Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ላለመደናገር ንቃትን እናዳብር!!

ላለመደናገር ንቃትን እናዳብር!!
አህባሾች እና መሰል ሽርክን ለማስፋፋት የሚሯሯጡ አንጃዎች፤ ለሚፈፅሙት የቀብር አምልኮ የሽርክ ተግባራት ሁሉ ደጋፊ የሚሆን መረጃ ለማቅረብ ዘወትር ደኢፍና መውዱእ የሆኑ ዘገባዎችን ሲቀባበሉና በከንቱ ሲዳክሩ ይስተዋላሉ። ይሁንና አህሉሱና ሀቅን ከመረጃው ጋር ግልፅ በማድረግ አንገት እንዲደፉ አድርገዋቸዋል።
{أَلَا لِلَّهِ الدِّينُ الْخَالِصُ ۚ وَالَّذِينَ اتَّخَذُوا مِن دُونِهِ أَوْلِيَاءَ مَا نَعْبُدُهُمْ إِلَّا لِيُقَرِّبُونَا إِلَى اللَّهِ زُلْفَىٰ إِنَّ اللَّهَ يَحْكُمُ بَيْنَهُمْ فِي مَا هُمْ فِيهِ يَخْتَلِفُونَ ۗ إِنَّ اللَّهَ لَا يَهْدِي مَنْ هُوَ كَاذِبٌ كَفَّارٌ} [الزمر : 3]
«ንቁ! ፍጹም ከማጋራት የፀዳና ምርጥ የኾነው ሃይማኖት የአላህ ብቻ ነው፡፡ እነዚያም ከእርሱ ሌላ (አማልክትን) ረዳቶች የያዙት «ወደ አላህ ማቃረብን እንዲያቀርቡን እንጅ ለሌላ አናመልካቸውም» (ይላሉ)፡፡ አላህ በዚያ እነርሱ በእርሱ በሚወዛገቡበት ነገር በመካከላቸው ይፈርዳል፡፡ አላህ እርሱ ውሸታም ከሓዲ የኾነን ሰው አያቀናም፡፡» ዙመር 3
የኢስላም መገለጫ አላህን ብቻ ማምለክ ‘ተውሂድ’ እንደሆነ የሚያስረዱ፤ ባእድ አምልኮን የሚኮንኑ፣ ለቀብር አምልኮ የሚያበቁ መንገዶችን ሁሉ ከወዲሁ የሚዘጉ የቁርአን እና የሱና መረጃዎች እጅግ በርካታ ናቸው።
አለሀምዱሊላህ! ቁቡሪዮች ለሚያነሷቸው ውዥንብሮች ሁሉ
አህሉሱና ከበቂ በላይ በሆኑ መረጃዎችና ማብራሪያዎች ምላሽ በመስጠት ሀቅን ግልፅ አድርገዋል። ሹቡሀቶቻቸውን ያንኮታኮቱ መሀይምነታቸውንም ያሳዩ ጥናቶች ቀርበዋል፤ በመቅረብም ላይ ናቸው!!
እነዚህ የቢድዓ አራማጆች እንደሸረሪት ድር የደከሙ መረጃዎቻቸው ሁሉ ተበጣጥሰው ከወደቁባቸው በኃላ፤ ከአመታት በፊት የመልእክተኛው ቀብር ምስል ነው በማለት የተሰራጨ የቀብር ፎቶግራፍ በአማርኛ "የነብዩ ሰ.ዓ.ወ ቀብር" የሚል መግለጫ ፅፈውበት በማህበራዊ ድረገፆች በተደጋጋሚ ሲለጥፉ አስተውያለው። ነገሩ አዲስ ነውና አንዳንድ ውንድሞችና እህቶችም በግል ፎቶዉን በመላክ ትክክለኛነቱን ጠይቀውኛል። ስለዚህም በፎቶው ዙሪያ የተባሉ ነገሮችን ከቃኘው በኃላ በፎቶው ዙርያ ጥቂት ነጥቦችን ለመጠቆም ብእሬን አንስቻለው።
