Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ታላቁ የዐሹራ ቀንን የሚመለከቱ ጥቂት ወሳኝ ነጥቦች

ታላቁ የዐሹራ ቀንን የሚመለከቱ ጥቂት ወሳኝ ነጥቦች
ያለንበት ወር የሙሐረም ወር ነው፡፡ ሙሐረም በሂጅራው አቆጣጠር የአመቱ መጀመሪያ ወር ነው፡፡ እናም 1435 አመተ ሂጅራን ጨርሰን ይሄው 1436 ላይ ገብተናል፡፡ እንደሚታወቀው በዲናችን የዘመን መለወጫ በአል የለም፡፡ የነብዩን ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከመካ ወደ መዲና ስደት ምክኒያት በማድረግም የምናከብረው ቀን የለም፡፡ ቢኖር ኖሮ እነዚያ ድንቅ ሶሓቦች ባከበሩት ነበር፡፡ ማክበሩ ኸይር ቢሆን ኖሮ ሶሐቦች ይቀድሙን ነበር፡፡ ስለሆነም ሶሐቦች የማያውቁት ዒባዳ ከንቱ ነው፣ የከንቱ ከንቱ፡፡
ይልቅ በዚህ ወር - ሙሐረም- ውስጥ የሚገኘውን የዐሹራን ቀን የሚመለከቱ ኢስላማዊ ስርኣቶች አሉና ጥቂት እንተዋወስ
1. በመጀመሪያ ወሩ ታላቅና የተከበረ ወር ነው ነው፡፡ አትተውባህ፡ 36 ነብዩም ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡ “አንድ አመት 12 ወር ነው፡፡ ከነዚህ ውስጥ አራቱ የተከበሩ ናቸው፡፡ (ከተከበሩት ውስጥ) ሶስቱ ተከታታይ ናቸው፡፡ ዙልቂዕዳህ፣ ዙልሒጃህ፣ ሙሐረም እና በጁማዳ እና በሸዕባን መካከል ያለው የሙደር ረጀብ ነው፡፡) (ቡኻሪ፡ 2958)
2. ሙሐረም ወርን መፆም እጅግ የላቀ ምግባር ነው፡፡ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላሉ፡ “ከረመዳን ቀጥሎ ከሁሉም በላጩ ፆም የአላህ ወር የሆነው ሙሐረም ነው፡፡” (ሙስሊም፡ 1163) ልብ በሉ! ሁሉም ወሮች የአላህ ሆነው ሳለ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሙሐረምን “የአላህ ወር” ሲሉ መጥራታቸው ያለውን ልዩ ደረጃ ያመላክታል፡፡ ልክ ሁሉም መስጂዶች የአላህ ቤቶች ሆነው ሳለ ከዕባ ለየት ባለ መልኩ “የአላህ ቤት” እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ የተፈለገው ያለውን ላቅ ያለ ደረጃ ማመላከት ነው፡፡ ይስተዋል! ሙሐረምን ወሩን ሙሉ መፆም አይገባም፡፡ ምክኒያቱም እናታችን ዓኢሻህ ረዲየላሁ ዐንሃ እንዳስተላለፈችው ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከረመዳን ውጭ ሙሉውን የፆሙት ወር የለምና፡፡ (ቡኻሪና ሙስሊም)
3. በዚህ ወር ውስጥ ታላቅ ቀን አለ፡፡ እሱም ሙሐረም 10 ነው፡፡ “ዐሹራእ” በመባል ይታወቃል፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከመካ ወደ መዲና ሲገቡ የሁዶች ዐሹራን ይፆሙ ነበርና “ምንድን ነው ይሄ የምትፆሙት ቀን?” ሲሉ ጠየቋቸው፡፡ እነሱም “ይሄ አላህ ሙሳንና ህዝቦቹን አትርፎ ፊርዐውንና ህዝቦቹን ያሰመጠበት ታላቅ ቀን ነው፡፡ ሙሳን አላህን ለማመስገን ሲሉ ፆመውታል፡፡ እናም እኛም እንፆመዋለን” አሉ፡፡ ነብያችን ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ይህን ጊዜ “ከናንተ ይልቅ እኛ ለሙሳ የተገባን ነን” በማለት ፆሙት፡፡ እንዲፆምም አዘዙ፡፡ (ቡኻሪ፡ 2004፣ ሙስሊም፡ 1130)
