Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

“ውርደትና ክብረ ቢስነት ትእዛዜን በጣሰ ላይ ሆኗል” ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም

ibnu-munewor 


ሰሞኑን ቡድናዊ አመለካከቶቻቸውን ስላልተጋሯቸው ብቻ ታላላቅ ዐሊሞችን ለጆሮ በሚሰቀጥጡ፣ ለመስማት በሚዘገንኑ ዘለፋዎች የሚያንቋሽሹ ፖስቶች ተበራክተዋል፡፡ ከተነሱት ውንጀላዎች ጥቂቶቹን እየመዘዝኩ በማስረጃ ለመመለስ እሞክራለሁ፡፡ አንባቢ ሚዛናዊ እንዲሆን በአላህ ስም እጠይቃለሁ፡፡
  1. ((ዑለማዎች ኢኽዋኖች ላይ የሚሰነዝሩት ትችት ከሴፕቴምበሩ የ2001 የኒዮርክ መንትያ ህንፃዎች ጥቃት በኋላ የተጀመረ የአሜሪካ ተፅእኖ ውጤት ነው)) ይላሉ፡፡
መልስ፡- ይሄ ውንጀላ ከንቱ ውሸት እንደሆነ ለማረጋገጥ ኢኽዋንን የተቹት ታላላቅ ዐሊሞች የሞቱት ከዚህ ክስተት በፊት መሆኑ ነው፡፡ ሸይኽ ዐብዱላህ አድዱወይሽ የሰይድ ቁጥብን የዐቂዳ ብክለቶች ብቻ የሚያጋልጥ አንድ ኪታብ ፅፈዋል፡፡ ኢኽዋንን ኢትዮጵያዊው ታላቅ ዐሊም ሙሐመድ አማን አልጃሚና ሸይኽ ሙቅቢል በሰፊው አጋልጠውታል፤ ኢብኑ ባዝ ከ72ቱ ጠማማ አንጃዎች ቆጥረውታል፤ አልባኒ ፀረ ሱና እንጂ አህሉ ሱና እንዳልሆነ እንዳውም በኢስላም ላይ የጋረጠው አደጋ ከአይሁድና ከነሳራ አደጋ በላይ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ እነኚህ ሁሉም የሞቱት ከኒዮርኩ ጥቃት በፊት ነው፡፡ አሕመድ ሻኪርና ሸይኽ ሙሐመድ ሃሚድ አልፈቂም እንዲሁ ኢኽዋንን ተችተዋል፡፡ ሁለቱም የሞቱት ከኒዮርኩ ጥቃት ከ40 አመታት በፊት ነው፡፡ የቁጥብን የዐቂዳ ብክለቶች በሰፊው ያጋለጡት ሸይኽ ረቢዕም ብዙዎቹን መልሶቻቸውን የፃፉት ከኒዮርኩ ክስተት ቀድሞ ነው፡፡ የታተሙበትን ጊዜ ማየት ይቻላል፡፡ እንዳውም አንዱን ተቅዲም ያደረጉት ሸይኹልአልባኒ በናቸው፡፡
ለነገሩ ይሄ መልስ የሚሰጥባቸው ኢኽዋኒዎች ዘንድ እነ አልባኒ፣ ኢብኑ ባዝ፣ ፈውዛን፣ ሙቅቢል፣ አሕመድ ሻኪር… ዑለማዎች አይደሉም!! ምክኒያቱም የኢኽዋንን ሴራ የሚያጋልጡ ዑለማዎች እንደ ዑለማ አይቆጠሩምና፡፡ ታዲያ “ዑለማ ተብዬዎቹ መናኛ ምክንያት እየፈለጉ “ኢኽዋን ኢኽዋን ይላሉ” ማለት ምን ማለት ነው? ተመልከቱ ኢኽዋንን በመተቸቱ ብቻ አንድ አሊም በቀላሉ ከዑለማ ተርታ ይሰረዛል፡፡ ስሜት የት እንዳደረሳቸው አያችሁ? ኢማሙ ሻፊዒ ረሒመሁላህ፡- “ከሺርክ ውጭ በስሜት እንደተፈተነ ሰው በከባድ ወንጀል የተፈተነ የለም!!” ይላሉ፡፡ ነብዩም ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ከህዝቦቼ ውስጥ ልክ የእብድ ውሻ በሽታ የያዘው ሰው የደም ቧንቧውም መገጣጠሚያውም ሳይቀር ሰርፆት እንደሚቅበዘበዘው ስሜቶች የሚያቅበዘብዟቸው ሰዎች ይመጣሉ” ይላሉ፡፡ እንጂማ በመናኛ ምክኒያት በዐሊሞች ክብር እየተረማመደ ያለው ማን ነበር? በተጨባጭ ጥፋት ኢኽዋንን የሚተቹት ምክኒያታቸው “መናኛ” የተባለው ጥፋቶቹ የኢኽዋን ስለሆኑ ብቻ ነው! እንጂማ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ሰሐቦቼን የተሳደበ የአላህ፣ የመላእክትና የሰዎች ሁሉ እርግማን በሱ ላይ ይሁን!” ካሉ በኋላ ሰሐቦችን በኒፋቅ መወንጀል እንዴት “መናኛ ምክኒያት ነው” ይባላል? ደግሞስ ከኒዮርኩ ጥቃት በፊት ሰሐባ መሳደብ ይፈቀድ ነበር እንዴ? “ማን ተሳደበ?” ከተባለ ሰይድ ቁጥብን ይስሙት፡- (የኡስማን ረዲየላሁ ዐንሁ የኺላፋ ዘመን በሶስቱ ኸሊፋዎች ዘመን ውስጥ የገባ ክፍተት እንጂ የእውነት የነገሰው እሱ ሳይሆን መርዋን ነው፤ ዑስማን በስልጣኑ ተከልሎ የሙስሊሙን ገንዘብ ያላግባብ የተጠቀመ፣ ለዘመዶቹ እያዳላ የነብዩን ወዳጆች ያራቀ፣ ኸሊፋ ሊሆን በማይገባው እድሜ ስልጣን ይዞ የመርዋን መጫወቻ የሆነ፣ አገዛዙ ከኢስላም ሩህ የራቀ ነበር፣ ከኡስማን ይልቅ የኡስማን ገዳዮች ለኢስላማዊ ሩሕ የቀረቡ ነበሩ፣ ኡስማን ላይ በተነሳው ፊትና የአቡ ዘር እጅ አለበት ይላል፡፡ (አልዐዳለቱልኢጅቲማዒያህ፡ 160-186) አስተውሉ! ነብዩ ዐለይሂሰላም የዑስማንን ገዳዮች ሙናፊቆች እንደሆኑ ቀድመው ተናግረዋል፡፡ "የአቡ ሱፍያንን እስልምና “የከንፈርና የምላስ እስልምና እንጂ የልብ ኢማንና እውነቱን የማግኘት አይደለም፡፡ ኢስላም ወደዚህ ሰውየ ልብ አልሰረፀም፣ ከሰለመ በኋላም የሙስሊሞችን ሽንፈት ሲመኝ የነበረ ነው!!” ይላል፡፡ አዑዙ ቢላህ! ተመልከቱ ነብዩ ዐለይሂሰላም ሙናፊቅ እንደነበር ሳይደርሱበት ሰይድ ቁጥብ ደረሰበት፡፡ እውነት ቁጥብን በዚህ መልኩ ብንገልፀው ኢኽዋኖች ምን ይላሉ? ለመሆኑ ከሰሐቦቹና ከሱ ማነው የሚበልጠው? ይህም ሳይበቃው “በኑ ኡመያ በጥቅሉ ኢማን ከልባቸው አልሰረፀም፡፡ ኢስላም ለነሱ እንደ ጥቅማቸው ሲያሻቸው የሚለብሱት ሲፈልጉ የሚያወልቁት ካፖርት ማለት ነው፣ ስነ ምግባር፣ ዲን፣ ልቦና የማይገታቸው ሰዎች ናቸው…” ይላል፡፡ (አልዐዳላህ ፡172) ይህን ቆሻሻ አገላለፅ፣ ይህን ዐይን