Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የመውሊድን በዓል ማክበር! ምንጭ፦ ኪታቡ አል-ኢርሻድ


የመውሊድን በዓል ማክበር!

ሙስሊሞች ባለፉት ዘመናትም ሆነ በአሁኑ ዘመን ከካህዲያን ጋር በመመሳሰል ከፈፀሟቸው ጥፋቶች ሁሉ ይበልጥ የጎላው የክርስቲያኖችን ፈለግ በመከተል የሚፈፅሙት የመውሊድን በዓል የማክበር ባህል ነው። ማሐይማንና ሰዎችን ለስህተት የሚዳርጉ ዑለሞች በየአመቱ በወርሃ ረቢዓል አወል ከነቢዩ ሙሐመድ የልደት ዕለት ጋር በተያያዘ ይህን በዓል ያከብሩታል። ከፊሎቹ ከመስጊዶች ላይ፣ ሌሎች ደግሞ በየቦታቸው ወይም ለዚሁ ዓላማ በተዘጋጁ የተለያዩ ሥፍራዎች ሲያከብሩ ይስተዋላሉ። ተራው ህዝብ ከዚህ በዓል ላይ በስፋት ይሳተፋል። ይህን የሚፈፅሙት የዒሳን የልደት ቀን በዓል ከሚያደርጉት ክርስቲያኖች ጋር በመመሳሰል ነው።

ይህ የመውሊድ በዓል በራሱ ቢድዓ ከመሆኑም በላይ ብዙ የሽርክና ሌሎችም ሊወገዙ የሚገቡ ተግባራት ይፈፀሙበታል። መልዕክተኛውን (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ወደ አምላክነት ደረጃ ከፍ የሚያደርጉ፣ እርሳቸውን መማፀንና እገዛ መጠየቅን የሚያስተምሩ ግጥሞችና ሙገሳዎች በዕለቱ ከሚፈፀሙት ውግዝ ነገሮች አንዱ ነው።

ነቢዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ከመጠን በላይ መሞገስና መወደስን አጥብቀው አውግዘዋል። እንዲህ ብለዋል፦
《 ክርስቲያኖች የመርየምን ልጅ ከመጠን በላይ እንዳሞገሱት እናንተም እኔን ከልክ በላይ አታወድሱኝ።እኔ ባሪያ ነኝ። የአላህ መልዕክተኛና ባሪያ ብቻ በሉኝ።》
【ቡኻሪና ሙስሊም】

ከነኝህ የዋህ የበዓሉ አክባሪያን መካከል መልዕክተኛው (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ከበዓሉ ላይ ይገኛሉ የሚል እምነት ያላቸው አይጠፉም። ከዚህ በዓል ጋር በተያያዘ የሚፈፀመው ሌላው ስህተት በከበሮ አጀብ በጋራ የሚባሉ የሱፍያህ ቢድዓ ዚክሮችና ነሺዳዎች ናቸው። በሴቶችና በወንዶች መካከልም የመቀላቀል ሁኔታ ይፈጠራል። ይህም ለመጥፎ ነገር ምክንያት ይሆናል። ብልግና እንዲፈፀም በመነሻነት ያገለግላል።

ይህ በዓል ከነኝህ ውግዝ አድራጎቶች የፀዳ፣ ተሰባስቦ ምግብ በመመገብና ደስታን በመግለፅ ብቻ የተወሰነ ሊሆን ቢችልም እንኳ በዓሉ በራሱ ቢድዓ ነው። አዲስ የተፈጠረ ነገር። 《አዲስ ነገሮች ሁሉ ቢድዓዎች ናቸው። ቢድዓ ሁሉ ደግሞ ጥመት ነው።》ቀስ በቀስም እያደገ ሄዶ ከሌሎች በዓላት ላይ የሚስተዋለው የተወገዙ ነገሮች ሁሉ የሚፈፀሙበት በዓል ይሆናል።

ይህን በዓል ቢድዓ ያልነው ከቁርአንና ከሐዲስ፣ እንዲሁም ከሰለፉሷሊሂንና ከመልካሞቹ ምዕተ አመታት መሰረት የሌለውና ከሂጅሪያ አራተኛው ምዕተ አመት በኋላ ፍጢምዩን የተሰኙ የሺአ አንጃ ተከታዮች የፈጠሩት በመሆኑ ነው።

ኢማሙ አቡ ሐፍስ ታጁዲን አል ፈሲሐን እንዲህ ሲሉ ፅፈዋል፦
《አንዳንድ ሰዎች በወርሃ ረቢዓል አወል መውሊድ በሚል ስያሜ በሚጠሩት ቀን መሰብሰባቸው ሸሪዓዊ መሰረት አለውን? የሚሉ በርካታ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ይሰማሉ። ጠያቂዎቹ ለዚህ ጥያቄአቸው የተብራራ ምላሽ ይሻሉ። በአላህ እገዛ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተናል፦

ለዚህ የመውሊድ በዓል ከቁርኣንም ከሐዲስም መሰረት አላገኘሁለትም። የቀደምቶቹን ፈለግ ከሚከተሉና በአርአይነታቸው ከሚጠቀሱ ዑለማዎች መካከል ይህን በዓል ያከበረ አንድም ሰው አናውቅም። በዓሉ መጥፎ ሰዎች የፈጠሩት ቢድዓ፣ ለሆዳቸው ያደሩ ወገኖች የሚጠቀሙበት የግል ስሜት ፍሬ ነው።》

ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያህ እንዲህ ሲሉ ፅፈዋል፦
《አንዳንድ ሰዎች ክርስቲያኖች ለዒሳ የልደት በዓል ስለሚያከብሩ የነርሱን ፈለግ በመከተል ወይም ነቢዩን ከመውደድና ከማላቅ በመነጨ ስሜት የሚያከብሩት የመውሊድ በዓል ነቢዩ የተወለዱበትን ዕለት በመወሰኑ ላይ ውዝግቦች ያሉ ከመሆኑም በላይ ያከበረው አንድም ሰለፍ የለም። ይህ ነገር መልካም ቢሆን ኖሮ ሰለፎች ከኛ ይበልጥ ሊያከብሩት በተገባ ነበር። ከኛ በበለጠ ሁኔታ ነቢዩን ይወዱና ያከብሩ ነበርና። ለመልካም ነገርም በጣም ጉጉዎች ነበሩና። ነቢዩን መውደድና ማላቅ ሊገለፅ የሚገባው አርአያነታቸውን በመከተል፣ ለትዕዛዛቸው በማደር፣ በግልፅም በስውርም የርሳቸውን ሱና ሕያው በማድረግ፣ መልዕክታቸውን በማስፋፋትና ለዚህ ተግባር በልቦናም፣ በእጅም በምላስም በመታገል ነው። የቀድሞዎቹ ሰዎች የሙሃጅሮችና አንሷሮች እንዲሁም የነርሱን ፈለግ የተከተሉ መልካም ስብእናዎች ተግባር ይህ ነበርና።》

በፊትም አሁንም ይህንን ቢድዓ የሚያወግዙ በርካታ ፅሁፎች ተከትበዋል። ይህ በዓል ቢድዓና ከካህዲያን ጋር መመሳሰል ከመሆኑም ባሻገር ሌሎች የልደት በዓላት፣ ለምሳሌ የወልዮች፣ የሸይኾችና የመሪዎች በዓላት እንዲፈጠሩ ምክንያት ይሆናል። ለበርካታ መጥፎ ነገሮችም መንገድ ይከፍታል።

ምንጭ፦ ኪታቡ አል-ኢርሻድ

https://telegram.me/ibnunasir12