Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የተካኑ ሃሜተኞች!!


የተካኑ ሃሜተኞች!!

እኔ እምለው ወንድሞች! ለካስ ሃሜትም ክህሎት ይጠይቃል!! አንዳንዱ ሃሜቱ ያፈጠጠ ያገጠጠ ስለሚሆን ሩሕ ያለው ሰው ሲሰማው ይቀፈዋል፣ ነገረ-ስራው ሁሉ ያንገሸግሸዋል፡፡ አንዳንዱ ግን እሳት የላሰ ሃሜተኛ አለ፡፡ ከሃሜት ባህር ውስጥ ሲያስቀዝፍህ ውሎ ነገር ግን ቅንጣት ታክል እያማ እንደሆነ የማትባንንበት መሰሪ፡፡ ባጭሩ የሰው ስጋ በሊታ የሆኑት ሃሜተኞች ከጥፋት ደረጃቸው ብቻ ሳይሆን ከአበላል ክህሎታቸውም አንፃር ሲታዩ ብዙ መልክ አላቸው፡፡ አንዳንዱ የሰው ስጋ ሲበላ ከነ ልብሱ ነው ከነጫማው፡፡ ያለምንም ጥንቃቄ ያገኘውን ሁሉ የሚጎሰጉስ፡፡ ሌላው ግን የተካነ ነው፣ እየዘለዘለ፣ እየመተረ፣ እያቁላላ የሚበላ፡፡ ክህሎቱ ግን በክፋት ላይ ስለሆነ በራሱ ላይ ነው፡፡ “ጭራቅ ሹካና ቢላዋ ቢጠቀም ሰለጠነ ይባላል ወይ?!”

አንዳንዱ ሃሜቱ ከቅጥፈት ጋር የተቀየጠ ነው፡፡ በባሌም በቦሌም ብሎ የሚያማውን ሰው ማሳጣት ነው ህልሙ፡፡ እንዲህ አይነቱ ሃሜተኛ የሚታማውን ሰው ባለበት ብቻ ሳይሆን በሌለበትም ጭምር ከማብጠልጠል አይመለስም፡፡ በርግጥ እንዲህ አይነቱን ቀጣፊ “ሃሜተኛ” የሚለው ቃል በበቂ ሁኔታ አይገልፀውም፡፡ ምክንያቱም ሃሜት ማለት በሰውየው ላይ በተጨባጭ ያለውን እንዲነሳ የማይፈልገውን ነገር በሌለበት ማንሳት ነውና፡፡ ስለዚህ አንድን ሰው ያልፈፀመውንም ጭምር እየጫነ በክፉ የሚያነሳ ሰው “ሃሜተኛ” ከሚለው ገላጭ በፊት “ቀጣፊ” የሚል “የማእረግ” ስም ሊታከልለት ይገባል፡፡

ወደ ነገሬ ስመለስ በዚህ ፅሁፍ ስር መጠቆም የፈለግኩት አጠቃላይ ስለ ሃሜት ምንነት፣ አስከፊነት እና አደጋዎች መዘርዘር አይደለም፡፡ ይልቁንም አንዳንዶች የህሊና ሙግት ውስጥ ሲገቡ ወይም አድማጫቸው ሃሜተኛ እንዳይላቸው በመስጋት የሚዘይዷቸው ብልጣብልጥ የሃሜት ታክቲኮች በብዛት የጋራ ጥፋቶች ስለሆኑ እራሴንም ጭምር ማስታወስ ነው፡፡ ባዲስ መስመር እንገናኝ

1. አንዳንዱ ግብዝ ነው፡፡ እራሱን እያጥራራ ለሃሜት አፉን የሚያሾል፡፡ “እኔ ማንንም በክፉ ማንሳት አልወድም፡፡ ሃሜትና ውሸት አይመቸኝም፡፡ የማወራችሁ በተጨባጭ ያለውን ነገር ነው፡፡ ለማማት አይደለም፡፡ ከፊቱም ቢሆን የምናገረው ነው” ይላል፡፡ አንተ የጂል ብልጥ ሆይ! ይሄ ብልጥነትህ የምታወራቸውን ፈዛዛ ወይም አድር ባይ ሃሜተኞች አፍ ከማዘጋት ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡ አንተ በተናገርከው እነሱ ባዳመጡት ነገ ከአላህ ፊት ትጠየቃላችሁ!!