ይህ ፅሁፍ ለምን አስፈለገ? የነብዩ ቀብር ነው ቢሉስ ምን የሚጨምርላቸው መረጃ አለ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ምንም እንኳ ቀብርን በዚህ መልኩ ከፍ አድርጎ መገንባት በማያጠራጥር መልኩ የተከለከለ በመሆኑ ይህ ፎቶ መረጃዎችን ሊሽር እንደማይችል የታወቀ ቢሆንም፤ ለአንዳንድ የዋሆች ግን "የመልእክተኛው ቀብር እንደዚህ ከሆነ፤ የሸኾቻችንን ዶሪህ ለምን አንገነባም? አናሸበርቅም?? የሚል ብዥታን ሊፈጥርባቸው ይችላል። ስለዚህም አላህ በመታገዝ ተከታዮቹን አጠር ያሉ ማስገንዘቢያዎች ለማስቀመጥ እሞክራለሁ።
[1] የቁቡርዮች ቅጥፈት፦
ተከታዮቹ ነጥቦች ፎቶው የመልእክተኛው ቀብር ምስል እንዳልሆነና ቅጥፈት መሆኑን ያመላክታሉ፤
1.1) በፎቶው ላይ ቀብሩ በአንድ ክፍል ውስጥ ለብቻው ተነጥሎ ይታያል። ይህ ደግሞ ከእውነታው በእጅጉ የራቀ ነው። ማንኛውም ቀብራቸ በአካል የጎበኘ ሰው ለመመልከት እንደሚችለው በመካከላቸው ምንም አይነት ርቀት የለም በሚያስብል መልኩ የመልእክተኛውን ቀጥሎ የአቡበክርን ቀጥሎም የዑመርን ቀብር ያገኛል። ይህ ፎቶ ከነብዩ ቀብር ጋር አንድ ሜትር ሸማይሞላ ርቀት ከጎናቸው ያረፉትን የሁለቱን ምትኮች ቀብር አለማካተቱ ትክክኛ ላለመሆኑ አይነተኛ ማሳያ ነው።
1.2) በፎቶው ላይ ቀብሩ ሰፋ ያለ ክፍል ውስጥ እንደሆነ ይታያል። ይህም ከእውነታው የራቀ ነው። በታሪክ እንደሚታወቀው መልእክተኛው የተቀበሩት ከመስጂዳቸው ጋር ግድግዳ በሚለየው የአዒሻ ቤት ውስጥ ሲሆን ይህ ቤት ደግሞ በጣም ጠባብ ነበር። እርዝመቱ በሰው ቁምት ያክል ሲሆን ስፋቱ ደግሞ ከበር እስከ ግድግዳ ከስድስት እስከ ሰባት ክንድ ያክል ጎኑም ከስምንት እስከ ዘጠኝ ክንድ ብቻ ነበር። ፎቶው ከቀብሩ ውጪ ሰፊ መንቀሳቀሻ ቦታ እንዳለውና ብዙ ቁሳቁሶች እንደተቀመጡበት ማሳየቱ ትክክለኛ ላለመሆኑ ግልፅ ማሳያ ነው።
1.3) ቤቱ እራሱ ሆኖ የቀድሞ ይዞታው ትንሽ ሲሆን አሁን ግን ሰፍቷል የሚል መከራከሪያ ቢቀርብ፤ ይህ የቤቱ ይዞታና ስፋት እንዳልተቀየረ የሚያሳየን፤ ታዋቂው ፍትሀዊ መሪ ኡመር ኢብኑ አብዲልአዚዝ በ86 አመተ ሂጅራ የመልእክተኛው ቀብር ያለበትን ይህንን ክፍል ምንም ክፍተት ሳይተው በጠንካራ ግንብ መድፈኑ ሲሆን፤ በተደጋጋሚ ቀብሩ ላይ ጥቃት የመፈፀም ሙከራዎች በመስተዋላቸው ምክኒያት በ557ዓ.ሂ የወቅቱ መሪ ኑረዲን ዚንኪ ረሂመሁላህ የቤቱን ዙሪያ አስስቆፈሮ የእርሳስ ማእድን በማቅለጥ በጠንካራ መሰረት ላይ ገንብቶታል። ለተጨማሪ ዝርዝሩር በ911ዓ.ሂ ያለፉት አሊ አብዲላህ አሰምሁዲይ የፃፉትን «ወፋኡል ወፋ ቢአኽባሪ ዳሪል ሙስጠፋ» 2/648–650 ይመልከቱ። ከዚህ በኃላ ቤቱ ሰፍቷል የሚል መከራከሪያ ሊቀርብ አይችልም።