ያወጣ ጅምላ ፍረጃ አያችሁ? ነገር ግን እነዚህ ቁጥብ በጅምላ በኒፋቅ የወነጀላቸው በኑ ኡመያ ውስጥ በጀነት የተመሰከረለት ኸሊፋው ዑስማን፣ የነብዩ ዐለይሂሰላም ባለቤት ኡሙ ሐቢባህ፣ ዐምር ኢብኑል አስ፣ ዐብዱላህ ኢብኑ ዐምር ኢብኑል አስ፣ አቡ ሱፍያን፣… አሉበት፡፡ ነገ የውመልቂያማ በክፉ ላነሳቸው ሰይድ ቁጥብ በመወገኑ እነዚህ ታላላቆች ሞጋቾቹ የሆነ ሰው ወዮለት!! ሊባኖስን፣ ሰሜን አፍሪቃን፣ ቆጵሮስን፣ ጆርጂያን፣ አርሜኒያን፣ እስፔንን፣ አዘርባጃንን፣ … የከፈቱ እነዚህ ናቸው፡፡ እስኪ ኢኽዋን ከቢድዐና መከፋፈል ውጭ ለኢስላም ምን አተረፈ?
አንዳንዶች “ሰይድ ቁጥብ ከዚህ ጥፋቱ ተመልሶስ ቢሆን” ይላሉ፡፡ ቢሆን ደስ ይለን ነበር፡፡ ግን በዘመኑ ታላቁ ሸይኽ መሕሙድ ሻኪር ሰሐቦችን እየወረፈ ለፃፈበት እርማት ቢሰጡት፣ እንኳን ምክር ሊቀበል እንዴት እንደመለሰላቸው ተመልከቱ፡- “እኔ የስሜቴን ልጓም የምቆጣጠር ነኝ፡፡ ትኩረት ልቸረው በምሞክረው ሐቅ ላይም የተረጋጋሁ ነኝ፡፡ ... ለጓደኛችን ሻኪር አላህ እንዲፈውሰውና እንዲያሽረው፣ ከሚያሰቃየው ህመሙ እንዲገላግለው ከመፀለይ ውጭ ምንም ላደርግ አልችልም፡፡  አላህ ለመናጢ ባሮቹ አዛኝ ነውና!!” እዩ ይሄን አደብ?! ለነገሩ ይሄ ሰሐቦችን በኒፋቅ ከወነጀለበት አይከፋም!
ሰውየው ሰሐባው ሙዐውያን ደጋግሞ በሚሰቀጥጡ ቃላት ወርፎታል፡፡ ነብዩ (ዐለይሂሰላም) ግን፡ ((ጌታዬ ሆይ (ሙዓውያን) ቅንና የሚያቀና አድርገው)) ማለታቸው ተዘግቧል፡፡ ሙጃሂድ፡- “ሙዓውያን ብታዩ መህዲ ይሄ ነው ትሉ ነበር!” ይላሉ፡፡ ኢብኑ ሙባረክ ከሙዓውያ እና ከዑመር ኢብኑ ዐብዱልዐዚዝ ማን እንደሚበልጥ ቢጠየቁ “ወላሂ ሙዓውያ ከነብዩ ጋር ሆኖ ባፍንጫው የገባው አቧራ ከዑመር ሺህ ጊዜ ይበልጣል” ብለው ነው የመለሱት፡፡ ሌላም ጊዜ “ሙዓውያ እኛ ዘንድ ፈተና ነው፡፡ እሱን በመጥፎ ሲመለከት ያየነውን በሶሐቦች ጉዳይ አናምነውም”  ብለዋል፡፡ ኢማሙ አሕመድ “ከሙዓውያና ከዑመር ኢብኑ ዐብዱልዐዚዝ ማን ይበልጣል?” ሲባሉ፣ “ሙዓውያ ነው የሚበልጠው፡፡ የነብዩን ሶሐቦች ከማንም ጋር አናወዳድርም” ብለዋል፡፡ አንድ ሰው ኢማሙ አሕመድን “አንድ ሙዓውያን የሚያንቋሽሽ አጎት አለኝ” ቢላቸው “ከሱ ጋር አብረህ እንዳትበላ!” ብለውታል፡፡
