Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

አሏህ በየሌሊቱ ወደ ቅርቢቱ ሰማይ ይወርዳል!

አሏህ በየሌሊቱ ወደ ቅርቢቱ ሰማይ ይወርዳል!
{ አሸናፊና የላቀው ጌታችን በየሌሊቱ የሌሊቱ መጨረሻ ሲሶ ሲቀር ወደ ቅርቢቷ ሰማይ ይወርዳል። "ማነው የሚጠራኝና የምመልስለት? ማነው የሚለምነኝና የምሰጠው? ማነው ምህረትን የሚጠይቀኝና የምምረው? " ይላል። } [ቡኻሪ: 1145፣ ሙስሊም: 1808]
የቢድዓህ አራማጅ አንጃዎች ይህንን ሀዲስ ዋጋ የማሳጣት የተለያዩ ብዥታዎችን ይረጫሉ። ለምሳሌ " የሌሊቱ ሲሶ የሚሆንበት ጊዜ እንደ ሀገራቱ አቀማመጥ ይለያያል። የአለም ምስራቃዊ አካባቢ ቀድሞ ሌሊቱ ሲገባ ቀስ በቀስም ወደ ምዕራቡ እየተሸጋገረ ይቀጥላል። ይኼ ከሆነ ደግሞ ሙሉ ሌሊቱን ሰማይ ላይ ነው የሚያሳልፈው ወይም ሲወጣ ሲወርድ ነው የሚቆየው ማለት ነው " በማለት ከጥንካሬው አንፃር መግቢያ ቀዳዳ ያላገኙለትን ሀዲስ መልእክቱን ዋጋ ለማሳጣት የሚሰቀጥጡ ሀተታዎችን ይዘረዝራሉ። ሌሎችን ፈጣሪ በፍጡር በማመሳሰል ይወነጅላሉ እንጅ የሚያነሷቸው ብዥታዎች በሙሉ ከማመሳሰል የሚመነጩ እንደሆኑ ይኼ ሀተታ ግልፅ አመላካች ነው። የፈጣሪን መውረድ ሳይሆን ልክ አንድ ፍጡር ቢወርድ የሚኖረውን ሁኔታ ከጭንቅላታቸው ውስጥ በመሳል ነው ይህን የሚሉት። ለዚህ ሁሉ አደጋ የሚያጋልጣቸው የመውረዱን እንዴትነት በደካማው ጭንቅላታቸው ለማግኘት መጣጣራቸው ነው። እንጂማ እንደሚወርድ እንጂ በምን ሁኔታ እንሚወርድ አልተነገርን? በአእምሯችን አሰላስለን የማንደርስባቸው ስንት እውነታዎች አሉ? ለምሳሌ ነብዩ ዐለይሁስሰላም አንድ ባሪያ " አልሐምዱሊላሂ ረቢልዐለሚን " ሲል አሏህ { ባሪያዬ አመሰገነኝ } እንደሚል " አርረሕማኒርረሒም " ሲል ደግሞ { ባሪያዬ በኔ ላይ ውዳሴን አደረገ } እንደሚል ነግረውናል። [ሙስሊም: 904]
በአለም ላይ በተመሳሳይ ሰአት ፋቲሀን የሚቀራው ስንትና ስንት ነው?! የዚህን ሁሉ ግን እንዴት እንደሚመልስ ልንደርስበት እንችላለን? በፍፁም!! በርካታ ህሊናችን የማይደርስባቸው ሐቂቃዎች አሉ። እንዴትነታቸውን ማግኘት ስላልቻልን ልናስተባብል ነውን? ሱብሓነሏህ!
[[ "ተውሂድ የሁለት ሀገር የስኬት ቁልፍ" ከሚለው መፅሀፍ የተወሰደ ገፅ 127 ]]