Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የአስተሳሰብ ለጋዎች

የአስተሳሰብ ለጋዎች
አይ ኤስ አይ ኤስ "እኔ የላኩት ነው" ያለው ግለሰብ ኦርላንዶ በተባለ ከተማ የሉጥ ህዝቦች መሸታ ቤት ገብቶ 50 ሰው ሲገድል በርካታ ሰዎችን ደግሞ አቁስሏል።
መልካም ጎን እና መጥፎ ጎን ማመዛዘኛ ሚዛኑ የተንጋደደበት ይህ የኸዋሪጅ ቡድን በተከበረው ረመዳን ወር ሙስሊሞች አንገታቸውን እንዲያቀረቅሩና ስጋት ላይ እንዲወድቁ ልክ እንደተለመደው የታሰረውን ሸይጣን ተክቶ እየሰራ ይገኛል።
በቅርቡ በተደረገ ጥናት ይህ ቡድን ምእራባውያን ሃገራት ላይ ለሽብር ተግባር የሚያሰማራቸው አባላቱ እንኳን የሸሪዓን ህግ ተፈጻሚ ሊያደርጉ ይቅርና ራሳቸው ፍርዱ የሚገባቸው የዱርዬ ጥርቅሞች መሆናቸው ታውቋል።
የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንደገለጿቸው እነዚህ እንጭጮች ለዲን የሚሰሩ እየመሰላቸው ዲንን የሚያፈርሱ የቀን ህልመኞች፣ የአስተሳሰብ ለጋዎች ናቸው።
በያዝነው አመት ፈረንሳይ ፓሪስ ውስጥ በሁለት የዐብዱልሰላም ወንድምማቾች የተባሉ የዳዒሽ አባላት አንድ ትልቅ የሽብር ድርጊት ተከስቶ እንደነበር ማንም አይጠፋውም። በጥቃቱ ከ137 ሰዎች በላይ ሞተዋል። ብዙዎች ቆስለዋል። ጥቃቱን ተከትሎ በአፀፋው ከኩፋሮች በኩል በርካታ መሳጂዶች በመጠጥና በአሳማ ጭንቅላት ተጨማለዋል። ባልሂጃብ ሴቶች ተደብድበዋል። የሱና ምልክት የሚታይባቸው ሙስሊሞች መንገድ ላይ ተፈንክተዋል።
ግን ይህን ጥቃት ስለፈፀሙት ወንድማማቾች ብትሰሙ በርግጥም ትገረሙ ይሆናል።
እነዚህ ሁለት ወንድማማቾች ዲነል ኢስላምን በቅጡ ሊያውቁት ቀርቶ ጥቃቱን ከመፈፀማቸው ከ6 ሳምንታት በፊት ቤልጅየም ውስጥ የነበራቸውን የመጠጥ ቤት (Bar) ሽጠውት እንደነበር ታውቁ ኖሯል?
በርካታ ሙስሊም ያልሆኑ አካላት አእምሮ ውስጥ ያሉ አሸባሪ ተብለው የሚታሰቡ ሙስሊሞች እምነቱን ጠንቅቀው የተረዱና የነቢዩ ሙሐመድ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለምን እርምጃ የሚከተሉ ሰዎች መሆናቸውና ከሚጠረጠሩበት ነገር ግን ተቃራኒ እንደሆኑ ይህ ምሳሌ በቂ ነበር።
ሌላም ልጨምርላቹ?
አንድ ሰሞን የዜና አውታሮችን ጉድ ያስባሉትና ብዙ ሽፋን ያገኙት ሁለት እንግሊዛውያን ወደ ሶሪያ ተሰደው አይ ኤስን በተቀላቀሉ ማግስት ልክ እንደነርሱ የብሪታኒያ ወጣቶችም ከሃገሩ አምልጠው ወደ አይ ኤስ ጉያ እንዲቀላቀሉ ሲወተውቱ በዩቱዩብ ድረ ገፅ ታይተዋል። ግን የሚገርማችሁ እነዚህ ሁለት ወጣቶች አይ ኤስን ለመቀላቀል ወደ ሶሪያ ከመሄዳቸው በፊት አማዞን (Amazon) የተባለ ኦንላይን መገበያያ ድረ ገፅ ላይ ሁለት መፃህፍቶችን አዘው ነበር። መፃህፍቱ ቡኻሪና ሙስሊም ናቸው ብላቹ ትግምቱ ይሆናል። በጭራሽ! የላኩት መፃህፍት Islam foR dummies እና The koran for dummies የሚል ኢስላምን ለአላዋቂዎች እና ቁርኣንን ለመሃይማን የሚያስተምር መፅሃፍት ነበሩ። ጉድ እኮ ነው!
