Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ሰልፍን በተመለከተ አንድ ጥያቄ አለኝ ?


ሰልፍን በተመለከተ አንድ ጥያቄ አለኝ
ሴት ልጅ ድምፁዋን ከፍ አድርጋ እየጮኸች፣ ከወንዶች ጋር እየተጋፋች ወይም እየተፋጠጠች፣ ለሚደበድባት አረመኔ ፖሊስና ሲሸሽ ረጋግጧት ለሚያልፍ ገልቱ ወንድሟ አደጋ እራሷን አጋልጣ፣ ከፊሏ ተገላልጣ፣ በሜካፕ ተሽሞንሙና፣… ጎዳና እንድትወጣ የሚፈቅድላት ማስረጃ ካላችሁ እስኪ ተባበሩኝ፡፡
እስከማውቀው ሴት ልጅ ሶላት ላይ ያለ ሰው ቢሳሳት እንኳን ለማረም ድፁዋን ከፍ አታደርግም፡፡ ይልቁንም በእጆቿ በማጨብጨብ ነው የምትገልፀው፡፡ ለሶላት እንኳን ቤቷ ለሷ እንደሚበልጥ “አይ እወጣለሁ” ካለችም ስርአቷን ጠብቃ መውጣት እንዳለባት፣ መንገድ ላይ ስትሄድ ስትመለስ እንኳን ከወንዶች ጋር እንዳትጋፋ፣ ዳር ዳሩን እንድትይዝ የማያሻሙ ነብያዊ ማስረጃዎች መጥተዋል፡፡ በቁርኣንም ለሙስሊም ሴቶች “ከቤታችሁ ተረጋጉ፣ የጃሂሊያ መራቆትን አትራቆቱ” መባሉ የሚታወቅ ነው፡፡ ምናልባት ሰልፉ ጂሃድ እንደሆነ የሚሞግት ካለም ጂሃድ ሴቶችን እንደማይመለከት የማያሻማ ማስረጃ አለን፡፡ እንዳውም እኮ ነብያችን ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሴቶች ጥንቃቄና እንክብካቤ የሚሹ መሆናቸውን ሲጠቁሙን “ብርጭቆዎች ናቸው” ብለውናል፡፡ ታዲያ እኛ የሚጠበቅብንን ጥንቃቄ፣ አልፎም ሸሪዓዊ ገደቦችን ጠብቀናል?
ወንድሞችና እህቶች ሆይ! እስኪ ከስሜት ሳይሆን ከህሊና እንሁን፡፡ ይሄ ልጓም የሌለው አካሄዳችን ትርፍ ወይስ ኪሳራ እያስከተለብን ያለውን አስተውለን ይሆን? በተረጋጋ ህሊናስ ሂሳቡን አወራርደን ይሆን? እውነት ስኬት የሚመጣው የአላህን ትእዛዝ በመጣስ ነው?? ሀያሉ ጌታችን አላህ፡- (አላህን ብትረዱ ይረዳችኋል) አላለንምን?? ታዲያ እኛ ከሸሪዐው በተቃራኒ እየተጓዝን ነው እንዴ ስኬትን የምናልመው፣ ፈረጃንስ የምንጠብቀው??
ወደ ጥያቄየ ልመለስ፡፡ ጥያቄዬ በማስረጃ ለሚያወሩ፣ ማስረጃን ለሚያከብሩ #ብቻ ነው፡፡ ማስረጃ የሌላችሁ#በአላህ_ይዣችኋለሁ ለአጉል ንትርክ በር እንዳትከፍቱ ዝም በሉ፡፡ ነገር ላለማንዛዛት ለሹብሃ በር ላለመክፈት ስል ጥያቄውን ገድቤዋለሁ፡፡ ጥያቄው እንዲህ የሚል ነው፡
ከሴቶች አንፃር ከላይ የተጠቀሱትን ሀሳቦች የሚደግፉ አያዎችንና ሐዲሶችን ገሸሽ በማድረግ #ሴቶች“ሰላማዊ” ሰለፍ መውጣት እንደሚችሉ የሚያሳምን #የማያወላዳ፣ #ፍንትው_ያለ፣ #ቀጥተኛ የቁርኣንና የሐዲሥ ማስረጃ ያላችሁ እባካችሁ ተባበሩን፡፡ ከሰሐቦች፣ ከታቢዖት፣ አትባዑት-ታቢዒን፣ ጀምሮ እስከ ዘመናችን የሱና ዐሊሞች (ከየትም ሀገር ይሁኑ) #ሚዛን የሚደፋ ማብራሪያ ካላችሁ ጀባ በሉን እስኪ፡፡ በማስረጃ ሳይሆን እንዲሁ ከመስለሐና ከመፍሰዳ አንፃር ብቻ መነጋገር የምትሹ ደግሞ እስኪ ያላችሁን አውጡትና በሰከነ መልኩ እንወያይ፡፡ ምናልባት “ይሄ ከኛ አቅም በላይ ነው፡፡ ዓሊሞቹ ይነጋገሩበት” የምትሉ ካላችሁ አንድ ተጨማሪ ጥያቄ አለኝ፡፡ “ታዲያ ሸሪዐዊ ብይኑ ክልክል ይሁን ፍቁድ የማናውቀውን ጉዳይ ነው ወይ እንዲህ የምናራግብለት? ሲፈፀም እያየንም ዝም የምንለው?” የሚል፡፡ ሀሳቤን የምትደግፉም የምትነቅፉም በስርኣት በማውራት እንደምትተባበሩኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ጀዛኩሙላሁ ኸይረን፡፡