Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

እውነትን ተናገር፣ ባይሆን ቦታና ጊዜውን አገናዝብ

እውነትን ተናገር፣ ባይሆን ቦታና ጊዜውን አገናዝብ
እውነትን ተናገር፡፡ ከመናገርህ በፊት ግን ለምን እንደምትናገር እራስህን ጠይቅ፡፡ ውስጥህ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠውንም መልስ በሰከነ መንፈስ አዳምጥ፡፡ አዎ እውነትን መናገርህ አላህን በማሰብ ካልሆነ ከንቱ ነው፡፡ በምትናገረው ነገር አላህን የምታስብ ከሆንክ በቅድሚያ የምትናገረው ነገር ሐቅ መሆኑን ታስረግጣለህ፡፡ ቀጥሎም ቦታና ጊዜውን የጠበቀ መሆኑንም ታስተውላለህ፡፡ በምትናገረው ሐቅ የሚፈተኑ ሰዎች ወይም የሚጎዱ አካላት ካሉ ወይ ተስማሚ ሁኔታዎችን ጠብቅ፡፡ አለያ ደግሞ ተስማሚ ቦታዎችን ተጠቀም፡፡ ካልሆነ ግን ተናግረህ ከምትፈትን ምቹ ሁኔታ እስከሚገኝ ልታቆየው የግድ ይልሃል፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ጥቅምና ጉዳቱን በማስላት ስንት ነገሮችን ሳይፈፅሙ ቀርተዋል፡፡ ለምሳሌ
1. “ሙሐመድ ጓደኞችን ይገድል ነበር” እንዳይባል ሲሉ በመናፍቃን ላይ እርምጃ ሳይወስዱ ቀርተዋል፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም]
2. አዲስ ሰለምቴዎች ኢማናቸው እንዳይወዛወዝ በመስጋት ከዕባን አስተካክሎ የመገንባት ፍላጎታቸውን ትተውታል፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም]
3. አንዳንድ ነገሮችን ደግሞ ከሶሐቦቻቸውም ነጥለው ለጥቂቶች ብቻ ተናግረዋል፡፡
ይሄ ጥቅምና ጉዳትን እያሰሉ መናገር ሶሐቦቻቸውም የተጓዙበት ፈለግ ነው፡፡ ዐልይ ኢብኑ አቢ ጧሊብ ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ ይላሉ፡- “ሰዎችን በሚያውቁት (ሊረዱት በሚችሉት) አናግሯቸው፡፡ አላህና መልእክተኛው ቢስተባበሉ ትወዳላችሁን?” [ቡኻሪ] ኢብኑ መስዑድም ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲሁ “አንተ የሆኑ ሰዎችን አእምሯቸው የማይደርስበትን ሐዲሥ አትነግራቸውም፣ ለከፊላቸው ፈተና የሚሆንባቸው ቢሆን እንጂ” ይላሉ፡፡ [ሙስሊም]
ሰለፎቻችንም በዚሁ ፍኖት ላይ ተጉዘዋል፡፡ ለአጥፊዎች መመርኮዣ፣ ለአላዋቂዎች መፈተኛ ይሆናሉ ብለው የሰጓቸውን ሐዲሦች ሳይቀር ከማውራት ተቆጥበዋል፡፡ ለምሳሌ አልኢማም ማሊክ ስለ አላህ መገለጫዎች የሚያትቱና አላዋቂዎች ይፈተኑባቸዋል ብለው የሰጓቸውን ሐዲሦች ከማውራት ተቆጥበዋል፡፡ አቡ ዩሱፍ ደግሞ እንግዳ መልእክት ያሏቸው ሐዲሦችን ከማውራት ተቆጥበዋል፡፡ አልኢማም አሕመድም እንዲሁ አንዳንድ ዟሂር መልእክታቸው በመሪ ላይ መውጣትን የሚደግፉ የሚመስሉ ሐዲሦችን ከማውራት ተቆጥበዋል፡፡ (ዛሬ የስሜት ተከታዮች የሚያደርጉትን ግን ተመልከቱ፡፡ ለጥመቶቻቸው “ያግዙናል” ብለው የሚያስቧቸውን ሐዲሦች መልእክታቸው ሌላ ቢሆንም ጠምዝዘው፣ ሰነዳቸው ደካማ ቢሆንም ሸፋፍነው ያለ የሌለ ሹቡሃዎችን ነው የሚያግበሰብሱት፡፡ ከዚያም አልፈው ይህን ድርጊታቸውን የማይደግፉ ዑለማዎችን ሳይቀር “የአንባገነን ጠበቃ” እንደሆኑ ይወነጅላሉ፡፡ ለመሆኑ አልኢማም አሕመድስ ይህን ሲያደርጉ ለጨቋኝ መሪ ጠበቃ ነበሩን? ልብ ያለው ልብ ይበል!!)
