Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ሐሰን በሰበሰበው የመውሊድ መሰላል ሲንጠላጠል

ሐሰን ታጁ መውሊድን መቃወም ፀለምተኛ አስተሳሰብ ነው፣ ታሪክ አልባ፣ ታሪካዊ ስብእና አልባ ያደርጋል ይለናል። ይህም አልበቃውም ሃይማኖታችን ላለፉት “14 ክ/ዘመናት የረባ ግለሰብ ማፍራት የተሳነው ስንኩል አድርገን እንድናየው ያደርገናል” ይላል። አልበቃውም “ይህ አይነቱ እይታ ተስፋ አስቆራጭ በመሆኑ የትኛውንም የተሃድሶ እንቅስቃሴ ገዳይ ነው። ምክንያቱም… ‘ትላንት በታላቅነት ዘመኑ ያልተሳካለት ዛሬ ወድቆና ደቆ እንዴት ሊሳካለት ይችላል?’ የሚል መልስ የሌለው ጥያቄ ከአዕምሮ ውስጥ ይፈጥራል” ይላል።
[መውሊድ፡ 218‐219]

ግን መውሊድን መቃወም ይህን ሁሉ ያስብላል?! ካስባለስ እውን መውሊድ ከሱ ዘንድ ከጥቃቅን ነገሮች ውስጥ ነው? እውን ኢስላም በታላቅነት ዘመኑ አልተሳካለትም? እውን እንዲህ የሚል ሙስሊም አለ? ደግሞስ በኢስላም የታላቅነት ዘመን መውሊድ ነበር? እውን በአራቱ ስመ‐ገናና ኸሊፋዎች ዘመን መውሊድ ህልውና ነበረው? ሙስሊሞች በሰሜን እሰከ ካውካስስ፣ ሲሰርጉ በምስራቅ እስከ ቻይና ጫፍ፣ በምእራብ እስከ እስፔን የተንጣለለ ግዛት ሲዘረጉ መውሊድ ህልውና ነበረውን? ነው ወይስ ይሄኛው የታሪካችን ክፍል አይደለም? የኢስላም የታላቅነት ዘመኑ ይሄ ካልሆነ የቱ ሊሆን ነው? ደግሞስ መውሊድ የ 14 ክ/ዘመን ታሪክ አለው እንዴ?! ግን ለምን ይሄ ሁሉ ውሸት?! ለአንድ የቢድዐህ በዓል ሲባል ይህን ያክል አዘቅት መውረድ ያስፈልጋል ማለት ነው? ዑለማዎች “ሐቅን ያልተቀበለን ሰው አላህ ሐሰትን በመቀበል ይፈትነዋል” ማለታቸው ምንኛ ጥልቅ የሆነ አነጋገር ነው?!!

እንዲያውም አዙረን ካየነው የዛሬ መውሊድ ጠበቆች በዚህ መጤ ድግስ ላይ የማይጋሯቸውን ሙስሊሞች “የነቢ ጠላት” እና መሰል ቅፅሎችን እየለጠፉ ነው። ስለዚህ ሶሐቦች፣ ታቢዒዮችና አትባዐትታቢዒን የነቢ ጠላት ነበሩ ማለት ነው። አራቱ የፊቂህ አኢማዎች ስለመውሊድ አለማስተማራቸው የነቢ ጠላቶች ስለሆኑ ነው ማለት ነው። ቡኻሪ፣ ሙስሊም፣ አቡ ዳውድ፣ ነሳኢይ፣ ቲርሚዚ፣ ኢብኑ ማጃህና የነሱ ሸይኾቻቸውና ተማሪዎቻቸው የነበሩ የሐዲስ ልሂቃን በሙሉ መውሊድን አለማክበራቸው፣ እሱም ቢቀር አለመደስኮራቸው የነቢ ጠላት ቢሆኑ ነው ማለት ነው። ነው እነዚህ ኢስላማዊ ስብእናዎቻችን አይደሉም? ነው ዘመናቸው የኢስላም ታላቅነት ዘመን አልነበረም? ነው ወይስ ስኬታቸው ስኬታችን ታሪካቸው ታሪካችን አይደሉም? ኢስላም በዚህ ወርቃማ ዘመኑ አንቱ የተሰኙ ስብእናዎችን ካላፈራ መቼ ነው የሚያፈራው? እንዲህ አይነቱ ቁንፅል አስተሳሰብ ፀለምተኛ ካልሆነ የፀለምተኝነት ትርጉሙ ምንድነው? ነዑዙ ቢላሂ ሚነልሐውሪ በዕደል ከውር!!!