2. አንዳንዱ የሚታማው ሰው ከሚወነጀልበት ወይም ቢያንስ ከከፊሉ እንኳን ንጹህ እንደሆነ እያወቀ በቦታው ያሉ ሌሎች ሃሜተኞችን ላለማስከፋት ሲል አብሮ የሚያማ አለ፡፡ ሲቆጡ ይቆጣል፣ ሲቀጥፉ ይቀጥፋል፣ ሲዋኙ ይዋኛል፡፡ “ኧረ አላህን እንፍራ! ሃሜት ላይ ነው ያለነው” እንዳይል ከሃሜት አራጋቢዎቹ ልቦና ውስጥ የሚፈጠረውን ነገር በማሰብ ይጨነቃል፣ ድፍረትም ያጣል፡፡ ስለሆነም ምናልባት ተሽሎ ምላሱ ከሃሜት ቢቆጠብ እንኳን ሃሜተኞቹ ሲስቁ እየሳቀ፣ በአዎንታ እራሱን እየነቀነቀ፣ ሳይደነቅ እየተደነቀ፣… የሃሜት ድግሳቸውን ያደምቃል፡፡ ወንድሜ ከነዚህ ሃሜተኞች ይልቅ ጌታህን ፍራ!! እነዚህ ሃሜተኞች እሳት የላቸው ጀነት የላቸው፡፡ ደግሞ “ነግ በኔ” በል፡፡ ዛሬ እከሌን ያሙ ሰዎች ነገ ተረኛ ያደርጉሃል፡፡ “ጓደኛህ ሲታማ ለኔ ብለህ ስማ” ይላል ብሂላችን፡፡ ስለዚህ “አላህን ፍራ” በልና ሁለቱንም ወንድሞችህን እርዳቸው፡፡ አንዱን በሃሜት ወንጀል ጌታው ፊት እንዳይጠየቅ፣ ሌላውን በሌለበት እንዳይበደል፡፡

3. አንዳንዱ ደግሞ “እከሌ! እሱ እኮ ሚስኪን ነው! ጥሩ ሰው ነው፡፡ ነገር ግን እንዲህ እንዲህ አለበት” ይላል፡፡ አድኖ መግደል መሆኑ ነው፡፡ ሃሜተኛ እንዳይባል፣ ሚዛናዊ ለመምሰል ጠንካራ ጎኑንም አብሮ ይጠቅሳል፡፡ እንዲህ አይነቱ ብልጥ መሳይ ከሰዎች ዘንድ “ሃሜተኛ” ከሚለው ቅፅል ሊያመልጥ ይችላል፡፡ ከጠቢቡ ጌታ ዘንድ ግን “ሃሜተኛ” ከመባል በዚህ ብልጠቱ አያመልጥም፡፡

4. አንዳንዱ ደግሞ የሆነ ሰው ስሙ በክፉ ሲነሳ “ተውን ተውን! እሱን አታንሱ! እኛንም እሱንም አላህ ይቅር ይበለን” ይላል፡፡ አላማው የሰውየውን ክብር ዝቅ ማድረግ ነው፡፡ ሃሜትን እያሽሞነሞኑ ዲናዊ ቅብ ቀብተው ያቀርቡታል፡፡ ልክ ፍጡርን እንደሚያታልሉት አላህን ሊያታልሉ ያስባሉ፡፡

5. አንዳንዱ ሌላውን ከፍ በማድረግ አስታኮ እራሱን የሚሰቅል እራሱን የሚቆልል አለ፡፡ “ሌሊት ላይ በሶላቴ ውስጥ ለእከሌ ዱዓእ አድርጌ ቢሆን ኖሮ ከእሱ እንዲህ አይነት ነገር ባልደረሰኝ ነበር” ይላል፡፡ ስልታዊ በሆነ መልኩ እራስን መስቀል፣ ስልታዊ በሆነ ታክቲክ ሌላውን ማውረድ!!

