Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ረመዷን 17 የታላቁ የበድር ዘመቻ ዕለት

ተንቢሃት የዋትሳፕ ግሩፕ
የረመዷን ማስታወሻ 0015
ረመዷን 17
የታላቁ የበድር ዘመቻ ዕለት
ረመዳን አጋማሽ አካባቢ የቁረይሾች የንግድ ቅፍለት ከሻም የገበያ ማእከል የሸመተውን ግዙፍ ሀብት ይዞ ወደ መካ እየተመለሰ ነበረና የአላህ መልዕክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ከሰሃቦቻቸው ጋር ሆነው የንግድ ቅፍለቱ ወደ መካ ለመጓዝ የሚያቋርጥበት መስመር ላይ ሆነው መጠባበቅ ጀመሩ።
አላማውም በ13ቱ የመካ የዳእዋ ዘመናቸው እሳቸውም ሆኑ ሰሃቦች በህይወታቸው፣ በአካላቸው፣ በክብራቸው፣ በንብረታቸውና ገንዘባቸው ላይ ይህ ነው ተብሎ በማይገለፅ ደረጃ የመብት ጥሰት ተደርጎባቸው ነበር።
በዚህም ንብረቶቻቸው ተዘርፏል። ቤቶቻቸው ተወርሰዋል። ተቃጥለዋል።
በሙስሊሞችና በጣዖታውያኑ መካከል ያለው ሁኔታም የጦርነት ነበርና ባገኙት አጋጣሚ ራሳቸውን መከላከል፣ ጠላትን ወይም ንብረቱን መማረክ፣ እንዲሁም ድንበር ጥሰቱን እንዲገታ ምላሽ መስጠቱ ግድ ነበር።
በመሆኑም በቁረይሾች የተዘረፉትን፣ የተቀሙትንና ጥለው እንዲሰደዱ የተገደዱትን ንብረት ገንዘባቸውን ተመሳሳዩን ቢችሉ ለማስመለስ ኣሊያም አላህ የሚረዝቃቸውን ያህል ለማግኘት ከመዲና ወጡ።
ይሁንና የንግድ ቅፍለቱ የመረጃ ምንጮች በደፈጣ እየተጠበቁ እንደሆነ በወቅቱ የንግድ ቅፍለቱን እየመራ ዚጓዝ ለነበረው የቁረይሾች አለቃ ለአቡሱፍያን መረጃው ሲደርስ ወደ ቁረይሾች ፈጣን መልዕክት በመላክ የኣድኑን ጥሪ ኣደረሰ። ሆኖም ሙስሊሞች ሳያገኙት የቅፍለቱን መስመር ቀይሮ በማምለጥ ወደ መካ እንዲገቡ አደረገ።
በዚህም ሙከራ ንብረታቸው በሰላም መካ እንደገባላቸው ሲያውቁ የመካ የቁረይሾች ሙስሊሞችን መውጋት እንደማያስፈልግ አቋም ሲይዙ ከሹማምንቶቹ ዋነኛው ግለሰብ አቡ ጀሀል ግን አሻፈረኝ በማለት የግድ ልንዘምትባቸው ይገባል በሚል አሳምኗቸው ለጦርነት ተዘጋጁ።
በዚህም ዝግጅታቸው አንድ ሺህ የሚጠጉ ተዋጊዎችን አዋቀሩ። ከነሱም መካከል 6 መቶዎቹ የጦርና የቀስት መከላከያ የለበሱ ሲሆን፣ አንድ መቶ ፈረስና ሰባት መቶ ግመሎችንም ለመጓጓዣና ለውጊያው አሰማሩ። በተጨማሪም በርካታ አዝማሪዎችን በመመደብ ዱፍ ማለትም ከበሮ እየደለቁ በመዝፈን ኢስላምንና ሙስሊሞችን ያንቋሽሹ ነበር።
በሙስሊሞች በኩል ቀድሞውንም የጦርነት ሃሳቡም ዝግጅቱም አልነበራቸውም። ከቀዬኣቸው የወጡትም በባዶ እጅ የንግድ ቅፍለቱን ንብረት ለመማረክ ነበር።
ይሁንና ነገሩ ተቀይሮ ጦርነት ተደገሰላቸውና የድንገተኛ ራስን መከላከያ ምላሽ ሊሰጡ ቆርጠው በቀጠሮው ቦታ በበድር ተሰለፉ።
አሰላለፋቸውም ሶስት መቶ አስራ ምናምን ሰዎች ሲሆኑ፤ ከነዚህ መካከል 83ቱ ሙሃጂሮች የተቀሩት 61ዱ ከአውስ ጎሳ፣ 170ዎቹ ከከዝረጅ ጎሳ የሆኑ አንሷሮች ነበሩ።
የትጥቃቸው ሁኔታም ሲታይ 70 ግመሎችና ሁለት ፈረሶች ብቻ ነበሯቸው። በዚህም መሰረት የተወሰኑት ግለሰቦች ብቻ አየተፈራረቁ ግመሎች ላይ ይሳፈሩ ነበር።
ከውጊያው በስተፊትም የአላህ መልእክተኛ [ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም] ሶሃቦችን በተለይ አንሷሮችን ጦርነቱ ውስጥ ስለመግባት አማከሩ።
