Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

አደም ይቺን ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የረገጠ ጊዜ

 አቡ ዓኢሻ

አደም ይቺን ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የረገጠ ጊዜ
ϟ ሽርክ (በአላህ ላይ ማጋራት)
ϟ ስላሴም (አላህ አንድም ሶስትም ነው ማለት )
ϟ ወህደተል ውጁድ (አላህ ዩኒቨርስ ነው ማለት) አልነበረም ።

✔ ለአስርት ምዕተ ዓመታት አላህ በብቸኝነት ተመለክ ። የሚመጣውንም ትውልድ ሸይጧን በጊዜው የነበሩ አምስት ፃድቅ ሰዎች ላይ ከሚገባው በላይ ድንበር እንዲያልፉ ገፋፍቷቸው ተውሒድን መፃረር መጣ ።
✔ አላህም መልዕክተኛው ኑህን ዐለይሂ ሰላምን ሰዎች በብቸኝነት አላህን እንዲያመልኩ ጥሪ ያደርጉ ዘንድ ላከ ። ከ950 አመት አድካሚ የተውሒድ ጥሪ በኋላ 80 የሚሆኑ ሰዎች ተውሒድን ተቀበለው አምልኳቸውን ሁሉ ወደ አላህ አዞሩ ።
✔ የሚቀጥለውንም ትውልድ ሸይጧን እንደልማዱ ታላላቅ ፃድቅ ሰዎችን ወደ አላህ ያቃርባቿል በማለት በድጋሚ አታለላቸው ። ሰዎችም የነዚህን ሰዎች ምስል በጣዖት በመስራት ያመልኳቸው ጀመር ።
✔ አላህም ኢብራሒም ዐለይሂ ሰላምን ልኮ እነዚህን ጣዖቶች በእጃቸው እንዲሰባብሩት አደረገ። ሰዎችም አላህን በብቸኝነት መገዛት ጀመሩ ። ኢብራሒም ዐለይሂ ሰላምም ወደ እሳት ተወረወሩ ሌሎችም ከባባድ ፈተናዎች ደርሰባቸው ። አላህም የነቢያትና የሩሱሎች አባት እንዲሆኑ አደረጋቸው።
✔ አሁንም ሸይጧን ተተኪውን ትውልድ ነቢያቶችን ፣ ፃድቃኖችን ፣ ደጋግ ሰዎችን ወደ አላህ እንዲያቃርቧቸው በሚል በአላህ ላይ እንዲያጋሯቸው በድጋሚ አታለላቸው ። ውሎ አድሮም ሰዎች ከዚያ በኋላ የተተኩትን ነቢያቶችና ደጋግ ሰዎች (ሙሳ ፣ ዒሳ ፣ መርየም..) ማምለኩን ገፍፉበት ። አምልኳቸውንም የሚያካሂዱት የመቃብር ስፍራዎች ላይ ነበር ።
✔ አላህ ሱብሃነሁ ወተዐላ ነቢዩ ሙሃመድ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለምን ልኮ የዐለም ሕዝብ ካለበት የሽርክ ፅልመት እንዲወጣና ተውሒድ እንዲነግስ አደረገ ። (ምስጋናና ጥራት ለሃያሉ ጌታችን ይገባው) ። በመጨረሻም ነቢዩ ሙሃመድና ባልደረቦቻቸው የሽርክ ሰዎችን ድል አድርገው መካን ተቆጣጠሩ ። የነበሩትንም ጣዖታት ሰባብረው የተከበረውን የአላህ ቤት ከዕባን አፀዱት ። ሕዝቡም ለአምልኮ ፊቱን ወደ አላህ አዞረ ።
ሽርክ በጣም ክፉና ከባድ በደል ነው ። መንስዔዎቹም:-
✔ መላዒካዎች ፣ መልዕክተኞች ፣ ነቢያቶች ፣ ፃድቃኖችና የአላህ ደጋግ ባሮች ላይ ከሚገባው ወሰን በላይ ማስቀመጥ ። (በመውደድ ፣ በመተማመን ፣ ልብን ወደነሱ በማንጠልጠል)
ሸይጧን ወደ ሕዝቡ ይዞ የሚመጣው ጣፋጭ የሆነ መርዝን ነው ። እሱም ፍጡርን ከፍ ከፍ ማድረግና ማክበር በሚል ሰበብ ሲሆን ከዚያም ቀስ በቀስ ወደ አላህ ያቃርቡናል ተብለው እንዲያዙ መንገዱን ይጠርጋል።
✔ ብዙውን ጊዜ ሸይጧን ሰዎች አላህ ላይ ላይ እንዲያጋሩ የሚጠቀማቸው ቀብሮችን ፣ ጣዖቶችን (ቅርፃ ቅርፅ ፣ ምስል(ፎቶ) ) ደጋግ ሰዎች የኖሩባቸውን ቦታዎች ፣ ይጠቀሙባቸው የነበሩ መገልገያዎች እና የመሳሰሉትን ሲሆን ወደዚህም የሰዎችን ድምፅ (ወደ ጥመት የሚጣሩ የሸር ተጣሪዎን) በመጠቀም ነው ።
✔ ተውሒደል ዑሉሂያ (የአላህ ብቸኛ ተመላኪነት) የኢስላም ዋነኛ መሰረት ነው ።የሁሉም ነቢያትም ጥሪ እና የተጎሳቆሉለት የተገደሉበትም አላማ ነው ። ተውሒደል ሩቡቢያ (የአላህ አንድነት) አንዱ የተውሒድ ክፍልም ነው። ነገር ግን እሱን ብቻ ማመን ለሙስሊምነት በቂ አይደለም ። በፊትም የነበሩት አጋሪዎች አሁንም ያሉት በዚህ (አላህ አንድ ብቻ መሆኑን) ያምናሉ ።
✔ አንድ ወደ ኢስላም የሚጣራ ተጣሪ የተውሒድን ርዕስ ሳያነሳ ማስተማር ብቻውን አይበቃለትም ። ወደ ኢስላም የሚጣራ ሰው ወደ አላህ ነው የሚጣራው! ወደ አላህ የሚጣራ ሰው ወደ አላህ ብቸኛ ተመላኪነት ነው የሚጣራው! ወደ አላህ ብቸኛ ተመላኪነት የሚጣራ ሰው ወደ ጀነት ነው የሚጣራው! ።
አላህ ከሽርክ ይጠብቀን ወደተውሒድ ከሚጣሩትም ያድርገን
አሚን አላሁመ አሚን

Post a Comment

0 Comments