Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የኢኽዋን ምሽጎችን ማንኮታኮት (ተከታታይ፣ ክፍል አምስት)


የኢኽዋን ምሽጎችን ማንኮታኮት
(ተከታታይ፣ ክፍል አምስት)
ኢኽዋንና ሺዐ
ሰሞኑን በሳዑዲ ዐረቢያ ሚና ላይ የደረሰውን አደጋ አስመልክቶ በርካታ ወንድሞች እና እህቶች በሳዑዲ ላይ የሚሰነዘረውን ከንቱ ውንጀላ በስፋት ሲከላከሉ ነበር፡፡ መከላከሉ የራፊዷ (ሺዐህ) እምነት ተከታይ ከሆነችዋ ኢራን የተሰነዘረውን ትችት ለማስተባበል ብቻ መስሎኝ ነበር፡፡ ለካስ እዚሁ ሃገራችን ውስጥ ያሉ ኢኽዋኖችም በሳዑዲ ላይ ጦራቸውን መዘው ኖሯል፡፡ በርግጥ ይሄ የተለመደና ብዙ የተባለበት ጉዳይ ስለሆነ ብዙም ማለት አልሻም፡፡ እኔን የደነቀኝ ግን ኢኽዋኖች ሳዑዲን ለማንቋሸሽ ሲሉ ያለወትሯቸው የሺዐ ጠላት መስለው መቅረባቸው ነው፡፡ በተደጋጋሚ የሺዐዎችን ከይሲነት በመጥቀስ ሳዑዲ እነዚህን ሰዎች ከሃገሯ አለማባረሯ ወንጀል መሆኑን በመጥቀስ ጫን አድርገው እየተቹ ነው፡፡ እንዳልኩት ርእሴ ከሳዑዲ መከላከል አይደለም፡፡ ይልቁንም የኢኽዋንን እና የሺዐን ቅርርብ እና ግንኙነት በመጥቀስ ማንነታቸውን ማጋለጥ ነው፡፡
እርግጥ ነው ራፊዳዎች (ሺዐዎች) ከኢስላም መሰረታዊ አስተምሮ ያፈነገጡ እጅግ በርካታ ጥመቶችን እንደ ፅድቅ የሚቆጥሩ ፈር የለቀቀ አንጃ ተከታዮች ናቸው፡፡ ከሚያንፀባርቋቸው አፈንጋጭ አስተሳሰቦች ጥቂቶቹን ብንመለከት
1. ታዋቂ እምነታዊ መሪዎቻቸው ቁርኣን ጎደሎ ነው ይላሉ፡፡ ይህን አቋማቸውን ቁንጮዎቻቸው በተለያዩ መዛግብት ስላንፀባረቁት መረጃ ለመዘርዘር ቦታው አይበቃም፡፡ ለናሙና ያክል ግን እነዚህን ኪታቦቻቸውን መመልከት ይቻላል፡፡ [አልካፊ፣ አልአንዋሩንኑዕማንያህ፣ ተፍሲሩልቁሚ፣…]
2. የነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የዘር ሃረግ ውስጥ ያሉ ቤተሰቦቻቸው ላይ በጣም ድንበር ያለፈ አቋም አላቸው፡፡ እንዳውም የኢራን አብዮታዊ መሪ የነበረው ኹመይኒ “ለመሪዎቻችን ቅርብ የሆነ መልአክም የተላከ መልእክተኛም የማይደርስበት ደረጃ አላቸው” ይላል፡፡ [አልሑኩመቱልኢስላሚያህ፡ 52] በዚህ ንግግሩ ሳቢያ ሸይኹልአልባኒ ረሒመሁላህ ይህን ሰውየ አክፍረውታል፡፡ ኢኽዋኒው አልመውዱዲ ግን ይህን ራፊዲ “የዐለም ሙስሊሞች ሁሉ መሪ ነው” ይላል፡፡ [አሸቂቃን፡ 3] የዚህን ቆሻሻ ራፊዲ “ኢስላማዊ” አብዮት ሊባርኩ በቱርክ፣ ፓኪስታን፣ ህንድ፣ ኢንዶኔዢያ፣ አፍጋኒስታን፣ ማሌዢያ፣ ፊሊፒንስ፣ አሜሪካ እንዲሁም በዐረቡ አለምና በአውሮፓና በአሜሪካ የሚገኙ የኢኽዋነልሙስሊሚን ተቋማት ወደ ኢራን፣ ቴህራን ልኡካን ልከዋል፡፡
