Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ስለ እናታችን አዒሻህ ምን ታውቂያለሽ?

‎تنبيهات على أحكام تختص بالمؤمنات    ተንቢሀት - ሙስሊም ሴቶችን የተመለከቱ ህግጋት‎'s photo.
🎀ተንቢሃት የዋትሳፕ ግሩፕ🎀
www.fb.com/tenbihat
🍁 ስለ እናታችን አዒሻህ ምን ታውቂያለሽ? 🍁
'እሷ' ብዬ ስጠራት ስቅቅ እያለኝ ነው። በአንቱታ ብጠራት ደስ ባለኝ ነበር፤ ግን እናት 'አንቱ' አትባልምና 'እሷ' እያልኩ እቀጥላለሁ ... እያከበርሻት ተከተይኝ።
ከፈቀድሽልኝ ላወጋሽ ያሰብኩት ስለእናትሽ ነበር። አዎን ስለአንቺ እናት!
እናትነቷን በደም ሳይሆን በተውሂድ ስላገኘሽው፤
በስጋ ሳይሆን በእምነት ለተዋሀድሽው፤
አይተሻት ሳይሆን ስለእሷ ሰምተሽ ያወቅሻት፣
አሳድጋሽ ሳይሆን ዲንሽን አስተላልፋልሽ የወደድሻት ...
ስለሷ! ያንቺ ብቻ ሳትሆን የምእመናን ሁሉ እናት ስለሆነችው፤ ሲዲቃህ ቢንት ሲዲቅ!
መካ ላይ ከምርጥ ከእናቷ ከኡሙ-ሩማን እና በጀነት ከተመሰከረለት የነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ቅርብ ባልደረባ አባቷ አቡበክር ሲዲቅ ተወለደች።
በኢስላም ብርሀን ባጌጠው ቤትም በመልካም እንክብካቤ፣ በኢስላማዊ አስተዳደግና በጥሩ ስነምግባር ተኮትኩታ አደገች።
ያ ወቅት ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ውድ ባለቤታቸውን ኸዲጃን(ረ.ዓ) አጥተው በሀዘን የተቆራመዱበት ጊዜ ነበር።
ያኔ ኸውላ ቢንት ሐኪም(የዑስማን ቢን መዝዑን ባለቤት) ነቢዩን (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ዘንድ ገባችና ጠየቀቻቸው ... "አታገባም እንዴ?"
ነቢዩም (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) መለሱ "ማንን?"
ኸውላ ቀጠለች "ከፈለክ ልጃገረድ ካሻህ ደግሞ ትልቅ?"
ነቢዩም (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) "ከልጃገረድ?" አሏት
ኸውላም "ከፍጡራን ሁሉ አንተ ዘንድ የተወደደውን ሰው ልጅ - ዓኢሻ ቢንት አቢበክር"
...
ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) በኸውላ ምርጫ ተስማሙ መልእክት እንድታደርስላቸውም ላኳት። ኸውላ ትቀጥላለች ...
"ወደ አቡበክር ቤት ሄድኩ የዓኢሻን እናት ኡሙ ሩማንን አገኘኋት እንዲህም አልኳት "ኡሙ ሩማን ሆይ! አላህ እንዴት አይነት ጥሩ ነገርና በረከትን ሰጣችሁ"
ኡሙ ሩማንም "ምንድን ነው እሱ?" አለችኝ
እኔም "ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ዓኢሻን እንዳጭላቸው ልከውኛል አልኳት" ከዛም 'አቡበክር ይመጣልና ቆዪ' ብላ አስጠበቀችኝ፤
አቡበክር (ረ.ዓ) ሲመጣ ... "አላህ እንዴት አይነት ጥሩ ነገርና በረከትን ሰጣችሁ" አልኩት
"ምንድን ነው እሱ?" አለኝ፤
"ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ዓኢሻን እንዳጭላቸው ልከውኛል" አልኩት
ይሄኔ አቡበክር ልጄ ገና ነች ብለው አልተግደረደሩም፣ እንዴት አስችሏቸው በነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ጥያቄ ላይ ይግደረደራሉ? ይልቁኑ በደስታ ፈነደቁ በጥያቄውም ተስማሙ!