ሰሐባ የሚሳደብን ሰው በተመለከተ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “የአላህ፣ የመላእክትና የሰዎች ሁሉ እርግማን በሱ ላይ ይሁን” ብለዋል፡፡ ኢማሙ ማሊክ፡- የአላህ መልእክተኛን ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሰሐቦች የሚሳደብ በኢስላም ውስጥ ምንም ድርሻ የለውም  ብለዋል፡፡ ኢማሙ አሕመድ፡“አንድ ሰው የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሰሐቦችን በክፉ ሲያነሳ ካየህ ሙስሊምነቱን ተጠራጠረው” ብለዋል፡፡ አቡ ዙርዐህ፡-አንድ ሰው ከአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሰሐቦች የየትኛውንም ክብር ሲያጎድፍ ካየኸው እወቅ እሱ አፈንጋጭ ነው” ብለዋል፡፡
ይሄ ሁሉ ግን ለኢኽዋኖቹ መናኛ ነገር ነው፡፡ እሱ ሰሐባን መሳደቡ ተራ ነገር ሲሆን ሌሎች ኢኽዋንን ሲያጋልጡ ግን ለመንግስት መስራት ነው፣ አንድነትን መናድ ነው፣ የኒዮርኩን አደጋ ተከትሎ ከአሜሪካ የመጣ ትእዛዝ ነው፡፡ ኡማውን በጅምላ ማክፈር፣ ቁርኣንን በሙዚቃዊ ቃና መግለፅ፣ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ስለደጃል የተናገሩትን ማስተባበል፣ በኩፍር ላይ የሞተን ጳጳስ “አላህ ይማረው” ማለት፣ ለሙዚቃ ሽንጥን ገትሮ መሟገት፣ ሌሎችም ፀጉር የሚያቆሙ የኢኽዋን ጥፋቶች ተራ ነገሮች ናቸው፡፡ እውነት እነኚህ ለዲን ነው የሚሟገቱት?

2. የሱና ዑለማዎች ኢኽዋንን የሚተቹበት ሌላኛው ምክኒያት “የሳዑዲ ንጉሣዊያን ቤተሰቦችን ስልጣን ለመጠበቅ ነው” አሉ፡፡
መልስ፡- ይሄ ውንጀላ የኢኽዋን ዐላማ ስልጣን እንደሆነ በግልፅ ያሳያል፡፡ እሺ የሳዑዲ ዐሊሞች ኢኽዋንን የሚተቹት ወደ ቤተመንግስት እንዳይቀርብ ነው እንበል፤ በሌላው አለም ያሉትስ ምን ፈልገው ነው? አሕመድ ሻኪር ኢኽዋን ላይ “የሸይኽ ሀሰነልበና እና የሙስሊም ወንድማማቾቹ ንቅናቄ የኢስላማዊ ደዕዋን ወደ አፍራሽ የጥፋት ደዕዋ የገለበጡ ናቸው፡፡ ኮሙኒስቶች እና አይሁዳውያን እንደሚረዱት በተጨባጭ እናውቃለን”  በማለት የሰላ ትችት ሰንዝረዋል፡፡ (ሹኡኑትተዕሊም ወልቀዳእ፡ 48) ታላቁ የዘመናችን ሙሐዲሥ አልባኒም “ኢኽዋነልሙስሊሚን ከአህሉሱና ናቸው ማለት ትክክል አይደለም፡፡ ምክኒያቱም ሱናን ይዋጋሉና” ብለዋል፡፡ ሙሐዲሥ ሸይኽ ሙቅቢልም “ሐሰን አልበና እና ሰይድ ቁጥብ ወደ አላህ በሚደረገው ጥሪ ላይ ኢማሞች (መሪዎች) ናቸው የሚል አለ” ተብለው ሲጠየቁ “አዎ ኢማሞች ናቸው ነገር ግን ኢማምነታቸው ለቢድዐ ባለቤቶች ነው…” ብለው ነው የመለሱት፡፡ ሸይኽ ሙሐመድ ኢብኑ ዐብዱረሕማን አልበና “በዘመናችን በመሪዎች ላይ የማመፅን ቢድዐ የጀመረው ሐሰን አልበና ነው፡፡ ይህንንም ያደረገው በተቃውሞ ሰልፍና በመፈንቅለ መንግስት መንገድ ነው፡፡ …” ይላሉ፡፡ እነኚህ ሁሉም ሳዑዲያውያን አይደሉም፡፡
