዱ
ጠልቀው ሲያዩት ተገንዝበው የጭካኔያቸው ሰነዱ
ስቀው በኛ ይፈርዳሉ እኛን በቁም እያረዱ!
[በሙሐመድ ሲራጅ መሐመድ ኑር - ጥር13/2009]
posted by Brother Abu Aisha

