Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ስለ ሻዕባን ወር መልዕክት በታላቁ ፈቂህ ሸይኽ ሙሐመድ ሷሊህ አል ዑሰይሚን [ረሂመሁላህ]

Abufewzan Ahmed's photo.
🍀ተንቢሃት የዋትሳፕ ግሩፕ🍀
📋ስለ ሻዕባን ወር መልዕክት
⑥ አንኳር ነጥቦች
በታላቁ ሊቅ ሸይኽ ሙሐመድ ሷሊህ አል ዑሰይሚን [ረሂመሁላህ]
« ሙስሊሞች ሆይ ያለነው በሻዕባን ወር ላይ ነውና በዚህ ወር ዙርያ አንድ ስድስት ነጥቦችን በማውሳት ልንከተለው ስለሚገባን ግዴታችን እናብራራለን።
💥የመጀመርያው ነጥብ
የሻዕባን ወር ከሌሎች ወራት በተለየ ሁኔታ በፆም ይለያልን?
አዎን ይለያል ። ምክንያቱም ነቢዩ [ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም] «በዚህ ወር ፆም ያበዛሉ። ከወሩ ጥቂት ቀናት እስኪቀራቸው ወሩን ይፆሙት ነበርና።»
በዚህም ሱና መሰረት የአላህ መልእክተኛን [ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም] በመከተል በዚህ በሻዕባን ወር ፆም ማብዛት አለብን።
💥ሁለተኛው ነጥብ
የሻዕባን ወር አጋማሽ ቀን ፆምን የተመለከተው ነው።
ይህንን ቀን ለይቶ መፆምን የሚመለከቱ ከነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ያልተገኙና ትክክለኛ ያልሆኑ ደካማ ሀዲሶች ተነግረዋል። በነዚህ ተመርኩዞ ይህንን ዒባዳ መፈፀም ደግሞ አይቻልም።
ከነቢዩ ለመተላለፉ ባልተረጋገጠ ማንኛውም ነገር አላህን ማምለክ አይፈቀድም። በመሆኑም የሻዕባን አስራ አምስተኛው ቀንን ለይቶ መፆም የሌለ ነገር ነው። ከመልእክተኛው ለመገኘቱ መረጃ ከሌለ ደግሞ ቢደዐ ነው።
💥ሶስተኛው ነጥብ
የሻዕባን ወር አስራ አምስተኛው ቀን ሌሊት ትሩፋትን ይመለከታል።
ልክ ቀኑን መፆም የተረጋገጠ መረጃ እንደሌለው ሁሉ ለሌሊቱም ከሌሎች ሌሊቶች በላጭ ነው ተብለው የተነገሩት ሀዲሶች ከነቢዩ [ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም] ለመነገራቸው ትክክለኛ መረጃ የሌላቸው ደካማዎች ናቸው።
ስለሆነም የሻእባን አጋማሽ ሌሊት ልክ እንደ ረቢዕ ወር ሌሊት፣ እንደ ረጀብ ወር ሌሊት እንጂ የተለየ ነገር የለውም። ተነገረ የተባለውም መረጃ ቀድሜ እንደገለፅኩት ደካማዎች ናቸው።
💥አራተኛው ነጥብ
ይህችን የአስራ አምስተኛዋን ሌሊት ለየት አድርጎ ዝግጅት ፈጥሮ ማሳለፍ ቢደዐ ነው።
ነቢዩ [ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም] ለየት አድርገው ያሳዩን፣ ሌሊቱን የሚሰገድ አምልኮትም ዝግጅትም የለምና። ስለዚህ ምሽቷ ልክ እንደ ሌሎች ምሽት ናት።