1.4) በፎቶው ላይ ቀብሩ ተለቅ ያለ ሳጥን ይመስላል። የመልእክተኛው አካል ደግሞ ለህድ ተቆፍሮ በክብር ቀብር ውስጥ አረፈ እንጂ በሳጥን አልተቀመጠም።
በመዲና እና በጀዚረተል አረብ ቅድመ ኢስላምም ይሁን አሁን
በሳጥን የመቅበር ልመድ የለም። ይህም ሌላኛው የፎቶዉን ትክክለኛ አለመሆን የሚያሳይ መረጃ ነው።
1.5) በሳጥን ተቀብረው ሳይሆን ቀብሩ ከፍ ያለ ስለሆነ ነው ከተባለ፤ መልእክተኛው በህይወት ሳሉ ቀብርን ከፍ አድርጎ ከመገንባት ባልደረቦቻቸውን ሲያሳስቡና ሲያስጠነቅቁ ኖረዋል።
عَنْ أَبِي الْهَيَّاجِ الْأَسَدِيِّ، قَالَ : قَالَ لِي عَلِيُّ بْنُ أَبِي طَالِبٍ : أَلَا أَبْعَثُكَ عَلَى مَا بَعَثَنِي عَلَيْهِ رَسُولُ اللهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ ؟ «أَنْ لَا تَدَعَ تِمْثَالًا إِلَّا طَمَسْتَهُ ، وَلَا قَبْرًا مُشْرِفًا إِلَّا سَوَّيْتَهُ» رواه مسلم
አቢልሀያጅ አል አስዲይ በተዘገበ ሀዲስ አሊይ ኢብኑ አሊ ጧሊብ እንዲህ ብለዋቸዋል፤ «የአላህ መልእክተኛ የሰጡኝን ተልእኮ ላስተላልፍልህን? "የሚመለክ ሀውልት አጊንተህ ሳትሰባብረው፤ ከመሬት ከፍ ያለ ቀብርም አጊንተህ ከመሬት ጋር ሳታስተካክለው አትተው» ሙስሊም ዘግበውታል
የኢስላም ሊቃውንት እንዳስገነዘቡን ቀብር መሆኑን ለማሳወቅ ያክል በአንድ ስንዝር ከፍታ ከመሬት ጋር ማስተካከል ተገቢ ነው።
ይህ ሀዲስ ብቻ ሳይሆን በርካታ ሀዲሶች ይህንን መልእክት ያጠናክራሉ። ታዲያ ሰሀቦች በዚህ መልኩ አደራ የሚባባሉበትን ጉዳይ ቸል በማለት የመልእክተኛውን ቀብር በዚህ ከፍታ የሚገነባ ማን አለ?? በፍፁም!! ይህ ፎቶ የቁቡሪዮች ማጭበርበሪያ መሆኑ አያጠረጥርም!!
1.6) ቀብሩ ያለበት ቤት እጅግ የሸበረቀ መሆኑ ቀብርን ማሸብረቅ ከሚከለክሉ መረጃዎች ጋር የሚጣረስ ሲሆን የጃሂሎች ተግባር መሆኑንም ያሳያል። በተለይም በቀብሩ አናት ላይ የሚታየውን ጥምጣም ስንመለከት ለቱሪስት መስህብ በጥንቃቄ ተጠምጥሞ የተሰናዳ ይመስላል። የመልእክተኛው ባልደረቦችም ይሁን ከነሱ በኃላ እስካለንበት ዘመን መዲናን ያስተዳደሩ መሪዎች ሁሉ የመልእክተኛውን ቀብር በሙዚየም መልክ አሳምረው ለጎብኚዎች ክፍት አድርገውት አያውቁም። ሰላምታን የሚያቀርቡትም ከግድግዳው ባሻገር ነው።
በእነዚህ ምክኒያቶች ይህ ፎቶ የመልእክተኛውን ቀብር እንደማይወክል፤ ቀብር አምላኪዎች የሸይኾቻቸውን ቀብር የሚገነቡበት እና የሚያሸበርቁበት አካሄድ የመልእክተኛው ቀብርን አርአያ አድርገው ለማቅረብ ያሰራጩት መሆኑ አያጠራጥርም!!