አንሷሮችም እንደመጠሪያቸው ሁሉ የአላህን ዲንና መልእክተኛውን ብሎም ሙስሊሙን በሚችሉት ሁሉ ሊረዱና መልእክተኛው ጦርነቱ ውስጥ እንዲገቡ ከፈለጓቸው ዝግጁ እንደሆኑ በመግለፅ መልካም አቋምና ንግግራቸውን አሰሟቸው።
በዚህም ስምምነት መሰረት ነቢዩ [ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም] በድር ወደምትባለዋ ቦታ ተጓዙ። በድር ማለት በአካባቢው የሚገኝ የ("ቢዕር") የጉድጓድ ውሃ ስያሜ ነው።
ይህን ስያሜ በመውረስም አካባቢው ባሁኑ ወቅት የበድር ከተማ ትባላለች። ከመዲና ከተማ 155 ከሎሜትር፣ ከመካ ደግሞ 310ኪሜ እንዲሁም ከቀይ ባህር ጠረፍ 30ኪሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ናት።
የአላህ መልዕክተኛ [ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም] በስፍራው ባለቿ የበድር የጉድጓድ ውሃ መግቢያ መስመር ላይ መሸጉ። የአዋጊነትና የአመራር መስጫ ቦታም ሰሩ።
የአላህ መልዕክተኛ [ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም] ከጦርነቱ መጀመር በፊትም የሰራዊቱን ሰልፍ አስተካክለው ለፍልሚያው ዝግጁ እንዲሆኑ በማነቃቃት ለመስዋዕትነት እንዲነሳሱ አጠናከሯቸው። ከዚያም ወደ አመራር ስፍራቸው ከአቡበክር ጋር ተመለሱ።
መልእክተኛው [ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም] አላህ ኢስላምን እንዲረዳና ሙስሊሞችንም የበላይ እንዲያደርግ በጣም ዱዓእ ማድረግን ተያያዙት። ከዚያም ጦርነቱ ጀመረ፤ ተጋግሎ ቀጠለም።
በስተመጨረሻም ድሉ የሙስሊሞች በመሆን ፍልሚያው አበቃ።
በዚህ ጦርንት ከሙስሊሞች 14 ጀግኖች መስዋእት ሲሆኑ ከአጋሪያን 70ዎቹ ተገድለው 70ዎቹ ተማርከዋል።
ሙሽሪኮቹ ምርኮኞቻቸውን ለማስለቀቅ በገንዘብና በመሳሰሉት ጥረት አደረጉ። ይሁንና የአላህ መልዕክተኛ [ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም] የአንዳንዶቹን ድህነት ግምት ውስጥ በማስገባት የቤዛ ገንዘብ ሳይቀበሉ ይቅርታ አድርገውላቸው በነፃ ለቀቋቸው።
የተወሰኑ ፊደል የቆጠሩ የሆኑትን ደግሞ የሙስሊሞችን ልጆች ማንበብና መፃፍ እንዲያስተምሯቸው አደረጓቸው።
ይህንን ዘመቻ በሚመለከትም ከጌታችን ቃል መካከል "ሱረቱል አንፋል ወረደ"። ሰሃቦች የምርኮ ንብረትን በተመለከተ ያቀረቡትን ቅሬታ በመንቀፍ እንዲሁም የጦርነቱን ጎጂ ጎን በመተረክና ከዚህ በኋላ በሚመጡት ዘመቻዎች ስህተቶች እንዳይኖሩ ምክሩን ለገሰ።
💥ማስታወሻ
ሀባብ ቢን ሙንዚር ረዲየላሁ ዐንሁ የተባለው ሰሃቢይ መልእክተኛው የመመሸግያ ቦታቸውን የበድር ውሃ ዘንድ እንዲያደርጉ ሀሳብ አቀረበ የሚባለው ትረካ ሰነዱ ደዒፍ መሆኑን አል-አልባኒ ገልፀውታል። እንዲሁም ኢማሙ ዝ'ዘሀቢ ዘገባው ሙንከር ነው ብለውታል።
【قال الشيخ الألباني -رحمه الله: "وهذا سند ضعيف لجهالة الواسطة بين ابن إسحاق والرجال من بني سلمة. وقد وصله الحاكم (3/ 426، 427) من حديث الحباب بن المنذر وفي سنده من لم أعرفه.
وقال الذهبي في تلخيصه (قلت: حديث منكر، وسنده) كذا الأصل، ولعله سقط منه (واه) أو نحوه.】
------------------
www.fb.com/tenbihat
🎐ረመዷን 17/1436
ጁላይ 04/2015

Post a Comment

0 Comments