አዎ ኢኽዋኖች የሱና ዑለሞችን “ስልጣን ጠባቂ” “የቤተመንግስት ፍርፋሪ ለቃቃሚዎች” የሚሉበት ዋናው ምክኒያት ይታወቃል፡፡ ለሃጫቸው የሚዝረከረክለትን ስልጣን ለማግኘት ሲሉ ስለኢስላም ከማስተማር በበለጠ መሪዎችን ማብጠልጠላቸውን፣ አመፅን መደገፋቸውንና ማነሳሳታቸውን ዑለማዎቹ በፅኑ ይቃወሙታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክኒያቱ ኢስላም በሙስሊም መሪዎች ላይ አምፆ መውጣትን ስለማይፈቅድ እንጂ እንደሚቀጠፍባቸው በመንግስት ተገዝተው አይደለም፡፡ አዎ የፍትህ መጓደል፣ አድሎ፣ ብዝበዛና ግፍ ቢኖር እንኳ በማያሻማ ሁኔታ ከኢስላም እስካልወጡ ድረስ ፊትና በማይፈጥር መልኩ መምከር እንጂ ብጥብጥ መቀስቀስ አይፈቀድም፡፡ በሙስሊም መሪ ላይ ማመፅን የሚከለክሉ ከመቶ በላይ ማስረጃዎች ቢኖሩም የነብዩን ትእዛዝ ለሚያከብሩ አንዱ ይበቃል፡፡ ለናሙና ያክል “አዋጅ! በሱ ላይ መሪ የተሾመበት ሰው፣ መሪው በአላህ ላይ ሲያምፅ ካየው ያየውን ነገር ይጥላ፡፡ ለአሚሩ ያለውን ታዛዥነት ግን እንዳያነሳ፡፡”  “ከኔ በኋላ በመመሪያየ የማይመሩ፣ በሱናየም የማይጓዙ መሪዎች ይመጣሉ፡፡ በነሱም ላይ ልቦቻቸው የሸይጧን አካላቸው ደግሞ የሰው የሆኑ ሰዎች ይነሱባቸዋል” አሉ፡፡ ሁዘይፋ ረዲየላሁ ዐንሁ “እንዲህ አይነት ሁኔታ ላይ ከደረስኩኝ ምን ላድርግ” ሲላቸው “አሚሩን ትሰማለህ፣ ለሱም ትታዘዛለህ- ጀርባህን ቢመታህም ገንዘብህን ቢነጥቅህም እንኳን” አሉት፡፡ (ሙስሊም የዘገቧቸው ናቸው) በኢማሙ አህመድ ጊዜ መሪው “ቁርኣን ፍጡር ነው” የሚለውን ኩፍር በጉልበት ሲያራምድ ምሁራኖች ሊያምፁ አሕመድን ቢያማክሯቸው “ጥፋቱን በልባችሁ ጥሉ፡፡ ለመሪው ያላችሁን ታዛዥነት አታንሱ፡፡ የሙስሊሞችን ህብረት አትክፈሉ፡፡ ደማቸውንም ደማችሁንም አታፍሱ፡፡ መጨረሻችሁን ጠብቁ፡፡ ደጉ እስከሚያርፍ ከክፉው እስከሚታረፍ ታገሱ” ብለው መልሰዋቸዋል፡፡ ኢማም አልበርበሀሪ “አንድ ሰው (ሙስሊም) መሪን ሲራገም ካየኸው የስሜት ተከታይ እንደሆነ እወቅ” ይላሉ፡፡ "በታሪክ በመሪ ላይ ያመፀ አካል ሁሉ ካስተካከለው ጥፋት ይልቅ በአመፁ የደረሰው ጥፋት የከፋ ነው፡፡ ከዚህ የተለየ ማግኘት ከባድ ነው” ይላሉ ኢብኑ ተይሚያህ፡፡ አስተዋይ ለሆነ የቅርቡ የዐረቦች አብዮት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡
