Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ተጨማሪ ስለ “ሰላማዊ” ሰልፍ ለመሐመድ አልፋቲሕ የተሰጠ ምላሽ



ተጨማሪ ስለ “ሰላማዊ” ሰልፍ
ለመሐመድ አልፋቲሕ የተሰጠ ምላሽ
በቅርቡ ከሰልፍ ጋር በተያያዘ የተወሰኑ ነጥቦች ከዚህም ከዚያም መውጣታቸው ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ቀድመው አቋም ይዘው እንደገና ማስረጃ ፍለጋ የሚባዝኑ ሰዎች የሚያያዝ የመሰላቸውን ሁሉ ያለምንም ማጣራት እያራገቡ ነው፡፡ ከፊሉ “በጊዜው ማዕከላዊ መንግስት ባለመኖሩ በዘመነ መካ ሰልፍ አልነበረም” እንዳላሉ ይሄው በጊዜው ሰልፎች እንደተደረጉ ለማሳየት ሹብሃዎችን መዘርዘር ይዘዋል፡፡ ከነዚህ ሹብሃዎች ሙሐመድ አልፋቲህ ብሎ እራሱን በሚጠራ የተጠቀሱት ይገኙበታል፡፡ ሹብሃዎቹ ብዙ ውሃ ባይቋጥሩም ውንጀላም ጭምር ስላላቸው የተወሰነ ቢባል አይከፋም፡፡
1. ((ኢስላም ሁለንተናዊና ለማንኛውም ጥያቄ መልስ ያለው ምሉዕ እምነት ነውና ከቻልክ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ትግል ስህተት መሆኑን በቁርአን ወይም በሀዲስ አልያም የቀደምት ሰለፎችን አቅዋል እንኳ ጠቅሰህ አስረዳ ))
መልስ፡- በመጀመሪያ በማስረጃ ቋንቋ የሚያወራ ሰው ምንኛ ደስ ይላል! እናም እዚህም ላይ ማስረጃ መጠየቅህ ደስ ይለናል እንጂ አይከፋንም፡፡ ነገር ግን ማስረጃ መጠየቅ ያለበት ማነው? ሰልፉ እየተደረገ ያለው ለዲን ከሆነ ያለማስረጃ የሚፈፀም ዲን የለም፡፡ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንደሚሉት “የኛ ትእዛዝ የሌለበትን ስራ የፈፀመ ስራው ተመላሽ(ውድቅ) ነው፡፡” እዚህ ላይ “እንግዲያውስ ለምን ይህን ትሰራላችሁ?” እያሉ ዱንያዊ አዳዲስ ነገሮችን መዘርዘር ከስሜት ባለፈ ረጋ ብሎ ለሚያስተውል ሰው ውሃ የሚቋጥር አይደለም፡፡ ምክኒያቱም ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “በዱንያዊ ጉዳያችሁ እናንተ ይበልጥ ታውቃላችሁ” ብለዋልና፡፡ “ሰልፉ ሸሪዐዊ ግቦችን ያሳካል” የሚል “እኛ ይሄ ነገር በዲን ውስጥ የተጨመረ ቢድዐ ነው፡፡ ቢድዐ ደግሞ ጥመት ነው” እያልን ነውና “አይ” የሚል ካለ ማስረጃ የሚጠየቀው እሱ እንጂ እኛ አይደለንም፡፡ ምናልባት ((ይሄ መዳረሻ ነው፡፡ በራሱ ፍቁድ እስከሆነ ድረስ ደግሞ መዳረሻዎችን መጠቀም ይፈቀዳል)) ልትል ትችላለህ፡፡ ልብ በል ይሄ ማለት ማስረጃ ብለህ የዘረዘርካቸው በሰሐቦች ጊዜ የተከሰቱ ክስተቶች ማስረጃ እንደማይሆኑ አመንክ ማለት ነው፡፡ በደንብ አጢነው!! ለማንኛውም ወደዚህ ነጥብ ከናንተ ሳይነሳ ከማሰፋ ስታቀርቡት ብመለስ ይሻላል ብየ የፃፍኩትን ቀንሼዋለሁ፡፡ በተረፈ ሰልፉ ከካፊር የተወሰደ የምእራባውያን ሱና ነው፡፡ ይሄን ደግሞ በርካታ ታላላቅ መሻኢኾች ገልፀውታል፡፡ በዐሊሞቹ ላይ ያለው እምነት የቀለለው ደግሞ የሰልፍ አነሳስ ከየትና እንዴት እንደሆነ ሚዛናዊ ሆኖ ያጣራ፡፡
2. ሌላው ሸይኽ አብዱረህማን አል ዐጅላንን ስለሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ጠይቀህ “የሀገራችሁን ዐሊሞች ጠይቁ የሚል ምላሽ ሰጥተውኛል” ብለሃል፡፡
መልስ፡- እንግዲያው ከተነካካህ አይቀር በሀገራችን ውስጥ ሱፍዮች በተለይም ቲጃኒዮች እንዳሉ፣ የቀብር አምልኮ በሰፊው እንዳለ፣ ጓዝ ጠቅልሎ ቀብር ዚያራ መጓዝ እንዳለ፣ መውሊድ በሰፊው እንደሚከበር፣ ወዘተ ንገራቸውና ግን ይሄ ሁሉ እያለ “በሀገራችን የዐቂዳ ልዩነት የለም” የሚሉትን “ከሱፍዮች ከቲጃኒዎች ጋር እርቅ የሚፈፅሙትን አሁን በደረሰብን ጉዳይ ፈትዋ እንጠይቃቸው ወይ” ብለህ ብትጠይቃቸው ምን ይመስልሃል? ሸይኽ ዐጅላን ጠንካራ የተውሒድ ሰው ናቸው፡፡ ከየአፅናፉ ለሐጅ በታደመ በርካታ እንግዳ ህዝብ ፊት ነው ስለ ተውሒድ ስለ ሸይኽ ሙሐመድ ኢብኑ ዐብዲልወሃብ ደጋግመው በግልፅ የሚናገሩት፡፡ ህዝቡ ሴቶች ሳይቀሩ ሰልፍ እየወጡ ብዙ የሞተ እጅግ በርካታ ወህኒ የታጎረ፣ አካሉ የጎደለ ወዘተ እንዳለም አብረህ ጠቁማቸው፡፡ በሰላት የምታደርጉትን “ጨዋታ” ወይም አድማም አትርሳ፡፡ ሐቅ ፈላጊ ሰው እውነታ አይደብቅም፡፡
3. ኢብን አል ጀውዚ [ታሪኽ ዑመር ኢብኑል ኸጣብ ] በሚለው ኪታባቸው ዑመር ኢብኑል ኸጣብ እንዲህ ማለታቸውን ዘግበዋል << እንደሰለምኩ "ያ ረሱለላህ ብንሞትም ብንተርፍም በ ሀቅ ላይ አይደለንምን? <<እንዴታ !ነብሴ በእጁ በሆነች ጌታ ይሁንብኝ ብሞቱም ብትተርፉም በሀቅ ላይ ናችሁ! >> አሉ ታዲያ ለምን እንደበቃለን? በእውነት በላከዎት ጌታ ይሁንብኝ እንወጣለን> > በአንደኛው ሰፍ ሀምዛ በሁለተኛው እኔ ሆነን ወጣን ........>> የወጡት ጂሀድ ነበር እንዳትሉኝ ጂሀድ ያለምንም ዝግጅት በባዶ እጅ ይወጣል እንዴ?
