አምባር እና ሌሎች የሚጠለቁ ነገሮችን እጅ ወይም አንገት ላይ ማሰር እንዴት ይታያል?
ዓረቦች ከኢስልምና በፊት በነበረው የድንቁርና ዘመን ክፋትን ለመመከት፣ መልካምን ለማግኘት ወይም ከቡዳ ለመጠበቅ ሲሉ አንባርና የመሳሰሉትን ነገሮች ያደርጉት ነበር፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡-
وَلَئِن سَأَلْتَهُم مَّنْ خَلَقَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ لَيَقُولُنَّ اللَّهُ قُلْ أَفَرَأَيْتُم مَّا تَدْعُونَ مِن دُونِ اللَّهِ إِنْ أَرَادَنِيَ اللَّهُ بِضُرٍّ هَلْ هُنَّ كَاشِفَاتُ ضُرِّهِ أَوْ أَرَادَنِي بِرَحْمَةٍ هَلْ هُنَّ مُمْسِكَاتُ رَحْمَتِهِ قُلْ حَسْبِيَ اللَّهُ عَلَيْهِ يَتَوَكَّلُ الْمُتَوَكِّلُونَ
«ከአላህ ሌላ የምትግገዟቸውን (ጣዖታት) አያችሁን? (ንገሩኝ) አላህ በጉዳት ቢፈልገኝ እነርሱ ጉዳቱን ገላጮች ናቸውን? ወይስ በችሮታው ቢፈቅደኝ እነርሱ ችሮታውን አጋጆች ናቸውን?» በላቸው፡፡ «አላህ በቂዬ ነው፡፡ በእርሱ ላይ ተመኪዎች ይመካሉ» በል፡፡ (አል ዙምር 38)
በሌላም አንቀጽ እንዲህ ይላል፦
قُلِ ادْعُوا الَّذِينَ زَعَمْتُم مِّن دُونِهِ فَلَا يَمْلِكُونَ كَشْفَ الضُّرِّ عَنكُمْ وَلَا تَحْوِيلًا
«እነዚያን ከእርሱ ሌላ (አማልክት) የምትሏቸውን ጥሩ፡፡ ከእናንተም ላይ ጉዳትን ማስወገድን (ወደ ሌላም) ማዞርንም አይችሉም» በላቸው፡፡ አል ኢስራህ 56
አምባር፣ ክርና የመሳሰሉትን ማጥለቅ ሸሪዓዊ ድንጋጌው ሀራም (ክልክል) ነው። አንድ ሰው አምባር ሲያደርግ በራሱ ያለ አላህ ፈቃድ ተፅእኖ ያሳድራል የሚል እምነት ካለው ከአላህ ውጭ አስተናባሪ ጌታ አለ ማለቱ በመሆኑ በአላህ ጌትነት ላይ ትልቁን ሽርክ አጋርቷል ማለት ነው::
ከዒምራን ኢብኑ ሁሰይን እንደተዘገበው ‹‹ነብዩ አንድ ሰውዬ እጁ ላይ ከመዳብ የሆነ አምባር አጥልቆ ሲያዩት፤ “ይህ ምንድነው?” ብለው ጠየቁት “ለድካም በሽታ ነው” አላቸው:: እሳቸውም እንዲህ በማለት ወቀሱት “አውልቃት! ድካምን እንጂ አትጨምርልህም። እጅህ ላይ እያለች ከሞትክ አትድንም፡፡›› አል ኢማም አህመድ ዘግበውታል
ከሁዘይፋ ኢብኑል የማን እንደተዘገበው ‹‹አንድን ሰው በመታመሙ እጁ ላይ ክር አስሮ አየውና ከበጠሰበት በኋላ ይህን አንቀጽ አነበበ፦
وَمَا يُؤْمِنُ أَكْثَرُهُم بِاللَّهِ إِلَّا وَهُم مُّشْرِكُونَ
‹‹አብዛኞቻቸውም፤ እነሱ አጋሪዎች ኾነው እንጂ በአላህ አያምኑም፡፡›› (ዩሱፍ 1ዐ6)
☞ አንዳንዶች ለደም ዝውውር እና ጤናዊ አላማ ነው የምናደርገው ይላሉ፤ እስካሁን ድረስ ለጤና ያለውን ጥቅም በተጨባጭ በመረጃና በሙከራ ያረጋገጠ ጥናት የለም። ፈውስ ሁሉ ከአላህ ነው። አላህ ፈውስ ካላደረገው ነገር ፈውስን መፈለግ ከባድ ስህተት ነው። ኢብራሂም አለይሂሰላም ይህንን እውነታ ለአጋሪዎች ሲያስረዱ ተከታዩን ብለው ነበር።
«وَإِذَا مَرِضْتُ فَهُوَ يَشْفِين»ِ الشعراء ٨٠
«በታመምኩም ጊዜ እርሱ ያሽረኛል፡፡» ሹዓራዕ 80
በዚህ መልኩ አንድ ሰው የነገሮች ሁሉ ተፈፃሚነት በአላህ እጅ እንደሆነና ያጠለቀው ነገር ግን ለፈውስ ምክንያት ብቻ እንደሆነ ቢያምን ደግሞ ትንሹን ሽርክ ፈፅሟል፡፡ ምክንያቱም ሰበብ ያልሆነን ነገር እንደሰበብ ቆጥሮ በልቡና በስራውም ከአላህ ሌላ ወደሆነ አካል ዞሯል፡፡ ይህ ደግሞ ወደ ትልቁ ሽርክ ለመሸጋገር በር የሚከፍት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡
ሸይኽ ኡሰይሚን እንዲህ ብለዋል፤
«وما لم يثبت كونه سببا شرعيا ولا حسيا لم يجز أن يجعل سببا ، فإن جعله سببا نوع من منازعة الله تعالى في ملكه وإشراك حيث شارك الله تعالى في وضع الأسباب لمسبباتها» مجموع الفتاوى 1/144
« ሸሪዓዊ ወይም ተጨባጭ የፈውስ ምክኒያት ያልሆነን ነገር ለፈውስ ምክኒያት አድርጎ መቁጠር አይፈቀድም። የፈውስ ምክኒያት አድርጎ መቁጠር የአላህን ስልጣን መቀናቀንና ማጋራትም ይሆናል።»
☞ አምባርን በዘመናችን በተለያየ ቅርፅና ይዘት እየተሰራ ወንዶች ለጌጥ በሚል ሰበብ እያደረጉት ይታያል። ታላቁ አሊም ሸይኽ ፈውዛን ስለዚህ ጉዳይ ተጠይቀው፤ ከችግር ያድናል ብሎ ካደረገው ኩፍር መሆኑን ለጌጥ የሚለውም ሁለት ችግሮች እንደማያጡት ተናግረዋል። እነሱም ከካፊሮች ጋር ወይም ከሴቶች ጋር መመሳሰል ነው።
አላህ ከጥፋት ሁሉ ይጠብቀን!
www.fb.com/emnetihintebiq