Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ሃሜት እና ነገር ማዋሰድ(ነሚማ) ሃሜት ከዝሙት የበለጠ አስቀያሚ ወንጀል መሆኑን ያውቃሉ???


ሃሜት እና ነገር ማዋሰድ(ነሚማ)

ሃሜት ከዝሙት የበለጠ አስቀያሚ ወንጀል መሆኑን ያውቃሉ???

ያማነው ሰው አፉ ካላለን በስተቀር የሃሜት ወንጀል በተውበት እይታበስም!!!!

በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ወገን ሃላል ነው የተባለ እስኪመስል ድረስ ሃሜት እና ነገር ማዋስድን ስራዬ ብለን ይዘነዋል፡፡ይህ ተግባር በኢስላም ውስጥ በጣም ከተጠሉ እና ትላልቅ ከሚባሉ ወንጀሎች መካከል ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

አላህ (ሱ.ወ) በቁርአን ላይ እንዲህ ይላል፡-

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا اجْتَنِبُوا كَثِيرًا مِّنَ الظَّنِّ إِنَّ بَعْضَ الظَّنِّ إِثْمٌ ۖ وَلَا تَجَسَّسُوا وَلَا يَغْتَب بَّعْضُكُم بَعْضًا ۚ أَيُحِبُّ أَحَدُكُمْ أَن يَأْكُلَ لَحْمَ أَخِيهِ مَيْتًا فَكَرِهْتُمُوهُ ۚ وَاتَّقُوا اللَّـهَ ۚ إِنَّ اللَّـهَ تَوَّابٌ رَّحِيمٌ ﴿١٢﴾

እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከጥርጣሬ ብዙውን ራቁ፤ ከጥርጣሬ ከፊሉ ኃጢአት ነውና፡፡ ነውርንም አትከታተሉ፡፡ ከፊላችሁም ከፊሉን አይማ፡፡ አንደኛችሁ የወንድሙን ስጋ የሞተ ኾኖ ሊበላው ይወዳልን? (መብላቱን) ጠላችሁትም፤ (ሐሜቱንም ጥሉት)፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ አላህ ጸጸትን ተቀባይ አዛኝ ነውና፡፡[49:12]

ወሬ አቀባዬች ወሬ ባመጡልን ጊዜ አፋችንን ከፍተን ወሬውን ከማዳመጥ እና ሳነጣራ ሰዎችን ከመጉዳታችንነ በፊት ማጣራት እንደሚኖርብን ቁርአን ያስተምረናል፡፡ እኛ ቁርአን እና ሃዲስን ጠንቅቀን እንከተላለን ስንል ለንግግር ማሳመሪያ ሳይሆን በተግባር ስራ ላይ ስናውለው ነው፡፡ ቁርአን እንዲህ ይላል ስለ ወሬ አምጪዎች እና መፍትሄው

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا إِن جَاءَكُمْ فَاسِقٌ بِنَبَإٍ فَتَبَيَّنُوا أَن تُصِيبُوا قَوْمًا بِجَهَالَةٍ فَتُصْبِحُوا عَلَىٰ مَا فَعَلْتُمْ نَادِمِينَ ﴿٦﴾

እላንተ ያመናችሁ ሆይ! ነገረኛ ወሬን ቢያመጣላችሁ በስህተት ላይ ኾናችሁ ሕዝቦችን እንዳትጎዱና በሠራችሁት ነገር ላይ ተጸጸቾች እንዳትኾኑ አረጋግጡ፡፡(49-6)

አላህ ሱ.ወ) ፍፁም ውሸት የሆነን ወሬ ተቀብሎ ለሚያናፍሱ ሰዎች የሚከተለውን ተግሳፅ ለግሷቸዋል፡፡

إِذْ تَلَقَّوْنَهُ بِأَلْسِنَتِكُمْ وَتَقُولُونَ بِأَفْوَاهِكُم مَّا لَيْسَ لَكُم بِهِ عِلْمٌ وَتَحْسَبُونَهُ هَيِّنًا وَهُوَ عِندَ اللَّـهِ عَظِيمٌ ﴿١٥﴾ وَلَوْلَا إِذْ سَمِعْتُمُوهُ قُلْتُم مَّا يَكُونُ لَنَا أَن نَّتَكَلَّمَ بِهَـٰذَا سُبْحَانَكَ هَـٰذَا بُهْتَانٌ عَظِيمٌ ﴿١٦﴾ يَعِظُكُمُ اللَّـهُ أَن تَعُودُوا لِمِثْلِهِ أَبَدًا إِن كُنتُم مُّؤْمِنِينَ ﴿١٧﴾