ሲጀመር ቁርኣንን ጠንቅቆ የተረዳ ሰው እንኳን ይህ ደም መጣጭ ቡድን ሊቀላቀል ቀርቶ ባለበት ቆሞ ባወገዛቸው ነበር።
ግን ሚዲያው ስለዚህ ጉዳይ ምን አገባው! ሙስሊሙን አይደለም እራሳቸውን መወከል ማይችሉ ህፃናት በሚፈፅሙት ጥቃት የሙስሊሙን ስም በአንድ ላይ ለማጠልሸት አጋጣሚው ምቹ ሆኖለታል።
ይህም ካልበቃ ሌላም ምሳሌ ልጥቀስ?
ባለፈው አንድ እምነቶች ላይ የሚያላግጥ ቻርሊ ሄብዶ የተባለ የካርቶን ምስል መጽሔት መስሪያ ቤት ውስጥ ትልቅ ጥቃት በኩዋቺ ወንድማማቾች የተባሉ ሰዎች ተፈፅሞ ነበር። በጥቃቱ መስሪያ ቤቱ ውስጥ የነበሩ በርካታ ሰራተኞች ተገድለዋል። ጥቃቱን የፈፀሙት በነቢዪ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ላይ የሚያላግጥ የካርቶን ምስል ስላችሗል በሚል ሲሆን ጥቃቱን ተከትሎ የአለም መንግስታት "የፕሬስ ነፃነት ተገፈፈ" በሚል ሽፋን ኢስላም ላይ በተዘዋዋሪ ጦርነት አውጀዋል። በርካታ የካርቱን ምስል ሰኣሊያን አፀፋዊ ምላሽ ብለውም የተለያዩ ካርቱን ምስሎችን በውዱ ነቢያችን ላይ በማላገጥ ስለዋል። ፈረንሳይ የሚገኙ ሙስሊሞች ጥቃት ደርሶባቸዋል። ሂጃብ የየለበሱ ሴቶች ተደብድበዋል። ኩፋሮች አጋጣሚውን አግኝተው ሂጃብ የለበሰች እርጉዝ ሴት ሳትቀር ደብድበዋል።
ምክንያቱም የሽብር ጥቃቱን የፈፀሙት ሰዎች ተግባሩን የፈፀሙት በኢስላም ስም ነበርና ነው።
ግን የሚገርማችሁ የነዚህ ሰዎች ጀርባ ሲጠና የተገኘው ግን ገራሚ ነው። ከጥቃት ፈፃሚዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ታላቅ ወንድምየው ሸሪፍ የሐሺሽ ሱሰኛ የነበረ፣ መጠጥ ጠጪ፣ መሸታ ቤት የሚዞር ኢስላም የከለከላቸውን ክልክላቶች የሚዳፈር ሰው እንደነበርና ጭራሽ ኢስላምን እና ካቶሊክ እምነትን መለየት የማይችል ደነዝ እንደነበር ከጥቃቱ በሗላ ጏደኛው ለሚዲያዎች ግልፅ ተናግሯል።
ታዲያ ይህ ዱርየ ነው ኢስላምን የሚወክለው?
አረረ ሌሎቹንም እናንሳ!
የቦስተን ማራቶን ጊዜ ቦንብ የጠመዱትና ጥቃት ያደረሱት ሁለት ወንድማማቾችን የሚያውቃቸው አለ?
በጥቃቱ በርካታ ሰዎች ሞተዋል። አሁንም ልክ እንደ ሌላው በኢስላም ስም የሚደረግ ሽብር የሙስሊሞችን ስም በጊዜው አጉድፏል። የጥቃቱ አድራሾች በ24 ሰአት ውስጥ በፖሊስ ተገድለው ነበር።
ታላቅ ወንድምየው ትንሽም ቢሆን ዲንን ተግባሪ የሚባል ቢሆንም ታናሽ ግን ከጏደኞቹ ጋር መጠጥ የሚጠጣ፣ ራፕ ሙዚቃ የሚያደምጥ፣ ሐሺሽ አጫሽ ነበር።
እሺ ሁሉን ትተን ወደ 9/11 የአሜሪካው መንትያ ህንፃዎች የሽብር ጥቃት እንምጣ?
የሽብሩ ፈፃሚዎች ጥቃቱን ከማድረሳቸው ከሳምንታት ቀደም ብሎ የቁማር ቤቶች ውስጥ ይታዩ እንደነበር የሚያውቅ ማን አለ? እዛም ጥቃት ሊፈፅሙ ቢሆንስ የሚል አይጠፋም። የዋህ! እንለዋለን እኛም በተራችን። ጥቃቱ ከፈፀሙት 19 አሸባሪዎች አብዛኞቹ ከጥቃቱ ሳምንታት ቀደም ብሎ የራቁት ጨፋሪ ሴተኛ አዳሪዎች የሚገኙበት መሸታ ቤት ውስጥ ሲጣቀሙ እንደነበር ግልፅ የሆኑ መረጃዎች አሉ።
ታዲያ አሁንም እንጠይቃለን?
እነዝህ አሸባሪዎች ኢስላምን ይወክላሉን?