Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ኢና ሊላሂ ወኢና ኢለይሂ ራጂኡን ‹‹አጫጭሱላቸው››፣ በሽርክ አይሳቅም፡፡

Sadat Kemal Abu Meryem's photo.
ኢና ሊላሂ ወኢና ኢለይሂ ራጂኡን
‹‹አጫጭሱላቸው››፣ በሽርክ አይሳቅም፡፡
በአላህ ፈቃድ ወደ መደበኛ ትምህርታችን እንመለሳለን፡፡ ሽርክ አላህ ታላቅ በደል ብሎ የጠራው ነው፡፡ ነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለምም) ታላላቅ አጥፊ ወንጀሎችን ሲጠቅሱ ከሽርክ ነው የጀመሩት፡፡ የአላህ መልክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) መዲና ተቀምጠው የመን ውስጥ የምትመለከዋ ቀብር እረፍት ነሳችኝ ብለው ነበር፡፡ ዛሬ አላህ ካዘነላቸው ውጭ፣ የሽርክ ጉዳይ ብዙም ቦታ አይሰጠውም ዱዓት በሚባሉት ዘንድ፡፡ አላህ ሁሉንም ተጣሪዎች ነብያቱን አስታጥቆ ወደላከበት አርስት ተውሂድ ይመልሳቸው፡፡
በሶዎች ሞባይል ውስጥ በተለይ በጫት ቃሚዎች መሃል አንድ በ ብሉ ቱዝ የሚቀባበሏት አፉ ላይ ጫት የያዘ ወጣት የሚያንጎራጉራት የሽርክ ስንኞች፣ አደብ ማጣት እና ኹራፋት ውስጥ የሚከተሉት ይገኛሉ
1) ‹‹የቦረናው ጌታ ነው እንደ ጡላጊ፣
ትልቁን ጠቃሚ፣
ትንሹን አሳዳጊ››
ይሄ ስንኝ በግልፅ የአላህን መብት አሳልፎ ለቦረናው ሸይኽ እየሰጠ ነው፡፡ ጠቃሚ ጎጂ፣ ሰጪ ነሺ አላህ ብቻ ነው፡፡ አላህ ብቻ ሊያደርገው በሚችለው ጉዳይ ፍጡራንን መጥራት ሽርክ እና ኩፍር ነው፡፡ የአላህ መልክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ደግሞ ከአላህ ውጭ ያለን እየጠራ የሞተ እሳት ገባ ብለዋል፡፡ ነፍሳችንን፣ ቤተሰቦቻችንን ከእሳት በአላህ ፈቃድ በታደግ ግድ ይለናል፡፡ ተውሂድን መማር እና ማስተማር ከምንም በፊት የሚቀደም ፈርድ ነው፡፡
2) ‹‹ፍየል ቅጠል በልታ ትወልዳለች መንታ፣
መቼም እርባን የለው በጫት የተመታ››
እዚህ ጋር በጫት ሱስ የተለከፈ እርባና የለውም ሊል ከሆነ የፈለገው ትክክል ነው፡፡ ከዛ ውጭ ግን ይህን አደንዛዥ ቅጠል ለተቃወሙ እና አልቅምም ላሉ ከሆነ ዉድቅ አባባል ነው፡፡ ወይንም ጫት ቅመን በቀልባችን ነደፍናቸው እያሉ የሚያሰሙት ተረተረት እና እርባና ቢስ ወሬ ውድቅ ነው፡፡ እርባና የሌለው ጫት እየቃመ የአላህን፣ የሚስቱን፣ የልጆቹን፣ የቤተሰቦቹን እና የፍጡራንን መብት ጀዝቦ የማያሟላው ነው፡፡
3) ‹‹ቶሎ በል ቶሎ በል፤
አንድዬ ቶሎ በል፣
እንደ ዘመኑ ሰው ነገ ዛሬ አትበል››
ኢናሊላሂ ወኢና ኢለይሂ ራጂኡን ተመልከቱ የዚህ የጫት ቃሚ ድፍረት እና መሃይምነት፡፡ ነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) እንዲህ ይላሉ ‹‹ማንም ሙስሊም በወንጀል እና ዝምድናን በመቁረጥ ዱዓ እስካላደረገ ድረስ አላህ ከሶስት አንዱን ይሰጠዋል፡፡ ወይ የለመነው ይደርሰዋል፣ ወይ ለአኸይራ ያዘገይለታል፣ ወይም አምሳያውን በላ ያነሳለታል››፡፡ አሁንም ነብዩ (አለይሂ ሰላቱ ወሰላም) በዱዓ እንዳንቻኮል ነገረውናል፡፡ አላህን እንዲህ አድርጎ መወሰፍ ምን የሚሉት በሽታ ነው፡፡ አላህ አደብ እና እውቀት ይስጠን፡፡
