Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ጥያቄ ፦ የተራዊህ ሰላት ሑክሙ ምንድን ነው? የረከዓው ብዛትስ ስንት ነው? (ሸይኽ መሐመድ ኢብኑ ሷሊህ አል-ዑሰይሚን ረሒመሁላህ)

Taju Nasir's photo.
ጥያቄ ፦ የተራዊህ ሰላት ሑክሙ ምንድን ነው? የረከዓው ብዛትስ ስንት ነው?
መልስ፦ የተራዊህ ሰላት የነቢዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ሱና ነው። ነቢዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) አንድ ሌሊት መስጊድ ውስጥ ሲሰግዱ ሰዎች ተከትለዋቸው ሰገዱ። በሦስተኛው ወይም በአራተኛው ቀንም ሰዎች በብዛት ተሰበሰቡ። ነቢዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ግን ወደ መስጊድ አልሄዱም። በነጋታው ነቢዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፦ <<ያደረጋችሁትን (መሰብሰባችሁን) በእርግጥ አይቻለሁ፤ ሰላቱ በናንተ ላይ ፈርድ (ግዴታ) ይሆናል ብዬ በመፍራቴ እንጂ ወደናንተ ከመውጣት የከለከለኝ ነገር የለም>> (ቡኻሪና ሙስሊም)። ይህም በረመዳን ውስጥ ነበር።
የረከዓውን ብዛት በተመለከተ ደግሞ አስራ አንድ ረከዓ ነው። ዓኢሻ (ረዲየላሁ ዐንሀ) በረመዳን የነቢዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ሰላት እንዴት እንደነበር ተጠይቃ << በረመዳንም ሆነ ከረመዳን ውጭ በአስራ አንድ ረከዓ ላይ ምንም አይጨምሩም >> ብላለች። (ቡኻሪና ሙስሊም)።
አስራ ሶስት ረከዓ ቢሰግድም ችግር የለውም። ኢብኑ ዓባስ << የነቢዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ሰላት አስራ ሦስት ረከዓ ነበር>> ብሏልና። ማለትም የሌሊት ሰላት (ቡኻሪና ሙስሊም)

ከኡመር ኢብኑ አልኽጣብም በትክክለኛ ሰነድ (ሰንሰለት) የተዘገበው አስራ አንድ ረከዓ ሲሆን በ<<ሙወጠእ>> ኪታብ ውስጥ ይገኛል። ከዚህ ቢጨምርም ችግር የለውም ነቢዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ስለ ሌሊት ሰላት ሲጠየቁ << ሁለት ሁለት>> አሉ እንጂ አልገደቡምና። ከሰለፎችም በዚህ ጉዳይ ላይ በተለያየ መልኩ ተዘግቧል። በዚህ ላይ ነገሩ ሰፋ ይላል። ግን ከነቢዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) በተዘገበው ላይ ብቻ ማለትም በአስራ አንድ ወይም በአስራ ሶስት ረከዓ መወሰኑ በላጭ ነው። ነቢዩም (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ሆኑ ከኹለፋኡራሺዲን አንድም ሃያ ሦስት ረከዓ መስገዳቸው በትክክለኛ ዘገባ አልደረሰንም። ዑመርም የሰገዱት አስራ አንድ ረከዓ ነው። ዑመር አብይ ኢብኑ ከዕብንና ተሚም አድዳሪን ሰዎችን አስራ አንድ ረከዓ እንዲያሰግዱ አዘዋቸውል። (ማሊክ ዘግበውታል)። ከዑመር የሚጠበቀውም ይህ ነው። የርሳቸው ስራ ከነቢዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ሥራ ጋር መጣጣም አለበትና።
ሰሃቦችም ከአስራ ሦስት ረከዓ በላይ መጨመራቸው የተዘገበና የምናውቀው ነገር የለም። እንዲያውም ገሀዱ የዚህ ተቃራኒ ነው። ዓኢሻ (ረዲየላሁ ዐንሀ) << በረመዳንም ሆነ ከረመዳን ውጭ ከአስራ አንድ ረከዓ አይጨምሩም ነበር >> ማለቷንም አውስተናል። የሰሃቦች ኢጅማዕ (ስምምነት) ማስረጃ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። እንድንከተላቸው በነቢዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) የታዘዝንባቸውና የዚህ ኡመት በላጭ የሆኑት ኹለፋኡራሺዲን ይገኙባቸዋልና።
የተራዊህ ሰላት ረከዓ ብዛትና የመሳሰሉት ነገሮች ሰዎች በኢጅትሃድ ሊለያዩባቸው የሚችሉ ጉዳዮች በመሆናቸው በሰዎች መከካል ልዩነትንና መቃቃርን ሊያስከትሉ አይገባም። በተለይም በዚህ ጉዳይ ላይ ሰለፎችም ልዩነት ነበራቸው። በዚህ ጉዳይ ላይ የኢጅትሃድን በር ዝግ የሚያደርግ ማስረጃ የለም።
አንድ ዓሊም በኢጅትሃዳዊ ጉዳይ ከርሱ ለተለየው ሰው ያለው ቃል ምንኛ ያማረ ነው! እንዲህ አለው፦ << አንተ ከኔ የተለየ ሐሳብ በመያዝህ ተስማምተህኛል። ኢጅትሃድን በሚቀበል ጉዳይ ላይ ሁለታችንም ሐቅ (ትክክለኛ ሐሳብ) ነው ብለን የምናምንበትን መከተል እንዳለብን እናምናለን (በዚህ ነው ስምምነታችን)። >> አላህ የሚወደውን ነገር ያሰራን።
(ሸይኽ መሐመድ ኢብኑ ሷሊህ አል-ዑሰይሚን ረሒመሁላህ)