በምላሶቻችሁ በምትቅበባሉት ጊዜ ለእናንተም በእርሱ ዕውቀት በሌላችሁ ነገር በአፎቻችሁ በተናገራችሁና እርሱ አላህ ዘንድ ከባድ ኀጢአት ኾኖ ሳለ ቀላል አድርጋችሁ ባሰባችሁት ጊዜ (ከባድ ቅጣት በነካችሁ ነበር)፡፡በሰማችሁትም ጊዜ በዚህ ልንናገር ለእኛ አይገባንም፡፡ ጥራት ይገባህ፡፡ ይህ ከባድ ቅጥፈት ነው፤ አትሉም ነበርን፡፡ምእመናን እንደኾናችሁ ወደ ብጤው በፍፁም እንዳትመለሱ አላህ ይገስጻችኋል፡፡(24፡15-17)

ታላቁ ነብያችን (ሰ.ዐ.ወ) በበርካታ ሃዲሶቻቸው ስለ ሀሜት እና ነገር ማዋሰድ አስጠንቅቀዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የሚከተለው ይገኙበታል፡-

የአላህ መልእክተኛ ለሰሐቦችቻቸው እንዲህ ማለታቸው ተዘግቧል: ህሜት ምን እንደ ሆነ ታውቃላችሁ ?" እነሱም አላህ እና መልእክተኛው ነው የሚያውቁት ሲሉ መለሱ ፡፡ ነብያችንም “ ወንድምህ በማይፈልገው ነገር መናገር ነው" አሉ፡፤ ከሰሐቦች መሐል አንዱ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው " በዛ ሰው ላይ ያወራነው ነገር እውነት ሐሆነስ?( አማነው ይባላል) ነብያችንም , " እውነት ከሆነ አማሀው ይባላል ካልሆነ ግን ቀጠፍክበት ይባላል አሉ." (ሙስሊም)

በሌላም ሃዲሳቸው ነብዩ(ሰ‹ዐ.ወ) በሚዕራጅ ጉዟቸው ወቅት በጀሃነብ ውስጥ ሰዎች በነሃስ የተሰራ ትላልቅ ጥፍሮች ተደርጎላቸው ፊታቸውን እና አካላቸውን ይቧጥጣሉ፡፡ ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) እነዚህ ሰዎች ምንድናቸው ብለው ለጅብሪል (አ.ሰ) ጠየቁት፡፡እሱም እነዚህ በዱኒያ ላይ ሰዎችን ሲያሙ እና ነገር ሲያዋስዱ የነበሩ ናቸው ሲል ምላሹን ሰጣቸው፡፡

እኛ ትክክለኛ ሙስሊሞች ስንሆን ምላሳችን ከመጥፎ ንግገሮች እንዲሁም ከሀሜት የተቆጠብን እንሆናለን፡፡

"ምላሱን ከ መጥፎን ንግግር እና ብልቱን ከሐራም ለጠበቀ እኔ ጀነት ለመግባቱ ዋስትና እሆንለታለሁ፡፡"(ቡሐሪና ሙስሊም)

አንድ ሰሐባ የ አላህ መልእክተኛን ጠየቃቸው ምርጥ ሙስሊም ማለት ማነው ሲል ነብያችንም " ያ ሙስሊሞችን በ አፉ እና በእጁ (አዛ ) ክፉ ከማድረግ ነፃ የሖነው ሲሉ መለሱ "(ሙስሊም)፡፡

ሃሜት እና ነገር ማዋሰድ በኢላም ውስጥ ታላላቅ ከሚባሉ ወንጀሎች ተርታ የሚመደቡ ሲሆን ሰለፎች ወሬ በመጣላቸው ጊዜ ወሬውን ተቀብለው ያዙኝ ልቀቁኝ አይሉም ነበር፡፡ የሚከተለው ታሪክ እንመልከት፡፡

