Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ስለ ኩሱፍ ወይም የፀሃይና የጨረቃ ግርዶሽ መረጃ እንለዋወጥ።


≅∷≅∷≅∷ ﷽ ∷≅∷≅∷≅
مسائل الكسوف
ስለ ኩሱፍ ወይም የፀሃይና የጨረቃ ግርዶሽ መረጃ እንለዋወጥ።

ኩሱፍ ወይም الكسوف ማለት የፀሃይ ግርዶሽ ማለት ሲሆን፤ ኹሱፍ ወይም الخسوف ሲባል ደግሞ የጨረቃ ግርዶሽ ለማለት ነው።
① *ኩሱፍ ወይም ኹሱፍ ለምን ይከሰታል?*
ግርዶሽ እንዲከሰት ሰበብ የሚሆኑ ተጨባጭና ሸሪዓዊ በመባል የሚገለፁ ሁለት አይነት ምክንያቶች ኣሉ።
☞ የሚታይና በቀላሉ የሚታወቀው ተጨባጭ ጉዳይ አንደኛው ገፅታ ጨረቃ ምድርን እየዞረች ባለበት በፀሃይና በምድር መሃል ስትደርስ የሚፈጠረው የመጨለም ክስተት ነው። ይህም የሚሆነው ጨረቃ በፈለኳ ላይ መስመሯን ጠብቃ ስትዞር በአንድ ጎኗ ፀሃይ በሌላኛው ጎኗ ደግሞ ምድር ሆኖ መሃከላቸው ላይ ስትገባ የፀሃይ ብርሃን ወደ ምድር እንዳይደርስ ግርዶ ስለምትሆን የፀሃይ ግርዶሽ ወይም *ኩሱፍ አልሸምስ* የተሰኘው ክስተት ይፈጠራል።
ሁለተኛው የግርዶሽ ገፅታ ደግሞ ምድር በፀሃይና በጨረቃ መሃል ስትሆን ጨረቃ ከፀሃይ ይደርሳት የነበረውን ብርሃን ታጣለች። ይህን ግዜ የጨረቃ ግርዶሽ ወይም *ኹሱፍ አልቀመር* ተከሰተ ይባላል።
☞ ሁለተኛውና ሸሪዓዊው የግርዶሹ መከሰት ምክንያት የባሮች ማለትም የሰው ልጆች በወንጀልና በኃጢኣት መዘፈቅ ነው። ለዚህም ነው የግርዶሽ ሰላት የስጋት መግለጫ ሰላት ወይም ክፉና መዓትን መከላከያ የሆነ ሰላት በመባል የታወቀው።
ሸይኽ አብዱል ዐዚዝ ኢብኑ ባዝ ረሂመሁላህ ስለዚሁ ጉዳይ እንደገለፁት «የፀሀይ ግርዶሽና የጨረቃ ግርዶሽ አላህ ባሮቹን ለማስፈራራት እንዲከሰቱ የሚያደርገው ክስተት ነው ሲሉ ነቢዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም መናገራቸው ተረጋግጧል።» ብለዋል።
"مجموع فتاوى ابن باز" (30 / 289-290)