3. ራፊዷዎች የነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሶሐቦች በጣት የሚቆጠሩ ሲቀሩ እንዳለ “አፈንግጠዋል” “ከፍረዋል” ይላሉ፡፡ [አልካፊ፡ 2/244፣ አልቢሓር፡ 22/345፣…] በተለይም ደግሞ ኸሊፋዎቹን አቡ በክርና ዑመርን እንደ ጣኦት ነው የሚቆጥሯቸው፡፡ በየሶላታቸው ሳይቀር ይረግሟቸዋል፡፡ የኸሊፋዎቹ ልጆች የሆኑትን እናቶቻችን ዓኢሻን እና ሐፍሷንም እንዲሁ በቆሻሻ ቃላት ይወነጅሏቸዋል፡፡ ለነገሩ ደረጃው ቢለያም ሰይድ ቁጥብም በርካታ ሶሖችን በኒፋቅ ወንጅሏል፣ ሰድቧቸዋልም፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ግን “ሶሐቦቼን የተሳደበ በሱ ላይ የአላህ የመላእክት እና የሰዎች ሁሉ እርግማን ይሁንበት” እንዳሉ የሚታወቅ ነው፡፡
4. ሺዐዎች የሀገራችን ሱፍዮች “ሲሪያ” እያሉ የሚጠቀሙትን ሙትዐህ ወይም የኮንትራት ጋብቻ በሰፊው ከመፈፀማቸው የተነሳ ከውስጣቸው ኤች አይ ቪ ኤድስ እና አባቶቻቸው በማይታወቁ ዲቃላ ልጆች ተጥለቅልቀዋል፡፡ የሚደንቀው ይህን ብልግናቸውን የማይቀበል “ከኛ አይደለም” ማለታቸው ነው፡፡ [ወሳኢሉሽሺዐህ፡ 4/438] ለመግለፅ ስለሰቀጠጠኝ እንጂ ከዚህም በላይ እንደ ዲን የሚቆጥሯቸውን ብዙ ዘግናኝ ወንጀሎችን በማስረጃ መዘርዘር ይቻል ነበር፡፡
5. ለሶሐቦች ባላቸው የተዛባ እይታ ምክንያትም በነሱ በኩል የተላለፉ ሐዲሦችን አይቀበሉም፡፡ ቡኻሪ፣ ሙስሊም፣ አቡ ዳውድ፣ ነሳኢይ፣… ሌሎችም የሐዲሥ ኪታቦች እነሱ ዘንድ ዋጋ የላቸውም፡፡
እነዚህ ጥመቶች ሺዐዎች ዘንድ ከሚገኙት በርካታ ሙሲባዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እነዚህና መሰል አደገኛ ጥመቶችን አጭቆ ከያዘ አንጃ ጋር የሚቀራረብ ሱኒ ይኖራልን? እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ በርካታ የኢኽዋን አመራሮች ከቡድኑ መስራች ከሐሰን አልበና ጀምሮ እንዲህ አይነት ጥመት ካላቸው አካላት ጋር ህብረት ሲፈጥሩ ነው የኖሩት፣ ዛሬም ድረስ ያሉት፡፡ ለምሳሌ፡-
1. ኢኽዋኖች “አለም አቀፉ የዑለማዎች ማህበር” እያሉ የሚጠሩት ድርጅት ሊቀመንበር ቀርዷዊ ከምክትሎቹ አንዱ የሺዐ እምነት ተከታይ ነው፡፡ ድንቄም የዑለማእ ማህበር! ሶሐቦችን ከሚያከፍሩ ሺዐዎች፣ ኸዋሪጅ ኢባዲዎች እና ሱፍዮች ጋር የሚመሰረት ህብረት ነው የዑለማእ ማህበራቸው፡፡ ስለዚህ ማህበር ሌላ ጊዜ…
