Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

መቼ ነው ሰው የሚጨቃጨቀው፣ የሚደብረው???

መቼ ነው ሰው የሚጨቃጨቀው፣ የሚደብረው???
የመካ ሙሽሪኮች የሚያምኑበት የነበረውን የአላህን ጌትነት (ፈጣሪነት፣ ተንከባካቢነት፣ ህያው አድራጊነት፣ ገዳይነት እና በጠቅላላ የአላህን ተግባራት) አንድ ሰው ቢያስተምር ለምሳሌ
*) የሚያበላን፣ የሚያጠጣን፣ እጅ የሰጠን፣ እንዲህ የሰጠን አላህ ነው ቢል ሁሉም ዝም ይለዋል። "ማንንም ያላስከፋ የሂክማ (የጥበብ) ዳእዋ አድራጊ" ነው ይሉለታል።
በተገላቢጦሹ ነብያት ሁሉ የለፉለትን፣ እኛ የተፈጠርንለትን፣ መለኮታዊ መፀሀፍት የወረዱለትን፣ ጀነት እና ጀሃነም የተዘጋጀለትን ተውሂደል ኡሉህያ (የአላህ ብቸኛ ተመላኪነትን፣ ባሪያዎች ለአላህ ብቻ የሚፈፅሙት) ቢያስተምር ለምሳሌ እንዲህም ሲል
"አላህን ብቻ አምልኩ ከእርሱ ውጭ ያሉትን (ጂብሪልን፣ ኢሳን፣ ኡዘይርን፣ መርየምን፣ ነብዩ ሙሃመድ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለምን፣ አልይን፣ ሁሴንን፣ ፋጢማን፣ በደዊን፣ አብድልቃድር ጀይላኔን፣ ኑርሁሴንን፣ ቃጥባሬን፣ አብሬትን፣ አልከሲየን፣ አሊ ጎንደርን፣ የዳንግላውን፣ ደግዮን፣ ጆኖችን ••••••)በጠቅላላ ራቁ" ሲል ጭቅጭቁ ይነሳል። አብዛኞች መንገድ ስተው ሽርኩን አንለቅም (ደጋጎችን ሷሊሆች ወደ አላህ ያቃርቡናል) ብለው ጥሩ ስም ሰጥተው ለጥፋታቸው እራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን ወደ እሳት ሲመሩ፣ አላህ ያዘነላቸው ጥቂቶች ውግዘት፣ ትችት፣ እና ሌላም ቢደርስባቸው አላህን በብቸኝነት አምልከው ሌሎችንም አላህን በብቸኝነት እንዲያመልኩ ይጠራሉ።
አስገራሚው ግን እውነት ውሸት፣ ውሸት እውነት ተደርጎ እያየን ስለ ሆነ እንዲህ ሲሉም ይሰማሉ
ሽርካቸውን እና አማልክቶቻቸውን ጥሩ ስም ሰጥተውት "ወደ አላህ ያቃርቡናል፣ ወደ አላህ ያማልዱናል"
በተገላቢጦሹ ወደ ተውሂድ የሚጣሩትን ደግሞ እንዲህ ሲሉ ይወርፋሉ "ሰለዋት የማይወዱ እና የሚከለክሉ፣ ዱኣ የሚከለክሉ፣ ነብዩን የማይወዱ፣ ኡማውን የሚበታትኑ፣ የኡማው ጉዳይ የማያስጨንቃቸው እና ሌሎችንም"
ጥራቻ ለአላህ ይገባው ፍርድ ሰጪው የባርያዎቹን ሂሳብ ከፋዩ እሱ ፍትሃዊው ስለ ሆነ በትግስት ሀቅ ላይ መፅናት ነው። አላህ ከሚፀኑት ያድርገን።
ሱናም ላይ ሲመጣ እንደዛው ነው። መስጂድ በቀኝ እግር ነው የሚገባው ብሎ አንድ ሰው ዳእዋ ቢያደርግ የሚቃወመው የለም። ነገር ግን በኢስላም የማንንም ይሁን የማን ልደት ማክበር የለም (መውሊድ ቢድአ ነው) ብትል፣ ከሰላት በኀላ ዚክር እንጂ ኢማሙ ወደ ህዝብ ዞሮ ህዝቡም ዚክሩን ትቶ ዱኣ መቀበል የለም ይሄ ቢድአ ነው፣ ሻእባን እና ሌላም የሚባል ሱና የለም ቢድአ እንጂ ብሎ ቢያስተመር ሌሎች የተለያየ ስም ይሰጡታል ከነዚህ ውስጥ አስገራሚው የሚከተለው ነው
"አንድነት በታታኝ" ጥራቻ ለአላህ ይገባው አንድነትን በተውሂድ እና ሱና ላደረገ። ደግሞ ከመቼ ጀምሮ ነው ኡማው በሽርክ እና ቢድአ አንድ እንዲሆን ኢስላም ያስተማረው???
ብቻ ለማጠቃለል ሀቁ ተፍረጥርጦ ሲወጣ የሚቆጡ የድሮዎቹ "ሙሃመድ አማልክቶቻችን ሰደበ" እንዳሉት የዛሬዎቹም "መሻኢኾችን የሚሳደቡ መጡ፣ ደረቆች መጡ" ማለታቸው የማይቀር ነው። የትላንቶቹ "የአባቶቻችንን መንገድ ነው የምንከተለው" እንዳሉት ሁሉ የዛሬዎቹም ሱናን ስታስተምራቸው ላለመቀበል "የአባቶቻችን መንገድ" ማለታቸው አይቀርም። ስለዚህ የአላህ ባርያ ሆይ! የዳእዋ ተቀባይነት መለኪያው ቲፎዞ መብዛት፣ የሰዎች አንተን አለመቃወማቸው አይደለም። ምክንያቱም ነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለምም) ሀቁን ስለተናገሩ ብዙ ተቃዋሚ ነበራቸው፣ ነብየላህ ኑህን (አለይሂ ሰላም) ይመስል 950 ህዝቦቹን ወደ አላህ ተጣርቶ ያመነለት በጣም ጥቂቶች ነበሩ። ነብያቱ አድርሱ የተባሉትን ማድረስ ብቻ ነው ድርሻቸው።
ማጠቃለያ ነፍሴንም እናንተንም መምከር የምፈልገው ሰዎች ስለተቃወሙ እና ቲፎዞዋቸው ስለበዛ ተብሎ ሃቅ ከመነገር ወደ ኃላ አይባልም። ባጢል ባጢል ነው የትም አይደርስም።
አላህ በነብያት መንገድ ላይ ከሚፀኑት ያድርገን። የአላህ ሰላት እና ሰላም በነብያት መደምደሚያ፣ በቤተሰቦቻቸው፣ በባልደረቦቻቸው ሀቅን በተከተለ ላይ ሁሉ ይሁን።