መልስ፡- ኧረ እኛ “ጂሃድ ነው” አላልንም! ይልቅ በጂሃድ ስም በየቦታው በከንቱ ለሚያፈነዱ እና ምግባራቸውን ለሚደግፉ ጥሩ ማስታወሻ ጠቁመሃል፡፡ አጥፍቶ ጠፊዎች ኢስላምን ከማጠልሸት ያለፈ አንድም የሚያተርፉት ነገር የለም፡፡ ጥፋታቸውን በኢስላም ስም ስለሚፈፅሙ ግን በርካቶችን መንገድ አስተዋል፡፡ እንዲህ አይነቱ ተግባር ጂሃድ ቢሆን ኖሮ ሰሐቦች መካ ላይ ሲሰቃዩ ይፈፅሙት ነበር፡፡ ወደ ነገረህ ስመለስ በጠቀስከው ቂሳ ላይ ሰሐቦች የወጡት የተቃውሞ ሰልፍ ነው እያልክ ነው፡፡ እና ታዲያ “ያኔ ሰልፍ ያላደረጉት ማዕከላዊ መንግስት ስላልነበረ ነው” ለምን ትላላችሁ? ኧረ እባካችሁ በመጀመሪያ እርስ በርስ ታረቁ!! ይሄ ሁሉ ቀድማችሁ አቋም ይዛችሁ እንደገና ደሊል ፍለጋ እንደምትባዝኑ አያሳይም? “በቃ በነብዩም ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ዘመን ሰልፍ እንደተደረገ ነው የምናምነው፡፡ ያንኛውን ሀሳብ ተውት” ካላችሁ ቂሳው ደካማ /ዶዒፍ ነው፡፡ ምክኒያቱም ሰነዱ ውስጥ የሚገኘውን ኢስሓቅ ኢብኑ ፈርዋህን ኢማሙ አሕመድ “እኔ ዘንድ ከሱ ማውራት አይፈቀድም!!” “እሱ ሊያስተላለፉለት የሚገባው አይደለም፤ ከሱ አይዘገብም” ብለዋል፡፡ ኢማም የሕያ ኢብኑ መዒንም እንዲሁ ሰውየዉን “ዉሸታም ነው!!” ብለውታል፡፡ ስለዚህ የምትጠቀሙትን ቂሳ “ሰነዱ ችግር አለበት” እያሉ ነው አኢማዎች፡፡ ምን ይሻላል? በዚያ ላይ ደግሞ ሴቶቹ አልወጡም በታሪኩ ላይ፡፡ መቼም “ተቀላቅለው ነው የወጡት ወይም የወንዱን ሰልፍ ሐምዛ የሴቱን ደግሞ ዑመር ነበር የመሩት” እንደማትል እጠብቃለሁ፡፡ ስለዚህ እንዳው ደሊል እናድርገው ብትሉ እንኳን ለምን ሴቶችን ታስወጣላችሁ? አኺ ዝም ብላችሁ ከዚህም ከዚያም የማይገናኘውንም ደካማውንም ባታግበሰብሱ መልካም ነው፡፡ “ሁሉን ለመያዝ የሚሞክር አንድ ቀን እባብ ጨብጦ ይሞታል” ይባላል፡፡
4. (የመልዕክተኛው (ሰዐወ) ሀዲስ
[من رأى منكم المنكر فليغيره بيده فإلم يستطع فبليسانه فإلم يستطع فبيقلبه وذالك أضعق الإمان] رواه مسليم
ከመካከላችሁ መጥፎን ያየ በእጁ ያስጥል ያን ካልቻለ በምላሱ ይቃወም ያንም ካልቻለ በውስጡ ይጥላ (ሙስሊም የዘገቡት፡፡) የአህባሽ መምጣት ሙንከር አይደለም እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ? የኢማሞች መባረር የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ሂጃብ መከልከል፣ የዱዐቶች መታሰር ሁሉ ለናንተ መስለሀ ከሆነ አላውቅም...)
መልስ፡- በመጀመሪያ ወንድሜ ሐዲሡን አስተካክለህ ፃፍ፡፡ መፃፍ ካቃተህ ከ “ሻሚላ” ኮፒ አድርግ እንጂ በድፍረት ባታበላሽ መልካም ነው፡፡ እንዴ ድፍረትህ ለከት ይኑረው እንጂ? መልክቱንም እንዲሁ በስርኣት ተርጉም፡፡ ካልሆነልህ “በዕውቀት ተናገር አልያም ችለህ ዝም በል!” ማለትህን ላስታውስህ፡፡ የምታወራውን ስራበት እንጂ? እውነት መምከር ነው የፈለግከው ወይስ አዋቂ መስሎ መታየት? ያለበለዚያ ሌሎችን “ይሄን ቀርታችኋል? ማን ላይ ቀርታችኋል?” እያልክ መጠየቅህ ምን ፋይዳ አለው? ይልቅ ጥያቄውን ለራስህ አቅርበው፡፡ በአንዲት መስመር ሐዲሥ ፅሁፍና ትርጉም ይህን ሁሉ ማተራመስ ምን ማለት ነው? ይሄውና የጠቀስከው ሐዲሥ ሰሒሕ ሙስሊም ላይ በዚህ መልኩ ነው ያለው
«مَنْ رَأَى مِنْكُمْ مُنْكَرًا فَلْيُغَيِّرْهُ بِيَدِهِ فَإِنْ لَمْ يَسْتَطِعْ فَبِلِسَانِهِ فَإِنْ لَمْ يَسْتَطِعْ فَبِقَلْبِهِ وَذَلِكَ أَضْعَفُ الإِيمَانِ ».
እስኪ አንተ የፃፍከው ጋር ያለውን ርቀት አስተውለው፡፡ ድፍረትህ የጤና ነው? “ሙስሊም” የሚለውን የዐረብኛ ቃልም እንዲሁ በትክክል አልፃፍከውም!! ተመሳሳይ ግድፈቶችን በቁርኣንም በሐዲሥም ላይ ሰርተሃል፡፡ ለምሳሌ፡-
]ولتكن منكم امة يدعون إلى الخير ويأمرون بالمعروف وينهون عن المنكر وألآئك هم المفلحون]العمران ١٠٤
{إذا حكم الحاكيم فجتحد ثم اصاب الحق فله اجران وذا حكم فجتهد ثم اخطأ فله اجر}
ለራስህ እዘን እንጂ! እንዲህ ሆነህ ነው እንዴ ገበያ የምትወጣው? ሱብሓነላህ!! ደግሞም “ሙንከርን በሙንከር ማስወገድ አይቻልም” አልን እንጂ ጭራሽ “ሙንከርን መቃወም አይቻልም” አላልንም፡፡ ለምን ያልተፃፈ እንደምታነብ፣ ያልተባለ እንደምታስተጋባ አላውቅም፡፡ “የኢማሞች መባረር የዩንቨርስቲ ሴት ተማሪዎች ሂጃብ መከልከል፣ የዱዐቶች መታሰር ሁሉ ለናንተ መስለሀ ከሆነ አላውቅም” አልከን፡፡ ግን ክፉ ጥርጣሬህ እዚህ ከደረሰ ለምን የውይይት በር ትከፍታለህ?! በዚህ መልኩ እየፃፍክ ነው እንግዲህ “ሰው አትሳደቡ” የምትለው፡፡ ስላቅ አይሆንም? “ጥፋት ባምሳያው አይወገድም” ማለት ጥፋቱን እንደ ልማት መቁጠር ነው አንተ ዘንድ? እስኪ አንድ ምሳሌ ልስጥህ፡፡ አንድ ባለጌ በተደጋጋሚ እህትህን ቢደፍርና እሱን ለማስቆም ብለህ አንተም በእህቱ ላይ አፀፋውን ለመውሰድ ብትነሳ ወንድምህ ግን “አላህን ፍራ! ቢሳካልህም ባይሳካልህም ይሄ ጤነኛ መፍተሄ አይደለም” ቢልህ “በእህታችን ላይ የሚፈፀመውን ግፍ ትደግፋለህ” ትለዋለህ? ቆይ በሀሳብ አለመግባባታችን እንዳሻችሁ እንድትወርፉን አረንጓዴ ያበራላችኋል ማለት ነው? አስተውል! የኛ አቋም ሰልፉ በራሱ ጥፋት ነው፡፡ ጥፋት ደግሞ በጥፋት አይወገድም” ነው፡፡ ይሄ ደግሞ መሰረታዊ የፊቅህ መርህ ነው፡፡ ደግሞም ከዘረዘርካቸው ፈተናዎች የተወሰኑት የደረሱት ወይም የተባባሱት ሰልፉ ከተቀጣጠለ በኋላ ነው፡፡ ስንት ሰው የሞተው፣ የታፈሰው፣ ሀገር ጥሎ የተሰደደው ሰልፉን ተከትሎ አይደል? እስኪ ሰልፉ ከተጀመረ ጀምሮ ያመጣችሁትን ለውጥና የደረሰብንን ፈተና አመዛዝኑ፡፡ ታዲያ ለናንተ ላባባሳችሁት “መስለሐ” ያልሆነው “ሙንከር” በምን ሂሳብ ነው እኛጋ እንደ “መስለሐ” የሚቆጠረው?