4) ‹‹ዝናቡ ዘነበ ጫቱ ለመለመ፣
የሚቅመው ቢያገኝ እያጉረመረመ››
ኡመተል ኢስላምን ያሽመደመደው፣ ያጀዘበው፣ የአላህንም የፍጡራንንም ሀቅ እንዲያጓድል ሰበብ የሆነው ይህን አደንዛዥ ቅጠል እንዲህ እያሉ ያስተዋውቁታል፡፡ አላህ ወንድም እና እህቶቻንን ከዚህ ሱስ ያውጣልን፡፡
5) ‹‹ወንድነት አይጠቅም ሴትነት አይጎዳ፣
መገኘት ነው እንጂ ከሳዳቶች ጓዳ››
ሳዳቶች ምርጦች ብለው የሚያስባቸው ሰዎች እነዚህ አይነት ሰዎች ዘንድ መጋረጃ ጋርደው የሚጠነቁሉ፣ ጀመዓ ሰላት የማይሰግዱትን ነው፡፡ ሸሪዓችን ከጥሩ ሰዎች ጋር እንድንጎዳኝ ነገሮናል፡፡ ይህ ማለት ግን መጋረጃ ጋርዶ ጫት የሚያኝኩ፣ ለጂን የሚያርዱ ሰዎች ጓዳ እንድንኳትን አይደለም፡፡
አማኝ ሆን አላህን መታዘዝ የእውነተኛ ወልዬች ባህሪ ነው፡፡ ወንዶች መስጂድ ይገኛሉ፣ ቂርዓት ይቀራሉ፣ ዝምድና ይቀጥላሉ በጠቅላላ ወንድም ሴትም አማኞች አላህ እና መልክተኛው ያዘዙትን ይሰራሉ እንጂ ጠንቋይ ቤት ወይንም የጠንቋይ ጓዳ አይመላለሱም፡፡
6) ‹‹አጫጭሱላቸው በሁለቱ ገሌ (ማጨሻ)፣
አንዱም የአብዶዬ ነው፣
አንዱም የኸድር››
ከላይ አብዶዬ የሚሏቸው አብድልቃድር ጀይላኔ (ረሂመሁላህ) ነው፡፡ ኸድር ደግሞ ነብየላህ ኸድርን (አለይ ሰላም) ነው፡፡ ልብ በሉ ብዙ እናቶች እና አባቶች ቡና ይፈላ ይባል እና ቁርስ ጀባ ቃሃ ጀባ እየተባለ እጣን ይጨሳል፡፡ እጣኑም ሲጨስ እንዲህ ከአላህ ውጭ ያሉን የሚጠሩበት ሁኔታ አለ፡፡ አንድ ሰው ቤቱ ላይ ቤቱ ጥሩ ሽታ እንዲኖረው ማጨስ ይችላል፡፡ ይህን የሚያጨሰውን ጭስ ግን ከአምለኮ ጋር አገናኝቶ ለአብድል ቃድር ጀይላኔ እና ለሰይድና ኸድር ሁለት ማጨሻ ተደርጎ አጭሱላቸው ማለት ሽርክ ነው፡፡
ስግደቴም፣ እርዴም ወይንም ሀጄም፣ ህይወቴም፣ ሞቴም ለአለማቱ ጌታ ለአላህ ነው፣ አጋር የለውም፡፡ ይህ ነው የኢስላም መልክት፡፡ የሚያሳዝነው ግን ሰዎች ይህን መሰል የሽርክ ስንኞች እና ተግባሮች ለሰዎች ሲያስተላልፉ እየሳቁ፣ ስማው እማ እያሉ ሙድ እየያዙ፣ ብሎ እስቲ ትንሽ ፈታ በል እያሉ ኩፍርን፣ ሽርክን፣ ኹራፋትን ሲቀባበሉ እና ሲስቁ ታያለህ፡፡
እውነት ሽርክ የሚያስቅ ወይንስ እረፍት የሚነሳ አስደንጋጭ ጉዳይ ነው?
አንዳንዶች ባክህ አታካብድ ይላሉ፡፡ ግን ያልገባኝ ሽርክ ያልተካበደ ምን ይሆን ሌላ የሚካበደው አጀንዳ?
የአላህ ባርያዎች ሆይ! እያንዳንዳችን በተለይ አገራችን ላይ አይን አፍጥጦ ሽርኩ በአደባባይ ላይ፣ በተለያዩ ሚድያዎች ላይ እየተሰራጨ ያለውን አደጋውን ተረድተን፣ ተውሂድን ተምረን ልናስተምር ግድ ይለናል፡፡ ይህም እኛ ላይ የተጣለ አማና ነው፡፡
አላህ ሆይ! አግዘን፣ እውቀትን ጨምርልን፣ ከሽርክ እኛንም ዝርያዎቻችንንም ጠብቀን፡፡ የአላህ ሰላት እና ሰላም በነብያት መደምደሚያ፣ በቤተሰቦቻቸው፣ በባልደረቦቻቸው እና ሃቅን በተከተለ ላይ ሁሉ ይሁን፡፡