Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ሻእባን የረመዳን የቅርብ ጎረቤት

by Hassen Mohammed
* ሻእባን የረመዳን የቅርብ ጎረቤት ነው:: ረመዳን ደግሞ ከባድ ጥንቃቄ የሚሻ የአዝእርት ቦታ ነው፥ የዘራህበትን ያበቅላል - መሬቱ ለም፣ እርሻውም ውሀማ ነው:: ጥቂት ዘርተህ ማበራከት ከሻህ ይሄ ወር ብቸኛ አማራጭ ሆኖ ታገኘዋለህ:: ይሁንና ለማስረገጥ የፈለግኩት ነገር ምርጥ ዘርን እንደወትሮ እመሬቱ ላይ ከመበተንህ በፊት መለቀም ስላለባቸው እንከኖች ይሆናል:: ብዙ እንከኖች አሉ:: መቼም በሬ የጠመደ ሁሉ አያርስም ታውቃለህ፥ ያረሱትም ቢሆን የተመኙትን ያህል አይፋፋም፥ የፋፋውም ቢሆን ካመት እስታመት ማድረሱን እንጃ:: ሸዋል ላይ በተለይም የኢድ እለት በርካታ ከረጢቶችን ለመሙላት ከፈለግክ ረመዳን ላይ ሌት ተቀን ተደፍተህ ማረስ አለብህ፥ ያረስከው ሁሉ ፍሬ እንዲሆን ደግሞ ከሻእባን ጅማሮው አንስቶ ሜዳውን በሙሉ ከእንከን በማጽዳት መታተር ይጠበቅብሀል:: እንደልጅነት ግዜው ሁላ ልክ ረመዳን አንድ ሲሆን ከመጀመርያው የተራዊህ ሰላት በፊት እንከኖቹ እንዳሉ ሆነው ገላህን ታጥበህ ብቻ የምትቀላቀለው ከሆነ (በአብዛኛው) ለኢድ እለት በምትወስደው ሻወር ምርቶችህ ይበሸቅጣሉ::
* አላህ በሱረቱል በቀራህ ላይ የረመዳንን ጉዳይ ሲዳስስ አብሮ ያነሳው ቁምነገር ሚስቶች ለባሎቻቸው፣ ባሎችም ለሚስቶቻቸው አንዱ አንዱን የሚሸፍን ልብስ እንደሆኑ ነው:: የሚሸፋፈኑት ነገር ደግሞ የዱንያም ይሁን የአኼራ ነውሮቻቸውን ብቻ ሳይሆን በዚህ በተጠቀሰው ወር ላይ የሚኖሩ የስራ ጫናዎችንም ጭምር ይሆናል:: እንደሚታወቀው ረመዳን ሴቶችን ይበልጥ ወደ ማድቤት የሚመልስ የተሳሳተ ገጽታ አለው፥ ወንዶች ደግሞ እስከ መግሪብ አዛን ድረስ ቁርአን የመቅራቱን እድል በሞኖፖል ይቆጣጠሩታል:: ለዚህም ይመስለኛል እብዙ ቤቶች ውስጥ በረመዳን ወር ላይ አንድ ግዜ እንኳ ቁርአን የማያኸትሙ እናቶች በርክተው ሳለ በዛው ቤት ውስጥ ቁርአኑን የትየለሌ ግዜ ያነበቡት አባቶች ቁጥር የትየለሌ ነው:: በነገራችን ላይ ሴቶች በቀብራቸው ውስጥ "ሾርባሽ ለምን ጨው ይበዛበታል?" የሚል ጥያቄ አይጠብቃቸውም፥ ልክ እንደ ወንዶቹ ሁሉ "መን ረቡኪ" ይባላሉ እንጂ:: ስለዚህም ባሎች ወንድሞችና አባቶች ለሴቶች ልብስ መሆናችሁን የምታስመሰክሩበት ወርቃማ አጋጣሚ ይህ ረመዳን ብቻ ነው:: ማድቤት ገብተህ ጥላሸት በጥላሸት ሆነህ ፍዳህን እየበላህ አንዲት ሳንቡሳ ብትጠብስ ኖሮ እርግጠኛ ነኝ ረመዳንን በሙሉ አደብ ገዝተህ ታሳልፋለህ:: ቢያንስ "ይሄ አይጣፍጥም፣ ይሄ እንደዚህ ሆነ፣ በዚ ገባ በዚ ወጣ" ስትል አትመናጨቅም:: ለነፍስህም ቢሆን ካለችበት የኩራት ተራራ ላይ በማውረድ ልኳን ማሳያ ይሆንሀል:: ከሁሉ በላይ ደግሞ የምታፈቅራቸውን ነብይ ሙሀመዱን ሰለ አላሁ አለይሂ ወአሊሂ ወሰለም ድንቅ ፈለግ መከተልም ይሆንልሀልና ጥቂትም ብትሆን ስራቸውን ተካፈል፥ በመልካም ከማዘዝ ባልተናነሰ መልኩ መልካም የሚሆኑበትን ግዜያቶች ማስፋትም ትልቅ ቁምነገር ነው:: 24 ሰአታት ቢዚ በሆኑበት ወር ላይ "ስንት ግዜ አኸተምሽ" ማለት ግብም አግባብም አይደለም::
ከኹጥባ ላይ የኮረጅኩት ነው፥ መልካም ሻእባን መልካም ረመዳን

Post a Comment

0 Comments