አላህም(ሱ.ወ) ይህን የነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ምር�ጫ አጠነከረላቸው። በህልማቸው ዓኢሻን በተዋበ መልኩ ተመለከቷት፤ ዓኢሻ ስለሁኔታው ስትናገር እንዲህ ትላለች ...
"ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) 'ሶስቴ በህልሜ አይቼሻለሁ' አሉኝ፤ '... መላኢካው ባማረ ሐር አድርጎ ይህች ያንተ ሚስት ነች ይለኛል፤ ግልጥ አድርጌ ሳይ አንቺ ነሽ ..."
ይህን ሲነግሯት ምንኛ ትደሰት ይሆን? የባሏ ምርጫ በመለኮታዊ ራእይ ሲደገፍ ያውም 'ይህች ያንተ ሚስት ነች' ብሎ አላህ ስለሷ መግለፁን ስትሰማ ምን ያህል ይሰማት?!
ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ዓኢሻን እንዳጩ ወዲያው አግብተው ወደቤት አላስገቡም፤ ይልቁኑ እስክትደርስ ድረስ አባቷ ቤት እንድትቆይ አደረጉ፤ እናቷን 'ደህና አርገሽ ያዢልኝ' ይሉ፣ ደጋግመው መዘየር ያበዙም ነበር። (መውደድ ነዋ!)
ነገሩ በእንዲህ እያለ የመካ ከሀድያን በሙስሊሞች ላይ የሚያደርሱት በደል አየለ። ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ከባልደረባቸው አቡበክር(ረ.ዓ) ጋር ወደ የስሪብ(መዲና) ተሰደዱ። ዓኢሻም እንዲሁ ከነቤተሰቧ መዲና ከተመች።
ሁለቱም ቤተሰቦች በመዲና ተገናኙ፤ አዲሲቷን ሀገር ሲላመዱም ያቀዱትን ትግበራ ተንቀሳቀሱ። ከሁለት አመት በኋላ ነበር በሸዋል ወር ዓኢሻ ወደ ነቢያት አለቃ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ቤት መግቢያዋ የደረሰው።
እናቷ እና ሌሎችም ለሰርጓ ያሰናዷት ጀመር። አስማእ ቢንት የዚድ(ረ.ዓ) ካስዋቧት አንዷ ነበረች፤ ከዛም ወደ ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ይዛት ገባች...
ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ከጎኗ ቁጭ አሉ። ከያዙት ወተት ተጎነጩና ለዓኢሻ ሰጧት፤ እሷ ግን አፍራ አንገቷን ደፋች፤ አስማእ ተቆጣቻትና ተቀብላ እንድትጠጣ ነገረቻት፤ ዓኢሻም ተቀብላ ፉት አለች።
ተመልከች እህቴ! አይናፋርነቷን፣ እንዳሁኑ ሴቶች በሰርጓ ቀን ልትደልቅ፣ ልትጨፍር፣ እስክታ ልትወርድ ቀርቶ አንገቷን እንኳ ቀና ለማድረግ አልደፈረችም። የአቡበክር ልጅ፣ የነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ሚስት፣ የአንቺ እናት፤ ዓኢሻ!
በሰርጓ ቀን ግመል አልታረደም፣ በሬም አልተጣለ ኧረ ፍየልም ቢሆን፤ በሳህን የቀረበ ምግብ እንጂ። ነቢዩም (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ጋር ስትገባ ምቹ አልጋ የተሟላ ቤት አልጠበቃትም፤ ደከም ያለ ፍራሽ ... አንስተ�ኛ እቃዎች ... በቃ!
እሷ ነቢዩን (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) አግኝታለች ታዲያ ሌላ ምን ትፈልጋለች?
መኸሯን ጠይቀሻል? ስንት ቢሆን ጥሩ ነው?
