Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

እውን ኢማሙ አሽሻፊዒይ ቢድዐን ለሁለት ከፍለዋል?



Taju Nasir

እውን ኢማሙ አሽሻፊዒይ ቢድዐን ለሁለት ከፍለዋል?
“መልካም ቢድዐህ” የሚባል እንዳለ የሚሞግቱ ሰዎች የሚያነሱት ምርኩዝ ይህ የኢማሙ አሽሻፊዒይ ንግግር ነው፦
“በዲን ውስጥ የተፈጠሩ መጤ ነገሮች ሁለት አይነት ናቸው። አንዱ ቁርአንን ወይም ሱንናን ወይም የቀደምቶች ቅሪትን ወይም ኢጅማዕን የሚፃረር መጤ ፈሊጥ ሲሆን ይሄ ቢድዐህ ጥመት ነው። ሁለተኛው አይነት ደግሞ ከነዚህ አንዱንም የማይፃረር በጎ የሆነ ፈጠራ ነው። ይሄ የማይወገዝ መጤ ነገር ነው። ዑመር ኢብኑል ኸጧብ ረዲየላሁ አንሁ የረመዷን ቂያምን አስመልክቶ ‘ይህቺ ያማረች ቢድዐህ ነች’ ብሏልና።”
[መናቂቡ አሽሻፊዒይ: 1/468‐469]