በዚሁ ገፅ ላይ ትንሽ ወረድ ብሎ የሰፈረው የኢብኑ ባዝ ንግግር ደግሞ የግርዶሹን ምክንያት የሰው ልጅ ኃጢኣት በመብዛቱ ለማስፈራርያነት የሚከሰት ከመሆኑና በተፈጥሯዊው የጨረቃ ወይም የምድር እሽክርክሪት ሰበብ የሚፈጠር ከመሆኑ ጋር የሚጋጭ ኣለመሆኑን ሲያስረዱ እንዲህ ይላሉ☞
«የግርዶሿ በባለሞያዎች ስሌት መታወቅ ለማስፈራርያነት ሲል ሀያሉ አላህ እንዲከሰቱ ከማድረጉ ጋር የሚጋጭ አይደለም። ክስተቱ ከእንከን አልባው ሀያሉ አላህ ለማስጠንቀቂያነት የተደረገ ነውና። ተዓምራቱን የሚያስኬዳቸውም እሱ ራሱ ነው። በተወሰኑ ግዜያት ፀሃይ እንደምትወጣውና እንደምትጠልቀው ሁሉ የግርዶሹን መገኛ ሰበብ ያስገኘው እሱ ነው። ጨረቃም፣ ከዋክብትም ልክ እንደዚያው ሁሉም ከአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ተዓምራት የሆኑ ናቸው።
የስነ ከዋክብት አጥኚዎች የገለፁት የግርዶሹ ሰበብም አላህ ያደረገው ሰበብ ነው። የግርዶሹን መከሰት የሚያውቁትም በዚሁ ነው። ሆነም ቀረ ለማስፈራሪያና ለማስጠንቀቂያነት ከአላህ ዘንድ የተደረገ መሆኑን የሚያግድ አይደለም።
ልክ እንደዚሁ በፀሃይ፣ በጨረቃና በከዋክብት እንዲሁም በሙቀትና በብርድ ላይ የሚታዩ ልዩ ተዓምራቱ ኣሉ። ታዲያ በነዚህ ተዓምራት ሁሉ ውስጥ ይህንን ፀጋውን በአግባቡ ባለመቀበል አላህን ላመፀ አካል ማስፈራርያና ማስጠንቀቅያ አለበት። በዚህም ትዕዛዛቱን በመፈፀም ላይ ፅኑ እስኪሆኑና ሀራም ያደረገባቸውን ነገር እስኪተዉ ድረስ በነዚህ ክስተቶች ሰበብ እንዲጠነቀቁት፣ እንዲፈሩትና እንዲሰጉት እንከን አልባው ጌታችን ይህን ነገር ያደርጋል።» ብለዋል።
"مجموع فتاوى ابن باز" (30 / 289-290)

ሸይኽ ሷሊህ አልዑሰይሚን ረሂመሁላህ በገለፁት ደግሞ ቀጣዩን መልእክት እናገኛለን☞
«ግርዶሽ የሚከሰተው ለማስጠንቀቅያ ሲሆን የሆነ የሚያስቀጣ ነገር በመገኘቱ የሚመጣ እንጂ በራሱ ቅጣት ሆኖ አይደለም የሚከሰተው። ነገር ግን ማስጠንቀቅያ ነው። ይህም ልክ የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም
( يخوف الله بهما عباده ) 
“በሁለቱም ባሮቹን ያስፈራራበታል።” ብለው እንደተናገሩት ነው። ስለዚህ ማስፈራርያ ነው ያሉት እንጂ ባሮቹን ይቀጣበታል አላሉም። ይሁንና ከማስፈራርያው በሰረተጀርባ የሚከተለውን አናውቅም።

ምናልባትም በህይወት ላይ ወይም በንብረት ወይም በልጆች ወይም በቤተሰብ ላይ ያነጣጠረች ዘግይታ የምትመጣ ወይም ወዲያው የምትከሰት ቅጣት ልትኖር ትችላለችና። ቅጣቱ ሁሉን አቀፍ ወይም በተወሰኑት ላይ ያነጣጠረም ሊሆን ይችላል። ግን አናውቀውም።
ለዚህም ነቢዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም “ያንን ግርዶሽ ስታዩ አላህን ወደ ማውሳት በርግጉ፣ በስጋት ሽሹ።” ነበር ያሉት። ተነሱ ቁሙ አላሉም። ስገዱም ዚክር አድርጉ ብቻም አላሉም። ነገር ግን እሳቸው ያሉት በስጋት ሽሹ ነው። አላህን ወደ ማውሳት በርግጉ። ምህረትን ጠይቁት፣ ሃያልነቱን ግለፁ፣ ሰደቃ ስጡ፣ ስገዱ፣ ባርያም ነፃ አውጡ ነው ያሉት። ታዲያ ይህ ሁሉ የሚጠቁመን የዚህ ግርዶሽ ጉዳይን ክብደት ነው። ለግርዶሽ መከሰት ደግሞ ሁለት ምክንያቶች ይኖሩታል።
አንደኛው ማስፈራርያ ነው። ይህም ኃጢኣት ሲበዛና ወንጀሎች በልቦች ላይ ሲጋገሩ አላህ ባሮቹን ያስፈራራበታል። አላህ ከእንደዚህ አይነቱ በሽታ ጠብቆ ኣፊያ ይስጠን እላለሁ።
ሁለተኛው የግርዶሽ መከሰት ሰበብ ደግሞ በዓለማችን ላይ እንዲከሰት አላህ የወሰነው ተፈጥሯዊ ክስተት ነው። እሱም ሰዎች እንደሚያወሩት ሁሉ የፀሃይ ግርዶሽ ሰበቡ የጨረቃ በፀሃይና በምድር መሃል መገኘት ነው።
የጨረቃ ግርዶሽ ሰበብ ደግሞ የምድር በፀሃይና በጨረቃ መሃል መገኘት ነው። በዚህም መሰረት አላህ አዝዘ ወጀልለ ባሮቹን ለማስፈራራት ሲል ተፈጥሯዊ የሆኑ ሰበቦች እንዲከሰቱ ከማድረግ ከልካይ ነገር እንደሌለበት ነው።» በማለት አብራርተዋል።
"لقاء الباب المفتوح" - (15 / 4-5)