አንድ ሰው ከዚያች ሌሊት በፊትም የለይል ሰላት መስገድ ልምዱ ከነበረ በዚያች ሌሊትም ተነስቶ መስገዱ ልክ እንደበፊቱ ነውና ችግር የለውም ። ካልሆነና በፊት የማይሰግድ ከነበረ ዛሬ በሻዕባን "ለይለቱ ኒስፍን" ለየት አድርጎ መስገድ የለበትም።
ምክንያቱም ከአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ያልተገኘ ተግባር ነውና።
ከዚህም የከፋው ደግሞ አንዳንዱ ሰው የሆነ ያህል ረከዓ በዚህ ምሽት ይሰገዳል በሚል ለየት ያደርገዋል። ይሁንና ከነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ይህንን ምሽት ነጥሎ ለየት ማድረግ ስላልተገኘ ይህችን ምሽት በሰላት ልዩ አናደርግም።
💥አምስተኛው ነጥብ
የአላህ ሱብሃነሁ ለነገሮች የሚያደርገው ውሳኔ በሻዕባን አስራ አምስተኛዋ (አጋማሽ) ምሽት ነውን
ምላሹም አይደለም ሲሆን፤ ምሽቷም የመወሰኛይቱ ሌሊት [ለይለቱል ቀድር] አይደለችምና ነው። ምክንያቱም "ለይለቱል ቀድር" በረመዳን ውስጥ የምትገኝ ምሽት ናት።
ልዕለ ሃያሉ አላህ እንዳለው
”إنا انزلناه“ "እኛ አወረድነው" ማለትም ቁርኣንን ለመጀመርያ ግዜ ያወረድነው ማለቱ ነው። ይህም ሙሉ ምዕራፉ ሲነበብ እንዲህ ይላል:
سورة القدر
بِّسْمِ اللَّـهِ الرَّحْمَـٰنِ الرَّحِيمِ
إِنَّا أَنزَلْنَاهُ فِي لَيْلَةِ الْقَدْرِ ﴿١﴾ وَمَا أَدْرَاكَ مَا لَيْلَةُ الْقَدْرِ ﴿٢﴾ لَيْلَةُ الْقَدْرِ خَيْرٌ مِّنْ أَلْفِ شَهْرٍ ﴿٣﴾ تَنَزَّلُ الْمَلَائِكَةُ وَالرُّوحُ فِيهَا بِإِذْنِ رَبِّهِم مِّن كُلِّ أَمْرٍ ﴿٤﴾ سَلَامٌ هِيَ حَتَّىٰ مَطْلَعِ الْفَجْرِ ﴿٥﴾
Al-Qadr☞ القدر:- [1-5]
[እኛ (ቁርኣኑን) በመወሰኛይቱ ሌሊት አወረድነው፡፡ (1)መወሰኛይቱም ሌሊተ ምን እንደ ኾነች ምን አሳወቀህ? (2)መወሰኛይቱ ሌሊት ከሺሕ ወር በላጭ ናት፡፡ (3) በርሷ ውስጥ መላእክትና መንፈሱ በጌታቸው ፈቃድ በነገሩ ሁሉ ይወርዳሉ፡፡ (4) እርስዋ እስከ ጎህ መውጣት ድረስ ሰላም ብቻ ናት፡፡ (5)]
ይህ ክስተትና ምሽቱም መቸ እንደሆነ ሲገልፅ እንዲህ ይላል☞
شَهْرُ رَمَضَانَ الَّذِي أُنزِلَ فِيهِ الْقُرْآنُ هُدًى لِّلنَّاسِ وَبَيِّنَاتٍ مِّنَ الْهُدَىٰ وَالْفُرْقَانِ ۚ فَمَن شَهِدَ مِنكُمُ الشَّهْرَ فَلْيَصُمْهُ ۖوَمَن كَانَ مَرِيضًا أَوْ عَلَىٰ سَفَرٍ فَعِدَّةٌ مِّنْ أَيَّامٍ أُخَرَ ۗ يُرِيدُ اللَّـهُ بِكُمُ الْيُسْرَ وَلَا يُرِيدُ بِكُمُ الْعُسْرَ وَلِتُكْمِلُوا الْعِدَّةَ وَلِتُكَبِّرُوا اللَّـهَ عَلَىٰ مَا هَدَاكُمْ وَلَعَلَّكُمْ تَشْكُرُونَ ﴿١٨٥﴾
