Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የጉዞ ማስታወሻ

የጉዞ ማስታወሻ
በቅርቡ ወደ ወሎ ተጉዤ ነበር፡፡ የተሳፈርኩበት ባስ አዲስ አበባ የለኮሰው ሙዚቃ ጆሯችንን እያደነቆረን ደሴ ከተማ ገባ፡፡ ስምንት ረጃጂምና አሰልቺ ሰአታትን ማሰለፍ ግድ ነበር፡፡ የተከፈተው ሙዚቃ ገጠር እስታይል ሆነ መሰለኝ በቅሬታ የሚጉረመርሙ የወጣት ድምፆች ይሰሙ ነበር፡፡ “ቡና ቤት አረገው እኮ” አለ አንዱ፡፡ ላፍታ ሲዘጋ “ምነው” ይላሉ፤ ሲከፈት ደግሞ በምርጫው አይግባቡም፡፡ ግን ለምን ድምፁን በልክ እንደማያደርጉት አይገባኝም፡፡ ቢነገርም ላፍታ ሳይቆይ እስከጫፍ ይለቁታል፡፡ በዚህ ሁኔታ ማንበብም፣ መተኛትም አቃተኝ፡፡ የሚከፈቱት ነገሮች በደምሳሳው በቀረርቶ፣ በፈረስና በተኩስ ድምፅ የታጀቡ ናቸው፡፡ ወደ ጦር ግንባር ነው እንዴ የሚወስዱን? “ጠርጥር በሰሜን ጦር አለ” ያለው ማን ነበር? “በለው! ግደለው፣ ቁረጠው፣…” ነው የሚያጠነጥኑበት ርእሰ-ጉዳይ፡፡ ቀድሞም ይገርመኝ የነበረ ባህላችንን ዳግም በህሊናዬ መቃኘት ያዝኩት፡፡ ዘፈኑ፣ ተረትና ምሳሌው፣ ቀረርቶው፣ … ባህላችን ምን ያህል መግደልን እንደሚያበረታታ ያሳያል፡፡
ከደሴ ወጥቼ ጉዞየን ቀጥያለሁ፡፡ ባሱ በሙቀት “ብው” ብሏል፡፡ ተሳፋሪውን ቃኘት ቃኘት ሳደርግ ብዙዎቹ በእጃቸውም በጉንጫቸውም ጫት ይዘዋል፡፡ ይህኔ “ከጫት ሙቀት እንጂ እውቀት አይገኝም” የሚሉት አባባል ትዝ አለኝ፡፡ ስለዚህ አረንጓዴ መርዝ ባቅራቢያ ካሉ ተሳፋሪዎች ጋር አንዳንድ መባባል ጀመርን፡፡ የሀገሬም የህዝቤም ጉዳይ እጅጉን አሳዘነኝ፡፡ የእርሻ ማሳዎችን ስመለከትም በጫት የተሸፈኑት ቀላል አይደሉም፡፡ የሁለት ሰአት ተኩል የእግር መንገድ ተጉዤ ስደርስም ይሄ አረንጓዴ ሊፒስቲክ (ጫት) አሁንም አልለቀቀኝም፡፡ ጧትም ጫት ማታም ጫት፡፡ በጧቱ “የጀበና” ብለው ይቅማሉ፡፡ በነገራችን ላይ “የጀበና” የሚለው ቃል “ኢጀ በና” ከሚለው ኦሮምኛ ቃል ተዛብቶ የተኮረጀ እንደሆነ መልእክቱም “የአይን መግለጫ” ማለት እንደሆነ ሰማሁኝ፡፡ በፖለቲካውም፣ በሀይማኖቱም፣ በታሪኩም፣ በማህበራዊ ህይወቱም፣ … በሁሉም ጉዳይ በድፍረት ሲያወሩ ሳይ እራሳቸውን እንዴት እንደሚያዩ ባላውቅም “ሁለገብ ምሁር እንደሆኑ ያስባሉ እንዴ” ብየ እስከምጠረጥር አድርሶኛል፡፡ ነው ወይስ ጫቱ ነው የሚያወራው? መደበኛው የከሰዐቱ ፕሮግራም ከተጠናቀቀ በኋላም ማታ ላይ ወደ ጫት የሚመለሱ ሰዎችን ስመለከት ይበልጥ ግራ ገብቶኛል፡፡ ለካስ ግራ የገባኝ እኔን ብቻ አልነበረም፡፡ ማታ ላይ በርከት ካሉ አብረውን ከነበሩት ውስጥ አንዱ ጫት ይዞ ኖሯል፡፡ ከዚያም ከዚህም “በዛ” በሚል አንድምታ በነገር መወጋጋት ያዙት፡፡ “ቆይ ከኔ አፍ ውስጥ አንድ ጥርስ ያዋጣ አለ እንዴ?” በማለት “እኔ ስለቃምኩ እናንተን ምን አገባችሁ?” በሚል መንፈስ ስቆ አሳቃቸው፡፡