እንግዲህ ተመልከቱ እነኚህን ማስረጃዎች አሽቀንጥረው ነው ኢኽዋኖች ሙስሊም መሪዎችን የሚያንቋሽሹት፡፡ ምክኒያቱ ደግሞ አላማቸው ዲን ሳይሆን ስልጣን መሆኑ ነው፡፡ የአመፅ ጥፋታቸው አልበቃ ብሎ “ተው” የሚሏቸውን ዐሊሞች የመንግስት ቅጥረኞች አደረጓቸው፡፡ ደግሞ እኮ እነሱ ስልጣን ይዘው በሸሪዐ ያስተዳደሩበት አንድም ሀገር የለም፡፡ እንዳውም ከሚተቿቸው ሙስሊም መሪዎች ይልቅ የኢኽዋን ሰባኪዎች የባሱ ናቸው፡፡ እውነት አላማቸው ዲን ቢሆን ኖሮ የነብዩን ሐዲሦች ባከበሩ፣ የቀደምት ዑለማዎችን መንገድ በተከተሉ ነበር፡፡
ኢኽዋን በ86 አመት ታሪኩ ዲን ማስተማሩን ጥሎ ወደ ኩርሲ ሲያንጋጥጥ ስልጣን ላይ ሲመጣ ጊዜ ትላንት ሲሳለቅባቸው የነበሩ ሐዲሦችን ኩርሲውን ለማስጠበቅ ቢያስተጋባቸውም አላዋጣውም፡፡ እንዴትስ አይዋረድ? ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ውርደትና ክብረ-ቢስነት ትእዛዜን በጣሰ ላይ ሆኗል!” አላሉም እንዴ? ሰዎቹ ግን አንጃቸው ከኩርሲ ሲፈነገል ጊዜ “ጀርባህን ብትመታም ገንዘብህን ብትነጠቅም ስማ ታዘዝ”  በሚለው የነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሐዲሥ ላይ ዳግም መሳለቅ ይዘዋል፡፡ በሙስሊም መሪዎች ላይ ማመፅ፣ ለአመፅ መቀስቀስ ወይም አመፁን መውደድ ከኸዋሪጅ መገለጫዎች እንደሆነ ወይ አያውቁም ወይም ሲያውቁ ጥመትን መርጠዋል፡፡ እንዳውም አንድ ሰው የአመፁ ቀጥተኛ ተካፋይ ባይሆን እንኳን ደጋፊና ሸላላሚ ከሆነ የኸዋሪጅ ተከታይ ነው፡፡ ይሄ ማንም ሙስሊም ቆም ብሎ እራሱን ሊፈትሽበት የሚገባ አደገኛ ጉዳይ ነው፡፡ ከኸዋሪጅ ቅርንጫፎች ውስጥ በመሪ ላይ መውጣትን እየቀባቡ እንደ ጥሩ የሚያቀርቡ ነገር ግን በራሳቸው የማይሳተፉት “ቀዕድያህ” በመባል ይታወቃሉ፡፡ (አልሃድዩስሳሪ፡ 459) እነዚህን የኸዋሪጅ ንዑስ ክፍሎች ከቀደምት አኢማዎች አንዱ የሆኑት ዐብዱላህ ኢብኑ ሙሐመድ አድደዒፍ “የመጨረሻ ቆሻሻዎቹ የኸዋሪጅ ክፍሎች” ናቸው ብለዋል፡፡ ኢኽዋንዮች ግን ሙስሊም መሪዎች ላይ መቀስቀሱን እንደ ንቃት ነው የሚቆጥሩት፡፡ ወደሚመኟት ኩርሲ እንደሚያደርሳቸው በማለም ሁሌ ዴሞክራሲን ያንቆለጳጵሳሉ፡፡ በኢስላም መነፀር ቢያዩ ኖሮ ዲሞክራሲ ከአምባገነንነት የከፋ እንጂ የተሻለ ስርኣት እንዳልሆነ በገባቸው ነበር፡፡