4. ይህን ቀን፣ ማለትም ሙሐረም አስርን መፆም እጅግ የላቀ ዋጋ አለው፡፡ ያለፈውን አንድ አመት ወንጀል እንደሚያሚያሳብስ ነብያችን ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ተናግረዋል፡፡ (ሙስሊም)
5. ይህን ቀን (ሙሐረም አስርን) ለመፆም ከወሰንን ዘጠነኛውንም ልንፆም ይገባል፡፡ ምክኒያቱም ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ስላሉ፡- “ለቀጣይ (አመት) ከቆየሁ በርግጥም ዘጠነኛውንም እፆማለሁ” (ሙስሊም፡ 1134)
6. ዘጠነኛው የሚፆምበት ምክኒያት ምንድን ነው? የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ዐሹራን ሲፆሙና እንዲፆም ሲያዙ ጊዜ “ይሄ እኮ የሁዶችና ክርስቲያኖች የሚያከብሩት ቀን ነው” አሉ (ሶሐቦች)፡፡ መልእክተኛውም ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ቀጣይ አመት ከደረስን ኢን ሻአላህ ዘጠነኛውን ቀን እንፆማለን” አሉ፡፡ ነገር ግን ቀጣዩ አመት ሳይደርሱ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሞቱ፡፡ (ሙስሊም፡ 1134) ከዚህ በመነሳት ከየሁዶች ጋር ላለመመሳሰል ዓሹራን አንድ ቀን አስቀድሞ መፆሙ መልካም ነው፡፡ አስራ አንደኛውን በተመለከተ ከኢብኑ ዐባስ የተገኘ ትውፊት ቢኖርም ይህን የሚመላክተው ሐዲሥ ግን ደካማ ነው፡፡ (ዶዒፉልጃሚዕ፡ 3506)
7. በነገራችን ላይ ዐሹራን የመካ ሙሽሪኮችም ይፆሙት ነበር፡፡ ነብያችንም ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ገና ወደ መዲና ሳይሰደዱ በፊት መካ እያሉ ይፆሙት ነበር፡፡ የረመዳን ፆም ከመደንገጉ በፊት ዐሹራን መፆም በሙስሊሞች ላይ ግዴታ ነበር፡፡ እነኚህን እውነታዎች የሚያመላክተው ውዷ እናታችን ዓኢሻህ ረዲየላሁ ዐንሃ እንዲህ ስትል የተናገረችው ነው፡- “ዓሹራእ ቁረይሾች በዘመነ ጃሂሊያህ (በጨለማው ዘመን) ይፆሙት የነበረ ቀን ነው፡፡ ነብዩም ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ይፆሙት ነበር፡፡ መዲና በመጡ ጊዜ እሳቸውም ፆሙት ሰዎችም እንዲፆሙት አዘዙ፡፡ የወርሃ ረመዳን ግዴታ በወረደ ጊዜ ግን ረመዳንን ሆነ (በግዴታነት) የሚፆሙት፡፡ ዓሹራን እንዲፆም (ማዘዙን) ተውት፡፡ እናም የፈለገ ይፆመዋል የፈለገ ደግሞ ይቶወዋል፡፡ (ቡኻሪና ሙስሊም)
8. ማስጠንቀቂያ! ዓሹራን እለቱን መፆም እንጂ በምንም መልኩ በአል አድርጎ ማክበር አይፈቀድም፡፡ አቡ ሙሳ ረዲየላሁ ዐንሁ እንዳስተላለፉት ዓሹራን የሁዶች ይፆሙት ነበር፡፡ እንደ ዒድ ይቆጥሩት ነበር፡፡ ሴቶቻቸውንም ጌጦቻቸውንና ጥሩ ጥሩ ልብሶቻቸውን ያለብሷቸውም ነበር፡፡ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ግን “እናንተ ፁሙት” በማለት መፆም እንጂ እንደዒድ እንዳይታሰብ ጥቆማ ሰጥተዋል፡፡ (ቡኻሪና ሙስሊም)
9. ማስታወሻ! ዘንድሮ ዓሹራ የሚውለው የዛሬ ሳምንት ሰኞ ነው፡፡
ሼር በማድረግ ለሌሎች ያሰራጩ፡፡