Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

በቢድዓ እና በቢድዓ ሠዎች ላይ ያልበረታን ብዕር አላህ ይስበረው!!!

በቢድዓ እና በቢድዓ ሠዎች ላይ ያልበረታን ብዕር አላህ ይስበረው!!!
የቢድዓና የቢድዓን ሰዎች እንዲሁም አንጃዎችን በተማረውና በተረዳው አቅም መዋጋት የሚፈልግ የሱና ወጣት ላይ “እውቀት ያንስሀል” , .. “ሂክማን አልተጠቀምክም” የሚሉ ና የመሳሰሉ ብጥስጥስ ተራ ትችቶችን በመሰንዘር አፉን እንዲለጉም እና ብእሩን እንዲጥል ጥረት የሚያደርጉ በርካቶች ናቸው _እራሳቸውን ወደ አህለ ሱና ከሚያስጠጉ ግለሰቦች ጀምሮ !
እነዚህ ግለሰቦች ሂክማ እና በመሳሰሉ ሽፋኖች ተኝተው ማስተኛት ተዘናግተወ ማዘናጋት የሚሹ በመሆናቸው ንግግሮቻቸውንና ጽሁፎቻቸውን መጠንቀቅ አማራጭ የሌለው መላ ነው
ሀቁ ግን ፦አንድ ሰው በሚናገረው ጉዳይ ላይ እውቀት ካለው እና ከአህለ ሡና ኡለሞች የተቀሰመን ት/ት እስካስተላለፈ ድረስ ቢድዓንና የቢድዓ አንጃዎችን ማስጠንቀቁ የሚያስመሰግን ስራ መሆኑ ነው።
መቼም በየመንደሩ የሚታዩ ቢድዓዎችንና የቢድዓ ሰዎችን ፈውዛንና መሰል ዑለማዎች እየዞሩ እንዲያስጠነቅቁ የሚጠብቅ የዋህ ያለ አይመስለኝምና ይህንን ክፍተት ጥቂት ወጣቶች ከዑለሞች በተገኘ እውቀት ቢሞሉት ተገቢ መሆኑ አያጠራጥርም።
ጥንቃቄ የሚሻ ነገር ቢኖር ግን ፦ ዑለማዎች ባልተናገሩባቸው ጉዳዮች ገብቶ ያላቅም መዘባረቅ እንዳይመጣ ነው። አላህ ይጠብቀን።
ረሱል ዓለይሂ አሰላቱ ወሰላም ሰሒሕ ሐዲስ ላይ የቢድዓን ሰዎች አደገኝነት እንዲህ ይገልጹታል ፦
“"من أحدث حدثا أو آوى محدثا فعليه لعنة الله والملائكة والناس أجمعين
" አዲስ መጤ ስራን የሰራ ወይንም ሰሪውን የሚያስጠጋ ሠው ላይ የአላህ የመላኢካ የሰዎች አጠቃላይ እርግማን በሱ ላይ ይሁን”
እዚህ ሐዲስ ላይ ቢድዓን መፈጸም ብቻ ሣይሆን የሚፈጽሙ ሠዎችን ማስጠጋት ትልቅ ወንጀል እንደሆነ እንገነዘባለን። ማስጠጋት ሲባል ደግሞ እነሱን መርዳት ፣ ከለላ መስጠትን እና የመሳሰሉ ነገሮችን የሚያጠቃልል ነው።
ሌላ ሙስሊም በዘገቡት ሐዲስ ላይ ነብዩ (ሰላለላሁ ዓለይሂ ወሰለም)የማይፈጽሙትን በሚናገሩና ያልታዘዙትን (ዒባዳ) በሚሰሩ ሰዎች ላይ እንዲህ ይላሉ
"فمن جاهدهم بيده فهو مؤمن ومن جاهدهم بلسانه فهو مؤمن ومن جاهدهم بقلبه فهو مؤمن وليس وراء ذلك من الايمان حبة خردل "
“ እነዚህን ሰዎች በእጅ የታገላቸው ሙእሚን ነው ።በምላሱ የታገላቸው ሙእሚን ነው። በቀልቡ የታገላቸው ሙእሚን ነው።ከዚህ በታች ግን የሰናፍጭ ፍሬ ታክል ኢማን የለም ይላሉ።”
አንድ ሙእሚን በቢድዓ ሠዎች ላይ ሊያረገው የሚገባና የሚችለው የመጨረሻ ዝቅተኛ ነገር በልቡ መጥላት ነው _ በእጅና በምላሱ መታገል የማይችልባቸው ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉና። በልብ የሚጠላ ሠው ደግሞ እነዚህን የቢድዓ ሠዎች ማወደስና ለእነሡ መከላከል የሚከብድ ሆኖ ያገኘዋል።
ታላቁ ታብዕዪ አቡ ኢድሪስ አል ኸውላኒ እንዲህ ይላሉ
“መስጂድ ውስጥ መቀየር የማልችለውን ቢድዓ ከማየት ማጥፋት የማልችለውን እሳት መመልከትን እመርጣለሁ።”
ሌላው ታላቁ ታብዕዪ ሓሰን አል በስሪ እንዲህ ይላሉ
“ከቢድዓ ሰው ጋር አትቀማመጥ፤ ልብህ ይታመማልና”
በሱሓቦች ዘመን ተከስቶ የነበረውን የቀደር ቢድዓ ( ቀደርን ከማስተባበል ጋር የተያያዘ ቢድዓ) በተመለከተ ሱሓቦች የሰጡትን ምላሽ ብንመለከት በወቅታችን ለከባድ ቢድዓዎች እየተሰጠ ያለው ምላሽ ያነሰና ተመጣጣኝ አለመሆኑን እንገነዘባለን።
ዓብደላህ ኢብን ዓባስ የነዚህን ቀደር አስተባባዮች ሁኔታ በሰማ ግዜ “ከፊሎችን አሳዩ ኝ አለ” አድማጮቹም ምን ታደርጋለህ አሉት “እጄን ራሱ ላይ አስቀምጬ አንገቱን እሰብረዋለሁ አለ።”
ገይላን ኢብኒ ሙስሊም የተባለን በዚህ የቀደር በሽታ የተለከፈን ግለሰብ (በ ዑመር ኢብን ዓብዱልዓዚዝ ዘመን ነበር) አውዛዒ እና የመሳሰሉ ታላላቅ ዑለሞች ከጥመቱ እንዲመለስ ያናገሩት ሲሆን በመጨረሻም እንዲገደል ብይን እስከመስጠት ደርሰዋል።
ዛሬ ትልልቅ ለሆኑ ቢድዓዎች (ሺርክና ኩፍርን ላዘሉ ቢድዓዎች) እየተሰጠ ያለው ምላሽ ተመጣጣኝ አለመሆኑ የሰለፎቻችን ታሪክ ግልጽ ማስረጃ ነው። ፅሁፉን ለማሳጠር ያህል እንጂ በርካታ ማስረጃዎችን ማምጣት ይቻል ነበር።
አላህ ቀጥተኛውን መንገድ ይምራን።
በ ሙሃመድ ሲራጅ አቡ ኢምራን (ሀፊዘሁላህ)

Post a Comment

0 Comments