5. (የዑለማዎች ቀውል ብቻውን ደሊል ሆኖ ሊቀርብ አይችልም ዝምብለን እንኳ እንቀበለው ቢባል ትምህርቱ የት፣ መቼና ለማን እንደ ተሰጠ ማጤን ይኖርብናል ለምሳሌ እነዚህ ታላላቅ ሸይኾች የጋዛ (እየሩሳሌም) ነዋሪዎች ለረጅም ጊዜ ሰልፍ ሲወጡና ከእስራኤል ፖሊስ ጋር ሲጋጩ ሰላማዊ ሰልፍ ከሰለፎች አልተገኘምና ቢድዐ ነው ብለው ያወገዙበትን አንድም ደርስ አታመጡም አንድም! ይልቁንም ዱዐ ሲያደርጉላቸውና የሱዑዲም መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ትልቅ ሚና ተጫውተዋል)) ብለሃል፡፡
መልስ፡- ስለዚህ እነዚህ ታላላቅ መሻኢኾች በጎንደር፣ በጂማ፣ በጎጃም ያሉ ቲጃኒያዎችን ቢድዐና ሺርኪያት የአካባቢውን ስም ጠቅሰው በደርሳቸው ካልተቃወሙ “ቲጃኒዎች ልክ ናቸው” እያሉ ነው ማለትህ ነው? እነዚህ ሱፊዎች እራሳቸውን እንደ ሙስሊም እስካሰቡ ድረስ ልናዝንላቸው ይገባል ብለው ዱዓ ቢያደርጉላቸውስ ስራቸውን ይደግፋሉ ማለት ነው? “አይ ተጨባጩን የሚያውቁ የሀገራችን ዑለሞች በቂ መልስ አላቸው” ብለን ስንጠይቅ ከነሱ ውስጥ ከቲጃኒዎች ጋር የሚታረቁና እንደሚያስታርቁ ከደረስንበትስ በቃ ቲጃኒያ ልክ ነው ማለት ነው? ይሄ ሁሉ ቀድሞ አቋም ይዞ እንደገና ደሊል ፍለጋ መባዘን እንደሆነ አያሳብቅም? እርግጥ ነው ማስረጃዎችን በራሱ የመፈተሸ አቅም ላለው ሰው የዑለማዎች ቀውል ብቻውን ደሊል አይሆንም፡፡ አስተውል የተፃፈ ማንበብ ለማይችል እያበላሸ ለሚገለብጥና ለሚረዳ አይደለም፡፡ እሱማ ከመጠየቅ ውጭ ምን ምርጫ አለው! ግን እናንተ እኮ ወይ በሁለት እግሩ የሚቆም ደሊል አላመጣችሁ፡፡ ወይ የታላላቅ ሱኒ ዓሊሞችን ፈትዋ አላመጣችሁ፡፡ በምን እንቀበላችሁ? “ሰልፉን ይደግፋሉ” ብለህ ከዘረዘርካቸው ዱዓቶች ይልቅ የሚቃወሙት መሻኢኾች እንደሚበልጡ እራስህ ምስክርነት ሰጥተሃል፡፡ “ሸይኾቹን አላነፃፀርኩም ይልቁንም በዚህ መስዐላ ተቃርነዋቸዋል እንጂ ኢብን አልቀይም ከሸይኹ ኢብን ተይሚያህ ብዙ መስአላ ላይ ይቃረን እንደነበረው” ማለትህን አስተውል!! ይሄን ደግሞ “ሰልፍ ይደግፋሉ” ብለህ የጠቀስካቸውም የሚያምኑት ሐቅ ነው፡፡ ጀዛከላሁ ኸይረን! ይሄ ሌሎች ጋር የማናየው ሚዛናዊነት ነው፡፡ ግና ኢብኑልቀይም ሌላ አንተ የምትጠቅሳቸው ሌላ! “ያ ሌላ እሄ ሌላ” አለ ሸማኔው ቀለሙን አንዴ ወደ ቀኝ አንዴ ወደ ግራ እየወረወረ፡፡ አንተ ሰልፍ “ኺላፍ ያለበት መስአላ ነው” ለማለት “ይፈቅዳሉ” ብለህ ከዘረዘርካቸው ውስጥ ከነሱ እንደሚበልጡ ፍንጭ በሰጠኸን ዑለማዎች “የስሜት ተከታይ” እንደሆነ የተጠቆመ አለ፡፡ “ኢኽዋኒ” እንደሆነ የተነገረ አለ፡፡ ግልፅ ከሆኑ ሐዲሦች በተቃራኒ በሙስሊም መሪ ላይ አምፆ መውጣትን የሚፈቅድ አለ፡፡ ታዲያ ጉዳዩ ላይ ኺላፍ እንዳለ ለማሳየት የምትሞክረው በዚህ መልኩ ነው? በአንድ በኩል ታላላቅ የሱና ዓሊሞች በሌላ በኩል እንዲህ አይነት ሰዎች? አቀራረብህ ጤነኛ ነው? እሺ “ኺላፍ አለበት” እንበል፡፡ ማስረጃው ሚዛን ባይደፋልን ከታላላቆቹ ዓሊሞች ነው መሆን የሚሻለው ወይስ በራሳቸው ምስክርነት ከነሱ በብዙው ከሚያንሱት? እሺ ይሄም ይቅርና ጉዳዩ ኺላፍ አለበት እንበል ፡፡ ከሁለቱ አቋም የመሰለንን መውሰዳችን ነው የሚያስተችንና የሚደርሰውን ግፍ እንደምንደግፍ የሚያስቆጥረን? ኧረ አላህን ፍሩ! ሚዛናዊ ሁኑ! ከሱፍያ ጋር እየተላለፋችሁ ከቲጃኒያህ ጋር እየተላለፋችሁ ከአሽዐሪያህ ጋር እየተላለፋችሁ ሰልፉን ከማይቀበል ጋር የማትተላለፉት ለምንድን ነው? በቃ ሰልፉ ከዐቂዳም በላይ ነው ማለት ነው? ሰልፍን አለመቀበል ቲጃኒዎች ጋር፣ አሻዒራዎች ጋር ካለው የዐቂዳ ብክለት የከፋ ነው ማለት ነው? የፊቅህ ልዩነትን እንደ ዐቂዳ ልዩነት እንደምናይ ሰልፍን ምሳሌ አድርገህ አቅርበሃል፡፡ ዐቂዳማ ያረጋችሁትማ እናንተ ናችሁ! ሰልፉን ስለተቃወምን አይደል እንዴ ከጠላት ጋር እንዳበርን እያራገባችሁት ያላችሁት?
