Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ኢስላማዊ ሀገራትን መወረፍ ዓላማው ምንድነው ..?

ኢስላማዊ ሀገራትን መወረፍ ዓላማው ምንድነው ..?
ምስጋናና ውዳሴ ለዓለማቱ ጌታ ለአሏህ ይሁን ሰላትና ሰላም በነቢዩ ሙሐመድና በተከታዮቻቸው ላይ ይስፈን
ኢስላማዊ ሀገራትን መጥላት የሙስሊም ባህሪይ ሳይሆን የኢስላምና የሙስሊሞች ጠላት የሆኑ ሰዎች እነዲሁም የሙናፊቆች መለያ ነው
ባለንበት ዘመን ዓለም ላይ የሳውዲ ዓረቢያን ያክል የኢስላምን ህግጋት በአግባቡ ተግባራዊ የሚያደርግ ሀገር አላውቅም፡፡ ከመሆኑም ጋር አንዳንድ ሰዎች የዚህችን የተውሒድና የሱና ሀገር በሆነ ባልሆነው ስሟን ስያጠፉ ይታያል
አንዳንዶችማ ትንሽ እንኳ ሳያፍሩ "ከዚህች ሀገር መሪዎችና ህዝቦች አይሁዶች ይሻላሉ" ሲሉም ይስማል ይህ በጣም ከባድ ንግግር ነው የተናጋሪውንም እምነት አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ነው
አሏህ በተከበረው ቃሉ ስለ ከሃዲያን ( አይሁዳዊያን) ሲናገር የሚከተለውን ብሏል (أَلَمْ تَرَ إِلَى الَّذِينَ أُوتُوا نَصِيبًا مِنَ الْكِتَابِ يُؤْمِنُونَ بِالْجِبْتِ وَالطَّاغُوتِ وَيَقُولُونَ لِلَّذِينَ كَفَرُوا هَٰؤُلَاءِ أَهْدَىٰ مِنَ الَّذِينَ آمَنُوا سَبِيلًا أُولَٰئِكَ الَّذِينَ لَعَنَهُمُ اللَّهُ ۖ وَمَنْ يَلْعَنِ اللَّهُ فَلَنْ تَجِدَ لَهُ نَصِيرًا) [سورة النساء 51- 52]
" እነዚያ ከመፃህፍት የተወሰነን ድርሻ የተሰጡ (አይሁዶችን) አልተመለከትክም እንዴ? በድግምትና ከአሏህ ውጪ ባሉ የከንቱ አማልክት ያምናሉ ከሃዲያንንም፥ እነሱ ከአማኞች (ከነቢዩ ተከታዮች) የተሻሉ ናቸው' ይላሉ እንዲህ አይነት ሰዎች አሏህ የረገማቸው ናቸው አሏህ የረገመው ሰውም ረዳት አታገኘለትም" ሱረቱንኒሳእ 51-52
ሌላው እንኳ ቢቀር እንዴት በአሏህ ብቸኝነት የሚያምንን ሰው ከሱ ካፊር ይሻለዋል ይባላል?!
ለመሆኑ በያመቱ የዓለም ሑጃጆችን ተቀብሎ በሚገባ የሚያስተናግደው ማነው? መካና መዲናን ሚንከባከበውስ ማነው? ሸሪዓው በሚያዘው መሰረት ወንድና ሴት ለየብቻቸው የሚማሩት የት ሀገር ነው ? የትስ ነው የሰላት ወቅት እንደገባ መስሪያ-ቤቶችና ንግድ ቤቶች በሙሉ የሚዘጉት? የትኛዋ ሀገርስ ናት በያመቱ ከ140 በላይ ሀገራት በነፃ ተማሪዎችን በመቀበል ትክክለኛውን የዲን ትምህርት አስተምራ ለደዕዋ ወደያገራቸው የምትልከው? ዓለም ውስጥ በመለካም ነገሮች የሚያዝ ከመጥፎ ነገሮችም የሚከለክል የፖሊስ ድርጅት በማቋቋም የዲንን ድንበር የምታስከብረዋ ሀገርስ ማናት ‪#‎ሶሪያ‬# የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ሰላም እንዲያጡ፣ ከሀገራቸው እንዲፈናቀሉ አንዱ ሰበብ ከሆኑት ሀያላን ሀገራት (የሚባሉት ) እንደ እነ አሜሪካና ፈረንሳይ ከ10 እና ከ30 ሺህ በሌይ ስደተኛ አንቀበልም ሲሉ ከ2 ሚለየን በላይ ስደተኞችን ተቀብላ ወንድሞቻችን ብላ በሚገባ ያስተናገደችውስ ሀገር ማነት!? ወዘተ.... መሰል የሆኑ ለኡማውና ለዲኑ ወደርየለሽ ስራ የምትሰራን ሀገረ መጥላትና መጥመድ፥ ምንም ከማያውቅ መሀይም ወይም ደግሞ ሐቅና መረጃን ትቶ ስሜቱን እየተከተለ ከሚጓዝ ሰው እንጂ በሙሉ ልቡ ከሚያስብና በያንዳንዱ ነገር አሏህ ፊት ቆሞ እንደሚጠየቅ ጠንቅቆ ከሚረዳ ሙስሊም የሚመነጭ አይደለም፡፡
ታላቁ የዲን ሊቅ ኢብኑ ባዝ رحمه الله እንዲህ ይላሉ " ይህቺን ሀገር መጥላትና መጥመድ ተውሒድን መጥላትና መጥመድ ነው" ይህንንም እውነታ ማንኛውም ለተውሒድና ለሱና ትክክለኛ ውዴታ ያለው ሰው በሙሉ በቀላሉ ሊያስተውለው ይችላል
ከሀገሪቱ ዑለማዎችም በተጨማሪ የተለያዩ ሀገራት ለመሳሌም፦ ህንድ፣ የመን፣ ግብፅ ወዘተ የሱና ዑለሞችም "ባለንበት ዘመን እንደ ሳውዲ ዓረቢያ የኢስላምን ህግጋት የሚተገብር ሀገር አላውቅም " ሲሉ ሰምቻለሁ... አምቢቤያለሁ
የዑለማዎች አመለካከት ይህ ሆኖ ሳለ ለምን ይሁን ታድያ አንዳንድ ሰዎች ሀገሪቷን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሚወርፉት? ለምንስ ነው ለመላው ሙስሊም በተለያዩ ሁኔታዎችና አጋጣሚዎች የምትውለውን ትልቅ ውለታ የሚዘነጉት?
በጣም የሚገርመው ከንዲህ አይነት ሰዎች ውስጥም በሀገሪቱ ፀጋዎች እየተንደላቀቀ የሚኖር አለ ከነሱ ውስጥም አምስት ወቅት ሰላቱን በአግባቡ የማይሰግድ፣ በራሱ ላይ ተግባራዊ ማድረግ የሚችለውን የነቢዩን صلى الله عليه وسلم ሱናዎች ሳይተገብር፣ የቤተ-ሰብና የጎረቤቶቹን ሐቅ እንኳ ሳይወጣ የተለያዩ ሀገራት ዜጎችን የምታስተናግድ፣ ብዙ ጠላቶች ያሉባትን ሀገር ስም ስያጠፋ፣ የሌለባትን ሲለጥፍ ይታያል
እንደው ይህ ሁሉ ምን አይተውባት ነው? ምንስ በድላቸው ነው?
ብዙዎች የሚያነሱት የኢቃማን ጉዳይ ነው ኢቃማ በቀላሉ አይሰጡም ሲታደስም ጣጣ ያበዛሉ የውጭ ዜጋን ይበድላሉ ወዘተ ይላሉ
ለዚህ ምላሽ የነቢዩን ሐዲሥ ላስቀምጥ عَنْ أَبِي أُمَامَةَ ، قَالَ : قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ : " مَنْ أَحَبَّ فِي اللَّهِ وَأَبْغَضَ فِي اللَّهِ وَأَعْطَى لِلَّهِ وَمَنَعَ لِلَّهِ فَقَدِ اسْتَكْمَلَ الإِيمَانَ " ( ለአሏህ ብሎ የወደደ ለአሏህም ብሎ የጠላ ለአሏህ ብሎ የሰጠ ለአሏህም ብሎ የነፈገ በርግጥም ኢማኑ ተሟልቷል) ለግል ጥቅም ብሎ አንደን ሰው ወይም ሀገር መጥላት የኢማን ጉድለት ነው፡፡ ይህ በንዲህ እንዳለ ሁሉም ሀገራት የውጭ ዜጎችን በተመለከተ ራሱን የቻለ ህግ አላቸው ህገ ወጥ የሚባሉ ወይም ህግን የማያከብሩ ሰዎች ላይም የሚወስዱት እርምጃ የተለያየ ነው ከኢሮፕ ሀገራት ውስጥም ህገ ወጥ የሚሉትን ሰው እስከነሀይወቱ ባህር ውስጥ ሲጨምሩ ታይቷል! ሳውዲ ውስጥ የመኖሪያ ህግና ደንብን ጠብቆ የሚኖርን ሰው ያላንዳች ምክንያት የውጭ ዜጋ ነህ ብቻ ብላችሁ በድሉ የሚል መመሪያ ሲተላለፍ ሰምተን አናውቅም
