Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ጥቂት አስደንጋጭ እውነታዎች ከአርሪሳላህ ፊልም

Ibnu Munewor's photo.
ጥቂት አስደንጋጭ እውነታዎች ከአርሪሳላህ ፊልም
መግቢያ፡-
ፅሁፌ ስለረዘመብኝ ስለፊልሙ አዘጋጅና ተያያዥ ነጥቦች ምንም አላልኩም፡፡ እንዳውም ሊነሱ የሚገባቸው ነጥቦችን ሁሉ ቆርጬ አውጥቻለሁ፡፡ ብቻ ቢቀድሙ አንባቢን ለማስተዋል ይጋብዛሉ ያልኳቸውን ጥቂት ነጥቦችን መርጬ አቅርቢያለሁ፡፡ ባይሆን አንድ ትልቅ ሐቅ ላስቀድም፡፡ ይሄ ፊልም ለእይታ የበቃው የሊባኖስ የሺዐ ምክር ቤት ከተስማማበት በኋላ መሆኑ ይታወቅ፡፡ ይህን እውነት ይዘን ፊልሙን ስንቃኘው ፊልሙ ለምን ሺዐ-ዘመም ቅኝቶች እንደበዙበት ይገለጥልናል፡፡ ቀጥታ ወደ ነጥቦቹ ልግባ
1. ዋሻውን የዘጋው የሸረሪቷ ድር፡- ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከአቡበክር ጋር በመሆን ከመካ አጋሪዎች ሸሽተው ወደ መዲና ሲሰደዱ ከዋሻ ውስጥ እንደተደበቁ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ዋሻውን ሸረሪት እንዳደራችበት እና ቁረይሾች ድሩን ተመልክተው ከዚህ ውስጥ ማንም አልገባም ብለው እንደተመለሱ የሚያትተው ክፍል “ዶዒፍ” ነው፣ ደካማ፡፡ የታላቁን ሙሐዲሥ ሸይኹልአልባኒ ረሒመሁላህ [አድዶዒፋህ፡ 1129፣ 1189] ይመልከቱ፡፡ ሸይኽ ኢብኑዑሠይሚን ረሒመሁላህ “ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በሠውር ዋሻ ውስጥ በተደበቁ እለት የሸረሪቷ ማድራትና የእርግቦቹ እንቁላል መጣል ማስረጃ መጥቶበታልን?” ተብለው ሲጠየቁ እንዲህ ብለው ነበር የመለሱት፡- “የለም! የታሪክ ሰዎች ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በሠውር ዋሻ ውስጥ በተደበቁ እለት ሸረሪቷ እንዳደራችና እርግቧም ከሆነች ዛፍ ቅርንጫፍ ላይ እንዳረፈች ይተርካሉ፡፡ ይሄ ግን ውሸት ነው፣ ትክክለኛ አይደለም፡፡ በዚህ ውስጥም ለነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሊጠቀስ የሚችል ተአምር የለበትም፡፡ የትኛውም ሸረሪት የምታደራበት እና በዙሪያው እርግብ የምታካብበው ሰው የሚመለከተው “ማንም የለም” ይላል፡፡ ነገር ግን መልእክተኛው ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ጠላቶቻቸውን ነው ያሳወረላቸው፡፡ ለዚያም እኮ ነው አቡበክር “የአላህ መልእክተኛ ሆይ አንዳቸው ‪#‎ወደ_እግሩ_ቢመለከት_በርግጥም_ያየናል‬ ” ያላቸው፡፡ ምክንያቱም ከልካይ የለምና፡፡ እናም ሸረሪቷም፣ እርግቢቷም ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በሠውር ዋሻ በተቀበቁበት እለት መወሳታቸው ትክክለኛ አይደለም፡፡…” [ሊቃኡ ባቢልመፍቱሕ፡ 229/4]