2. የኢኽዋን መስራች የሆነው ሐሰን አልበና “የመዝሐብ ልዩነት አንድነታችንን ሊያናጋን አይገባም፡፡ ጌታችን አንድ፣ ነብያችን አንድ፣ ቁርኣናችን አንድ፣ ቂብላችን አንድ ነው” በሚል ከሺዐዎች ጋር ለመቀራረብ ብዙ ባክኗል፡፡ [መውቂፉ ዑለማኢልሙስሊሚን ሚነሽሺዐህ ወሥሠውረቲልኢስላሚያህ፡ 23]
3. ሺዐንና “ሱኒን” “ለማቀራረብ” ተብሎ በሐሰን አልበና ዘመን የተመሰረተ ማህበር አላቸው፡፡ ለዚሁ አላማ የተቋቋሙ ቢሮዎችና በዓመት 4 ጊዜ የሚታተም ‘ሪሳለቱ አትተቅሪብ' የሚባል መፅሄት አላቸው፡፡ የሚገርመው ግን የኢኽዋን መሪዎች ሺዐዎችን አዝሀር ዩኒቨርስቲ ውስጥ እንዲያስተምሩ ሲፈቅዱና እንደ 4ቱ መዝሀቦች በመቁጠር “እነሱን ተከትሎ መስገድ ይቻላል” ብለው ፈትዋ ሲሰጡ ሺዐዎች ግን ለአራቱም መዝሀቦች እውቅና እንደማይሰጡ በግልፅ አውጀዋል፡፡
4. የቡድኑ ቁንጮዎች እንደ ሐሰነልበና፣ ገዛሊ፣ ቲልሚሳኒ፣ ፈትሒ የከን፣ ሰዒድ ሐዋ፣ መውዱዲ፣ ነደዊ፣ ገኑሺ፣ ቀርዷዊ፣ ቱራቢ፣ ዒዘዲን ኢብራሂም… በሺዐና በሱኒ መካከል ሊያለያይ የሚችል መሰረታዊ ልዩነት የለም፡፡ ሺዐዎች ከአራቱ የፊቅህ መዝሀቦች ብዙም የተለዩ አይደሉም እያሉ ብዙ ለቅልቀዋል፣ ፈትዋም ሰጥተዋል፡፡ ለማሳጠር እንጂ የእያንዳንዳቸውን ሰቅጣጭ ንግግር በማስረጃ መዘርዘር ይቻል ነበር፡፡ ለናሙና ያክል ‘ዐለማኡል ሙስሊሚን ወመውቂፉሁም ሚነሠውረቲሺዒያህ' ኪታብ ይመልከቱ፡፡ ልብ ይበሉ ፀሀፊው ዒዘዲን ኢብራሂም የተባለ ኢኽዋኒ ነው፡፡
5. ኢኽዋኒው ዓኢድ አልቀርኒ እራሱ “ከሺዐህ ጋር ልንቀራረብ ግዴታ ነው፡፡ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ይሳተፉ ዘንድ መድረክ ሊሰጣቸው የግድ ይላል” ይላል፡፡ [ጀሪደቱልመዲናህ፡ 21/10/1425]
6. ኢኽዋኒው ጧሪቅ አስሱወይዳን ምን እንደሚል ተመልከቱ፡- “እኔ ለሺዐዎች እምነት ስል ህይወቴን መስዋእት ለማድረግ ዝግጁ ነኝ!” ድምፁን በዚህ ይስሙት፡፡ https://www.youtube.com/watch?v=8Nit494ZJTw
ወላሂ ለማሳጠር እንጂ ከዚህም በላይ ብዙ መዘርዘር ይቻል ነበር፡፡ ምናልባት “አይ የአሁኑ ሺዐዎች እንደ ድሮዎቹ አይደሉም” ሊሉ ይችላሉ፡፡ ነገሩ ሀሰት ከመሆኑ ጋር አንድ ጥያቄ ግን እንጠይቃቸው፡- የአሁኑ ሺዐዎች ከድሮዎቹ ከተለዩ አሁን ባሉት ሺዐዎች ሳቢያ ለምን ሳዑዲን ታብጠለጥላላችሁ?