ቀደም ብሎሞ ከሶሐቦችም ተመሳሳይ ማስተዋል የተንፀባረቀበት አካሄድ ተስተውሏል፡፡ ስለዚህ አንድ ሐዲሥ ጤናማ መልእክት ኖሮት ሳለ የቢድዐህ ሰዎች መልእክቱን ጠምዝዘው ለቢድዐቸው ማጠናከሪያ የሚታገዙበት ሆኖ ከተገኘ “ይፈተናሉ” ተብሎ የሚሰጉ ሰዎች ዘንድ አለማውራት ይገባል፡፡ [ፈትሑልባሪ፡ 1/225 ይመልከቱ]
ይሄ ሀሳብ በሐዲሥ ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ የስሜት ተከታዮች የታላላቅ ሱንናህ ዑለማእ ንግግሮችን
I. ያለ አግባብ እንደሚመነዝሩ፣
II. ለቢድዐዎቻቸውና ለቁንጮዎቻቸው መከላከለያ እንደሚያውሉ፣
III. ተንኮላቸውን የሚያጋልጡ መሻኢኾችን እና ዱዐቶችን ለማሳጣት እንደሚጠቀሙ የታወቀ ነው፡፡
ታዲያ ይህን እንደሚደርጉ ከታወቀ የዑለማዎችን ንግግር ስንጠቀምም ሆነ ለሌሎች ወንድሞቻችን መምከርን ስንፈልግ የስሜት ተከታዮች ለጥፋታቸው ማጠናከሪያ፣ የሱንናህ ሰዎችን ማንቋሸሽያ፣ የሱንናህ ሰዎችን እርስበርሳቸው ማበጣበጫ አድርገው እንዳይጠቀሙት ጥንቁቅ ልንሆን ይገባል፡፡ ስለሆነም እያንዳንዱ የምንናገረው ወይም የምንፅፈው ነገር ሐቅ ከመሆኑም ባሻገር ቦታና ጊዜውን የጠበቀ መሆኑን ማስተዋል ይበጃል ማለት ነው፡፡
አንድ ተግባራዊ ምሳሌ እንመልከት፡- በዘመናችን ታላቁ የሱንናህ ዓሊም ዐብዱልሙሕሲን አልዐባድ (አላህ ይጠብቃቸውና) በሱንናህ ሰዎች መካከል መተዛዘንና መከባበር ሊኖር እንደሚገባ ያተቱበት “ሪፍቀን አህለ አስሱንናህ ቢአህሊስሱንናህ” የምትል ገፁዋ ቀለል ያለች ኪታብ ይፅፋሉ፡፡ የኪታቧ ዋና መልእክት በጥቅሉ ርእሷ እንደሚናገረው በሱንናህ ሰዎች መካከል መተዛዘን ሊኖር እንደሚገባ ማሳሰብ ነበር፡፡ አጋጣሚዎችን በመጠቀም የተካኑት ኢኽዋኖች ግን ኪታቧ ከነሱ ለመከላከል እንደተዘጋጀች አድርገው አራገቡ፡፡ የሰለፍያህ ዑለማዎችን ትነካለች ብለው ያሰቧትን ይህቺን ኪታብ በነፃ እያሳተሙ በመላው አለም በገፍ አከፋፈሏት፡፡
ታዲያ ከሱንናህ ዑለማዎች ከፊሎቹ የሸይኽ ዐብዱልሙሕሲንን ኪታብ በዚህ መነሻ አጥብቀው ነቀፉ፡፡ ለምሳሌ ሸይኽ አሕመድ አንነጅሚን መውሰድ ይቻላል፣ ረሒመሁላህ፡፡ በምክንያትነት ካነሷቸው ነጥቦችም አንዱ በዚህ ኪታብ የተጠቀሙት “የስሜት ተከታዮች ናቸው” የሚል ነበር፡፡ ሸይኽ አንነጅሚይ ለሸይኽ ዐብዱልሙሕሲን ከተናገሩት ቀንጨብ ላድርግማ፡-
“4. ይህን አቋምህን የቢድዐህ ሰዎች ተጠቅመውበታል፡፡ አንተንም ከነሱ የምትከላከል፣ የነሱ ሞጋች እንደሆንክ አድርገውሃል፡፡ በደረሰን መረጃ መሰረት ኪታብህን በመቶዎች ኧረ እንዳውም በሺዎች አባዝተውታል፡፡ እስኪ በዚህ ኪታብህ ማንን እንደጠቀምክ፣ ከማን ጎንም እንደቆምክ ተመልከት!!