አል በቀራህ ☞ البقرة:- 185
[(እንድትጾሙ የተጻፈባችሁ) ያ በርሱ ውስጥ ለሰዎች መሪ ከቅን መንገድና (እውነትን ከውሸት) ከሚለዩም ገላጮች (አንቀጾች) ሲኾን ቁርኣን የተወረደበት የረመዳን ወር ነው፡፡ ከእናንተም ወሩን ያገኘ ሰው ይጹመው፡፡ በሽተኛ ወይም በጉዞ ላይ የኾነም ሰው ከሌሎች ቀኖች ቁጥሮችን (በልኩ) መጾም አለበት፡፡ አላህ በእናንተ ገሩን (ነገር) ይሻል፡፡ በእናንተም ችግሩን አይሻም፡፡ ቁጥሮችንም ልትሞሉ አላህንም ቅኑን መንገድ ስለመራችሁ ታከብሩትና ታመሰግኑት ዘንድ (ይህን ደነገግንላችሁ)፡፡ (185)]
በዚህም መረጃ መሰረት ለይለቱል ቀድር ማለትም ፈጣሪያችን አላህ ለማንኛውም ነገር ሁሉ አመታዊ ውሳኔ የሚሰጥበት ምሽት በረመዳን ወር ውስጥ የምትገኝ አንዲት ሌሊት መሆኗን እንረዳለን።
ምክንያቱም ሌሊቷ ቁርኣን የወረደባት ሌሊት ነች ። ቁርኣን ደግሞ የወረደው በረመዳን ወር ነውና የመወሰኛይቱ ምሽትም የምትገኘው በረመዳን እንጂ በሌላ ወር አይደለም።
ስለሆነም የሻዕባን አጋማሽ ሌሊት " ለይለቱል ቀድር" የመወሰኛይቱ ምሽት አይደለችም። በዚያች ሌሊትም ለአመቱ የሚሆን ምንም የሚወሰን ነገር የለም።
💥ስድስተኛው ነጥብ
የሻዕባን ወር አጋማሽ ቀን ላይ አንዳንዶች ምግብ አዘጋጅተው ለድሆች በሚል የሚያከፋፍሉትና የእናት እራት፣ የአባት እራት ወይም የወላጆች እራት የሚሉት [እንዲሁም ባገራችን የእህል ዘሮችን ባንድ ላይ ሰብስቦ በመቀቀልና ከዚያም መጀመርያ ግቢ ውስጥና ውጪም በመበተን አመቱ የጥጋብ የርጋታ ይሁንልን የሚሉት] ሁሉ ከነቢዩ ያልተላለፈልን ከሰሃቦችም ሪድዋኑላሂ አለይሂም ያልተገኘ መጤ የሆነ ቢድዐ ነው።
እነዚህን ጉዳዮች ስድስቱን ጠቅሼ ብቆጥራቸውም ሌሎች ላብራራቸው የሚገቡ ሆነው ያለፍኳቸው እንዳሉ አላውቅም። አላህ እኛንም እናንተንም ሱናን የሚያሰራጩ፣ቢድዐን የሚያስጠነቅቁና ተመርተው የሚመሩ (ቅን ሆነው የሚያቀኑ) ያድርገን።
ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በጁምዓ ኩጥባቸው ወቅት እንደገለፁት ከምሪቶች ሁሉ በላጩ የሳቸው ምሪት ነውና ቅኑን መንገድ የሚከተሉ፣ በሳቸው አመራርም የሚመሩ ያድርገን።
« በማስከተል: ከንግግሮች ሁሉ በላጩ የአላህ ኪታብ ነው። ከአመራሮች ሁሉ በላጩም የሙሀመድ ምሪት ነው። መጥፎ ጉዳይ ማለት መጤዎቹ ናቸው። ሁሉም ፈጠራዎች ጥመት ናቸውና።» ብለዋል።
🍀〰〰〰〰〰〰🍀
በታላቁ ፈቂህ ሸይኽ ሙሐመድ ሷሊህ አል ዑሰይሚን [ረሂመሁላህ]👆
__________
🎐16ሻዕባን 1436 / 05 ጁን2015
النقل من شبكة الإمام الآجري رحمه الله
http://bit.ly/1ERYKzQ
www.facebook.com/tenbihat

Post a Comment

0 Comments