Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ከተፍሲር ማኅደር መብትዎን ሲያስከብሩ የሌሎችንም ያክብሩ


🌐 ከተፍሲር ማኅደር

መብትዎን ሲያስከብሩ
የሌሎችንም ያክብሩ

ራስን ከመበደል ሰውን መበደል የከፋ ነውና የማንንም በተለይ የትዳር አጋርህን መብት አትጣስ

በ 27ኛው "ሊቃእ ባበል መፍቱህ" ፕሮግራም ሸይኽ ሷሊህ አል-ዑሰይሚን (ረሂመሁላህ) ሱረቱል ሙጠፊፊንን ሲተነትኑ የራስን መብት ማስጠበቅና የሌሎችን መሸራረፍ ምን እነደሆነ በገለፁበት ምሳሌ በተለይ ስለ ባሎች የመከሩንን በቀጣዩ መልክ ወደ አማርኛ መልሼዋለሁና ያንብቡት።
🌴 💐 🌴

بسم الله الرحمن الرحيم
"وَيْلٌ لِلْمُطَفِّفِينَ ፨ الَّذِينَ إِذَا اكْتَالُوا عَلَى النَّاسِ يَسْتَوْفُونَ ፨ وَإِذَا كَالُوهُمْ أَوْ وَزَنُوهُمْ يُخْسِرُون َ፨
[المطففين:1-3]
«ለሰላቢዎች (ለአጉዳዮች) ወየውላቸው! ለእነዚያ ከሰዎች ባስ'ሰፈሩ ጊዜ የሚያስሞሉ፡፡ ለሰዎቹ በሰፈሩ ወይም በመዘኑላቸው ጊዜ ግን የሚያጎድሉ ለኾኑት (ወየውላቸው)፡፡»
【አልሙጠፊፊን: 1- 3】

[{ 📖 ጌታችን አላህ ይህንን ምዕራፍ "ወይሉን" ማለትም ወየውላቸው በሚል ቃል ጀመረው። ይህን "ወይል" የሚለውን ቃል አላህ ጀልለ ወዓላ በቁርኣን ውስጥ ለበርካታ ግዜያት ጠቅሶታል። ትክክለኛ በሆነው የሊቃውንት ንግግር መሰረትም አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ትእዛዛቱን ለጣሱት ወይም የከለከለውን ለፈፀሙት ያስጠነቀቀበት የማስጠንቀቂያ ቃል ናት። ይህም ከማስጠንቀቂያው ቃሉ በኋላ የተጠቀሰውን ጁምላ ወይም ጥቅል መልእክት በማስመልከትም ነው።

በዚህም መሰረት "وَيْلٌ لِلْمُطَفِّفِينَ " *ለአጉዳዮች ወየውላቸው* ኣለ። ለመሆኑ "ሙጠፊፊን" ማለትም ኣጉዳዮች እነማን ናቸው ?

የ"ሙጠፊፊንን" ማንነት ቀጣዩ አንቀፅ ተርጉሞታል። እሱም
الَّذِينَ إِذَا اكْتَالُوا عَلَى النَّاسِ يَسْتَوْفُونَ * وَإِذَا كَالُوهُمْ أَوْ وَزَنُوهُمْ يُخْسِرُونَ [المطففين:2-3]
« ለእነዚያ ከሰዎች ባስሰፈሩ ጊዜ የሚያስሞሉ፡፡ ለሰዎቹ በሰፈሩ ወይም በመዘኑላቸው ጊዜ ደግሞ የሚያጎድሉ ለኾኑት (ወየውላቸው) ፡፡»
(إذا اكتالوا على الناس)
"ከሰዎች ባስሰፈሩ ግዜ" ሲል የሚለካ የሚሰፈር ነገር ከሰዎች ሲገዙ ያለምንም ጉድለት ሀቁን አስጠብቀው ሙሉ አድርገው ያስሰፍሯቸዋል።
(وإذا كالوهم أو وزنوهم)
"ለሰዎቹ በሰፈሩ ወይም በመዘኑላቸው ጊዜ" ሲል ደግሞ ለሰዎች ምግብ በስፍር ሽጠው ሲሰፍሩላቸው ወይም የሚመዘን ነገር በሚዛን ሲሸጡላቸው يخسرون
ያጎድላሉ።

አላህ ይጠብቀንና እነዚህ ሰዎች የራሳቸው ሀቅ እንዲሟላ ያደርጋሉ። የሌሎችን ሀቅ ግን ያጓድላሉ። በዚህም ሁለት አይነት ባህርያትን ይላበሳሉ። እነሱም بين الشح والبخل ስግብግብነትና ንፉግነት ነው። የራሳቸውን ሀቅ ያለምንም ይቅርታ ሙሉውን በመፈለጋቸው የተነሳ ተስገብጋቢ ይሆናሉ። ሚዛኑንና ስፍሩን በመሙላት ረገድ የሚጠበቅባቸውን በመንፈጋቸው ደግሞ ንፉጎች ይሆናሉ።