500 ዲርሀም - Enough! የዓኢሻ ቤተሰቦች ለልጃችን ጥሎሽ ለኛም ስጦታ ብለው ግብግብ አልፈጠሩም፣ እንዴት ሳይደገስ እንዴት ሳይበላ ብለው 'ቡራ-ከረዩ' አላሉም። ዲን አጠንክሯቸዋልና!
አስቢ! ያገባችው እኮ ወደ ሰባት ሰማያት ያረገ ነቢይ ነው፤ እሷኮ ከቁረይሽ ያውም ከነቢያት ቀጥሎ በኢማኑ ተስተካካይ ከሌለው አቡበክር የተገኘች ነች፤ ግን ኢማን እንዲህ ነው!
ዛሬ የወደፊት የትዳር አጋራቸውን አሊያም በቅርብ የምታገባ ዘመድ/ ጓደኛቸውን ባል በተለያዩ ወጪዎች ቁም-ስቅል የሚያሳጡ ሰዎች እዚህ ጋር በእናታችን ዓኢሻ ታሪክ ሊመከሩ ይገባል።
መኸር በአስር ሺህ ቤቶች ይቆጠር የሚሉ፣ ጥሎሽ ለሙሽሪት ሳያንስ ቤተዘመድ ካልለበሰ የማይጠረቁ፣ ወርቅ በየአይነቱ የሚያማርጡ፣ ባለብዙ ክፍል ቤት የሚያማትሩ፤ ሞዝቮልድ አልጋ ካልተዘረጋ፣ ቁምሳጥን ካልተገዛ፣ ፍሪጅ ካልተገተረ ፣ አረቢያን መጅሊስ ካልተደረደረ ትዳር መስሎ የማይታያቸው ቆም ሊሉ ይገባል፤ የትዳር ደስታ በገንዘብ አሊያም በቁሳቁስ ብዛት የሚገኝ አይደለም በኢማን እንጂ!
ዲን ካለ ግን ሁሉም ነገር አለ። ለዚህም ነበር እነ ዓኢሻ ህይወታቸው በፍቅር የተሞላ የነበረው። ኢማን ሞልቶ የተትረፈረፈበት ነበርና።
ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ስለሷ አንስተው አይጠግቡም "ከሴቶች ሁሉ የምወደው ዓኢሻን ነው" እስኪሉ ድረስ�፤ ዓኢሻ ጠጥታ ያስቀመጠችው ኩባያ ዳግም የነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) መጠጫ ነበር። የሷ ከንፈር ያረፈበትን ፈልገው ይጠጡበት ነበር፤ ያ-ረብ!
እህቴ ይህን የመሰለ ፍቅር ማግኘት አትሺም? ወዶሽ እንስፍስፍ እንግብግብ የሚልልሽ የትዳር አጋር አትመኚም?
አታስቢ! ብቻ አንቺ ዲንሽን አጥብቀሽ ያዢ፤ ከዛ እየከነፈ ይመጣል። የት ያመልጣል?! አንቺ ለአላህ ብለሽ ዲነኛ ሁኚ! በቃ!
ግንኮ እናትሽ እንዲህ በፍቅር ስትኖር ችግሮችም አልተለያትም ነበር። ፈተናዎች ተፈራርቀውባታል ግን ፅኑ ነበረች፤ አላማዋ ጀነት እንጂ ዱኒያ አልነበረምና አልተበገረችም።
በቤቷ የሚበስል ምግብ �ባለመኖሩ ለወራት እሳት ሳይነድ ያልፍ ነበር። የገብስ ቂጣ እንጂ የሚላስ የሚቀመስ እስኪጠፋም ይቸገሩ ነበር። አንዳንዴማ ባስ ሲል ተምር እና ውሀ ብቻ እየተጠቀሙ ያሳልፋሉ።
ዓኢሻ እንደዛሬው በሰፊ ቤት በቅምጥል ህይወት አልኖረችም። ጀነትን እያለመች ከውድ ባለቤቷ ጋር በችግር አሳለፈች እንጂ ... ቢሆንም ይህ ችግሯ ደስታዋን አልቀነሰባትም። ኧረ እንደውም ፍቅር ጨመረ እንጂ!