ለታላቁ ታቢኢን ሀሰነል በስሪ አንድ ሰው መጣና እከሌ ጋር አብሬ ነበርኩኝ፡፡ አንተን እኮ እንዲህ እንዲህ እያለ ሲያማህ፣ስላንተ መጥፎ ነገር ሲናገር ነበር.፡፡በክብርህ ላይ ሲዘምትብህ ነበር አላቸው፡፡ ሀሰነል በስሪም አንተ ሰው ትልቅ በደል ሁለታችንንም በደልክ አሉት፡፡ ሰውየው ደነገጠ እና እንዴት ሆኖ ነው ሁለታችሁንም የጎዳሁት፡፡ ላንተ እኮ ያለህን እኮ ነው ይዜ የመጣውልህ አላቸው፡፡ እሳቸውም ሲመልሱ ያማኝ ሰውዬ አሁን የነገርከኝን ነገር እኔ ብሰማ ደስ አየለውም፡፡ ሚስጥሩን አባከንክበት ፡፡እኔም ደግሞ እሱ እንዲህ ማለቱን ስሰማ ደስ አይልም አሉት፡፡ ቀጠሉና ላማቸው ሰውዬ ሊያስተምሩት አስበው ሂድና ሀሰነል በስሪ የአላህ ሰላም ባንተ ላይ ይሁን ይልሃል፡፡ቀጥልና ይህን ብሎሃል ብለህ ንገረው አሉት፡፡ሞት ሁላችንንም ይነካናል፣ቀብርም ሁለታችንንም አቅፋ ትይዘናለች፣ቂያማም እንሰበሰባለን፣ወደ አላህም ተመላሾች ነን፡፡ አላህም በመካከላችን ይፈርዳል፡፡አላህም ከፈራጆች ሁሉ በላጭ ነው በለው አሉት ይባለል፡፡

በአንድ ወቅት ፉዴል ኢብኑ በዝዋን የሚባሉ አንድ ትልቅ አሊምን አንድ ሰው ወደሳቸው ይመጣና እከሌ እኮ እንዱህ ብሎ አማህ ይላቸዋል፡፡እሳቸው ደግሞ ይህን ሲሰሙ እኔን እከሌ አማኝ ብለው ዘራፍ ሳይሆን ያሉት ቀጠል አደረጉና በአላህ ይሁንብኝ እኔንም እሱንም አላህ ይማረን፡፡እንዲያማኝ የገፋውን አካል ነው የማሳፍረው አሉ፡፡ ቀጠሉና ማነው ግን እኔን እንዲያማኝ ያዘዘው ወይም የገፋፋው አሉት፡፡ ሸይጣን ነዋ ሌላ ማን ይገፋፋዋል አላቸው፡፡ እንግዲህ ሸይጣንን ነዋ ለአኔም ላማኝም ሰው አላህ ይማረን ብዬ የማሳፍረው ብለው ምላሽ ሠጡት፡፡
ይህን ያሉበት ምክንያት በሃሜቱ ሸይጣን የፈለገው በሁለቱ ሰዎች መካከል ፀብ እና ጥል እንዲኖር በመሻቱ ነብር፡፡ እኚህ ታላቅ የሰለፍ አሊም ግን ሴራውን አከሸፉበት፡፡እኛስ እከሌ አማህ ሰንባል ምን እንል ይሆን????

ነብያችን (ሰ.ዐ.ወ) በሃዲሳቸው ወንድሙ ከፊቱ ሲታማ ሄሜቱን ያስቆመ (አላህ ሱ.ወ) ከፊቱ የጀሃነብን እሳት ዞር ያደርግለታል ይላሉ፡፡በሌላ ሃዲሳቸወ ደግሞ የወንድሙ ስጋ ሲበላ ያስቆመ አላህ (ሱ.ወ) በራሱ ላይ ይህን ሰው ከጀሀነብ እሳት ነጃ ሊያወጣው ግዴታ አድርጓል ብለዋል፡፡

