Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የሶላታችንን ነገር አደራ! (ክፍል አንድ)


የሶላታችንን ነገር አደራ!
(ክፍል አንድ)
ሶላት የዲን ምሰሶ የአማኞች ብርሃን ናት፡፡ ሶላት ከሁለቱ ሸሃዳዎች ቀጥሎ ቀዳሚዋ የኢስላም መሰረት ናት፡፡ በሶላት ጭንቆች ይወገዳሉ፡፡ ፈተናዎች ይታለፋሉ፡፡ ሶላት ለነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የዐይን ማረፊያ፣ የእርካታቸው ቦታ ናት፡፡ ((ሶላት ከመጥፎና ከሚጠላ ነገር ሁሉ ትከለክላለች፡፡)) [አልዐንከቡት፡ 45] ሶላት ከላያችን ላይ ወንጀልን የምታረግፍ መጥረጊያ የሃጢኣት ቆሻሻን የምታፀዳ ወራጅ ውሃ ናት፡፡ [ሙስሊም]
ሶላት የማይሰግድ ሰው ምድቡ ከአማኞች ምድብ እንዳልሆነ የሚያመላክቱ እጅግ አስፈሪ የሆኑ ሐዲሦች ተላልፈዋል፡፡ እነዚህን ሐዲሦች መነሻ በማድረግም ሶላት የማይሰግድ ሰው “ሙስሊም ነው” “አይ አይደለም” በሚል በዑለማእ መካከል ጠንካራ የሀሳብ ልውውጥ አለ፡፡ አደጋ ላይ በመሆኑ ላይ ግን ቅንጣት ታክል ውዝግብ የለም፡፡ ኧረ እንዳውም “ሙስሊም ነው” ያሉት ሳይቀሩ “መገደል አለበት”፣ “መታሰር አለበት” … እያሉ ጥብቅ ሀሳብ የሰነዘሩት ቀላል አይደሉም፡፡ አንተ ከሶላት የተኳረፍከው ተላላ ሆይ! ይሄው የዲኑ ምሁራን “አንተ እጣ ፈንታህ ዘላለማዊ ቅጣት የሆነ ከሃዲ ነህ” በሚሉና “አይ ጥፋትህ ጫፍ የደረሰ፣ እጅግ አስፈሪ አደጋ የተደቀነብህ ጋጠ-ወጥ ሙስሊም ነህ” በሚል ጎራ ለይተው እየተወዛገቡብህ ነው!! ህሊና ካለህ ከዚህ በላይ ምን አስደንጋጭ ነገር አለ?!!
በርግጥ አሁን ርእሴ ከናካቴው ስለማይሰግድ ሰው አስፈሪ ሁኔታ መዘርዘር አይደለም፡፡ ይልቁንም የሶላት አሰጋገድ ህግና ደንቡን እንጠብቅ ዘንድ በስሱ ለማስታወስ ነው፡፡
አዎ መስገድ ብቻ ሳይሆን አሰጋገድን ማሳመርም ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ጌታችን አላህ ((ለሰጋጆች ወዮላቸው!)) ማለቱን አንዘንጋ፡፡ አዎ ((ለነዚያ ከሶላታቸው ተዘናጊዎች ለሆኑት!!)) [አልማዑን፡ 4-5] መልእክተኛው ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የሶላት አሰጋገድን በቃልም አስተምረዋል፣ በተግባርም አሳይተዋል፡፡ ለዚህም ሲሉ ሚንበር ላይ ወጥተው እስከሚሰግዱ ደርሰዋል፡፡ ሚንበሩ ላይ ይቆማሉ፣ ሩኩዕ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ካጠናቀቁ በኋላ “ይህን የሰራሁት በኔ እንድትመሩ ነው፡፡ አሰጋገዴንም እንድትማሩ” ብለዋል፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም] እንዳውም ሶላትን በስርኣት ለሰገደ ከአላህ ብስራት ነግረውታል፣ እንዲህ ሲሉ፡- “አምስት ሶላቶችን በርግጥም አሸናፊውና የላቀው አላህ ደንግጓቸዋል፡፡ ውዱኣቸውን ያሳመረ፣ በወቅታቸው የሰገደ፣ ረኩዓቸውን፣ ሱጁዳቸው እና ኹሹዐቸውን ያሟላ ሰው በአላህ ላይ ሊምረው ቃል አለው፡፡ (እንዲህ) ያላደረገ ግን በአላህ ላይ ቃል የለውምና ከፈለገ ይምረዋል፣ ከፈለገም ይቀጣዋል፡፡” [ቡኻሪ]
አዎ የምናገኘው ያስገኘነውን ያክል ነው፡፡ “ሶላት መለኪያ ነች፡፡ መለኪያውን የሞላ ይሞላለታል፡፡ መለኪያውን ያጓደለ ግን ስለ ስፍር አጉዳዮች ምን እንደተባለ ታውቃላችሁ” ይላሉ ሰልማን አልፋሪሲ፡፡ ቀደምቶቻችን ከአንድ ሰው ዒልም ሊወስዱ ሲፈልጉ ቀድመው አሰጋገዱን ይመለከቱ ነበር፡፡ ሶላቱን በስርኣት ሲፈፅም ከተመለከቱት እሰየው! ካልሆነ ግን ለሶላቱ ታማኝ ያልሆነን ሰው እጃቸውን ከሱ ይሰበስቡ ነበር፡፡ በርግጥም ሶላት የአንድ ሙስሊም ስብእና ቀዳሚ መለኪያ ነች፡፡