ይህንን ነው እንግዲህ አላህ አዝዘ ወጀልለ ስፍርና ሚዛንን በማስመልከት የጠቀሰው። በእውነቱ ይህ ነገር ምሳሌ ነውና በዚህ ላይ በመመርኮዝ ማንኛውም ለራሱ ያለውን መብት ሙሉ በሙሉ ማስጠበቅ ፈልጎ በሱ ላይ ያለውን ደግሞ የሚከለክል ሰው በዚህ ክቡር በሆነው አንቀፅ ማስጠንቀቅያ ውስጥ ይገባል።

አንድ ባል ሚስቱ ሙሉ በሙሉ መብቱን እንድታከብርለትና ቅንጣትም ታክል እንዳትዘናጋም ይፈልጋል። ነገር ግን እሱ የሷን መብት በማክበሩ ጉዳይ ላይ ይዘናጋል፣ መብቷን አያከብርላትም።

አላህ ይጠብቀንና የዚህ አይነቱን የመብት ጥሰት በተመለከተ ብዙሃን ሴቶች በባሎቻቸው ላይ ቅሬታቸውን በማቅረብ ላይ ናቸው።

ይህም ባል ሚስቱ መብቱን ሙሉ በሙሉ እንድታከብርለት ይሻል፤ በአንፃሩ የሷን መብት ሙሉ በሙሉ ማክበር አይፈልግም (አያከብርም)። ወይም እንደ ወርሃዊ ወጪና በመግባባት በጥሩ ፀባይ አብሮ የመኖር አይነት ያሉና ሌሎች አብዛኛው መብቷን አይጠብቅላትም።

ውድ ወንድሞቼ በጣም አስገራሚው ነገር ባብዛኛው ይህ ክስተት እየተንፀባረቀ የሚገኘው ላይ ላዩን የሀይማኖተኝነት ምልክት የሚታይባቸው ባሎች ላይ መሆኑ ነው።

ከፊል ሴቶችም ዲነኛ የመሰለን ሰው ለትዳር መምረጣቸው መልካም ዝና ስላለውና ዲኑን ጠበቅ አድርጎ ስለያዘ እንጂ ለምንም እንዳልሆነ ይጠቅሳሉ። ይሁንና ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ ከሌሎች ጥፋት ላይ ካሉ ግለሰቦች (ከፋሲቆች) በባስ መልኩ ሚስቱ ላይ ክፉ ሆኖ አረፈው

እንግዳ የሚሆንብን ነገር … እንደው እነዚያ ከላይ ሲታዩ ዲንን የጠበቁ የሚመስሉ ሰዎች ዲንን መያዝ ማለት በግል ዒባዳ ብቻ ላይ ጠንካራ ሆኖ የሰዎችን መብት ኣለማክበር (ማበላሸት) ይመስላቸው ይሆን ?

ሰዎችን መበደል እኮ የአላህን ሀቅ በመጣስ ራስን ከመበደል የከፋ ነው። ምክንያቱም አንድ ሰው የአላህን ሀቅ በመጣስ ራሱን ቢበድል ጉዳቱ የአላህ መሺዓ ውስጥ ይገባልና የሽርክ ደረጃ ካልደረሰ ሲፈልግ ይምረዋል፣ ከፈለገም ይቀጣዋል።

ነገር ግን የሰው ልጆችን መብት መጣስ በመሺዓ ውስጥ የሚገባ ሳይሆን የግድ መሟላት፣ መካካስ የሚገባው ነገር ነው።

ለዚህም ነው ነቢዩ (ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) « “ድሃ ማን እንደሆን ታውቃላችሁን” ? ሲሉ… ሰሃቦችም "እኛ ዘንድ ድሃ ማለት ዲርሃምም ንብረትም (ገንዘብ) የሌለው ሰው ነው "! ሲሉ … ነቢዩ ግን “ ድሃ ማለት … አንድ ሰው የትንሳዔው (የቂያም) ዕለት በርካታ ሀሰናቶችን ይዞ ይመጣል፤ ነገር ግን ይኸንን በድሎ፣ ያንን ሰድቦ፣ ይኸንን ደብድቦ፣ የዚያኛውን ገንዘብ ወስዶበት ነውና የመጣው በዚህ ሰበብ ያኛው ከመልካም ስራው፣ ይኸኛውም ከመልካም ስራው፣ ያኛውም ከመልካም ስራው ይወስዱበታል። መልካም ስራው ካልበቃ ግን መጥፎ ስራቸው ይወረወርበትና ይወስዳል። በዚህም ወደ እሳት ይጣላል። ድሃ ማለት ይኸ ነው።” ኣሉ።

