Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

አስማእ ቢንት አቢበክር ረዲየላሁ ዐንሁማ የታላቁ ሶሐባህ የዙበይር ኢብኑልዐዋም ረዲየላሁ ዐንሁ ሚስት ነበረች፡፡ አባቷ ደግሞ ታላቁ ሲዲቅ አቡበክር ረዲየላሁ ዐንሁ ናቸው፡፡ ከሷ በተላለፈው ታሪክ እንዲህ ትላለች


አስማእ ቢንት አቢበክር ረዲየላሁ ዐንሁማ የታላቁ ሶሐባህ የዙበይር ኢብኑልዐዋም ረዲየላሁ ዐንሁ ሚስት ነበረች፡፡ አባቷ ደግሞ ታላቁ ሲዲቅ አቡበክር ረዲየላሁ ዐንሁ ናቸው፡፡
ከሷ በተላለፈው ታሪክ እንዲህ ትላለች፡-
ዙበይር ሲያገባኝ ጊዜ ምድር ላይ ውሃ ከሚቀዳባት ግመልና ከአንድ ፈረስ ውጭ ምንም ገንዘብ አልነበረውም፡፡ ፈረሱን እመግባለሁ፤ ውሃ እቀዳለሁ፤ የሚታለብበትን ከቆዳ የሚዘጋጅ አኮሌ እሰፋለሁ፤ እንዲሁም አቦካለሁ፡፡ ማብሰሉን ግን በቅጡ አልችልበትም ነበር፡፡ እናም የአንሷር ልጃ-ገረዶች ነበሩ የሚያበስሉልኝ፡፡ የእውነት ሴቶች ነበሩ፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ለዙበይር ቆርጠው ከሰጡት መሬት ተምር በእራሴ ተሸክሜ አመጣ ነበር፡፡ ሶስት ፈርሰኽ ያክል ከኔ ይርቅ ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን በእራሴ ተሸክሜ እየመጣሁ ሳለ የአላህ መልእክተኛን ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አገኘኋቸው፡፡ ከሳቸው ጋር ከአንሷር የሆኑ ሰዎች አሉ፡፡ ጠሩኝና ግመሉን እያሳረፉት “ኢኽ፣ ኢኽ” አሉ፡፡ እኔን ከኋላቸው ግመሉ ላይ ሊያስቀምጡኝ ግመሉን እያስተኙ መሆኑ ነው፡፡ ግን ከወንዶች ጋር ለመሄድ አፈርኩኝ፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ዙበይርንና ቅናቱን አስታወስኩኝ፡፡ እጅግ ቀናተኛ ሰው ነበር፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዳፈርኩኝ ስላወቁ ጥለውኝ ሄዱ፡፡ ከዚያም ዙበይር ዘንድ መጣሁና “በእራሴ ተምር ተሸክሜ የአላህ መልእክተኛ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከሶሐቦቻቸው ጋር ሆነው አግኝተውኝ ነበር፡፡ ግመላቸው ላይ ሊያፈናጥጡኝ ግመሉን አስተኝተውልኝ ነበር፡፡ ግን አፈርኳቸው፤ ቅናትህንም አሰብኩኝና (ተውኩት)” አልኩት፡፡ ዙበይር ታዲያ ምን አለ? “ወላሂ! ተምር መሸከምሽ ከሳቸው ጋር ግመል ላይ ከመቀመጥሽ እኔ ዘንድ የከበደ ነው!!” አለ፡፡
ከዚህ በኋላ (አባቴ) አቡበክር የፈረሱን መግራት የምትወጣኝ አንዲት አገልጋይ ላከልኝ፡፡ ልክ ነፃ ያወጣኝ ያክል ነበር የተሰማኝ!!”
[ቡኻሪና ሙስሊም]
ከዚህ ታሪክ ውስጥ ብዙ ቁም-ነገሮችን መቅሰም እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ያክል
1. አስማእ ምን ያክል ለባሏ ታዛዥ እንደነበረች፡፡
2. የአስማእን ሃላፊነት ብዛት
3. አስማእ የአንሷር ሴቶችን ማድነቋ ምን ያክል ከምቀኝነት የራቀች እንደነበረች ያስረዳል፡፡ ዛሬ ሌላው ቀርቶ ተመሳሳይ አቋም ባላቸው ሰዎች መካከል እንኳን የሚታየው ምቀኝነት እራሱ እጅግ አስቀያሚ ነው፡፡
4. የነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ለሶሐቦቻቸው ያላቸው መቆርቆርና ትህትና፡፡
5. የአስማእን አይን አፋርነት
6. የአስማእን በሌለበት እንኳን የባሏን ስሜት መጠበቋ
7. የዙበይርን ቀናተኝነት፡፡ ይስተዋል! ቅጥ ያጣ እንዳይሆን እንጂ ሰው በሚስቱ ላይ መቅናቱ አግባብ ነው፡፡ ማንም እንዳይደርስባት፣ ማንም እንዳያይበት፣ ማንም … ማለቱ እሷን ከመጥላትም ከማሰቃየትም የመጣ አይደለም፡፡ “የኔ ብቻ” ከማለት እንጂ፡፡ እንደ ከሃዲዎች ልቅ የሆነ መዛለል እውነተኛ ሙስሊም ሊታገሰው አይገባም፡፡ እንዳውም ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እራሳቸው ከሌሎች በበለጠ ቀናተኛ ነበሩ፡፡ ጤነኛ በሆነ መልኩ ማለት ነው፡፡