ሌሎች ደግሞ ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት አላቸው ይሉሃል ለመሆኑ ባለንበት ዘመን ከዓለም ሀገራት ጋር በምንም ሳይገናኝ በርና ድንበሮቹን ሙሉ ለሙሉ ዘጋግቶ የሚኖር ሀገር አለን?! ዋናው ግንኙነት መኖሩ ሳይሆን ሉአላዊነትና አመራር ላይ ተፅእኖ መኖር አለመኖሩ ላይ ነው እስከምናውቀው ድረስ ሀገራቸውን የሚያሳድጉባቸው ነገሮች ላይ ከመተባበር ውጪ ሌላ የሀገሪቱ ጉዳይ ላይ የማንንም ጣልቃ ገብነት አይቀበሉም
አስፈላጊ ሆኖ በተገኘበት ወቅት ነቢዩም صلى الله عليه وسلم በዘመናቸው ከነበሩ ከሃዲያን ጋር የሰላም ስምምነት ተፈራርመዋል የስምምነቱን ረቂቅም ነቢዩ እየተናገሩ ዐሊይ ኢብን አቢጧሊብ በተከበረው እጃቸው ፅፈዋል الرحمن....محمد رسول الله. ..መስል ቃላትንም ሙሽሪኮች እንዳይፃፉ ብለው ነቢዩም እሺ ብለው እንዲሰረዙ አዘዋል ከዚህም አልፎ "ዘንድሮ ዑምራ ሳታደርጉ ከመጣችሁበት ተመልሳችሁ ቀጣይ ዓመት ላይ ለሶስት ቀናት ብቻ መካ ቆይታችሁ ዑምራ አድርጋችሁ ትወጣላችሁ ከኛ ውስጥ ሰልሞ ወደናንተ የሄደን ሰው በሙሉም ወደኛ ትመልሳላችሁ" እያሉ ይህን ሁሉ ነቢዩ ተቀብለው ፈርመዋል' ይህም የሆነው አሏህ ስላዘዛቸውና በዚህ ስምምነት መሰረትም ለተከታታይ 10 ዓመታት ጦርነት ቆሞ ሙስሊሞች እንዲያገግሙ በማለት ነው በጊዜው ብዙ ሰሓቦች በፀጋ ባይቀበሉትም ሇላ ላይ ግን ተደስተውበታል ይህንንም ታሪክ በሰፊው ቡኻሪን ጨምሮ የሐዲሥና የሲራ ዘጋቢዎች ጠቅሰውታል
ወደ ዋናው ርዕሳችን እንመለስና፦ በሁሉም ነገር አሏህን እንፍራ ስሜታዊ አንሁን ውዴታችንም ይሁን ጥላቻችን መጠን ይኑረው ሁሌም ቀጥሎ ያለውን የጌታችንን ንግግር እናስታውስ
(يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا كُونُوا قَوَّامِينَ بِالْقِسْطِ شُهَدَاءَ لِلَّهِ وَلَوْ عَلَىٰ أَنْفُسِكُمْ أَوِ الْوَالِدَيْنِ وَالْأَقْرَبِينَ ۚ إِنْ يَكُنْ غَنِيًّا أَوْ فَقِيرًا فَاللَّهُ أَوْلَىٰ بِهِمَا ۖ فَلَا تَتَّبِعُوا الْهَوَىٰ أَنْ تَعْدِلُوا ۚ وَإِنْ تَلْوُوا أَوْ تُعْرِضُوا فَإِنَّ اللَّهَ كَانَ بِمَا تَعْمَلُونَ خَبِيرًا) [سورة النساء 135] "" እናንተ ምእምናን ሆይ በፍትህ ላይ ቋሚ ሁኑ ለአሏህ ስትሉም መስክሩ እራሳችሁም ላይ እንኳን ቢሆን ወላጆችና ዘመዶችም ላይ ቢሆን የምትመሰክሩለት ወይም የምትመሰክሩበት አካል ሀብታም ወይም ደሀ ቢሆን እንኳ አሏህ ከሱ ይልቅ ሊፈራና ውዴታው ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ታዳሉ ዘንድም ስሜታችሁን አትከተሉ ብትቀጥፉ ወይም ሐቁን ከመናገር ወደ ሇላ ብትሉ አሏህ የምታደርጉትን በሙሉ ጠንቅቆ የሚያውቅ ጌታ ነው"" ሱረቱንኒሳእ 135