እንዳውም የሱኒውን ዐለም በጅምላ ማውገዝ የሚቀናቸው ራፊዳ ሺዐዎች ኢኽዋኒው ሰይድ ቁጥብን አልፎም የኢኽዋን አልሙስሊሚን አንጃን እያደነቁ ሁሉ የተናገሩበት አጋጣሚ አለ፡፡ ለምሳሌ የሺዐ እምነት ተከታዩ ራፊዲው ነዋብ ሶፈዊ “ትክክለኛ ጀዕፈሪ (ሺዐ) መሆን የፈለገ ወደ ኢኽዋን አልሙስሊሚን ህብረት ይጠጋ” ይላል፡፡ [መውቂፉ ዑለማኢልሙስሊሚን ሚነሽሺዐህ ወሥሠውረቲልኢስላሚያህ፡ 15] ልብ ይበሉ! ፀሀፊው ኢኽዋኒ ነው!!
የውሸት ቋት ስለሆኑት ሺዐዎች (ራፊዷዎች) ቀደምቶች ከተናገሩት ጥቂቱ፡-
1. ዓሚር አሽሸዕቢይ፡- “እንደ ሺዐህ ያለ ቂል ህዝብ አላየሁም!!” ይላሉ፡፡ [አስሱናህ ሊልኸላል፡ 1/497]
2. ሐሰን ኢብኑ ዐምር፡- “ውዱእ ላይ ባልሆን ኖሮ ራፊዷዎች የሚሉትን እነግርህ ነበር!!” ይላሉ፡፡ [አልኢባነቱልኩብራ፡ 2/557]
3. አልኢማም ማሊክ፡ “የነቢዩን ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሶሐቦች የሚሳደብ ኢስላም ውስጥ ድርሻ የለውም” ይላሉ፡፡ [አሱና፡ 3/493]
4. አቡ ዩሱፍ፡- “ከጀህሚይ፣ ራፊዲ (ሺዐህ) እና ከቀደሪ ኋላ አልሰግድም” ይላሉ፡፡ [ሸርሑ ኡሱሉ ኢዕቲቃዲ አህሊስሱናህ፡ 4/733]
5. ኢማሙ ሻፊዒይ፡ “ከስሜት ተከታዮች ውስጥ እንደ ራፊዷ (ሺዐዎች) በአላህ ላይ በውሸት የሚመሰክር አላየሁም” ይላሉ፡፡ [ኡሱሉል ኢዕቲቃድ፡ 8/2811]
6. አልኢማም አሕመድ፡- አቡበክርን ዑመርን እና ዓኢሻን ስለሚሰድብ ሰው ሲጠየቁ “ኢስላም ውስጥ ነው ብየ አላስበውም” ብለዋል፡፡ [አስሱናህ ሊልኸላል፡ 2/557-558]
7. አልቡኻሪይ፡- “ከጀህሚይና ከራፊዲ ኋላ መስገዴን እና ከየሁድና ከክርስቲያን ኋላ መስገዴን ልዩነት አላይበትም!!” ይላሉ፡፡ [ኸልቁ አፍዓሊልዒባድ፡ 125]
8. አቡ ዑበይድ አልቃሲም ኢብኑ ሰላም፡- “እንደ ራፊዷ ያለ እጅግ የነተበ፣ እጅግ የቆሸሸ፣ ማስረጃው የደከመ እና ቂል አላየሁም!” [አስሱናህ ሊልኸላል፡ 1/499]
የአላህ ፈቃድ ከሆነ ክፍል ስድስት ይቀጥላል፡፡
(ኢብኑ ሙነወር፣ መስከረም 21/2008)

Post a Comment

0 Comments