2. ሌላው ደካማ ማስረጃ ላይ ተመርኩዞ ፊልሙ ላይ ከወጡ ነገሮች አንዱ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከመካ ወደ መዲና ሲገቡ “ጦለዐልበድሩ ዐለይና ሚን ሠኒየቲልወዳዕ” እያሉ ሰዎች እንደተቀበሏቸው መጠቀሱ ነው፡፡ የዚህ ተረክ ሰነድ ደካማ ከመሆኑም ባለፈ በግጥሙ ውስጥ የተገለፀው “ሠኒየቱልወዳዕ” የተባለው ቦታ የሚገኘው ከመዲና በስተሰሜን በኩል ስለሆነ ከመካ ወደ መዲና (ደቡብ) የሚገባ ሰው እንደማያገኘው ኢብኑልቀይዪም ገልፀዋል፡፡ ሸይኹል አልባኒም ረሒመሁላህ ደካማ እንደሆነ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ [አድዶዒፋህ፡ 598]
3. በፊልሙ ላይ ትልቅ ሸፍጥ ከተፈፀመባቸው ስብእናዎች አንዷ ታላቋ ሶሐቢያህ ሂንድ ነች፡፡ የክፋትና የተንኮል ሁሉ ቋት ተደርጋ ነው የተሳለችው፡፡ ደካማ ማስረጃ ላይ በመመስረት ያልፈፀመችው ተለጥፎባታል፡፡ ያለ ተጨባጭ ማስረጃ ወንድ ጋር እያሽካካች፣ እየጨፈረች ተስላለች፡፡ እርግጥ ነው በጊዜው ሙስሊም አልነበረችምና ብትፈፅመውም ላይደንቅ ይችላል፡፡ ቢሆንም ግን ያለ በቂ ማስረጃ ኋላ ታላቅ ሴት የሆነችዋን ሶሐብያ ቀርቶ ማንንም መወንጀል አይቻልም፡፡ እምነታችን ካፊርንም መበደል አይፈቅድም፡፡ ደግሞም ከመስለሟ በፊት ብዙ ጥፋትን በመስራት ሂንድ ከሌሎች የተለየች አይደለችም፡፡ ነገር ግን ፊልሙ የሺዐ እጅ የገባበት ስለሆነ ሆነ ተብሎ ከሌሎች በተለየ መልኩ በኑ ኡመያህ ላይ አነጣጥሯል፡፡ ሂንድ ኋላ መስለሟ የሚታወቅ ነው፡፡ ኢስላሟም ምን ያማረ ነበር፡፡ መስለሟ ቀድሞ የተፈፀመን ነገር በሙሉ ያብስላታል፡፡ ስለሆነም እውነት ተፈፅሞ እንኳን ቢሆን ጤነኛ ጭንቅላት በቀድሞ ነገር አይወቅሳትም፡፡ በፊልሙ ላይ
a. ሂንድ ሐምዛን እንዳስገደለች የቀረበው ሶሒሕ ማስረጃ ላይ የተመረኮዘ አይደለም፡፡ ይልቁንም ሶሒሕ ቡኻሪ ላይ እንደተዘገበው የሐምዛ ገዳይ የሆነው ‪#‎እራሱ_ወሕሺይ_እንደገለፀው‬ ‪#‎ሐምዛን_እንዲገድል_የላከው_ጁበይር_ኢብኑ_ሙጥዒም‬ ነው፣ የአጎቱን ደም ለመበቀል ብሎ፡፡ [4072]
b. በፊልሙ ላይ ሂንድ የሐምዛን ጉበት እንዳኘከች የሚያሳየው ትክክለኛ (ሶሒሕ) ማስረጃ ላይ የተመረኮዘ አይደለም፡፡ ሸይኹልአልባኒ ረሒመሁላህ የዚህን ቂሳ ደካማነት ካፀኑ በኋላ “ሶሒሕ ነው” ያሉ ሰዎች ትክክል እንዳልሆኑ ጠቁመዋል፡፡ [ፊቅሁስሲራ፡ 279-280፣ ቁ. 02]
4. ታላቁ ሶሐባህ ዑመር ኢብኑልኸጣብ ረዲየላሁ ዐንሁ በኢስላም ታሪክ ከመካ ጀምሮ ያለው አንፀባራቂ ዝና ጠላት ወዳጅ የሚያውቀው ነው፡፡ ግና በዚህ ፊልም ውስጥ ዑመር የሚባል ስብእና ሆን ተብሎ ገሸሽ ተደርጓል፡፡ አንድ ቦታ ብቻ ነው ከሙሃጂሮች ዝርዝር ውስጥ ስሙ የተወሳው፣ አለቀ፡፡ ልክ ዑመር ሊጠቀስ የሚችል ታሪክ እንደሌለው፡፡ ነገሩን ሆን ተብሎ እንደተፈፀመ የሚያጠናክርልን የዑመርን ሚና በሌላ እንደተፈፀመ እያደረጉ ማቅረባቸው ነው፡፡ ፊልሙ ውስጥ የተደረገን አንድ ምልልስ እንመልከትማ፡፡ ዐማር ኢብኑ ያሲር ረዲየላሁ ዐንሁ ምርኮኞችን ይዞ ይመጣል፡፡ ከዚያም ሐምዛ፡- “የአላህ መልእክተኛ ምርኮኞቹን ማሰራችሁን አይወዱም” አለ፡፡ ዐማር፡- “እኛ እነሱ ቦታ ብንሆን ኖሮ ገድለውን ነበር” አለ፡፡ ሐምዛ፡- “ምርኮኞቹን የሚመለከተውን የነብዩን አደራ ልንከተል ይገባናል፡፡ አስራችሁ አትጎትቷቸው፡፡ ስንቆቻችሁን አካፍሏቸው፡፡ ማንበብና መፃፍ የሚያውቅ አስር ሙስሊሞችን እያስተማረ ነፃ ይውጣ፡፡”