② *መስገዱ ለምን አስፈለገ?*
ጌታችን አላህ የፀሃይ ወይም የጨረቃ ግርዶሽ እንዲፈጠር በማድረግ ባሮቹን ያስፈራራበታል። በዚህም ሊወርድባቸው የሚችል ቅጣትና መዓት እንዳለ በመጠቆም ለዚያ ጥበበኛና ሃያል ፈጣሪያቸው ሰግደው በመፀለይ፣ ከኃጢኣታቸው በመመለስ ይቅርታንና ምህረትን በመጠየቅ፣ የሱን ሃያልነትና ታላቅነት በተክቢር በመግለፅና ለሱ ሲሉ ሰደቃ በመስጠት ሲለማመኑት ሊከሰት ከሚችለው አደጋ ይጠብቃቸዋል።
ነቢዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ስለ ክስተቱ ሲገልፁ
( هَذِهِ الْآيَاتُ الَّتِي يُرْسِلُ اللَّهُ لَا تَكُونُ لِمَوْتِ أَحَدٍ وَلَا لِحَيَاتِهِ وَلَكِنْ يُخَوِّفُ اللَّهُ بِهِ عِبَادَهُ ؛ فَإِذَا رَأَيْتُمْ شَيْئًا مِنْ ذَلِكَ فَافْزَعُوا إِلَى ذِكْرِهِ وَدُعَائِهِ وَاسْتِغْفَارِهِ ).
«ይህች ተዓምር ማንም ስለሞተ ወይም በህይወት ስለተገኘ አላህ የሚልካት አይደለችም። ነገር ግን አላህ ባሮቹን የሚያስፈራራበት ክስተት ነውና ከዚህ ጉዳይ የሆነ ነገር ካያችሁ አላህን ወደ ማውሳት፣ ወደ መለመንና ምህረቱን ወደ መጠየቅ በፍራቻ ሽሹ።» ብለዋል።
وروى البخاري (1059) ومسلم (912)

ኢብኑ ሀጀር ረሂመሁላህ ወደዚያ ደንብሩ የሚለውን ቃል ሲተነትኑ «ፈፍዘዑ (فَأَفْزَعُوا) ማለት ወደሱ ተመለሱ፣ ተቅጣጩ ለማለት ነው። በዚህ አገላለፅ ውስጥ ወደ ታዘዙት ነገሮች መሽቀዳደምን የሚጠቁም መልዕክት ኣለ። አስጊ ነገር ሲገጥም ወደ አላህ የሚሸሸው ደግሞ ድንበር ጥሰው የፈፀሙት ወንጀል እንዲሰረይ ሰበቡን ለማድረስ እሱን በመለመንና ምህረቱን በመጠየቅ ነው።
በዚህ ተግባር የሚሰጋው ነገር እንደሚወገድ ይከጀላል። ምክንያቱም ወንጀሎች ለመዓት መውረድና ለቅርቡም ሆነ ለሩቁ ቅጣት መምጣት ሰበብ ናቸውና።» ብለዋል።
"فتح الباري" (2/534) .