ዛሬ ስንቶች በቪላ ቤቶች፣ በተሟላ የቤት እቃ በተትረፈረፈ ሀብት ተከበው ደስታ ማግኘት ሲሳናቸው፣ በበሽታ ሲወረሩ፣ በጭንቀት ሲወጠሩ፤ ጭራሽ ተፈጥሮአዊውን እንቅልፍ እንኳ ሲያጡ እያየን፤
ከነሱ ሊነፃፀሩ የማይችሉ የእለት ጉርስ እንኳ የሌላቸው ምስኪኖች፤ ነገር ግን የኢማን ሀብት የሞላቸው ቆሎ ቆርጥመው በውሀ አወራርደው በፍቅር ሲዋኙ እናያለን!
ይህ ነው የኢማን ፍሬው። የዓኢሻ ደስታ ምስጢሩ!
ዓኢሻ ትናገራለች "ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ለይል እየሰገዱ እኔ ከፊታቸው እተኛ ነበር፤ ሱጁድ ለማድረግ ሲወርዱ እግሬን ቆንጠጥ ያደርጉኝና እሰበስበዋለሁ፤ ሲነሱ ደግሞ እዘረጋዋለሁ" ትላለች።
ዓኢሻ (ረ.ዓ) "የዛኔ በቤታችን መብራት አልነበረም" አለች። ምነው ስትባል "ለመብራት የሚሆነን ጮማ ቢኖረንማ በበላነው ነበር!" ሱብሀን አላህ!
ዛሬ አንቺ በኢማን የታነፀ ባል መጥቶልሽ ወይም አግብተሽ በእንዲህ ያለ ቤት ላኑርሽ ቢል ትቀበይው ይሆን? ወይስ ዞርበል ትይዋለሽ? እናትሽ ግን እንዲህ አልነበረችም!
ዓኢሻ ምንም ቢቸግራት፣ ምን ያህል ብትጎሳቆል ከውድ ባለቤቷ ተለይታ ዱኒያን ማጣጣም አልተመኘችም። በፍፁም!
አንዴ አላህ (ሱ.ወ) በወህይ ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ባለቤቶቻቸውን ወይ ከሳቸው ጋር ቀጥለው አኸይራን አሊያም መለየትን እንዲያስመርጡዋቸው አዘዛቸው። ይህንኑ ይዘው ወደ ዓኢሻ መጡ... እንዲህ ትተርካለች
"ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉኝ 'እኔ አንድ ነገር አወሳሻለሁ ወላጆችሽን ሳታማክሪ ለውሳኔ እንዳትቸኩይ' አሉኝ፤ መቼም ወላጆቼ እሳቸውን እንድለይ እንደማይመክሩኝ ያውቃሉ። ከዚያም እንዲህ አሉኝ 'አላህ እንዲህ ብሏል
...
((አንተ ነብይ ሆይ! ለሚስቶችህ ፤ 'የዱንያን ህይወትና ጌጦቿን የምትፈልጉ እንደሆናችሁ መልካም መልቀቅን(ፍቺን) እለቃችኋለሁ' በላቸው)) ብሏል አሉኝ፤
እኔም ታዲያ በምኑ ነው ወላጆቼን የማማክረው እኔ እንደሆንኩ አላህን፣ መልእክተኛውንና የአኸይራን አገር እፈልጋለሁ አልኳቸው" ሱብሀን አላህ! እናትሽ እንዲህ ነበረች።
ሌላው ዓኢሻን(ረ.ዓ) የገጠማትን ላውሳልሽ ...