ፊልሙ ላይ ያለው ሀሳብ ይሄው ነው፡፡ ነገር ግን የበድር ምርኮኞችን በማስመልከት ቁርኣን የወረደው ከሐምዛም፣ ከዐማርም ይልቅ የዑመርን ሀሳብ ተከትሎ ነው፡፡ ምርኮኞቹን አስመልክተው ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አቡበክርን እና ዑመርን ያማክራሉ፡፡ አቡበክር “የአላህ ነብይ ሆይ! እነሱ የአጎቶቻችን ልጆች ዘመዶቻችን ናቸው፡፡ ቤዛ እንድትቀበላቸው ሀሳብ እሰጣለሁ፡፡ በዚህም በከሃዲዎች ላይ ሀይል ይኖረናል፡፡ አላህ ወደ ኢስላም ሊመራቸውም ይከጀላል” ሲሉ ዑመር ግን “በጭራሽ! ወላሂ የአላህ መልእክተኛ ሆይ እኔ አቡበክር ያሰበውን አይደለም የማስበው፡፡ ግን እኔ የምለው አመቻችልን አንገታቸውን እንበላቸው፡፡ ለዐልይ (ወንድሙን) ዐቂልን አመቻቸው አንገቱን ይበለው፡፡ እከሌን (ዘመዱን) አመቻችልኝና አንገቱን ልበለው፡፡ እነዚህ የክህደት መሪዎችና ቁንጮዎች ናቸው” አለ፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ወደ አቡበክር ሀሳብ አዘነበሉ፡፡ በማግስቱ የአላህ መልእክተኛ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከአቡበክር ጋር ተቀምጠው ያለቅሳሉ፡፡ ዑመር “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! እስኪ ንገረኝ አንተና ጓደኛህ ስለምን ታለቅሳላችሁ? የሚያስለቅሰኝ ካገኘሁ አለቅሳለሁ፡፡ የሚያስለቅሰኝ ካላገኘሁ አላቅሳችኋለሁ” አለ፡፡ … በዚህ ሳቢያ ቁርኣን ወረደ፡፡ [ሶሒሕ ሙስሊም] ተመልከቱ ታሪኩ ላይ ሐምዛም ዐማርም አልተወሱም፡፡ በታሪኩ ውስጥ ስማቸው የተወሳው ሁለቱ ታላላቅ ሶሐቦች ናቸው፣ አቡበክር እና ዑመር፡፡ ግና ገድላቸው እንደዋዛ ታልፏል፡፡
የኡሑድ ጦርነት ከተገባደደ በኋላ አቡ ሱፍያን፡- “በውስጣችሁ ሙሐመድ አለ?” ብሎ ጠየቀ፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “እንዳትመልሱለት” አሉ፡፡ “በውስጣችሁ የአቡ ቁሀፋ ልጅ (አቡበክር) አለ” ሲል ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “እንዳትመልሱለት” አሉ፡፡ “በውስጣችሁ (ዑመር) ኢብኑልኸጣብ አለ?” ካለ በኋላ “እነዚህ ተገድለዋል፡፡ በህይወት ቢኖሩ ኖሮ ይመልሱ ነበር” አለ፡፡ ዑመር እራሱን መቆጣጠር አልቻለምና “ዋሸህ አንተ የአላህ ጠላት! አላህ የሚያዋርድህን (የሚያሳዝንህን) አስቀርቷል” [ይሄው የአላህ መልእክተኛ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም፣ ይሄው አቡበክር፣ እሄው እኔም ዑመር ነኝ] አለው፡፡ “ሁበል ሆይ ከፍ በል” እያለ ጣኦቱን ሲያሞካሽ ጊዜ ዑመር ኢብኑልኸጣብ “አላህ ከሁሉም በላይ ከፍ ያለና የላቀ ነው” ብሎ መለሰለት፡፡ “የበድርን ቀን ዛሬ ተክሰናል፡፡ ቀኖች ይቀያየራሉ፡፡ የጦር (ድልም) ይለዋወጣል (አምና እናንተ ዘንድሮ እኛ)” ሲል ኡሱፍያን ዑመር “እኩል አይደለም፡፡ ሟቾቻችን የጀነት ናቸው፣ ሟቾቻችሁ ግን የእሳት ናቸው” አለው፡፡ …” [ቡኻሪና አሕመድ]
