Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ቴሌ የሚለቀው ጥንቆላ

Ibnu Munewor ሙሐመድ አሕመድ ሙነወር 

ቴሌ የሚለቀው ጥንቆላ
ከስር የምትመለከቱት ትላንት በቴሌ በኩል የተላከ የጥንቆላ መልእክት ነው፡፡ ይሄኛው በግልፅ እንደምታዩት የኮከብ ቆጠራ (ተንጂም/ አስትሮሎጂ) ነው፡፡ ከዚህ በፊት ሌላ መልክ ያላቸው ጥንቆላዎችም ሲቀርቡ ነበር፡፡ ቴሌ ከህዝባዊ ሃላፊነት ይልቅ በዚህ አይነት ርካሽ ንግድ የሚያገኘውን ሳንቲም ማስቀደሙ የሚያሳፍርም የሚያስተዛዝብም ተግባር ነው፡፡ አንድ የንግድ ሸቀጥ ገበያ ላይ በጠፋ ቁጥር የግል ጥቅማቸውን በሚያሳድዱ ስግብግብ ነጋዴዎች የተፈጠረ ሰው ሰራሽ ችግር ነው እያሉ መግለጫ ማውጣት ዛሬ ዛሬ የተለመደ ሆኗል፡፡ እዚህ ግን ግዙፉ የመንግስት ተቋም ቴሌ በእንቶ ፈንቶና በአጉል እምነት የአላዋቂዎችን ሳንቲም ለመሞጭለፍ ለተሰማሩ አታላዮች የገበያ እድል ፈጥሮላቸዋል፡፡ አሳዛኝ፡፡
እኛ ከእምነታችን አንፃር ስንነጋገር ሃይማኖታችን እንዲህ አይነቱ ሁለት አገር የሚያበላሽ የነቀዘ እምነት ላይ ቆራጥ እርምጃ ነው ያለው፡፡ “የሩቅ አውቃለሁ” ብሎ የሞገተው ቀርቶ እውነት ብሎ ያመነው እራሱ ከኢስላም ይወጣል፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላሉ፡
"مَنْ أَتَى كَاهِنًا فَصَدَّقَهُ بِمَا يَقُولُ فَقَدْ كَفَرَ بِمَا أُنْزِلَ عَلَى مُحَمَّدٍ - صلى الله عليه وسلم"
{ጠንቋይ ዘንድ ሄዶ በሚናገረው ያመነ፣ በሙሐመድ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ላይ በወረደው ክዷል፡፡} [አስሶሒሐህ፡ 3387]
ጠንቋይ ዘንድ የሄደ ሰው የተነገረውን ባያምን እንኳን የሚከተለው ቅጣት ከባድ ነው፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላሉ፡-
"مَنْ أَتَى عَرَّافًا فَسَأَلَهُ عَنْ شَىْءٍ لَمْ تُقْبَلْ لَهُ صَلاَةٌ أَرْبَعِينَ لَيْلَةً"
{ጠንቋይ ዘንድ ሄዶ ስለሆነ ነገር የጠየቀው የአርባ ቀን ሶላቱ ተቀባይነት የለውም፡፡} [ሙስሊም፡ 5957]
በዘመናችን በአብዛሃኛው ጥንቆላና ድግምት ላይ ሲወድቅ የሚታየው ንቃተ-ህሊናው ዝቅ ያለው ያልተማረው ክፍል ነው፡፡ ዘመናዊ ትምህርት የቀሰመው ክፍል ግን ሁሉም ባይሆን እንኳን አብዛሃኛው ሌላው ቀርቶ ተጨባጭ የሆነውን የድግምት ተፅእኖ እንኳን ከተራ ማጭበርበር የማይዘል ባዶ እምነት ሊያደርገው ሲዳዳው ይታያል፡፡ የሚገርመው ግን ይሄ ሳይነቃ “የነቃው” “ተምሬያለሁ” ባዩ ክፍል እራሱ በጥንቆላ መረብ ሲጠለፍ መታየቱ ነው፡፡ ዘመናዊ ኮከብ ቆጠራ በሬዲዮ፣ በጋዜጣ፣ በማህበራዊ ድረ-ገፅ በሰለጠኑት ነጮች ተነድፎ ህጋዊ ፈቃድ አግኝቶ መንሸራሸር ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ የነጩን ሰው ስራ እንደ ወረደ ሳያኝክ የሚውጠው ሌላው አለምም ህዝባዊ የመገናኛ ብዙሃንን ሳይቀር እየተጠቀመ በራሱ ህዝብ ላይ ደባ ሲሰራ ይታያል፡፡ ይህን እውነታ ሸይኽ ሷሊሕ ኣሊሽሸይኽ እንዲህ ይገልፁታል፡-
“በዚህ ዘመን ብዙ ሰው ቢዘነጋውም በግልፅ ከኮከብ ቆጠራ ጥንቆላ ውስጥ የሚገባው በመፅሄቶች በብዛት የሚለቀቀው “ኮከብ ቆጠራ” (astrology) እየተባለ የሚጠራው ነው፡፡ ጋዜጦች ላይ አንድ ገፅ ወይም ከዚያ ያነሰ ይመድቡለታል፡፡ “ሊዮ”፣ “አስኮርፒዮን”፣ “ታውረስ” ወዘተ እያሉ የአመቱን ኮከብ ንድፍ ይሰራሉ፡፡ ከእያንዳንዱ ኮከብ ፊት ይከሰታል ብለው የሚያስቡትን ይፅፋሉ፡፡ ይሄ የከዋክብትን እንቅስቃሴና ሁኔታ ተመልክቶ ምድር ላይ የሚደርሰውን ማወቅ ይቻላል የሚል ትምህርት ነው፡፡ ይሄ ከጥንቆላ አይነቶች አንዱ ነው፡፡ በመፅሄቶችና ጋዜጦች ላይ በዚህ መልኩ ከኖረ ጥንቆላ አለባቸው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሺርክ፣ የሩቅ እናውቃለን የሚል ሙግት፣ ጥንቆላና ኮከብ ቆጠራ ስለሆነ የያዘው ሊቃወሙት ይገባል፡፡ እያንዳንዱ ሙስሊም እንዲህ አይነቱን ነገር ከቤቱ ሊያስገባ አይገባም፡፡ ማንበብና መከታተልም የለበትም፡፡ ምክንያቱም ይህን ኮከብ ቆጠራና በውስጡ ያለውን መከታተል ማለት እንዲሁ ለማወቅ ብቻ ቢሆን እንኳን የተከለከለ ነው፡፡ ምክንያቱም ላይቃወም ጠንቋይ ዘንድ መሄድ ነውና፡፡
የተወለደበትን ኮከብ ሊያውቅ ወይም ከሱ ጋር የሚሄደውን ኮከብ ሊያውቅ አስቦ የኮከብ ቆጠራ ያለበትን ገፅ ያነበበ ሰው ልክ ጠንቋይ እንደጠየቀ ነው፡፡ ስለዚህ አርባ ቀን ሰላቱ ተቀባይነት የለውም፡፡ በነዚህ የኮከብ ቆጠራ ውስጥ ያለውን ካመነ ደግሞ በሙሐመድ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ላይ በወረደው ያለጥርጥር ክዷል፡፡” [ኪፋየቱል ሙስተዚድ፡ 193]