Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ክርስቲያኖች የስሌት ቀመራችሁን አስተካክሉ

የስሌት ቀመራችሁን አስተካክሉ
—————————————

የአይ ኤስን ድርጊት የምንቃወመው ከምንም በላይ አንጃው አፈንጋጩ የኸዋሪጅ አንጃ እንደሆነ በታላላቅ ዑለማዎች አንደበት ስለተነገረ፣ ድርጊቶቹም ሃይማኖታችን የማይደግፋቸው ምግባሮች ስለሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪም አንጃው በሚፈፅማቸው ድርጊቶች እምነታችንን ከሚያንቋሽሹ ጭፍኖች ለመከላከል ነው፡፡
እንጂ የምንቃወመው ፍጡርን ለማስደሰት አይደለም፡፡ ወይም ከፍርሃት የመነጨም አይደለም፡፡
ምን ሲባል እንፈራለን? ድርጊቱ እኮ የተፈፀመው ሊብያ እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ አይደለም፡፡ ጥፋቱ እኮ የተፈፀመው በሊቢያ ወሮበሎች እንጂ በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች አይደለም፡፡ ታዲያ በምን አመክንዮ ነው ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ተጠያቂ ሊሆን የሚችለው? በኢስላም ስም የተፈፀሙ ወይም የሚፈፀሙ ጥፋቶችን ከኢስላም ጋር እምቢ ብሎ አስተሳስራለሁ የሚል ካለ በራሱ ስሌት በክርስቲያኖች የሚፈፀሙ ጥፋቶችንም ከራሱ ከክርስትና ጋር ለማስተሳሰር ወደ ኋላ እንዳይል፡፡
ስለዚህ
- አፄ ቴዎድሮስና አፄ ዮሀንስ የወሎ ሙስሊሞችን መጨፍጨፋቸው መፅሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት አለው ማለት ነው? ቃሉ ላይ ብቻ በዮሀንስ በ3 ቀን ውስጥ ሃያ ሺህ ሙስሊሞች ናቸው የተገደሉት፡፡ ልብ ይበሉ! ጭፍጨፋው እምነታቸውን ለመቀየር ፈቃደኞች ስላልሆኑ ነው፡፡ እጅግ በርካቶች ሀገር ንብረታቸውን ጥለው እምነታቸውን ይዘው ተሰደዋል፡፡ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ በግድ እምነታቸውን እንዲቀይሩ ተደርገዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን የቤተ-ክህነት ድጋፍ ከዮሀንስ ጎን እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ዛሬም ድረስ ይህን ድርጊት በግልፅ ከማውገዝ ይለቅ ሽፋን መስጠት ነው የሚቀናቸው፡፡
- የመስቀል ጦርነት ጊዜም ቁድስ ከተማ ውስጥ ያሉ ሙስሊሞች እንዳለ ተፈጅተዋል፡፡ ጨፍጫፊዎቹ እስከ ጉልበታቸው በደም ተውጠው ሲንቀሳቀሱ ነበር፡፡ እጅግ በርካታ የአስከሬን ቁልሎች ከተማዋን ሞልተዋት እንደነበር እራሳቸው መስቀለኞቹ የፃፉት ታሪክ ያስረዳል፡፡ ጦርነቱ በጳጳሶች ቡራኬ እንደተካሄደ ያስታውሱ፡፡ ሙስሊሙ ሰላሁዲን አልአዩቢ ቁድስን ሲቆጣጠር ግን የበቀል እርምጃ አልወሰደባቸውም፡፡
- ቅኝ ገዢዎች በተለይ አፍሪካውያን ላይ ያደረሱት ተቆጥሮ የማያልቅ ግፍ ታሪክ አይረሳውም፡፡ አፍሪካውያንን ለመበዝበዝ ከምክንያቶቻቸው አንዱ ክርስትናን ማስፋፋት እንደነበር ግልፅ ነው፡፡
“እስኪ ወደ ኋላ ሄደህ ምን ታሪክ አስጠቀሰህ?” የሚል እንደሚኖር እጠብቃለሁ፡፡ ምክንያቴ
1. ጥቂት በኢስላም የተተፉ፣ በሃይማኖቱ ምሁራን የተወገዙ ወሮ በሎች በኢስላም ስም የሚፈፅሙትን ድርጊት ከእምነታችን ጋር ለማያያዝ የሚዳዳው ህሊና ስሌቱን እንዲያጤን ለመጋበዝ ነው፡፡
2. እንዳውም ሙስሊሞቹ ላይ የተፈፀሙት ግፎች ምናልባት የሁሉም ካልሆነ የብዙሃኑ ክርስቲያን ድጋፍ የነበራቸው ሲሆኑ በኢስላም ስም የሚፈፀሙትን ግን ማንም እንደሚያየው ብዙሃኑ ሙስሊም ተቃዋሚ ነው፡፡ ይሄ ወርቅ የሆነ ልዩነት ነው፡፡