እኛ ጀነት ለመግባት እየሰራነው እያልን ሰው ወሬ ይዞ መቶልም በውሸት ሲያማ ወሬ ያመጣውን ሰው ላለማስቀየም ስንል አላህን አስቆጥተን አብረን እናማለን፡፡ ወሬውንም ተቀበለን ሳናጣራ ሰዎች ላይ ምላሳችንን አርዝመን እንሳደባለን.እንተቻለን እንወነጅላለን፡፡አላሁ ሙስተአን::

ሀሜተኛ ሆነን ነገር አዋሳጆች ያመጡልንን ወሬ ተቀብለን ሰዎችን ለምንወነጅል ሰዎች አላህ (ሱ.ወ) የሚከተለውን በማለት ያስጠነቅቀናል

وَيْلٌ لِّكُلِّ هُمَزَةٍ لُّمَزَةٍ ﴿١﴾ الَّذِي جَمَعَ مَالًا وَعَدَّدَهُ ﴿٢﴾ يَحْسَبُ أَنَّ مَالَهُ أَخْلَدَهُ ﴿٣﴾ كَلَّا ۖ لَيُنبَذَنَّ فِي الْحُطَمَةِ ﴿٤﴾ وَمَا أَدْرَاكَ مَا الْحُطَمَةُ ﴿٥﴾ نَارُ اللَّـهِ الْمُوقَدَةُ ﴿٦﴾ الَّتِي تَطَّلِعُ عَلَى الْأَفْئِدَةِ ﴿٧﴾ إِنَّهَا عَلَيْهِم مُّؤْصَدَةٌ ﴿٨﴾ فِي عَمَدٍ مُّمَدَّدَةٍ ﴿٩﴾

ለሃሜተኛ ለዘላፊ ሁሉ ወዮለት፡፡ ለዚያ ገንዘብን የሰበሰበና የቆጣጠረው (ያደለበውም) ለኾነ ፤(ወዮለት)፡፡ ገንዘቡ የሚያዘወትረው መኾኑን ያስባል፡፡ ይከልከል፤ በሰባሪይቱ (እሳት) ውስጥ በእርግጥ ይጣላል፡፡ ሰባሪይቱም ምን እንደ ኾነች ምን አሳወቀህ? የተነደደችው የአላህ እሳት ናት፡፡ ያቺ በልቦች ላይ የምትዘልቅ የኾነችው፡፡ እርሷ በእርግጥ በእነርሱ ላይ የተዘጋጀች ናት፡፡ በተዘረጋች አዕማድ ውስጥ (የተዘጋች ናት)፡፡[104:-1-9)

ሰዎችን በሃሰት መወንጀል እና በሃሜት ፍቅር አብደን ወንድም እና እህቶቻችንን በክፉ የምናነውር ሰዎች ቁርአን የሚከተውን ተግሳፅ ይለግሰናል፡

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا لَا يَسْخَرْ قَوْمٌ مِّن قَوْمٍ عَسَىٰ أَن يَكُونُوا خَيْرًا مِّنْهُمْ وَلَا نِسَاءٌ مِّن نِّسَاءٍ عَسَىٰ أَن يَكُنَّ خَيْرًا مِّنْهُنَّ ۖ وَلَا تَلْمِزُوا أَنفُسَكُمْ وَلَا تَنَابَزُوا بِالْأَلْقَابِ ۖ بِئْسَ الِاسْمُ الْفُسُوقُ بَعْدَ الْإِيمَانِ ۚ وَمَن لَّمْ يَتُبْ فَأُولَـٰئِكَ هُمُ الظَّالِمُونَ ﴿١١﴾

እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ወንዶች ከወንዶች አይቀልዱ፡፡ ከእነርሱ የበለጡ ሊኾኑ ይከጀላልና፡፡ ሴቶችም ከሴቶች (አይሳለቁ)፡፡ ከእነርሱ የበለጡ ሊኾኑ ይከጀላልና፡፡ ነፍሶቻችሁንም አታነውሩ፡፡ በመጥፎ ስሞችም አትጠራሩ፡፡ ከእምነት በኋላ የማመጽ ስም ከፋ፡፡ ያልተጸጸተም ሰው እነዚያ እነርሱ በዳዮቹ ናቸው፡፡(49-11)
በአንድ ወቅት የተከሰተውን ታሪክ ላስታውሳችሁ እና መልጭክቴን ልጨርስ፡፡