8.1. በቅድሚያ “ሰነዱ ውስጥ ያለው ሙሐመድ ኢብኑ ሙሳ የሚባል ሁኔታው በውል የማይታወቅ (መጅሁል) ሰው አለ። ስለዚህ ይህንን ንግግር ማስረጃ ማድረግ አይቻልም” ያሉ ዓሊሞች አሉ።
8.2. በመቀጠል ሶሒሕ ከሆነም “ጥሩ የሚባል ቢድዐህ አለ” ሲሉ በቋንቋ ደረጃ እንጂ ሙሉ በሙሉ አዲስ የሆነ ፈጠራን አይደለም። ኢብኑ ረጀብ ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ፦ “ሻፊዒይ ረሒመሁላህ ማለት የፈለጉት ቀድመን የጠቀስነውን ነው። ጥሩ የምትባለው ቢድዐህ ከሱንናህ ጋር የምትገጥመዋ ናት። ማለትም ከሱንናህ መነሻ መሰረት ያላት የሆነችዋ። ቢድዐህ የተባለችው ከቋንቋ አንፃር እንጂ ከሸሪዐህ አንፃር አይደለም፣ ከሱንናህ ጋር ተስማሚ ናትና። ይህንን ግልፅ የሚያደርግ ከራሳቸው ከሻፊዒይ እንዲህ የሚል ዘገባ አለና ‘ቢድዐ ሁለት አይነት ነው። መልካም የሆነ ቢድዐህና የተወገዘ ቢድዐህ። ከሱንናህ ጋር የገጠመ ጥሩ ነው። ከሱንናህ ጋር የተፃረረ ደግሞ የተወገዘ ነው።’”
[ጃሚዑል ዑሉም ወልሐኪም: 2/131]
8.3. “አይ” የሚል ካለ፡ ሶሒሕ እንኳን ቢሆን ከነቢዩ(ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም)ሐዲሶች ጋር እኩል ሚዛን ላይ አይቀመጥም። እራሳቸው ኢማሙ አሽሻፊዒይ ረሒመሁላህ “የአንድ ሶሐብይ ንግግር ብቻውን መረጃ መሆን አይችልም” እንዳሉ ባልደረቦቻቸው ዘግበዋል። ስለዚህ የሶሐብይ ንግግር መረጃ ካልሆነ እንዴት የሳቸው ንግግር መረጃ ይሆናል?! ስለ ቢድዐህ የተናገሩትን ነጥለው የሚያራግቡ ሰዎች ረጋ ብለው ቢያስተውሉ መልካም ነው። ነቢዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) “ቢድዐህ ሁሉ ጥመት ነው” ያሉ ከሆነና የሆነ ዓሊም ግን “አይ ሁሉም ቢድዐማ ጥመት አይደለም። ቢድዐ ጥሩም መጥፎም አለ” ቢሉ ከማን በኩል ነው የምትሆነው? ኢማሙ አሽሻፊዒይ “በኪታቤ ውስጥ ከአላህ መልእክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ሱንናህ ተፃራሪ የሆነ ነገር ካገኛችሁ የመልእክተኛውን (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ሱንናህ ያዙ። የኔን ንግግር ተው” ይላሉ። [አልሒልያህ፡ 9/107]ምክራቸውን ተቀብለን የመልእክተኛውን (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ሱንና አስቀድመናል።
8.4. ኢብኑ ረጀብ የጠቀሱትን የኢማሙ አሽሻፊዒይ ንግግር አቡ ኑዐይም ዘግበውታል። [ሒልየቱል አውሊያእ፡ 9/113] መውሊድን ከዚህ በኩልም ስንመለከተው ከሱንናህ ጋር የሚገጥም አይደለም። ሱንናህ ማለት የነቢዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ንግግር ወይም ተግባር ወይም ይሁንታ ነው። መውሊድ ከነዚህ ከየትኛውም ውስጥ አይካተትም። ከብዙ መቶ አመታት በኋላ የመጣ መሆኑ ለዚህ በቂ መረጃ ነው። እንዳውም ኢማሙ አሽሻፊዒይ “ጥመት ነው” ካሉት ክፍል የሚመደብ ነው። ምክንያቱም ቁርኣንንም፣ ሱንናንም፣ የቀደምቶች ቅሪቶችንም፣ የሰለፎች ኢጅማዕንም የሚፃረር መጤ ፈሊጥ ነውና። ሌላው ቀርቶ ከራሳቸው ከሻፊዒይ እንኳን በቃልም አልተገኘም።
8.5. ደግሞም “መልካም ነው” እያሉ አዳዲስ ነገሮችን መደንገግን እራሳቸው ኢማሙ አሽሻፊዒይ ደጋግመው በሰፊው አውግዘዋል። [አርሪሳለህ፡ 507]፣ [አልኡም 7/293‐304] ስለዚህ የተጠቀሰው ንግግር ወይ የሳቸው አይደለም። ከሆነም መልእክቱ ከሌሎች እራሳቸው ካሰፈሯቸው መርሆዎች አንፃር ሊቃኝ ይገባዋል። [አልቢድዐህ ወአሠሩሃ አስሰይዪእ ፊልኡማህ] ወይም ደግሞ ስህተት ነው ተብሎ ይጣላል።
8.6. ኢብኑ ተይሚያህ ረሂመሁላህ እንዲህ ይላሉ፦ “ ‘ቢድዐህ ሁሉ ጥመት ነው’የሚለውን የመልእክተኛው (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ጠቅላይ ንግግር ‘አይ ሁሉም ቢድዐማ ጥመት አይደለም’ ብሎ ሊላተምና ጠቅላይነቱን ሊነሳ ለማንም አይፈቀድለትም። ይሄ ከተእዊል ይልቅ ወደመፃረር የቀረበ ነውና።”[አልኢቅቲዷእ፡ 248]
8.7. በነገራችን ላይ ሻፊዒይ መውሊድን አላከበሩም። የሞቱትም መውሊድ ከመከበሩ ከብዙ ዘመናት በፊት ነው። ስለዚህ እሳቸው ላላከበሩት ቢድዐህ ንግግራቸውን ማዋል አግባብ አይደለም። ያውም በውስጡ እሳቸው የሚያወግዙት ነገር እያለበት ለምሳሌ መንዙማ። እንዲህ ማለታቸው ይታወስ፦ “ባግዳድ ላይ አፈንጋጮች ሰዎችን ከቁርአን ለማዘናጋት የፈጠሩት ተግቢር የሚባል ነገር ጥየ መጣሁ።”(37) [ሒልየቱል አውሊያእ፡ 9/146]
(37) “ተግቢር” ማለት ዱንያን የሚያስንቅ ወደ አኺራ ፊትን የሚያዞር የሆነ በዜማ የታጀበ ግጥም ነው። ከተካፋዮቹ ከፊሎቹ እንጨት ይዘው ቆዳ ላይ ወይም ትራስ ላይ በሪትም ወይም ኖታ እየመቱ ያጅቡታል። በሃገራችን “መንዙማ” ከምንለው ጋር ተመሳሳይ ነው። በግልፅ እንደሚታየው ኢማሙ አሽሻፊዒይ በከባድ ቃላት ነው የኮነኑት። ኢማሙ አህመድም ተጠይቀው “ቢድዐህ ነው” በማለት ሰዎች እንዳይሰሙት ከልክለዋል። ከዚህም አልፈው “ይህንን የሚፈፅሙ ሰዎችን መንገድ ላይ ካየሃችሁ መንገድ ቀይር” ብለዋል። [መስኣለቱ አስሰማእ፡ 124]
[መውሊድ፡ ታሪክ ፤ ግድፈት ፤ እርምት ከሚለው የኢብኑ ሙነወር መፅሀፍ ከገፅ 245‐248 የተወሰደ]