እስኪ እራስሽን በዓኢሻ ቦታ አድርጊውና ተከትዪኝ፤ እንዲህ ባልሽን በፍቅሩ ተማርከሽ እየወደድሽ፣ ምንም ቢቸግርሽ ለዲኑ ስትዪ በሱ ጥላ ስር መሆንን መርጠሽ፤ እሱ በያዘው ተልእኮ ላይ ስኬታማ እንዲሆን እያበረታሽው፤ የሚጠበቅብሽን ሁሉ እያደረግሽ፣ በታማኝነት እየጠበቅሽው ...
ድንገት! በቃ ድንገት ... የሆኑ ሰዎች ... በአንቺ ንፁህነት ላይ ጥላሸት የሚቀባን ወሬ ቢነዙ፣ እጅግ ፀያፍ በሆነ ነውር ቢያሙሽ፣ ቀስ በቀስ ወሬው ቢሰራጭ፣ በከተማው ሁሉ ስምሽ ቢጠፋ፣ ሳር ቅጠሉ እርግጠኛ ሆኖ ቢወነጅልሽ፤ የምትወጂው ባልሽ የምታምኛቸው ወላጆችሽ የሚሆኑት ጠፍቷቸው በጭንቀት ቢዋጡ ...ምን ትሆኚ?
ባላደረግሽው፣ ባልቀረብሽው ጭራሽ ባላሰብሽው ዚና ብትጠረጠሪ ... ምን ይውጥሻል?
ከበደሽ?!
እናትሽ ግን ይህ ገጥሟት ነበር። አጥንቷን የሚሰብር፣ ማንነቷን የሚከ�ሰክስ፣ ሞራሏን የሚያደቅ አስቸጋሪ ወቅት ...
ሙናፊቆች ላማቸው ወልዳለች፤ በዓኢሻ(ረ.ዓ) ክብር በመረማመድ ጮቤ እየረገጡ ነው። እየፈለሰፉ ይቀባጥራሉ፤ እየጨማመሩ ይንደቀደቃሉ፤ እየተሳለቁ ይንቦለቦላሉ ... ቱሪናፋቸውን አሜን የሚል ተገኝቷል የነርሱን ቱልቱላ የሚነፋ ሞልቷል። ብቻ ለመናፍቃን አለም ዘጠኝ ሆነች!
ወር ያህል መዲና በወሬ ታመሰች፤ የምእመናን ቤት በአሉባልታ ተንጧል! ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ግራ ግብት ብሏቸዋል...
ውሸት መሆኑ አልጠፋቸውም ግን ኸልቁ ሁሉ እያወጋው ነው፤ ወሬው ሲጠና 'ፍታት' ብሎ የሚመክርም ነበር፣ 'የለም እንታገስ' የሚልም አለ።
ዓኢሻ አይኖቿ እንባ ማዝራት እንጂ ሌላ አያውቁም። ስታለቅስ ትውላለች እንዲሁ ታነጋለች። ጭንቅ ሆነ!
የሚገርምሽ ግን እናትሽ ይሄኔ አልተማረረችም፣ በጌታዋም አልተበሳጨችም፤ በእድሏም አልተቆጨችም! ብቻ ሀቁን እንዲየወጣው ጌታዋን ለመነችው። እሱም ተቀበላት!
አላህ እውነቱን ገለፀ፤ የዓኢሻ(ረ.�ዓ) ንፅህና አወጀ። አሉባልታ ያናፈሱትን አሳፈረ፣ በቅጣትም ዛተባቸው።
ምእመናን ፈነደቁ! ዓኢሻ ትላለች "አላህ ለኔ የቁርአን አንቀፅ ያወርዳል ብዬ አላሰብኩም ነበር"
ግን አላህ አደረገው፤ ስለሷ ንፅህና ለመግለፅ የሀሜተኞቹንም �ውሸት ለማጋለጥ አስር ተከታታይ አንቀፆችን አዥጎደጎደ። አልሀምዱሊላህ!