3. (“እኛ ብቻ ልክ፤ ሌላው ውግዝ ነው፤ የጀሃነም ማገዶ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፤ እኛን የማይመስል ሁሉ ለጀሀነም የተፈጠረ ፊርቃ ነው ይላሉ) በማለት ሰለፍዮችን ወንጅለዋል፡፡
በርግጥ ኢኽዋን ሰፈር ውሸት ብርቅ አይደለም፡፡ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “አራት ነገሮች በውስጡ ያሉበት ጥርት ያለ ሙናፊቅ ሆኗል” ብለው ከነዚህ ውስጥ “ሲያወራ ይዋሻል፤ …ሲሟገት ያምፃል” ይላሉ፡፡ ወላሂ “ከኛ ውጭ ያለው የጀሀነም ማገዶ ነው” የሚል አንድም ሰለፊ የለም! እንዳውም ዘመናዊ የተክፊር አንጃ መሰረቱ ኢኽዋን ነው፡፡ ይህን የሰይድ ቁጥብ ንግግር ተመልከቱ፡- “እሄ የምንኖርበት ማህበረሰብ እራሱ ሙስሊም ማህበረሰብ አይደልም፡፡ ለዚያም ነው ኢስላማዊ ስርኣት ያልዘረጋው…” “በመጨረሻም ከነዚህ የጃሂሊያ ስብስብ ውሰጥ የሚካተቱት እነዚህ ሙስሊም እንደሆኑ የሚሞግቱት ህዝቦች ናቸው፡፡” (ፊ ዚላሊልቁርኣን፡ 3/1816፣ 4/2009-2010) “ጉዳዩ የማመንና የመክፈር ጉዳይ ነው፡፡ ሰዎች እንደሚሞግቱት ሙስሊሞች አይደሉም፣ የሚኖሩት የጃሂሊያ ህይወት ነው፣ ደዐዋችን የተነሳው እነኚህን ጃሂሊዮች ወደ ኢስላም ለመመለስ ነው-እንደ አዲስ ሙስሊም ለማድረግ” (መዓሊሙን ፊጦሪቅ፡ 173) “የሙስሊሙ ኡማ ህልውና ከብዙ ከፍለ-ዘመናት በፊት ተቋርጧል፣ እንደ አዲስ መመለስ ይኖርብናል” (መዓሊሙን ፊጦሪቅ፡ 6)፣ “ዛሬ ያለነው ኢስላም ሲነሳ ያጋጠመው ዓይነት ጃሂሊያ ውስጥ ነው ወይም ከዚያ የከፋ!” (መዓሊሙን ፊጦሪቅ፡ 21)፡፡ “መልእክቱ ሌላ ነው” የሚል ካለ የቀርዷዊን (አውለውያቱል ሀረከቱል ኢስላሚያህ፡ 110)፣ የፈሪድ አብዱል ኻሊቅን (አልኢኽዋኑል ሙስሊሙን ፊሚዛኒልሀቅ፡ 115) ይመልከት፡፡ በተጨማሪ ዐልይ ዐሽማዊ (የሰይድ ቁጥብ ቅርብ ሰው ነው) በአንድ ወቅት ከሰይድ ቁጥብ ጋር ያጋጠመውን እንዲህ ይገልፃል፡- “የጁሙዐ ወቅት ሲደርስ “ተወንማ እንነሳና እንስገድ” አልኩት፡፡ አስደንጋጭ ነበር! ለመጀመሪያ ጊዜ ሰይድ ቁጥብ ጁሙዐ እንደማይሰግድ አወቅኩኝ፡፡ “ኢስላማዊ ኺላፋ ከሌለ ጁሙዐ የለም፡፡ ያለ ኺላፋ ጁሙዐ የለም!” አለ፡፡ (አትተንዚሙ አስሲሪ፡ 112) “በአሁኑ ጊዜ ያሉ ሙስሊሞችን እርድ መብላት ይቻላል ወይ” ተብሎ ሲጠየቅ “እንደ አህሉልኪታብ (አይሁድና ክርስቲያን) እርድ ቆጥራችሁ ብሉ” ብሎ ነው የመለሰው፡፡ (አታሪኹሲሪይ ሊጀማዐቲል ኢኽዋነል ሙስሊሚን፡ 80) እስኪ ህሊና ያለው ይፍረድ ማነው ተክፊሩ?