[2] ይህ ፎቶ የማን ነው? ለሚለው ጥያቄ:–
በዚህ ፎቶ ዙሪያ ጥናት ያደረጉ ሁሉ እንደሚስማሙት ይህ ቀብር በቱርክ አልመውለዊያህ በመባል የሚታወቀውን የሱፊያ ጦሪቃ የመሰረተው ገጣሚ ጀላሉዲን አሩሚይ ቀብር ነው።
ጀላሉዲን አሩሚይ ( እ.ኤ.አ 1207-1272) ከፃፋቸው የግጥም መድብሎች እና አጫጭር ፅሁፎች በመነሳት የኢብኑ አረቢን የአላህ መለኮታዊ ሀይል ሁሉም ነገር ውስጥ እንደሚሰርፅ የሚሰብከው የ"ሁሉል ወል ኢቲሀድ" አስተሳሰብ አቀንቃኝ እንደሆነ ግልፅ ነው። (ዲራሳት ፊተሰውፍ) ሷሊህ አረቂብ ገፅ 195 ይመልከቱ
ጀላሉዲን አሩሚ የመውለዊ ጦሪቃ ተከታዮች የታወቁበትን ለረጅም ሰአታት ክብ ሰርቶ በዝግታ መደነስን ያዘለ ‘መንፈሳዊ’ የሙዚቃ ስርአት የቀረፀ ሲሆን፤ በእነሱ አስተሳሰብ ሸይኻቸውን መሀል አድርገው ክብ እየሰሩ በለስላሳ ሙዚቃ ታጅበው መደነሳቸው ከአለማዊነት አውጥቶ መንፈሳቸውን የሚያጠራ በረከትንም የሚያወርድ ተግባር ነው።
እነዚህ ሰዎችና ሸይኻቸው የሚጓዙበት የተሰውፍ አካሄድ ባጢል መሆኑን የሚያሳይ እውነታ ነው።
አላህ የመካ የሙሽሪኮችን አምልኮ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፤
{وَمَا كَانَ صَلَاتُهُمْ عِندَ الْبَيْتِ إِلَّا مُكَاءً وَتَصْدِيَةًَ} [الأنفال : 35]
«በቤቱ (በካዕባ) ዘንድም ስግደታቸው ማፏጨትና ማጨብጨብ እንጂ ሌላ አልነበረም!» አል አንፋል 35
የዚህ ፅሁፍ አላማ ስለ ጀላሉዲን እና ስለጦሪቃው መውለዊያህ ማሳወቅ ስላልሆነ የአላህ ፍቃድ ከሆነ በሌላ ፅሁፍ የምለው ይኖረኛል።

∴ ሳጠቃልለው፤ ለዘብተኝነትን የማስፋፋት እቅድ አካል አድርገው በመሳልና ከፍተኛ በጀት በመመደብ የቀብር አምልኮን በማስፋፋት ላይ ያሉ አንዳነድ ሀገራትን ድጋፋቸውን አጠናክረዋል። ተውሂድ ተፈጥሯዊ እምነትጨበመሆኑ ይህ ፍላጎታቸው እቅድ ከመሆን አያልፍም!
إِنَّ الَّذِينَ كَفَرُوا يُنفِقُونَ أَمْوَالَهُمْ لِيَصُدُّوا عَن سَبِيلِ اللَّهِ ۚ فَسَيُنفِقُونَهَا ثُمَّ تَكُونُ عَلَيْهِمْ حَسْرَةً ثُمَّ يُغْلَبُونَ ۗ وَالَّذِينَ كَفَرُوا إِلَىٰ جَهَنَّمَ يُحْشَرُونَ} [الأنفال : 36]
«እነዚያ የካዱት ከአላህ መንገድ ሊከለከሉ ገንዘቦቻቸውን ያወጣሉ፤ በእርግጥም ያወጡዋታል፤ ከዚያም በነሱ ላይ ጸጸት ትሆንባቸዋለች፤ ከዚያም ይሸነፋሉ፤ እነዚያም የካዱት ወደ ገሃነም ይሰበሰባሉ» አል አንፋል 36
የሚያሳዝነው ግን... ከአላሀ ውጪ ወደ ሙታን እጅ መዘርጋት፣ ስለት መሳል እና የቀብር አምልኮን ሁሉ ሸሪዓ አስመስሎ በማቅረብ የዚህ ተልእኮ አስፈፃሚዎች የሆኑት አህባሾችና አንዳንድ ኢስላምን ከምንጩ ያልተረዱ ሱፊዮች መሆናቸው ነው።
የዱንያ ጥቅማ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ሽርክን ለማንገስ ለሚንቀሰቀሱት ለእነኚህ የሸይጣን መልእክተኞች ጆሮ የሚያውሱ መሀይማንን በጥሩ ዘዴ የማስተማር፣ የማንቃትና የሚዘውሯቸውን አካላት ሴራም ማጋለጥ እጅግ ተገቢ ነው።
የሽርክ እና የቢድዓ አራማጆች በከሀዲያን ቢመኩም በሀያሉ አላህ በመመካት ትክክለኛውን ተውሂድ በሰዎች ልቦና ውስጥ ለማስረፅ መጣር የጋራ ሀላፊነታችን ነው።
ላለመደናገር ንቃትን እናዳብር!!
አኹኩም ፊላህ ሳላህ አህመድ