( إن الذين جاؤا بالإفك عصبة منكم لا تحسبوه شراً لكم بل هو خير لكم لكل امرئ منهم ماكتسب من الإثم والذى تولى كبره منهم له عذاب عظيم )
"እነዚያ መጥፎን ውሸት (ዓኢሻን በማነወር) ያመጡ፣ ከናንተው የሆኑ ጭፍሮች ናቸው፤ ለናንተ ክፉ ነገር ነው ብላችሁ አታስቡት፤ በውነቱ እርሱ ለናንተ መልካም ነገር ነው፤ ከነርሱ (ከጭፍሮቹ) ለያንዳንዱ ሰው፣ ከኀጢአት የሰራው ሥራ ዋጋ አለው፤ ያም ከነሱ ትልቁን ኀጢአት የተሸከመው (ወሬውን ያጋነነው) ለርሱ ከባድ ቅጣት አለው" 24፥11
ከላይ ያነበብነው አንዱን አንቀፅ ብቻ ነው፤ ለትምህርት እንዲሆነን ከወረዱት አስር አናቅፅት መሀል አንዱን ልድገም ...
"እነዚያ በነዚያ ባመኑት ሰዎች ውስጥ መጥፎ ወሬ እንድትሰፋፋ የሚወዱ ለነሱ በቅርቢቱም በመጨረሻይቱም ዓለም አሳማሚ ቅጣት አላቸው፤ አላህም ያውቃል፤ እናንተ ግን አታውቁም" 24፥19
ቀሪውን ከሱረቱ ኑር አንቀፅ ፥12 ጀምረሽ ኮምኩሚ ...
ዓኢሻ(ረ.ዓ) ከሰማየ ሰማያት በወረደው የአላህ ቃል ነፃ ወጣች፤ እነዛ ነውርን ለማሰራጨት ይጣደፉ የነበሩ መናፍቃንም አፈሩ፣ በነርሱ ሀሰተኛ አሉባልታ የተሸነገሉ ጥቂት አማኞችም ታረሙ፤ የእውነተኛው አቡበክር ልጅ እውነተኛነቷ ተረጋገጠ። ሲዲቃህ ቢንት ሲዲቅ!
ዓኢሻ(ረ.�ዓ) ከባለቤቷ ጋር በፍቅር ቀጥላለች። ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) በመልካም ሁናቴ ይኗኗሯት፣ ያጫውቱና ያዝናኗትም ነበር፤ እሷን ለማስደሰት ሩጫም ይሽቀዳደሟት ጭምር ነበር፤ መጀመሪያ ትላለች ዓኢሻ እቀድማቸው ነበር ኋላ ላይ ስወፍር ግን ይቀድሙኝ ጀመር smile emoticon
በስተመጨረሻ ዓኢሻ ከነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ጋር የመሰናበቻውን ሐጅ አድርጋ ነበር። በመንገዳቸው ላይ የገጠማቸውን ስትናገር ...
"ከነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ጋር ሙህሪሞች(የሐጅ ስርአት ላይ) ሳለን ጋላቢዎች በኛ በኩል ያልፉ ነበር፣ (ተጓዦቹ) ወደ እኛ ሲቀርቡ አንደኛችን ጅልባቧን በፊቷ ላይ ትለቃለች ሲያልፉን ደግሞ እንገለጣለን" ትላለች ዓኢሻ።
እንዴት ነው እህቴ አንቺስ ሂጃብ አጠቃቀምሽ እንደ እናትሽ ነው? ፊትሽን ትሸፍኛለሽ? ነው ወይስ ጅልባቡም አልገራልሽም? ... አትዘናጊያ ሲስቱካ ከዚህ በኋላ ምን ትጠብቂያለሽ ...
ሞት እንደሆነ ነጋሪት እየጎሰመ፣ መለከት እየነፋ፣ አዋጅ እያስለፈፈ አይመጣ፤ ድንገት ነው ከተፍ የሚል ... ታዲያ ምን አዘጋጅተሻል? አስቢበት!