ሐሰን ወረድ ብሎ እንዲህ ሲል ይቀጥላል፦ “መውሊድ የኢትዮጵያ እስልምና ታሪክ አካል ሆኗል።… መውሊድን ከታሪካችን ነጥለን ማውጣት የሚቻል አይሆንም። እርሱን ስንጥል የሚተርፈን ነገር የለምና ሙሉ ታሪካችንን አብረን እንወረውራለን።” [መውሊድ፡ 219]

ምን አይነት ድምዳሜ እንደሚሰራ ተመልከቱ። ከመቼ ጀምሮ ነው አንድ ነገር በህዝብ ውስጥ መንሰራፋቱ ሸሪዐዊ መረጃ ሆኖ መቅረብ የጀመረው? ሺርክ በህዝባችን ውስጥ ቢንሰራፋ “ታሪካችን ነው ባህላችን ነው” ብለን ብንሞግት እንደ እምነት ያዋጣናል?

ነቢዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) “ኢስላም እንግዳ ሆኖ ነው የጀመረው። እንግዳ ሆኖ ይመለሳል።” አላሉምን?
[ሙስሊም 389]

ምናልባት እሱ ዘንድ ይሄ ዘመን አልደረሰ ይሆናል። ይሄ ነቢያዊ ትንቢት የሚረጋገጥበት ዘመን ሲያጋጥም በታሪክና በባህል መሞገት ያዋጣል ማለት ነው እንደ ሐሰን።
ኢብኑ መስዑድ ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ ይላሉ፦ “ትንሹ በውስጧ የሚያድግባት ትልቁ የሚያረጅባት ሱንናህ ተደርጋ የምትያዝ ፈተና ስትወጣችሁ እንዴት ልትሆኑ ነው? የተቀየረች ጊዜ ‘ሱንናው ተቀየረ’ የሚባልበት ዘመን።”
“መቼ ነው ይሄ የሚሆነው የዐብዱራህማን አባት ሆይ?” ሲባል “አስተማሪዎቻችሁ ሲበዙ፣ ምሁራኖቻችሁ ሲቀሉ፣ ገንዘቦቻችሁ ሲበዙ፣ ታማኞቻችሁ ሲቀሉ፣ በአኺራዊ ስራ ዱኒያ ሲፈለግ እና ዲናዊ ላልሆነ አላማ ዲንን ሲማሩት ነው” አሉ።
[አልቢደዕ ሊብኒ ወዷሕ፡ 277]

ሱንናው ቢድዐህ ቢድዐው ሱንና ተደርጎ የሚያዝበት፣ ሐቁ የሚረሳበት ዘመን እንደሚመጣ ሰለፎች ተናግረዋል። ያኔ እንደ ሐሰን ታጁ ባሉ ዳኞች ህዝብ ዘንድ በነገሰው ቢድዐህ ሱንና ላይ ይፈረዳል ማለት ነው።

ደግሞም መውሊድን ከታሪካችን ነጥለን ማውጣት በደንብ ይቻላል። እርሱን ስንጥልም ሙሉ ታሪካችንን ሳይሆን በታሪክ ሰርገው የገቡብንን ኮተቶችና እንቶ ፈንቶዎች ነው አሽቀንጥረን የምንጥለው። በምንም መልኩ መውሊድ ስለተጣለ ታሪካችን አብሮ አይወድቅም። መውሊድ አርካኑል ኢስላም ነው ወይስ አርካኑል ኢማን? ሐሰን ታጁ እስከ እስፔን ድረስ ያቀኑትን ባለገድሎቹን ኡመያውያንን ሲያበጠለጥል “እስፔን የኛ ነበረች?” እንዳያዜም አግዶታል?! ግን ለምን የተለያየ መለኪያ ይጠቀማል? ስለዚህ የአባቶቻችንን የአያቶቻችንን ውለታ አንረሳም። ዘግናኝና አሳዛኝ የሆኑ ታሪኮችን አሳልፈው ኢስላምን አቀብለውናል። ከፊሎቹ ጋር ስለነበረው ክፍተት አላህ ይቅር ይበላቸው። ደግሞም ብዙዎቹ ለነበረባቸው ክፍተት አሳማኝ ምክንያት አላቸው። ስላደረሱን መልካም ሁሉ ደግሞ አላህ ውለታቸውን ይክፈላቸው።

ባጭሩ አላህ እንዲህ ይላል፦
{ይህቺ በርግጥ ያለፈች ህዝብ ናት። ለእርሷ የሰራችው አላት። ለናንተም የሰራችሁት አላችሁ። ይሰሩት ከነበሩት አትጠየቁም።} [አልበቀራህ፡ 141]

[መውሊድ፡ ታሪክ ፤ ግድፈት ፤ እርምት ከሚለው የኢብኑ ሙነወር መፅሀፍ ከገፅ 312‐313 የተወሰደ]