6. አንዳንዱ እራሱን ከፍ ለማድረግ ሲል ሃሜት ላይ የሚወድቅ፣ በሌሎች ክብር የሚረማመድ አለ፡፡ “እከሌ ደደብ ነው! አስተሳሰቡ የደከመ!” ይላል፡፡ አላማው እራሱን ማወደስ ነው፣ ከሚታማው ሰው እራሱን አስበልጦ ማቅረብ፡፡ በተለይ የሚታማው ሰው ዘንድ የሆነ ከሱ የተሻለ ነገር ካለ ጥፋቱ ድርብ ይሆናል፡፡ ምቀኝነትና ሃሜት!! ምቀኝነቱ እየጋለበው በሃሜት ይጨማለቃል፡፡

7. አንዳንዱ ደግሞ ሃሜቱን በቀልድና በሹፈት መልክ የሚያወጣው አለ፡፡ በቀልድ እያዋዛ፣ በሳቅ እየጠቀለለ ለፉዞ አድማጮቹ ሃሜት ያውጣቸዋል፡፡ ክፉ ብልሃት!! በሹፈት መልክ የሌላውን ነውር ያወጣል፡፡ በሹፈት መልክ አነጋገሩን፣ አለባበሱን፣ አካሄዱን፣ አሳሳቁን፣ … እያሳቀ፣ እያስመሰለ፣ እየፎገረ፣… ያቀርባል፡፡ በዚህ ተንኮሉም ሌሎችን በሳቅ፣ በፉገራ እንዲያጅቡት ይጋብዛል፡፡ ሰይጣናዊ ታክቲክ!!

8. አንዳንዱ ደግሞ ሃሜቱን በመደነቅ መልክ የሚያወጣው አለ፡፡ “እኔ ግን የሚገርመኝ የእከሌ ነገር ነው!! እንዴት እንዲህ ይላል? እንዴት እንዲህ ያደርጋል?! እንዴት እንዲህ ይለብሳል?!” እያለ በማያገባው ለሃሜት ያኮበኩባል፡፡ ይሄ አደገኛ ብልጠት አላህ የጠበቀው ሲቀር አድማጭንም የጥፋቱ አካል የሚያደርግ ነው፡፡ የዋህ የሆነ አድማጭ አፉን ከፍቶ ሲያዳምጥ ይቆይና የሚያውቀውንም የማያውቀውንም ከሃሜቱ ላይ ይጨምራል፡፡

9. አንዳንዱ ደግሞ ተቆርቋሪ መስሎ ሃሜቱን የሚያቀርብ አለ፡፡ “እኔ ግን የእከሌ ነገር ያሳዝነኛል” ይልና ወይም ደግሞ “ግን እከሌ እንዲህ ማድረጉ ለሱ ጥሩ ይመስላችኋል?” ብሎ አዛኝ በሆነ ሙድ የሚያማ አለ፡፡ “አስመሳይ ቅቤ አንጓች” ይሏል እንዲህ ነው፡፡ አድማጭ ከመቆርቆር የመነጨ ስለሚመስለው አብሮ ይጨነቃል፡፡ አቶ ሃሜተኛ ግን የሚፈልገው ቂም ያረገዘ ውስጡን ስልታዊ በሆነ መንገድ በሃሜት ማርካት ነው፡፡ “ሃሜተኛ” እንዳይባል ግን እንዲህ አይነት ዘዴ ዘይዷል፡፡ የጥፋቱ ውጤት ወደራሱ እንደሚመለስ ቢያስተውል ኖሮ ይሄ ብልጠቱ ቂልነት እንደሆነ ይገባው ነበር፡፡

10. አንዳንዱ ደግሞ ሆን ብሎ አንድን ሰው ከሚጠሉት ሰዎች መሃል ያወሳል፡፡ አላማው ሰውየውን የነሱ የሃሜት ሲሳይ ማድረግ ነው፡፡ ቂማቸውን እንዲያራግፉበት አሳልፎ መስጠት፡፡ ይሄ እጅግ አስቀያሚ ከሆኑ የልብ በሽታዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ አላህንም ሰውንም ለመሸወድ አጉል መጣር፡፡

11. አንዳንዱ ደግሞ ሃሜቱን ለአላህ ብሎ በመቆጣት፣ ጥፋትን በመቃወም ስም የሚፈፅም አለ፡፡ አላማው ግን ከውጭ እንደሚያንፀባርቀው ሳይሆን በቀል ወይም ምቀኝነት ይሆናል፡፡ በርግጥ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ አጥፊን ስሙን ጭምር አንስቶ ማስጠንቀቅ ሊወደድ አልፎም ግዴታም ጭምር ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህን ሸሪዐዊ ልዩ ፈቃድ አስታኮ፣ ለዲን መቆርቆር አስመስሎ በሌላ ኒያህ ሌላውን የሚያጎድፍ ከሆነ ያለጥርጥር ድርጊቱ ሃሜት ነው፡፡