(وَلَا يَجْرِمَنَّكُمْ شَنَآنُ قَوْمٍ عَلَىٰ أَلَّا تَعْدِلُوا ۚ اعْدِلُوا هُوَ أَقْرَبُ لِلتَّقْوَىٰ ۖ وَاتَّقُوا اللَّهَ ۚ إِنَّ اللَّهَ خَبِيرٌ بِمَا تَعْمَلُونَ) [سورة المائدة 8] "" የሰዎች ጥላቻ ኢፍትሐዊ ለመሆን አያነሳሳችሁ ፍትሐዊ ሁኑ ይህም አሏህን ፈሪ ለመሆን የቀረበ -የተሻለ- ነው አሏህን ፍሩ እርሱም የምታደርጉትን በሙሉ ጠንቅቆ የሚያውቅ ጌታ ነው ""
ጭፍን ጥላቻ የአሏህ ፍራቻ ከቀልባችን እንዲጠፋ ያደርግል ሰዎች ላይ የሌለባቸውን ነገር እንደንለጥፍና ጥሩ ጎናቸውንም እንድንደብቅ ያደርገናል
በጣም ሲበዛም ከአሏህ ቀደር ጋር ያጋጨናል ሰሞኑን መካ ሐረም ውስጥ አሏህ ሽቶ የመስጂደል ሐራምን የማስፋፋት ስራ ይሰራበት የነበረ የግንባታ እቃዎች ማንሻ ብረት በከፍተኛ ንፋስ ምክንያት ወድቆ የበርካታ ሰዎችን -የሐጅ እንግዶችን- ህይወት መቅጠፉ ይታወቃል
የሀገሪቱ ባለስልጣናት ምንም ባላጠፉበት ሁኔታ አንዳንድ ሰዎች ብዙ አላስፈላጊ ንግግሮችን ተናግረዋል በየሚዲያውም የሀገሪቱን ስም አጥፍተዋል የሀገሪቱ መንግስትና የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚንስተር ሳይቀር ከቦታው ዘልቀው ሀዘናቸውን በመግለፅ ሁኔታውን ከማጣራታቸውና ለተጎጂዎችም አስፈላጊውን እርዳታ ከማድረጋቸው፣ የሞቱትንም በተቀደሰችው ሀገር ከሰሓቦችና ከልጆቻቸው አቅራቢያ እንዲቀበሩ ከማድረጋቸው ጋር "ነገሩን ደበቁት የሀገሪቱም ሚዲያዎች አልዘገቡትም" ብለዋል አጂብ!! (ካላፈርክ የሻህን ስራ)ብለው የለ ነቢያችን صلى الله عليه وسلم አሏህ ምን ይለኛል ማለት ሲጠፋ ሰው ምን ይለኛል ማለትም አብሮ ይጠፋል
እንደው በአደጋው ምክንያት የአካለ ጎዶሎነት አደጋ ለደረሰባቸውና በአደጋው ለሞቱ ሰዎች ቤተሰቦቻቸው በሙሉ ለያንዳንዱ አንድ ሚሊየን ሪያል ቀላል አደጋ ለደረሰባቸው ደግሞ ግማሽ ሚሊየን ሪያል መለገሳቸውን፣ ቀጣይ ዓመት ላይም በሀገሪቱ ወጪ የተወሰኑ ቤተሰቦቻቸውን ሐጅ ለማስደረግ ቃል መግባታቸውን ከሀገሪቱ ሚዲያዎችም አልፎ የውጭ ሚዲያዎች ዘግበዋል
የዒድ ለትም አሏህ ሽቶ ሚና ላይ ጠጠር ወርውረው ሲወጡ ለመመለሻ በተዘጋጀው ሳይሆን በሐጅ ኮሚቴና አስተናጋጆች የተቀመጠውን የመንገድ አጠቃቀም ህግ ሳይጠበቁ ሊወረውሩ የሚሄዱ ሰዎች በሚጓዙበት መንገድ በመመለሳቸው ሰበብ ከፍተኛ ግፊያ ተፈጥሮ የሞቱ ሑጃጆችንም በተመለከተ የሀገሪቱን መሪዎች የሚተቹ አልጠፉም!