ፊልሙ ላይ ግን ታሪኩ እጅግ ቁንፅል ሆኖ ከመቅረቡም በላይ ምልልሱን ያደረገው ዑመር ሳይሆን ዘይድ ኢብኑ ሓሪሠህ ተደርጎ ነው የቀረበው፡፡ ፊልሙ ላይ ባጠቃላይ የዑመር አንፀባራቂ ገድሎች ልክ በዚህ መልኩ እንዳይነሱ ተደርገው ተገድፈዋል፡፡
5. ፊልሙ ላይ አቡ ጧሊብ የተውሒድ ተጣሪ ተደርጎ ተስሏል፡፡ ፊልሙ ላይ አቡ ጧሊብን የሚሞግተው አቡ ሱፍያን እንደሆነ ተደርጎ ቀርቧል፡፡ ቡኻሪ ላይ ያለው ግን አቡ ጀህል እና ዐብዱላህ ኢብኑ አቢ ኡመያህ እንደሆኑ ነው፡፡ ፊልሙ ላይ አቡ ጧሊብ አቡሱፍያንን ወደ ላኢላሀኢለላህ ከልቡ ይጣራል፡፡ ሶሒሑ ማስረጃ ላይ ያለው ሐቅ ግን ሌላ ነው፡፡ ፊልሙ ላይ ነገሮችን በመቀጣጠልና በመቅጠፍ ጭምር ተመልካች አቡ ሱፍያንን እና ቤተሰቡን እንዲጠላ የሚያደርጉ ነገሮች በያጋጣሚው ተሰግስገዋል፡፡
6. ፊልሙ ላይ ዐልይን ከሁሉም በላይ ለይቶ ማግነን በግልፅ ይስተዋላል፡፡ እርግጥ ነው ዐልይ እጅግ ጀግናና ታላቅ ሰው ነው፡፡ ቢሆንም ከዐልይ በምንም የማይተናነሱ በርካቶች አብረው ነበሩ፡፡ ነገር ግን የሌሎቹ ተድበስብሶ የሱ ብቻ እንዲጎላ ተደርጓል፡፡ ፊልሙ ላይ ዐልይ በኢስላም ታሪክ የመጀመሪያው ሰይፍ የመዘዘ ተደርጎ ተስሏል፡፡ ሐቂቃው ግን ዐልይ ሳይሆን ዙበይር ኢብኑ አልአዋም ነበር፡፡ [አስሲየር፡ 1/41-42]
7. የአቡ ጀህል መገደል፡- አቡ ጀህል ቀንደኛ የሙስሊሞች ጠላት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ የሱ መገደል ለሙስሊሞች እጅግ አስደሳች ዜና ነበር፡፡ አገዳደሉም ገዳዮቹም በሚገባ ይታወቃሉ፡፡ ከምንም ተነስቶ ተራራ የሚገነባው ፊልም ላይ ግን ይህን ያክል የሺርክ ተራራ በሁለት የአንሷር ወጣቶች ሲገነደስ ይህ ነው የሚባል ትኩረት አልተቸረውም፡፡ ይልቁንም አቡ ጀህል ማንነቱ በውል ባልተለየ ሰው በጦር ተገድሎ ይቀራል-ፊልሙ ላይ፡፡ አንድ እዚህ ግባ የማይባል ማንነቱ በውል ያልታወቀ ሰው የተገደለ ያክል ይሄ ነው የሚባል ሽፋን ሳያገኝ እንዲሁ ያልፋል፡፡
ፊልሙ ላይ ሌሎችም በርካታ ጥፋቶች አሉ፡፡ የወሕደቱልውጁድ ብልሹ ዐቂዳ፣ ጭፈራ፣ በካፊር መመሳሰል፣ ወንድና ሴት መቀላቀል፣ ሙዚቃ፣ ወዘተ፡፡ “ለማስተማር ነው” እንዳይባል፡፡ ለማስተማር ተብሎ መጨፈር፣ በካፊር መመሳሰል፣ ከአጅነቢ ጋር መቀላቀል፣ ኩፍር መናገር፣… ይፈቀዳልን? አንባቢ ረጋ ብሎ እንዲያስተውለው እጋብዛለሁ፡፡ በጥቅሉ ይህን ፊልም የተመለከተ አላህ የጠበቀው ሲቀር ለአቡ ሱፍያንና ለሂንድ ጤነኛ እይታ አይኖረውም፡፡ ኋላ ከሰለሙት ከነሱ ይልቅ ምናልባትም ለአቡ ጧሊብ ይበልጥ ሊራራ ይችላል፡፡ ይህን ፊልም የተመለከተ ፊልሙ እስከሸፈነው ረጂም የጊዜ ታሪክ ድረስ ይሄ ነው የሚባል የዑመርን ገድል መናገር አይችልም፡፡ ሆን ተብሎ እንዲዋጥ ተደርጓልና፡፡
ሰፋ ያለ ዳሰሳ ከፈለጉ የዚህ ፅሁፍ መልእክት የተወሰደበትን ይህን ሊንክ ይከተሉ፡፡ (ዐረብኛ ነው፡፡) http://www.al-amen.com/vb/showthread.php?t=11003