በመጨረሻም ምን ያህል ኢስላማዊ አደብ ያልሸተታቸው ወጥ ረገጦች እንደሆኑ ታላላቅ ዑለማዎችን የገለፁባቸውን ቃላት ተመልክታችሁ ፍረዱ፡፡ (ሆዳም ዓሊም ተብዬዎች፣ የቤተ መንግሥት ፍርፋሪ ለቃቃሚዎችና የቱጃር አሽከሮች፣ ስልጣን ጠባቂ ዑለማ፣ ምንደኞች…) አዑዙቢላህ! ሰው ውሎውን ይመስላል፡፡ የገረመኝ ግን ይህን ሁሉ የስድብ ዶፍ ያወረደ ሰው “መሳደብ በየትኛው የነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሐዲስ እንደተፈቀደ አናውቅም” ማለቱ ነው!! ምናልባት ቁርኣን የሚገስፃችሁ ከሆናችሁ ((እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ለምንድን ነው የማትሰሩትን የምታወሩት? የማትሰሩትን ማውራታችሁ አላህ ዘንድ አስቆጭነቱ ከፍ አለ!)) ይላል፡፡ (አስሰፍ፡ 2-3)
በርግጥ የነዚህ ሰዎች ጩኸት እራሳቸውን እንጂ ዐሊሞቹን ቅንጣት ታክል አይጎዳም፡፡ ስሜት እየጋለበው ለጠማማ አንጃዎች በጭፍን ከሚሟገት ሰው ከዚህ የተሻለ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ እንዳውም ጩኸታቸው ተፅእኖ የሚያሳድርበት አይጠፋም በሚል ስጋት እንጂ በነሱ ላይ ጊዜ ማጥፋትም አይገባም ነበር፡፡ ኢብኑልቀይም እንዲህ ይላሉ፡- “ጭፍን ተከታይ ለሆነው መሀይምማ ቦታም አትስጠው፡፡ መሳደቡም፣ ማክፈሩም፣ እንደጠመምክ መግለፁም አይክፋህ፡፡ ምክኒያቱም ይሄ ልክ የውሻ ጩኸት ማለት ነው፡፡ በጮኸ ቁጥር እየመለስክለት ውሻው አንተጋ ቦታ እንዲኖረው አታድርግ፡፡ ቶወው ይጩህ! …” (አሰዋዒቁልሙርሰላህ፡ 3/1158) ኢማሙ አዝዘህቢም እንዲሁ “ጃሂል የራሱን ልክ አያውቅም ታዲያ እንዴት የሌሎችን ልክ ሊያውቅ ይችላል?” ይላሉ፡፡
ጌታዬ ሆይ! ስሜትን ከመከተል አንተ ጠብቀን፡፡ ሼር በማድረግ ከዑለማዎቻችን እንከላከል፡፡