አሏህ ግን ያለው እንዲህ ነበር (أَلَّا تَزِرُ وَازِرَةٌ وِزْرَ أُخْرَىٰ) [سورة النجم 38]
"አንዲት ነፍስ የሌላን ነፍስ ወንጀል አትሸከምም"
ሁላችንም አሏህን እንፍራ ነገ ወደሱ ተመላሾች መሆናችንንም አንዘንጋ የተሳሳተ እምነት ባስያዝናቸው አላዋቂ ሰዎች ልክም አሏህ ዘንድ እንደምንቀጣ እንወቅ መካና መዲናን ያቀፈችዋን ሀገር መጥመድና ሰዎችም እሷን እንዲጠሉ ማድረግ የተሸከመችውን የኢስላም ተልእኮ፣ ዑለማዎቿንና በውስጧ የሚገኙ መላውን ኡማ የሚያገለግሉ ተቋማትንም ጭምር እንዲጠሉ ማድረግ ነው ይህም አሏህ ዘንድ ትልቅ ተጠያቂነትን ያስከትላል የኡማውንም አንድነት ለአደጋ ያጋልጣል
ስንትና ስንት የዲን ጠላት የሰላም ፀር የሆኑ ሀገራትን በተመለከተ ትንፍሽ እንኳ የማይሉ ይህቺን ሀገር ግን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሚያጥላሉ ይህም ጀግንነት የሚመስላቸው ሰዎች አሉ! ወገኖቼ ሆይ አሏህን ፍሩ ከሙስሊም የማይጠበቅን ስራ አትስሩ ነቢዩ صلى الله عليه وسلم የተናገሩትንም ሐዲስ ቅሩ عن عَبْدِ اللَّهِ بْنِ عَمْرٍو -رَضِيَ اللَّهُ عَنْهُمَا -عَنْ النَّبِيِّ -صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ -قَالَ: " الْمُسْلِمُ مَنْ سَلِمَ الْمُسْلِمُونَ مِنْ لِسَانِهِ وَيَدِهُِ" رواه البخاري " ትክክለኛ ሙስሊም ማለት፥ ከምላሱ ጣጣ-ዘለፋ-እና ከእጁ ጥቃት ሙስሊሞች ሰላም የሆኑ ወይም የዳኑ ሰው ነው "
በመጨረሻም፡ ይህ ሲባል ሀገሪቷ ላይ ምንም ስህተት የለም ማለት በፍፁም አይደለም የሰው ልጅ ባለበት ቦታ ሁሉ ስህተትም ይኖራል በነቢዩ صلى الله عليه وسلم ዘመን በመዲና ግዛት ኸምር የጠጡ፣ ዝሙት ላይ የወደቁ ግለሰቦች እንደነበሩ የሐዲሥ መዛግብት ላይ ሰፍሯል የጥቂቶችን ጥፋት የሁሉ ጥፋት አናድርገው የህዝቡንም መሪው ላይ አንጫነው
ስህተት ስናይ ከቻለን ቀጥታ እንምከር ካልቻለን የሚችሉ ሰዎች እንዲመክሩ መልእክት እናስተላልፍ ምንም ማድረግ ካልቻለን ግን መራገምና ስም ማጥፋት ሳይሆን ዱዓ እናድርግ የአንድ ትክክለኛው አማኝ ግዴታም ይሄው ነው
ጌታዬ ሆይ ወገኖቼን ለመምከር የማውቀውን ተናግሬያለሁ የልቤን አንተው ታውቃለህ ነገም እፊትህ ታቆመኛለህ መልእክቴን አድርስልኝ ግቡንም የሚመታ አድርግልኝ
ያረብ--- ለኢስላምና ለሙስሊሞች የቆመን በሙሉ እርዳታህን ለግሰው ለኢስላምና ለሙስሊሞች ፀር የሆነን በሙሉ እድሜውን አሳጥረው ሴራውንም አክሽፈው አሏሁመ አሚን
سبحانك اللهم وبحمدك أشهد أن لا إله إلا أنت أستغفرك وأتوب إليك አሕመድ አደም ዙል-ሒጃ 12/1436 ዓ.ሂ