3. በክርስቲያኖች የተፈፀሙት ግፎች አብዛሃኞቹ የቤተ-ክህነት ድጋፍ እንደነበራቸው መረጃ መዘርዘር ይቻላል፡፡ ዛሬ በኢስላም ስም የሚንቀሳቀሱ አንጃዎች የሚፈፅሙትን ግን የኢስላም ታላላቅ ምሁራን አጥብቀው ይኮንኑታል፡፡ ያስተውሉ! ይሄ መሰረታዊ ልዩነት ነው፡፡
ከዚህ ባለፈ ዛሬም በክርስቲያኖች የሚፈፀሙ አይን ያወጡ ሽብሮች ነበሩም አሉም፡፡ በጀርመን፣ በአሜሪካ፣ በአየርላንድ፣ በአፍሪካ ሀገራት፣ …ወዘተ ማየት ይቻላል፡፡ ከዚህ ውስጥ ሙስሊሞች ላይ የደረሰውን ነጥለን ብናይ መካከለኛው አፍሪካ ላይ አንቲ ባላካ እያለ እራሱን የሚጠራው አካል በጅምላ ሲጨፈጭፍ፣ ሲያቃጥል ነበር፡፡ በሚገርም ሁኔታ ሙስሊሞችን ስጋቸውን ሁሉ ሲበሉ ታይተዋል፡፡ ጥያቄ፡
ስለዚህ ክርስትና ይህን ያዛል ማለት ነው? ክርስትና የእልቂት ሃይማኖት ነው እንበል? ስሌታችሁን አስቡበት፡፡
አንዳንዶች ደግሞ ጭራሽ ከማያውቁት እምነት ውስጥ ገብተው ቁርኣናዊ ጥቅሶችን በማጣቀስ ኢስላምን ጭራቅ ለማድረግ ሲሞክሩ እያየን ነው፡፡ አሁንም የራሳቸውን መፅሐፍ ጥቅሶች በመዘርዘር ስሌታቸውን እንዲያጠየኑት ለናሙና ያክል ብቻ ጥቂት እንጋብዛለን
1. “አሁንም ሄደህ አማሌቅን ምታ፣ ያላቸውንም ሁሉ ፈጽመህ አጥፋ አትማራቸውም ወንዱንና ሴቱን ብላቴናውንና ህጻኑን በሬውንና በጉን ግመሉንና አህያውን ግደል፡፡” [መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 15፡3]
2. “…እርሱን ተከትላችሁ በከተማይቱም መካከል እለፉ ግደሉም፤ አይናችሁ አይራራ አትዘኑም፤ ሽማግሌውንና ጎበዙን ቆንጆይቱንም ሕጻናቶቹንና ሴቶቹን ፈፅማችሁ ግደሉ …” [ትንቢተ ሕዝቅኤል 9፡5-6]
ነብዩ ሙሐመድ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ግን ህፃናት፣ ብላቴና፣ ሴቶች እና አዛውንቶች እንዳይገደሉ በግልፅ አስጠንቅቀዋል፡፡ ምናልባት “እነዚህ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች ናቸው ተሽረዋል አዲስ ኪዳን ግን ግራህን ለሚመታህ ቀኝህን ስጠው አይነት ፍቅር ነው የሚሰብከው” ሊባል ይችላል፡፡ እስኪ ጥቂት ከአዲስ ኪዳን ደግሞ እንመልከት
1. “በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም፡፡” [ማቴዎስ፡ 10፡34]
2. “በምድር ላይ እሳትን ልጥል መጣሁ፣ አሁንም የነደደ ከሆነ ዘንድ ምን እፈልጋለሁ?” [ሉቃስ፡ 12፡49]
3. “ነገር ግን እነዚያን በላያቸው ልነግሥ ያልወደዱትን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጡአቸው በፊቴም እረዱአቸው፡፡” [ሉቃስ፡ 19፡27]
4. “…አሁን ግን ኮረጆ ያለው ከእርሱ ጋር ይውሰድ፣ ከረጢትም ያለው እንዲሁ፣ የሌለውም ልብሱን ሸጦ ሰይፍ ይግዛ፡፡” [ሉቃስ፡ 22፡36]
እነዚህ ምሳሌ ብቻ ናቸው፡፡ እንጂ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ የፈለግኩት አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ ወደ ኢስላም ጣታችሁን ከመቀሰራችሁ በፊት ቀድማችሁ ስሌታችሁን አጢኑት፡፡ በሚገባም መርምሩት፡፡ ህሊናችሁ በቂ መልስ ማግኘቱንም በሚገባ ፈትኑት፡፡ ያለበለዚያ ትርፉ እፍረት ነው የሚሆነው፡፡ “አንድ አይና ባፈር አይጫወትም!!” ለሁሉም ሰላምን እና ኢስላምን እመኛለሁ፡፡