ጊዜ ጊዜን ሲወልድ ነቢዩም (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ለሞታቸው ሰበብ የሆነው ህመም ሲይዛቸው ሚስቶቻቸውን አስፈቅደው ዓኢሻ ቤት ተኙ፤ በዓኢሻ ጉያ ውስጥም ሁነው የማይቀረውን የሞት ፅዋ ተጎነጩ። (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም)
ዓኢሻ ከነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ህልፈት በኋላ የአኸይራ አገሯን ፍለጋ በዒባዳ መማሰኗን ቀጠለች። ለይል በመቆም፣ ቀን በመፆም፣ ባሪያ ነፃ በማውጣት፣ ሚስኪኖችን በመርዳት፣ በመልካም በማዘዝ ከመጥፎ በመከልከል፣ የነቢዩን (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ሐዲስ በማስተማር ተሰማራች።
ዓኢሻ እያንዳንዱን የነቢዩን (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንቅስቃሴ በመከታተል ለኛ ካስተላለፉልን ባለውለታዎች ቀንደኛዋ ናት። በተለይ ደግሞ ሌሎች ሶሀቦች ሊታደሙበት በማይችሉት የቤት ውስጥ ተግባራቶቻቸው ሁነኛ የሐዲስ ምንጭ ነበረች።
ከ1500 በላይ ሐዲሶችን በማስተላለፍ ለነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ሱና መተላለፍ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክታለች። ከነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ማለፍ ጀምሮ እስከ ህልፈቷም ድረስ ግር በሚያሰኙ ሸሪዓዊ ጉዳዮች ላይ ብያኔ(ፈትዋ) ትሰጥ ነበር።
ስለዓኢሻ ዒልም ዚዎች ተናግረዋል ለምሳሌ ርዐት ኢብኑ ዘበይር (ረድየላሁ አንሁ) እንዲህ ስለዓኢሻ ብሏል ፡-
«በፊቅህም ይሁን በህክምና እንዲሁም በግጥም ከአዒሻ የበለጠ አዋቂ አንድንም አላየሁም» (ታሪኽ አጠበሪ ሃዋዲሱ ሰና 58)
አል ኢማሙ ዙህሪ ደግሞ እንዲህ ብለዋል ፡-
"የአዒሻ ዕውቀት ተሰብስቦ ከሁሉም የነብዩ ባለቤቶችና ወደ ሁሉም ሴቶች ዕውቀት ጋር ቢወዳደር የአዒሻ ዕውቀት ይበልጥ ነበር"
አንቺስ እንደሷ መሆን አትሺም? ታዲያ ምን ትጠብቂያለሽ!? ዲንሽን የምትማሪባቸው መንገዶች እጅግ በዝተዋል፤ ቂርአት፣ ሙሐደራዎች፣ ፅሁፎች፣ መፃህፍት፣ በተለያዩ ዘዴዎች ቀርበዋል፤ ተጠቀሚበት!
ጊዜ ሳይሄድ ወቅት ሳያልፍሽ ልክ እንደናትሽ አሪፍ ሁኚ፣ በዘመን አመጣሽ ፋሽኖች ጊዜሽን አትፍጂ እንደፋራ ራስሽን የምእራባውያንና የአመፀኞች ዲዛይን መሞከሪያ አትሁኚ፤ ብልጥ ቆፍጣናና የዲኑ ሙድ የገባሽ ሁኚ!
ጀግናዋ እናትሽ ዓኢሻ(ረ.ዓ) ከነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ከተለየች ከ 48 አመታት በኋላ ለውድ ባለቤቷ ያልተመለሰው ሞት ለሷም ቀረበ።
ዓለም የማይረሳውን ስራዋን ለታሪክ አሳልፋ በተወለደች በ66 አመቷ በ58ኛው አመተ ሂጅራ ረመዷን 17 ማክሰኞ ቀን ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች። ታላቁ ሶሀቢይ አቡሁረይራ ተቀድመው አሰገዱ በበቂዕ መካነ መቃብር ተቀበረች።
ረድየላሁ ዓንሀ
ሙሀመድ ኢብራሂም
-------------
🎐ሻዕባን 15/1436H
🎐 02/06/2015