እናም ለሶላታችን በምንሰጠው ዋጋና አፈፃፀም ልክ የምናገኘውም ደሞዝ ይለያያል፡፡ ይህን አስመልክተው ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላሉ፡- “በእርግጥም አንድ ባሪያ ሰላትን ይሰግድና ነገር ግን ከሷ አንድ አስረኛዋ (ወይም) አንድ ዘጠነኛዋ (ወይም) ወይም አንድ ስምንተኛዋ (ወይም) አንድ ሰባተኛዋ (ወይም) አንድ ስድስተኛዋ (ወይም) አንድ አምስተኛዋ (ወይም) አንድ አራተኛዋ (ወይም) ወይም አንድ ሶስተኛዋ (ወይም) ግማሹዋ እንጂ አይፃፍለትም” ይላሉ፡፡ [አልባኒ ሶሒሕ ብለውታል] ስለዚህ እንደ አሰጋገዳችን መለያየት የምናስመዘግበውም ምንዳ ይለያያል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ከሶላታችን በደንብ መጠቀም እንችል ዘንድ አሰጋገዳችንን ከነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አሰጋገድ ጋር ለማመሳሰል መጣር ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህም “ስሰግድ እንዳያችሁኝ ስገዱ” የሚለው የነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም መመሪያ ጥሩ ዋቢ ይሆነናል፡፡ [ቡኻሪ]
በአንድ በወቅት ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከመስጂዱ አንድ ጥግ ላይ ሳሉ የሆነ ሰው መስጂድ ገባና መስገድ ያዘ፡፡ ሶላቱን ግን በጣም አሳጠራት፡፡ ሲጨርስም ከነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ዘንድ መጣና ሰላምታን አቀረበ፡፡ እሳቸውም “ወዐለይከስሰላም፡፡ ተመለስና ስገድ፣ ምክንያቱም አንተ አልሰገድክምና” አሉት፡፡
ተመለሰና ሰገደ፡፡ ከዚያም ሰላምታ አቀረበ፡፡
አሁንም “ወዐለይከስሰላም፡፡ ተመለስና ስገድ፣ ምክንያቱም አንተ አልሰገድክምና” አሉት፡፡
በሶስተኛው ጊዜ ሰውየው እንዲህ አለ፡- “በሐቅ በላከህ ይሁንብኝ! ከዚህ ውጭ ማሳመር አልችልም፡፡ ስለሆነም አስተምረኝ” አላቸው፡፡
ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉት፡- “ለሶላት ስትዘጋጅ
ውዱእህን አሳምር፤
ከዚያም ወደ ቂብላ ተቅጣጭ፤
ከዚያም ‘አላሁ አክበር’ በል፤
ከዚያም ከቁርኣን የተገራልህን ቅራ፤
ከዚያም ሩኩዕ አድርግ፣ በሩኩዑህ ላይ እስከምትረጋጋ ድረስ፤
ከዚያም እራስህን (ከሩኩዕ) አቅና፣ ተስተካክለህ እስከምትቆም ድረስ፤
ከዚያም ሱጁድ ውረድ፣ በሱጁድህ ላይ እስከምትረጋጋ ድረስ፤
ከዚያም ከሱጁድ ተነስ፣ ቀጥ ብለህ እስከምትቀመጥ ድረስ፤
ከዚያም ሱጁድ ውረድ፣ በሱጁድህ ላይ እስከምትረጋጋ ድረስ፤
ከዚያም ተነስ፣ ተስተካክለህ እስከምትቆም ድረስ፤
ከዚያም ይህን (መረጋጋትህን) በሶላትህ በሙሉ ላይ ፈፅም፡፡
[ቡኻሪ፣ ሙስሊም፣ ኢብኑ ማጃህ፣ አልበይሀቂ፣…]
ከዚህ ክስተት እና የነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እርማት ብዙ ቁም ነገሮችን መማር እንችላለን፡፡ ከምንም በላይ ግን “አልሰገድክም ተመለስ ስገድ” እያሉ ማመላለሳቸውን እናስምርበት፡፡ ከራሳችን ሶላትም ጋር እናነፃፅረው፡፡ በጥቅሉ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ስሰግድ እንዳያችሁኝ ስገዱ” ያሉት፡፡ [ቡኻሪ] ሶላታችንን ከሳቸው ሶላት ጋር ለማመሳሰል አሰጋገዳቸውን ጠንቅቆ ማወቅ ይጠይቃል፡፡ አሰጋገዳቸው በተለያዩ የሱናህ ኪታቦች ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ በተለይም ደግሞ “ሲፈቱ ሶላቲንነቢይ” የሚለው የታላቁን ሙሐዲሥ የሸይኹልአልባኒይ ረሒመሁላህ ኪታብ በዚህ ረገድ እፁብ ድንቅ የሆነ ስራ ነው፡፡ እባኮትን በጥሞና አንብበው አሰጋገደዎን ይታዘቡ፡፡ በተግባርም ይጠቀሙት፡፡ ሌሎችንም ያስጠቅሙ፡፡ በአላህ ፈቃድ ከዚህ ኪታብ እና መሰል ስራዎች እየቀነጨብኩ እጅግ አንገብጋቢ ናቸው ብየ የማምንባቸውን በተከታታይ ለማቅረብ እሞክራሉ፡፡
(ኢብኑ ሙነወር፣ መስከረም 19/2008)

Post a Comment

0 Comments