ሸይኽ ሳሊህ አስስንዲ ሀፊዘሁላህ ስለ ግርዶሹ ባስተላለፉት መልእክት መካከል የሚቀጥለውን ብለዋል።☞
«አላህ ባሮቹን ያስፈራራበታል የሚለውን ቃል ሲያስረዱ “ማስፈራራት ማለት ማስፈራርያን የሚያስከትል ነገር ሲገኝ ይከሰታል ለማለት ነው። ይህ ደግሞ ለቅጣት ሰበብ የሚሆን ወይም ለዚያ የሚዳርግ ምልክት ሲገኝ እንጂ ማስፈራርያ አይመጣም። ግርዶሽ ደግሞ ለምድር ነዋሪዎች የቅጣት መከሰት ምልክት ሆኖ መምጣቱ ይታወቃል።” ብለዋል በማለት የኢብኑ ተይሚያን ንግግር ጠቅሰዋል። ረሂመሁላህ።

በግርዶሽ መከሰት ሊደረጉ የሚገባቸውን ነገሮች ሲገልፁ ደግሞ
«በጨረቃ ግርዶች መከሰት ሰበብ ሊደረጉ የሚገቡ የሆኑ በሱና የተጠቆሙ ጉዳዮች ወደ ሰባት ነገሮች ናቸው። እነሱም በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገቡ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ በአንዳቸው ብቻ የተዘገበ ነው። ዝርዝሩም
1ኛ/ الصلاة ሰላት
2ኛ/ الدعاء ዱዓእ
3ኛ/ ذكر الله አላህን ማውሳት ማወደስ
4ኛ/ الاستغفار ምህረትን መጠየቅ
5ኛ/ التكبير ተክቢር
6ኛ/ الصدقة ሰደቃ
7ኛ/ العتق ባርያን ነፃ ማውጣት ናቸው።» ብለዋል። በማስከተልም የሰው ልጅ ይህን መሰረታዊ ጉዳይ መዘንጋቱን ሲገልፁ

«የሚያሳዝነው ጉዳይ ግን ይህች በሰው ልጆች ላይ እየተመላለሰች የምትከሰተው የጨረቃ መጋረድ ታላቅ የሆነ ተዓምር ከመሆኑም ጋር የተወሰኑ ሰዎች ሙንከር ነገርን እየተጠጡም ሳሉ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አይታዩም። ኢና ሊላሂ ወኢና ኢለይሂ ራጂዑን።
ነቢዩﷺ ግን በዘመናቸው ፀሃይ ስትጋረድ በርግገው በፍጥነት ወደ መስጂድ ሄዱ። ከድንጋጤያቸው የተነሳም ሽርጣቸውን መሬት ላይ እየጎተቱ ነበርና ለሰሃቦቹ «فافزعوا» በስጋት ሽሹ እስኪሏቸው ድረስም ስለ ልብሳቸው አላሰቡምና ከመሰብሰብ ዘግይተው ነበር።» ብለዋል።
• موعظة عن آية الخسوف للشيخ أ. د. صالح سندي.

*ኩሱፍ የሚከሰትበትን ወቅት መገመት ብሎም ማወቅ ይቻላልን?*
የፀሃይ ወይም የጨረቃ ግርዶሽ ሊከሰት የሚችልበትን ወቅት ማወቅ ወይም መገመት ከሩቅ ሚስጥር ወይም ጘይብን ለማወቅ ከመጣር የሚቆጠር አይደለም። ይልቁንም እሽርክሪቶቻቸውን በማስላት መቸና የት ሊከሰት እንደሚችል መገመት ይቻላል። ይሁንና በካልኩሌሽኑ ላይ ብቻ በመመርኮዝ በግርዶሹ ሰበብ የሚሰገደው ሰላት እንዲሰገድ አይታዘዝም። ሰላቱ የሚሰገደው ግርዶሹ በግልፅ ተከስቶ በዐይን ከታየ በኋላ ነውና።
በዚሁ አጋጣሚ የሚመከረው ጉዳይ የፀሃይ ወይም የጨረቃ ግርዶሽ ባለተከሰተባቸው አካባቢ ያሉ ሙስሊሞች አጎራባች ሀገራት ላይ መከሰቱን በመስማት ብቻ ሊሰግዱ አይገባም። ነቢዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም መስገድን ያቆራኙት ግርዶሹን ከማየት ጋር ነውና በዜና ወይም በከዋክብት ተማራማሪዎች ግምታዊ ስሌት ብቻ መስገድ አይፈቀድም። ለዚህም ከልካይ የሚሆን መመርያ ኣለ።
አላህ አዝዘ ወጀልለ በቅዱስ ቃሉ በሱረቱል አህዛብ 21ኛው አንቀፅ ላይ «በአላህ መልዕክተኛ ላይ በእርግጥም መልካም የሆነ አርዓያነት አለላችሁ።» ብሏል። በአል ሀሽር ሱራ ሰባተኛው አንቀፅ ላይ ደግሞ « መልዕክተኛው የሰጣችሁን ውሰዱት። የከለከላችሁን ደግሞ ተዉት።» በማለት ለማንኛውም አምልኳዊም ሆነ ሌላ ስርዓት እሳቸው በሰጡን መመርያ ብቻ እንድንራመድ አዝዞናል። በአል ኑር ምዕራፍ 68ኛው አንቀፅ ደግሞ «እነዚያ የሱን ትዕዛዝ የሚፃረሩ ሰዎች ፈተና እንዳትገጥማቸው ወይም አሳማሚ የሆነች ቅጣት እንዳትደርስባቸው ይጠንቀቁ።» ሲል በዲን ጉዳይ ላይ ቀልድ ሆነ ፍልስፍና ቦታ እንደሌለው በዛቻ ገልፇል።
*የኩሱፍ ሰላት ሸሪዓዊ ብይን ምን ይሆን?*
በግርዶሹ ምክንያት የሚሰገደው ሰላት ሸሪዓዊ ብይኑ ጠንከር ያለ ሱና ማለትም "ሱንና ሙአከዳህ" በመባል በፉቀሃእ ዘንድ ይታወቃል። ስለዚህ ግርዶሹ በተከሰተበት አካባቢ ያሉ ሙስሊሞች ተጠራርተውና ተሰባስበው አላህን ለመለመን መስገዳቸው ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን አላህ እንዲመልስላቸው ከመማፀንም ባለፈ ከፍ ያለ ምንዳ የሚያስገኝ ተግባርም ነው።
*ሰዎች ለሰላቱ እንዴት ይሰበሰባሉ?*
ለኩሱፍ ሰላት የያከባቢውን ሙስሊም ማህበረሰብ ጠርቶ በጋራ በመስገድ አላህን መለመን ከላይ እንደተገለፀው ጠንከር ያለ ሱንና ነው። ለዚህም ራሱን የቻለ የአጠራር ስልት አለው። እሱም "አስሰላቱ ጃሚዓ" የሚል ሲሆን ሰዎች መስማታቸው እርግጠኛ እስኪኮን ድረስም ይህን ቃል መደጋገም ይቻላልና ይህን ያህል ግዜ ብቻ ነው ጥሪ የሚደረገው ተብሎ የተገደበ ነገር የለውም። ይህም ቃል በነቢዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ዘመን ተፈጥሮ በነበረው የጨረቃ ግርዶሽ ወቅት በተሰገደው ሰላት ታሪክ ላይ ተዘግቧል።
*የሚታየው ነገር በምን ደረጃ ሲሆን ነው ሰላቱ የሚሰገደው?*
ሰማይ በጉም ከተሸፈነች ግርዶሹ በዐይን እስኪታይ ድረስ ለኩሱፉ አይሰገድም። በስነ ኮከብ አጥኚዎች ዜናና ትንታኔ ላይ ብቻ በመመርኮዝም አይሰገድም። ዞሮ ዞሮ ግርዶሹ በተጨባጭ ከታየን ብቻ ነው የሚሰገደው። በሌላ በኩል "የክልከላ ግዜያት" በመባል በሚታወቁ ሰላት ከመስገድ እንድንቆጠብ በተደረጉባቸው ጊዜያትም ቢሆን የኩሱፍ ሰላት ይሰገዳል።
*የኩሱፍ ሰላት አሰጋገድ እንዴት ይሆን?*
① የኩሱፍ ሰላትን በህብረት ሆኖ መስገድ ይቻላል። ሱንናም ነው። ጀማዓ ያመለጠው ወይም ያላገኘ ሰው ግን ልክ በጀማዓ ሲኮን እንደሚሰገደው ለብቻውም ቢሆን የሱንና ሰላቶችን እንደሚሰግደው እቤቱ ሆኖ መስገድ ይችላል።
② ሰላቱን ረዘም ማድረግ የተደነገገ ጉዳይ ነውና በተለይ በጀማዓ በሚሰገድበት ግዜ
ኢማሙ ቁርኣንን በቃሉ ያልሸመደደ የሆነ እንደሆን እንኳን ቁርኣንን ከፍቶ እያነበበ ማስሰገድ ይችላል።