12. አንዳንዱ ደግሞ “እነ እከሌ ሃሜተኞች ናቸው!” እያለ የነሱን “ክፋት” የሃሜትን አስቀያሚነት እያጣቀሰ ሊያስረዳ ይሞክራል፡፡ የሱ ድርጊት ሃሜት እንደሆነ ግን ወይ አይገባውም፡፡ (አንድ ክፋት!!) ወይ ደግሞ እንዲገባው አይፈልግም፡፡ (ድርብ ጥፋት!!) ሌሎችን በሃሜት ምክንያት ያብጠለጥላል፡፡ እሱ ግን ፈቃድ የተሰጠው ይመስል እንዳሻው ከሃሜት ባህር ውስጥ ይዋኛል፡፡ እንዲህ አይነቱን “አትሙ” እያለ የሚያማ ከህሊናው ጋር የተኳረፈ የዋህ “አንተስ ምንድን ነው እየሰራህ ያለኸው?” ብሎ አፉን ማስያዝ ያስፈልጋል፡፡ ምናልባት ማስተዋሉን ካልተነጠቀ ዳግም ወደዚህ ጥፋት እንዳይመለስ ያግዘዋልና፡፡

እነዚህን ሀሳቦች ብዙዎቹን የወሰድኳቸው ከታላቁ ዓሊም ከአሕመድ ኢብኑ ተይሚያ ነው ረሒመሁላህ፡፡ (መጅሙዑልፈታዋ፡ 28/236-238)

ወንድሞች እህቶች ሆይ! እስኪ ረጋ ብለን እራሳችንን እንፈትሽ፡፡ እውን እኛ ከነዚህ የጥፋት መስመሮች ተርፈናል? ከሆነ ምንኛ መታደል ነው?!! እኔ ግን እጅግ አስፈሪ ሆኖብኛል፡፡ ብዙዎቻችሁም እኔን የሚሰማኝ እንደሚሰማችሁ እጠብቃለሁ፡፡ አላህ ምላሳችንን ሃሜት ከመፈፀም፣ ጆሯችንን ሃሜት ከማዳመጥ ይጠብቅልን፡፡ አጥፊዎችን “አላህን ፍሩ!” የማለት ወኔውንም ያድለን፡፡

በመጨረሻም አስተዋይ የሚማርበት አንድ ከርእሳችን ጋር የሚዛመድ የሚደንቅ ክስተት ላንሳና ፅሁፌን ልቋጭ፡፡ ድርጊቱ የተፈፀመው ጥንት ነው፣ በሰለፎቹ ዘመን፡፡ ታሪኩን የሚተርከው ሱፍያን ኢብኑ ሑሰይን ይባላል ረሒመሁላህ፡፡ ከራሱ አንደበት ይሄውና፡-

“በአንድ ወቅት ኢያስ ኢብኑ ሙዓውያ ዘንድ ነበርኩ፡፡ ከሱ ጋር የሆነ ሰው አለ፡፡ ተነስቼ ብሄድ ሰውየው በክፉ ያነሳኛል ብየ ሰጋሁ፡፡ እናም ተነስቶ እስከሚሄድ ድረስ ተቀመጬ መጠበቅ ያዝኩኝ፡፡ ተነስቶ ሲሄድ ጊዜ ለኢያስ ስለሰውየው ማውራት ያዝኩት፡፡ እኔ ሳወራ ኢያስ ፊት ፊቴን ይመለከተኛል፡፡ እስከምጨርስ ድረስ ምንም አልተነፈሰም፡፡ ከዚያም

“ደይለም ሃገር ዘምተሃል?” አለኝ፡፡ “አልዘመትኩም” አልኩት፡፡

“ሲንድ ዘምተሃል?” አለኝ፡፡ “አልዘመትኩም” አልኩት፡፡

“ሮም ዘምተሃል?” አለኝ፡፡ “አልዘመትኩም” አልኩት፡፡

ከዚያም፡- “(ከሃዲዎቹ) ደይለም፣ ሲንድ፣ ህንድ እና ሮም ካንተ ሰላም አግኝተው ሳለ ይሄ ወንድምህ ግን ካንተ ሰላም አያገኝም ማለት ነው?!!” አለኝ፡፡ [አልመዕሪፋህ ወትታሪኽ ሊልፈሰዊ፡ 2/95]

(ኢብኑ ሙነወር፣ ህዳር 26/2008)