ስለሆነም ለነዚያ ዲናቸውን ለሚያንፀባርቁትም ሆኑ ለሌሎቹ ወንድሞቼ የምመክረው ልዕለ ሃያሉ አላህን እንዲፈሩት ነው። ነቢዩ (ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሙስሊሙ ዓለም ካስተናገደው ስብስቦች ሁሉ በላቀው የመሰብሰቢያ ዕለት ማለትም በመሰናበቻው ሀጅ የዐረፋ እለት እንዲህ ብለዋል☞
(اتقوا الله في النساء،
فإنكم أخذتموهن بأمان الله،
واستحللتم فروجهن بكلمة الله)

“ ሴቶችን በተመለከተ አላህን ፍሩ። እናንተ የያዛችኋቸው (ማለትም በቁጥጥራችሁ ስር ያደረጋችኋቸው፣ ያገባችኋቸው) በአላህ ዋስትና ነው። ብልቶቻቸውንም ለናንተ የተፈቀደ ያደረጋችሁት በአላህ ቃል ነውና። (አላህን ፍሩ) ” ኣሉ። በዚህ መልኩ ስለ ሴቶች አላህን እንድንፈራው አዝዘውናል።

በሌላም አነጋገራቸው
(استوصوا بالنساء خيراً
فإنهن عوان عندكم) أي: بمنـزلة
“ለሴቶች መልካምን ዋሉ። እነሱ እናንተ ዘንድ እንደ ምርኮኛ (ተያዥ) ናቸው።” ብለዋል።

ምርኮኛን የማረከው አካል ሲፈልግ ይፈታዋል፣ ሲፈልግም በቁጥጥሩ ስር ስለሚያቆየው ሴቶችም በባሎቻቸው ስር ያላቸው ሁኔታ በዚህ ተመስሏል። ምክንያቱም አብሮ መኖር ካልፈለገ ይፈታታል፣ ከፈለጋት ደግሞ ያቆያታልና። ስለዚህም በቁጥጥሩ ስር ናትና መብቷን ባለመጣስ አላህን ሊፈራ ይገባል

ልክ እንደዚያው አንዳንዶች ልጆቻቸው መብታቸውን በተሟላ መልኩ እንዲያከብሩላቸው ይፈልጋሉ። እነሱ ግን በልጆቻቸው መብት ላይ አጉዳይ ናቸው። ልጆቹ መልካም እንዲውሉለት፣ መብቱን እንዲጠብቁለት ይፈልጋል። በገንዘብም በአካላቸውም መልካም በሆነ ነገር ሁሉ በጎ እንዲውሉለት ይሻል። እሱ ግን ለነዚያ ልጆቹ አጥፊ፣ አበላሽ ነው። ስለነሱ ግዴታ የሆነበትን አይወጣምና።

ይኸ "مطفف" ማለትም "አጉዳይ" ልክ ቀድሞ ባለው መጠይቅ ማለትም ባል ከሚስቱ ጋር ስላለው መጠይቅ ላይ እሷ የሱን መብት ሙሉ በሙሉ ማሟላቷን ፈልጎ ሳለ የሷን መብት ደግሞ የሚያጎድል እሱ "ሙጠፊፍ" ነው እንላለን።

ይኸም አባት ልጆቹ በተሟላ መልካምነት በጎ እንዲውሉለት እየፈለገ የነሱን መብት ግን የሚያጓድል ከሆነ እሱንም "ሙጠፊፍ" ነው እንላለን።

ስለሆነም
وَيْلٌ لِلْمُطَفِّفِينَ * الَّذِينَ إِذَا اكْتَالُوا عَلَى النَّاسِ يَسْتَوْفُونَ * وَإِذَا كَالُوهُمْ أَوْ وَزَنُوهُمْ يُخْسِرُونَ.“
[المطففين:1-3].
«ለሰላቢዎች ወየውላቸው! ለእነዚያ ከሰዎች ባስ'ሰፈሩ ጊዜ የሚያስሞሉ፡፡ ለእነርሱም (ለሰዎቹ) በሰፈሩ ወይም በመዘኑላቸው ጊዜ የሚያጎድሉ (ለኾኑት)፡፡»
(አልሙጠፊፊን:1-3)
የሚለውን የአላህ ቃልም አስታውስ እንለዋለን።📖 }]
【لقاء باب المفتوح: 27】
♻ ♻ ♻

ኑሮዎ "ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ" እንዳይሆንብዎት ሚዛናዊና ፍትሃዊ ይሁኑ

≅≅≅≅≅🌴🌴≅≅≅≅
የአማርኛ ትርጉሙ ኦዲዮ ☞
aac - https://drive.google.com/file/d/0B9tNo_F6usABMktrLUFkRUZvRW8/view?usp=docslist_api

የአረብኛው ኦዲዮ ምንጭ☞
http://audio.islamweb.net/audio/index.php?page=FullContent&audioid=111376
---------------
22 ሙሀርረም 1437
03 ኖቨምበር 2015

Post a Comment

0 Comments