Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ቀልብ የፅድቅም የጥፋትም የእዝ ማዕከል

ቀልብ የፅድቅም የጥፋትም የእዝ ማዕከል
ጀነት ነፍስ በምትጠላቸው ነገሮች ተከባለች፤ ጀሀነም ደግሞ ነፍስ በምትወዳቸው ሸይጧን በሚያስውባቸው አማላይ ነገሮች፡፡ በብዙ ሁኔታዎቻችን ከአረሕማን ይልቅ ለሸይጧን የቀረብን ነን፡፡ ዐይኖቻችን፣ ጆሮዎቻችን፣ እጆቻችን፣ እግሮቻችን፣ እንዲሁም ምላሳችን ለሸይጧናዊ ተልእኮ የሰሉ ናቸው፡፡ ቀላሉን አምላካዊ ክልከላ መታገስ አቅቶን ከባባድ ሸይጧናዊ ልፋት ላይ እንተጋለን፡፡ ሁሉም የሰውነታችን ክፍሎች ለጥፋት ሲተባበሩ፣ አንዳቸው ብቻ ለሚበቁት ኸይር ግን ተባብረውም ይዝላሉ፡፡ ይሄ ሁሉ የሚሆነው እንግዲህ ማዕከሉን “ዋግ” ሲመታው ነው፡፡ ቀልብ በሺርክ፣ በቢድዐ፣ በስሜት፣ ለሙስሊሞች በምታረግዘው ክፋት፣ … ከተበከለች ታማ፣ ታውካ፣ አመርቅዛ ትሞታለች፡፡ታዲያ ቀልብ ስትሞት ሞቷ ለኸይሩ እንጂ ለሸሩማ ኢንኩቤተር ትሆናለች- ክፉ የሸር መፈልፈያ፡፡ብቻ ሂወቷ በኢማን ካልኩሌተር ሲሰላ ያለኢማን ሂወት የለምና ሞታለች - የምር ሞት! ከዚያስ? ከዚያማ ቀልብ ተበላሽታ ሌላው ሰውነት ምን ጤና ሊኖረው? የአካል እንቅስቃሴ በሙሉ ደመ-ነፍሳዊ ይሆናል- ተንቀሳቃሽ ሙት!!! ግድግዳ የተጠጋ እንጨት ሆኖ ሄወት እንዳለው ያስባል፡፡
ከዚህ በኋላ ዐይንም ዐይን ጆሮም ጆሮ አልሆነም፡፡ የሰማያትና የምድር አፈጣጠር፤ የሌሊትና የቀን መተካካት ለሱ ከታክሲዎች መተላፍ፣ ሽንት ቤት ደርሶ ከመመለስ ብዙም ልዩነት የለውም፡፡ ችግሩ ከማዕከሉ ነዋ!!!
((ለነርሱም በነርሱ የሚያውቁባቸው ልቦች ወይም በነርሱ የሚሰሙባቸው ጆሮዎች ይኖሩዋቸው ዘንድ በምድር ላይ አይሄዱምን እነሆ ዐይኖች አይታወሩም ግን እነዚያ በደረቶች ውስጥ ያሉት ልቦች ይታወራሉ፡፡)) (አልሐጅ፡ 46)
በሌላ በኩል ልብ ከተስተካከለች፣ በኢማን ከተዋበች፣ በኢማን ካሸበረቀች መላ ሰውነት ጤና ይኖረዋል፡፡ ፊትም ኑር ይላበሳል፡፡ ዐይኖች በሐራም አይገግሙም፡፡ ጆሮዎች ለሙዚቃ አይቆሙም፡፡ ምላስም የሀሜት ማሽን አትሆንም፡፡ ከውጭ ሙስሊም ያልሆነ ገፅታ እየተስተዋለ ምላስ “ዋናው ልብ ነው” እያለች አታሽቃብጥም፡፡ ማዕከሉ ነቅቶባታላ!!!
ልብ ስትስተካከል እውነተኛ ማንነት ይገኛል፡፡ ከውስጥም ሙስሊም፣ ከውጭም ሙስሊም! በሐያእ የለሰለሰ፣ በውጭ ገፅታው ያልተኮፈሰ፣ በልቡ የመጠቀ፣ ከእንቶ ፈንቶ የራቀ ልዩ ስብእና!!! አቡበክር አሲዲቅ ረዲየላሁ ዐንሁ ከሌሎች የመጠቀው በሶላቱና በፆሙ አልነበረም፡፡ ይልቁንስ ልቡ ላይ በፀደቀ ነገር ነበር- ኢማን!!! የቀልብ ልዩ ክብር!!!
ባጭሩ ጥፋታችንም ልማታችንም ከልብ ጋር የተሳሰረ ነው ማለት ነው፡፡ ታዲያ እኔና እርሶ የቱጋ ነን? ሰገነት ወይስ ጫማ ተራ? ነው ወይስ መሀል ሰፋሪ? በሌላ አነጋገር ልባችን ጤነኛ ነው፣ በሽተኛ ነው፣ ወይስ ሙት ነው?
ለካ ይህንንም ለማወቅ ልብ ያስፈልጋል፡፡ ((ባለ ልቦናዎቹ እንጂ አይገነዘቡም)) አይደል ያለው ኻሊቁ?
አንተ ልቦችን ገለባባጭ የሆንከው ጌታችን ሆይ! ልቦቻችንን ወደ ትእዛዝህ ኡዙርልን፣ በዲንህም ላይ አፅናን፡፡ አላሁመ ኣሚን፡፡