ዘለቄታዊ ደስታ።
ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም "ለፆመኛ ሰው ሁለት ደስታ አለው። ሲያፈጥርና ጌታውን ሲገናኝ።" አሉ።
ለአላህ ትእዛዝ ከምግብ፣ ከመጠጥ ተቆጥቦ መልካምን በመስራት ከመጥፎ በመቆጠብ ቀኑን መፆም እውነትም አፍጥር ላይ
ተርቦ የዋለ ሰው ሲያፈጥር በጣም ይደሰታል። ጌታውን ሲገናኝም እንዲሁ አላህ ትእዛዛቱን ለፈፀሙ ክልከላውን
ለተከለከሉ ባርያዎች ከእሳት ጠብቆ ጀነት አስገብቶ ያስደስታቸዋል።
የአላህ ባርያዎች ሆይ! ታድያ ለምን አላህ ከረመዳን ውጭ የሚታመፀው? ለምን ይሆን ከመስጂድ የሚጠፋው? ለምን ይሆን ቁርአን የሚተወው?
አላህን ከነበር በረመዳን ያመለክነው፣ ከረመዳንም ውጭ አላህ አለ።
ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ሲሞት ከፊል ሰሀባዎች ግራ ተጋቡ። አቡበክር ረድየላሁ አንሁ የሚከተለውን ተናገረ
"ሙሐመድን ሲያመልክ የነበረ በእርግጥ ሙሐመድ ሞቶዋል። አላህን የሚያመልክ አላህ የማይሞተው ህያው ነው።" አለ
ታድያ ከዚህ ከባድ ትምህርት እንወስዳለን የአላህ ባርያዎች።
አላህ እንዲህ ይላል
ጌታህን ሞት እስኪመጣህ ድረስ ተገዛው።
ከእኛ የሚጠበቀው አላህን ሞት እስኪመጣን እንድናመልከው ነው።
በአምልኮ ላይ ለመፅናት ከሚረዱ ዋና ዋና ቁልፎች ውስጥ ሁለቱን ልጥቀስ
1) አላህ እንዲያግዘን መለመን
ዘውትር ሰላት ጨርሰን እንዲህ ስንል እንድንለምነው ነብዩ አስተምረውናል
"አላህ ሆይ! አንተን እንዳወሳ፣ እንዳመሰግንህ፣ ያማረ አምልኮህን እንድፈፅም አግዘኝ።"
አዎን የአላህ እገዛ ከምንም በላይ ያስፈልገናል። ሁሌ እንለምነው
2) መልካም ጓደኛ መምረጥ። የአላህ ባርያዎች ሆይ! ረመዳን ላይ ብዙ መልካም ነገሮች የገሩልንና፣ ከብዙ መጥፎ ነገሮች የተቆጠብነው ከአላህ እርዳታ ቀጥሎ ውሎዋችንና ጓደኞቻቻን ስለተቀየሩ ነው።
የአላህ ባርያዎች ሆይ! አደራ አደራ አደራ መልካም ጓደኛ በመምረጥ ላይ።
አላህ መልካም ጓደኞችን፣ በመልካም የሚያዙ ከመጥፎ የሚከለክሉ ይለግሰን፣ እኛንም ያድርን።
አላህ ስንኖርም በተውሒድ፣ ስንሳሳት በተውበት፣ ስንሞትም በተውሂድ መንገድ ላይ ያድርገን።
መልካም ኢድ።