አሁን ለሌላ የእግር ጉዞ ተነስቻለሁ፡፡ ከተራራ ጀርባ ላይ የሚገኙ ቀጫጭን መንገዶችን እያቋረጥኩ ነው፡፡ ከስራቸው ያለው ገደል ነው፡፡ “ሱብሐነላህ! ሺ አመት አይኖሩ ምን አሰቃያቸው አሁን የታመመ ሰው በቃሬዛ በዚህ መንገድ ሲወስዱ አንዱን ሸተት ቢያደርገው እዚሁ ገደል አስገብተው ገደሉት አይደለም ወይ?” ስል “አላህ እየጠበቃቸው ነው እንጂ እሱማ አደጋ ነው” አለቺኝ እናቴ ፡፡ ጥቂት ከተጓዝን በኋላ ቅድመ- አያቴን አገኘሁኝ፡፡ የእናቴን የእናቷን እናት፡፡ አላውቃትም አታውቀኝም፡፡ ስታየኝ አምርራ አለቀሰች፡፡ ቅድመ አያቴ ቤተ-ዘመዱ በመራራቁ ምክኒያት በዐይኗ ባታያቸውም የልጅ ልጅ ልጅ ልጅ አድርሳለች፡፡ ከቅድመ አያት ቀጥሎ ምንድን ነው ያለው? ቅማንት ወይም ምንጅላት ሆናለች ማለት ነው፡፡ ዐቅሏም አይኗም ደህና ነው፡፡ ከቤት እቤት ደህና ትንቀሳቀሳለች፡፡ “ሶስት የመንጋጋ ጥርሶችን አብቅያለሁ” ስትለኝ እንዲህ አይነት ነገር እንዳለ ለመጀመሪያ ጊዜ መስማቴ ነውና ተደመምኩኝ፡፡ አይኗን ሳላያት ሞት እንዳይለያን ስጋት ነበረኝ፡፡ ስላየኋት በጣም ደስ ብሎኛል አልሐምዱሊላህ፡፡
በገጠር ቆይታዬ አስደንጋጭ ሺርካሺርኮችንም አስተውያለሁ፡፡ ከሴቶች አካባቢ ጥንቆላ ጋር የተያያዙ፣ “መሻኢኽ” ከሚባሉት ጋር ደግሞ ወልዮች ጋር የተያያዙ ብልሹ እምነቶችን ሰምቻለሁ፡፡ በርግጥ ካሁን በፊት ክር የሚተበተቡ፣ ቅቤ የሚቀቡ፣ እንደነዛቱ አንዋጥ ለአምልኮት የሚሰባሰቡባቸው ዛፎችን፣ የሚማልባቸው ረጃጂም ብትሮችን፣ አፈር ለበረካ የሚሰጥባቸው መቃብሮችን ስላየሁ ብዙም አልደነቀኝም፡፡ ይልቁንም ትኩረቴን የሳቡ ሁለት ነገሮችን አብሬ አስተዋልኩ፡፡ አንዱ ሐቁ ሲነገራቸው ምንም ሳያቅማሙ የሚቀበሉ ብዙ ወገኖችን ስመለከት ደስ ቢለኝም ካሉበት ድረስ ተገኝቶ የሚያስተምራቸው አለመኖሩ እጅጉን አሳዘነኝ፡፡ ሌላኛው ያስተዋልኩት ነገር ፌስቡክ እስከዚያ አካባቢ መድረሱ ነው፡፡ እንዳውም “እከሌን ታውቀዋለህ” እያሉ ፌስቡክ ላይ ደዕዋ የሚያደርጉ ወንድሞቼን ስም ሲያነሱልኝ የሆነ ደስታ ተሰማኝ፡፡ የፌስቡኩን ደዕዋም እየተሰጠ ካለው በላይ ዋጋ ሊሰጠው እንደሚገባ አመንኩኝ፡፡ አቅማችን በፈቀደ ግን እስካሉበት እየተጓዝን ወገኖቻችንን መጎብኘት እንዳለብን ተሰምቶኛል፡፡ ወሰላሙ ዐለይኩም