③ ኢማሙ ከሰላቱ በኋላ በቃሉም ሆነ ከወረቀት እያነበበ ሰዎችን ለመምከር፣ ለማስታወስ፣ የአላህን ቅጣት እንዲጠነቀቁት በማስፈራራትና ንስሃ እንዲገቡ በመገፋፋት አንድ ግዜ ኹጥባ ማድረጉ ሱና ነው።
④ ኢማሙ እያሰገደ ሳለ ዘግይቶ የመጣ ሰው አንድ ሙሉ ረከዓ አግኝቷል የሚባለው ቢያንስ የመጀመርያዋ ሩኩዕ ላይ የደረሰ እንደሆነ ነው። ይህች የመጀመርያዋ ሩኩዕ ካመለጠችው ግን አንድ ሙሉ ረከዓ እንዳመለጠው ነውና የሚቆጠረው ሩኩዖችንም ሱጁዶችንም ሙሉ በሙሉ መተካት አለበት። እንደሚታወቀው የኩሱፍ ሰላት አሰጋገድ በየ እለቱ አምስቴ ከምንሰግደው የግዴታ ሰላት ለየት ያለ ነውና በአንድ ረከዓ ላይ ሩኩዕ የሚደረገው ማለትም ጎንበስ የሚባለው ሁለቴ ነው። በዚህ ጨኳኋን ከሌሎቹ ሰላቶች ይለያል። ሱጁድ ግን ልክ ሌላው ሰላት ለያንዳንዱ ረከዓ ሁለት ሁለቴ ነው የሚደረገው።
⑤ ሴት ልጅ የኩሱፍ ሰላትን መስገድ ከፈለገች እንደ ወንዶቹ ሁሉ መስጂድ ሄዳ በጀመዓ መስገድ ትችላለች። ከፈለገች ደግሞ እቤቷ ሆና መስገድ ትችላለች።
*የአሰጋገድ ገፅታው ምን ይመስላል?*
የኩሱፍ ሰላት ሁለት ረከዓ ነው። በእያንዳንዱ ረከዓ ሁለት ግዜ ተቁሞ የፋቲሃ ምዕራፍ እና ተጨማሪ ሌላ ምዕራፍ ይቀርራል። ሁለት ግዜ ሩኩዕ ይደረጋል። ሱጁዱ ደግሞ እንደ ማንኛውም ሰላት ሁለት ግዜ ብቻ ሲሆን ተሸሁድና ሰላምታም እንደሌሎቹ ሰላቶች ይሆናል።
*አሰጋገዱን በዝርዝር ብናየውስ?*
በቅድሚያ በተክቢረቱል ኢህራም ማለትም አላሁ አክበር በማለት ወደ ሰላቱ ይገባል።

 ከዚያም ሱረቱል ፋቲሃ ይቀርራል።
 ከዚያም ተጨማሪ በጣም ረዘም ያለ ምዕራፍ ይነበባል።
 ከዚያም ረዘም ያለ ሩኩዕ ይደረጋል። ማለትም ረዘም ላሉ ደቂቃዎች ይጎነበሳል።
 ከዚያም ቀና በማለት ቀጥ ተብሎ ይቆምና እንደገና ሱረቱል ፋቲሃ ይነበባል። 
 ከዚያም በመጀመርያው ረከዓ ላይ ከተቀራው የቁርኣን መጠን በተወሰነ ደረጃ አነስ ባለ መጠን ይቀርራል። 
 ከዚያም እንደገና ለሩኩዕ ጎንበስ ይባላል።
 ከዚያም ቀና ይባላል። 
 ከዚያም ወደ ሱጁድ ይወረድና ሁለት ግዜ በረዥሙ ሱጁድ ይደረጋል። በዚህ አይነት የመጀመርያው ረከዓ የተሟላ ይሆናል።
 ከዚያም ለሁለተኛው ረከዓ በመነሳት ይቆማል። ፋቲሃ ይቀርራል። ልክ እንደ የመጀመርያው ረከዓ ሁሉም ስርዓት ይደገማል።
 ከዚያም ለተሸሁድ በመቀመጥ አትተህያ ይነበባል። በመጨረሻም በሁለቱ ሰላምታዎች ሰላቱ ይጠናቀቃል።

والله أعلم وصلى الله وسلم على نبينا محمد وعلى آله وصحبه أجمعين.

≅∷≅∷≅∷≅∷≅∷≅∷≅∷≅

✍🏽Abufewzan

ዙል ቂዕዳ 15/1439
July 28/2018

Post a Comment

2 Comments