Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ከእኛ አይጠበቅም! እንደው ግርም ከሚሉኝ ፍጡራን መካከል መንገድ ላይ ቆሞ፤ ጀርባውን ለኛ .. ፊቱን ደግሞ ለግድግዳው ሰጥቶ፤ ሃፍረተ ገላውን ገልጦ፤ ልክ እንደ መንደር ውሻ ሰው የሚተላለፍበት መንገድ የሚሸና ሰ...ው ነው!!

Abu Aisha
ከእኛ አይጠበቅም!
እንደው ግርም ከሚሉኝ ፍጡራን መካከል መንገድ ላይ ቆሞ፤ ጀርባውን ለኛ .. ፊቱን ደግሞ ለግድግዳው ሰጥቶ፤ ሃፍረተ ገላውን ገልጦ፤ ልክ እንደ መንደር ውሻ ሰው የሚተላለፍበት መንገድ የሚሸና ሰ...ው ነው!!
ደግሞ ’ኮ እኔ የሚገርመኝ ... ተመስጦና ፈታ ብሎ ሲሸና ሲታይ .. እየሸና ሳይሆን የቤቱን አበባ ውሃ እያጠጣ ነው የሚመስለው! ሆሆ!
ድልድይ ውስጥ ፣ የሕዝብ መተላለፊያ ግድግዳዎች ላይ የሚሸናው የሽንት መአት እንደጉድ አፍንጫ ይቆርጣል! ደግሞ “እዚህ የሸና አስር ብር ይቀጣል!” የሚለው ማስታወቂያ “አስር ብር ይሸለማል! ” የተባለ ይመስል እንደውም ማስጠንቀቂያው ከተለጠፈባቸው ግንቦች የሚወጣው የሽንት ሽታ ምርጥ የፓሪስ ሽቶን ያስንቃል!
አንዳንዴ በብዛት ባይስተዋልም ሙስሊሞችም የዚህ ፀያፍ ተግባር ተሳታፊ ሲሆኑ ይታያል! ይህ በጣም የሚያሳፍርና ከእኛ ከንፁሆቹ ሙስሊሞች የማይጠበቅ ተግባር ነው።
ሽንትን የሰው መተላለፊያ መንገድ ላይ መሽናት ከበርካታ ሸሪዓዊ እይታዎች አንፃር የተወገዘ ተግባር ነው!
1) አንደኛውና የመጀመሪያው ሃያእ (እፍረት) ማጣት ነው። እንደ ሙስሊም አንድ ወንድ ሃፍረተ ገላውን በሰው መሃል አውጥቶ መፀዳዳቱ እጅግ የሚያሳፍርና ስብእናን የሚያዋርድ ተግባር ነው። “ካላፈርክ ያሻህን ስራ!” የሚሉት ነቢይ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ይሉናል “ሁለት ሰዎች ሃፍረተ ገላቸውን ገልጠው እየተያዩ ማውራታቸው አላህ ዘንድ የተጠላ ተግባር ነው።” [አቡ ዳውድ እና አሕመድ ዘግበውታል] ሌላው ቲርሚዚይ በዘገቡት ሐዲስ ሙጊራህ ቢን ሹዕባህ እንዲህ ይላል: – “ከአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ጋር ተጉዤ ነበር። መገለጥ (መፀዳዳት) በፈለጉ ጊዜ ከኔ ርቀው ሩቅ ይሄዱ ነበር።”
2) ሁለተኛው የንፅህና ጉዳይ ነው። አንድ ሙስሊም በቅድሚያ ግድግዳ ላይም ሆነ መሬት ሲሸና ሽንቱ ተፈናጥሮ ወደልብሱ ይረጫል። ይህ ማለት በቀላሉ ልብሱ ተነጅሷል ማለት ነው። ሲቀጥል ጡሃራ ለማድረግ ውሃ የሚያገኝበት አጋጣሚ አይኖርም ። በድንጋይ አሊያም በሶፍት ላደራርቅ ማለቱ ባይከፋም ስንቶች ናቸው መንገድ ላይ ከአሁን አሁን የሚያቀኝ ሰው አየኝ፣ ሰው ምን ይለኛል ... እያሉ በደንብ ሳያደራርቁ ልብሳቸውን የሚለብሱት?
እናታችን ዓኢሻ ለሰሐቢያቶች እንዲህ ብላ መንገሯ ተዘግቧል: – “ባሎቻችሁ በውሃ እንዲፀዳዱ ንገሯቸው። እኔ ለመንገር አፍሬ ነው ። እንደዚህ ነበር የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በብዛት የሚያደርጉት ።” [ቲርሚዚይ ዘግበውታል]
አንድ ሙስሊም ሲፀዳዳ ካገኘ ውሃ ካላገኘም ሶስት ድንጋይ ሊጠቀም ይገባል ። ሲፀዳዳም በደንብ እስኪፀዳ ሊፀዳዳ የተገባ ነው ። ኢብን አባስ ረዲየላሁ ዐንሁ ባስተላለፉት ሐዲስ ረሱል ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የአንድ ሰውየ ቀብር ዘንድ እያለፉ በቀላል ጥፋት እየተቀጣ መሆኑን ተናግረው ምክንያቱን ሲያስተላልፉ “ (በበቂ ሁኔታ) ባለመፀዳዳቱ ነው ” ብለው መመለሳቸውን ቡኻሪ ዘግበውታል።
3) ቆሞ መሽናት የተጠላ መሆኑ! እናታችን ዓኢሻ ረዲየላሁ ዓንሃ እንዲህ ትላለች “የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ቆመው ሸንተዋል የሚላችሁን አትመኑት። ሁሌም ቢሆን ሲሸኑ ቁጭ ይሉ ነበር።” [ነሳኢይ፣ ኢብን ማጃህ፣ አሕመድ]
የዓኢሻን ቃል ታኮ ሁዘይፋ ረዲየላሁ ዐንሁ የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አንድ ክስተት ላይ “ቆመው ሲሸኑ ተመለከትኳቸው” የሚለውን ሐዲስ አያይዘው የኢስላም ሊቃውንት “ቆሞ መሽናት የተከለከለ ተግባር ባይሆንም ሱናውና የተወደደው ግን ተቀምዶ መሽናት ነው።” የሚል ፈታዋ ሰጥተዋል ። [አሽሸይኽ ዐብዱ’ላህ ኢብን ቀዑድ፣ አሽሸይኽ ዐብዱ’ረዛቅ አልዐፊፊ፣ አሽሸይኽ ዐብዲ’ላህ ኢብን ጙዳያን፣ ዐብዱል’ዐዚዝ ቢን ዐብዱላህ ኢብን ባዝ ናቸው።]
የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዳሉት:
«ንፅህና የኢማን ግማሽ ነው።» [ሙስሊም ዘግበውታል]
((አላህ ንፁሆችን ይወዳል)) [ቁርአን 9:108]