5. በዚህም አንተ ያን ዝቅተኛ የሆነውን በላጭ በሆነው ለውጠሃል፡፡ ማለትም - ታውቃለህ- ሰለፊዮችን በመርዳትና ከነሱ በመከላከል ፋንታ ሙብተዲዖችን በመርዳትና ከነሱ መከላከልን ተክተሃል፡፡ ተረዳሀውም አልተረዳሀውም ይህ ነው የተከሰተው፡፡
በኪታብህ ማን እንደተደሰተ፣ እንዲሁም ማን እንዳዘነ ተመልከት፡፡ ያለጥርጥር ሒዝቢዮች (ቡድንተኞች) ተደስተዋል፤ ሰለፊዮች ደግሞ አዝነዋል፡፡” [ሪሳለቱ አሽሸይኺንነጅሚ ሊልዐባድ፡ 3-4]
ውድ የሱንናህ ወንድሞችና እህቶች በዚህ ነጥብ ላይ ሸይኽ አሕመድ አንነጅሚ ረሒመሁላህ ያነሱትን በሚገባ እናስተውል፡፡ ሸይኽ ዐብዱልሙሕሲን “ሪፍቀን..” ኪታባቸውን የፃፉት ከኢኽዋኖች ለመከላከል አልነበረም፡፡ ኢኽዋኖች ዛሬም ድረስ እውነታውን በመገልበጥ እንዲያ ቢያስመስሉትም ሸይኹ እራሳቸው ኪታቧን የፃፏት ከኢኽዋኖች ለመከላከል እንዳልሆነ ኋላ ላይ ግልፅ አድርገዋል፡፡ በተለይ ደግሞ “ወመረተን ኡኽራ ሪፍቀን አህለስሱንናህ ቢ አህሊስሱንናህ” በምትለዋ ኋላ ላይ በፃፏት ሪሳላህ ላይ ኢኽዋኖችን በግልፅ በመንቀፍ ኢኽዋኖች እንደመጀመሪያው እንዳያራግቡ አፋቸውን አዝዘግተዋቸዋል፡፡
ይሄ ክስተት አስተዋይ ለሆነ አካል ጥልቅ መልእክት አለው፡፡ የምትሰጠው ትምህርት፣ እርምት፣ ማስተካከያ በቅድሚያ ልክ መሆኑን እርግጠኛ ሁን፡፡ ከዚያም ባለፈ መሬት ላይ ሲወርድ ሊያስከትል የሚችለውን በግራም በቀኝም ቀላል ዳሰሳ አድርግ፡፡ ትምህርትህ ለሆኑ ሰዎች ፈተናን ካስከተለ አቀራረብህን አጢነው፡፡ መቼስ መጥቀም እንጂ መጉዳትን አላለምክምና፡፡ በስራህ የሚቀርቡህ እንዲከፉ፣ በአንፃሩ ራቅ ያሉት ደግሞ በደስታ እንዲቦርቁ፣ አንተ ከነሱ እንደሆንክ እስከሚገልፁም ካመቻቸህላቸው ይሄ ልፋትህን ከንቱ የሚያስቀር፣ “የኔ” የምትለውን አንገት የሚያስደፋ፣ ሌላኛውን በጥፋቱ ወኔ የሚሰጥ አጉል ብልሃት ነው፡፡
ሱፍያን አሥሠውሪ ረሒመሁላህ ምን እንደሚሉ እንመልከት፡- “ረዋፊድ (ሺዐዎች) የዐልይን ገድሎች ማውራትን እንድጠላ አድርገውኛል፡፡” [ሲየሩ አዕላሚ አንኑበላእ፡ 7/253] ሱብሓነላህ!!! ሱፍያን ይህን የሚሉት ዐልይን ከመጥላት እንዳልሆነ የሚያውቃቸው ሁሉ አያጣውም፡፡ ዐልይ ረዲየላሁ ዐንሁ ተቆጥረው የማያልቁ ገድሎች ያሏቸው ታላቅ ሶሐብይ መሆናቸው ለሱፍያን አይሰወርም፡፡ ነገር ግን ሱፍያን አሥሠውሪ ይኖሩ የነበሩት ቆሻሻዎቹ ሺዐዎች በሚበዙበት ኩፋ ምድር ነበር፡፡ እነዚህን ትክክለኛ መሰረት ያላቸው ስለ ዐልይ ታላቅነት የሚያትቱ ሐዲሦችን ያለ አግባብ በመመንዘር ለቢድዐቸው ማጠናከሪያ እንዲያውሏቸው አልፈለጉም፡፡ እስኪ ይህን የታላቁ ሰለፍ የሱፍያን አሥሠውሪን አርቆ አሳቢነት ተመልከቱ፡፡ ልብ ይበሉ፡- ይሄ ማለት ገና ለገና ሰዎች አንድን ሐቅ ለባጢላቸው ይጠቀሙታል ተብሎ ይዳፈን ለማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ተስማሚ ቦታና ጊዜ መፈለጉ ይበጃል ለማለት ነው፡፡ የግድ መናገር የሚኖርብን ከሆነም በተቻለን የስሜት ተከታዮች በዚያ ሐቅ ላይ ተመርኩዘው ይበልጥ ለጥፋት እንዳይነሳሱ የሚያደርግ አካሄድን መዘየድ ጥሩ ብልሃት ነው፡፡ ለዚህም እራሳቸው ሱፍያን አሥሠውሪ የተናገሩትን ማጤን ይጠቅማል፡፡ እንዲህ ይላሉ፡- “በሻም ምድር ስትሆን የዐልይን ገድሎች አውራ፡፡ በኩፋ ስትሆን ደግሞ የአቡበክርን እና የዑመርን ገድሎች አውራ፡፡” [አስሲየር፡ 7/260] ልብ በሉ! ሻም ውስጥ ለዐልይ ጥሩ እይታ የሌላቸው ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ ስለዚህ መሀይሙ ይማር ዘንድ፣ አውቆ አጥፊው ይጋለጥ ዘንድ ሰለ ዐልይ ታላቅነት የሚያትቱ ማስረጃዎችን እውነቱን ሊያዳፍኑ ከሚሹት ዘንድ ማሰራጨት፡፡ በሌላ በኩል ኩፋ ላይ “የዐልይ ወዳጆች ነን” በሚሉ ሺዐዎች የአቡበክርና የዑመር ስብእና እየተጠለሸ፣ ገድላቸው እየተደበቀ ስለሆነ ለዘነጉት ማንቂያ፣ ለአፈንጋጮቹ አፍ ማዘጊያ ይሆን ዘንድ የሲዲቅን እና የፋሩቅን ገድል ከፍ ባለ ድምፅ ማሰራጨት እንደሚገባ እየጠቆሙን ነው- ሱፍያን አላህ ይማራቸውና፡፡
ስለዚህ!! በምንሰጠው ትምህርት፣ በማስተማሪያ ዘዴያችን እኛ ባላሰብነው የስሜት ተከታዮች ለስሜታቸው ማጠናከሪያ የሱንናህ ሰዎችን በነገር መውጊያ የሚጠቀሙበት እንዳይሆን እንጠንቀቅ፡፡ የኛ ፍላጎት ያ ባይሆን እንኳን መሬት ላይ ያለው ሐቅ ሌላ ከሆነ ልፋታችን እየፈጩ ጥሬ ነው የሚሆነው፡፡ የግድ መደረግ ካለበትም እነዚህ የስሜት ተከታዮች ስራችንን ለጥፋት እንዳይጠቀሙት ወይም የሚጠቀሙት ቢኖሩ እንኳን ተንኮላቸው ክብደት እንዳይኖረው የሚያደርግ እስትራቴጂ ልንጠቀም ይገባል፡፡ ይሄ ደግሞ የማይቻል ነገር አይደለም፡፡ ከከሃዲዎች አንፃርም በተመሳሳይ አካሄዳችንን ልናጤን ይገባል፡፡
(ኢብኑ ሙነወር፣ ህዳር 30/2008)