በእምነት ላይ መፈላሰፍ አላህን ያስክዳል
الرَّحْمَنُ عَلَى الْعَرْشِ اسْتَوَى
“አረህማን ከዐርሽ በላይ ከፍ አለ (ሆነ)” (ጣሃ 5)
‘ኢስተዋ’ (ከበላይ ሆነ) የሚለውን ቃል ‘ኢስተውላ’ (ስልጣንን ተቆናጠጠ) በሚል ከዚህ ጋር በማይጣጣም ሌላ ቃል በመተርጎም “አላህ ከዓርሽ በላይ ነው” ብሎ መናገርም “ኩፍር ነው” ይላሉ። ይህ አረፍተ ነገር ቁርዓን ላይ ያለና አላህ እራሱን የገለጸበት ቃል መሆኑ ሲነገራቸው፤ ይህ “ሌላ ትርጓሜ ሊሰጠው ይገባል እንጂ የቃሉ ቀጥተኛ ትርጉም “ተሽቢህ በመሆኑ ኩፍር ነው” ብለው ይመልሳሉ። በአላህና እና በመልዕክተኛዉ ንግግር ያመነ ሰው በፍጹም ለኩፍር የሚዳርግ መልዕክት ያስተላልፋሉ ብሎ አያስብም። “አላህ ከዓርሽ በላይ ነው” የሚለውን አረፍተ ነገር የሚረዱት ፈጡራን ከነገሮች በላይ የሚሆኑበትን ሁኔታ እና ይዘት መሰረት ባደረገ መልኩ ስለሆነ፤ “አላህ ከዓርሽ በላይ ነው” ማለት፤ «አላህን ዓርሽ ተሸክሞታል ማለት ነውና አላህን ከዚህ ማንጻት አለብን» ይላሉ። እነዚህን ሰዎች ይህ ጥመታቸው የተለያዩ መስመሮችን እንዲይዙ አድርጓቸዋል። ከፊሎቹ “አላህ ሁሉም ቦታ አለ” የሚል ፍልስፍና ሲያራምዱ ሌሎቹ ደግሞ “ለላህ የሚገኘው ካለ ቦታ ነው፤ ለአላህ ቦታ “መካን” እና አቅጣጫ “ጂሀ” የለዉም” የሚል ሌላ ፍልስፍና ያራምዳሉ። አላህን ከ‘ጂሀ’ እና ከ“መካን” ማጥራት ማለት ምን እንደሆነ ሲያብራሩም፤ «አላህ ከፍጥረታት በላይ የለም፤ ከታችም፣ ከቀኝም፣ ከግራም፣ ከኋላም፣ ከፊትም የለም፤ ከፍጥረተ አለሙ ውስጥም አይደለም፤ ከፍጥረተ አለሙ ውጭም አይደለም» በማለት እርስ በእርሱ የተምታታ፣ ሰሀቦችና ታቢዒዮችም ዘንድ ይታወቅ ያልነበረ እና መቋጫውም “አላህ የለም” የሆነን ፍልስፍና ያስተምራሉ።
http://www.facebook.com/