በአንድ ዘመን በሰላም ተዋደው በፍቅር የሚኖሩ ባልና ሚስቶች ነበሩ ፡፡ አንድ ቀን ቤት ስራ ይቸግራቸውና ባልየው ባሪያ ሊገዛ ይወጣል እናም ሲፈልግ አንድ ባሪያ ያገኝና ስለ እሱ ባህሪ ነጋዴውን ይጠይቃል ሻጩም ሐቀኛ ስለነበር "ይህ ባሪያ አንድ ችግር አለበት ነገር ያሳብቃል ከዛ ውጪ ግን ምንም ችግር የለበትም ይለዋል" ባለቤቱም ነገር ማሳበቅን ክብደት ስላስሰጠው ችግር የለውም ይልና ይህን ባሪያ ገዝቶ ወደ ቤቱ ይሄዳል፡፡ ይህ ባሪያም ቤት ውስጥ መኖር ከጀመረ በኋላ አንድ ቀን አሳዳሪው ወደ ስራ ሲሄድ ለሚስቱ እንዲህ ይላታል "ባልሽ ካንቺ ውጪ ያፈቀራት ሴት አለች በተደጋጋሚ አይቸዋለው ከ ሌላ ሴት ጋር እናም ይህን የመሰለ ባል ከምታጪ ድግምት እንስራበት ከዛ አንቺን ብቻ ያፈቅራል ከአንቺም ጋር ተዋዶ ይኖራል አለች፡፡ " ሚስትየዋም እሱን ማጣት ስላልፈለገች በዚሁ ሐሳብ ትስማማ እና በምን መልኩ ድግምት እንደምታደርግበት ትጠይቀዋለች ይህም ባሪያ እንዲህ ይላታል " ማታ ሲተኛ ከሱ ፀጉር ላይ በቢላዋ ትንሽ ፀጉር ቆርጠሸ አምጪልኝ " ከዛ እኔ ድግምት አደርግባታለው ይላታል ፡፡ በዚህም ይስማማሉ ……

ባልየው ከስራ ሲመጣ ሚስቱ ወደ ደጅ ወጣ ማለቷን ያስተዋለው ይህ ነገር አሳባቂ ባሪያ ለባልየው እንዲህ ይለዋል " ሚስትህ ዛሬ በቤትህ ከሌላ ወንድ ጋር ነው የዋለችው፡፡ ስታወራ በ ድብቅ ስሰማት ማታ አንተ ስትተኛ በቢላዋ አርዳ ገላህ ጠቅልላ ያንን ወንድ ልታመጣብህ ነው እና አሳዳሪዬ ተከታተላት ይለዋል" እናም እውነቱን ከሆነ እስኪ አያለው ይልና ባልየው መጠባበቅ ይጀምራል፡፡ እንደ መሸም ከ ሚስቱ ጋር አብረው ተኙ … ሚስቱም ባሏ የተኛ መስሏት ቢላዋ ለማምጣት ተነሳች እናም ቢላዋ ይዛ መጥታ ፀጉሩን ልትቆርጥ ስትል በመጠባበቅ የነበረው ባሏ ቀድሞ ይይዛት እና ይገላታል፡፡ በዚህ አሳባቂ ባሪያ ሰበብ የሚስትየው ጎሳዎች ይመጡና ባልየውን ይገሉታል …. የባልየውም ጎሳዎች ይሰሙና ከነዛ ጎሳዎች ጋር ደም አፋሳሽ እልቂት ውስጥ ገባ፡፡ ይህን ይመስላል የነገር አዋሳጆች ስራ፡፡

ነብዩ(ሰ፣ዐ.ወ) በሃዲሳቸው ቀድሞውንም ነገር አዋሳጅ ፈፅሞ ጀነት አይገባም ሲሉ አስተምረውናል፡፡

አላህ (ሱ.ወ) በትክክል በተግባር የሰለፎቾን መንገድ ተከታይ ያድርገን፡፡ በምላስ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ሁሉንም የሰለፎቻችንን መንገድ የምንከተል ያድርገን፡፡

አላህ ከሃሜት፣ከወሬ አሳባቂዎች ፈተና እና ወሬ ተቀብለን ሰዎች ክብር ላይ ከመዝመት ይጠብቀን፡፡አሚን!!!