6. ((የሶሪያ ህዝብ … ሰልፍ ሲወጡ …ዶ/ር ፈውዛንን ጨምሮ (ሀፊዘሁላህ) ሌሎች ዑለሞች <<ተዐውን መዐል ኢኽዋ>> ወንድሞቻችን ማገዝ አለብን በማለት እንዲረዱና በሁለቱም ሀረሞች … በየተራዊህ ሰላቱ ዱዐ ሲደረግላቸው እንደነበር ፀሀይ የሞቀው እውነታ ነው ልብ በሉ ይህ ሁሉ ሰላማዊ ተቃውሞ እያደረጉ ሳለ ነው ታዲያ እውነታው ይህ ከሆነ " ሰላማዊ ተቃውሞ ሀራም ነው ለምን አሉ? " የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል... ፈትዋው ግልፅ ኩፍር (كفرا بواحة) ያልታየባቸውን የሙስሊም መሪዎች ነው የሚመለከተው ))
መልስ፡- ታዲያ ሸይኽ ፈውዛን “ሰልፍ ይፈቀዳል” ብለዋል እንዴ፡፡ ሸይኹ እንኳን ሰልፍና አቅምን ያላገናዘበ “ጂሃድንም” አይፈቅዱም፡፡ አንተ “ሰልፍን የሚከለክለው ፈትዋቸው በሙስሊም መሪዎች ላይ ብቻ የተገደበ ነው” እያልክ ነው፡፡ እሳቸው ግን “ይሄ ሰልፍ ፈተና ነው የሚቀሰቅሰው፡፡ ደም መፈሰስን ነው የሚያስከትለው፡፡ ንብረት መውደምን ነው የሚያስከትለው፡፡” እያሉ ነው፡፡ እንግዲህ ተመልከቱ ሰልፉ እኛም ጋ ያስከተለው ይሄው ነው፡፡ አንተ ምንም ሳትሸማቀቅ በድፍረት “ሰሐቦች ሰልፍ ወጥተዋል” እያልክ ፈትዋ እየሰጠህ ነው፡፡ ሸይኽ ፈውዛን ግን “ሰልፍ የሙስሊሞች ስራ አይደለም፡፡ ሙስሊሞች ቀድሞ አያውቁትም” ይላሉ፡፡ “ማናችሁን እንመን” ብየ ለንፅፅር ባቀርብህ ይመችሃል? ስለሐረም እና የተራዊሕ ዱዓ ለምን እንደምታወራ አይገባኝም፡፡ ርእሱን ከመለጠጥ ያለፈ ፋይዳ የለውምና፡፡ አስተውል! አጀንዳው ዱዓ ይፈቀዳል አይፈቀድም አይደለም!! كفرا بواحة ያልከው ደግሞ ግልፅ የዐረብኛ ስህተት ነው፡፡ ስህተትህ አይደለም የገረመኝ፡፡ እኛ እራሳችንን እንደ ሙፍቲ አድርገን እንደምናቀርብ ገለፅክ፡፡ ይሄን ያስባለህ ግን አንተ የማታምንበትን ሀሳባችንን ማስፈራችን ነበር፡፡ ያለበለዚያማ እራሱን እንደሙፍቲ የሚቆጥረው አንተ ነበርክ፡፡ “የት” ካልከኝ ርእስህን ተመልከተው፡፡ “#ሰላማዊ_ተቃውሞ_በሸሪዐ_መነፅር!” እስኪ ተመልከቱ! አንድ መስመር በማይሞላ ሐዲሥ እያተራመሰ የሚፅፍ ሰው እንዲህ አይነት የተካበደ ርእስ ይሰጣል? “የዑለማዎች አቅዋል ደሊል አይሆንም” እያለ ገሸሽ አድርጎ የራሱን ቁንፅል አመለካከት ሊተካስ ይዳፈራል? አላሁመ ሩሕማክ!
7. ((እነ አብደላ ኢብን ዙበይር የሀጃጅን የግፍ አገዛዝ ሰዎችን አሰባስቦ ተቃውመዋል በስተመጨረሻም እሱም ሆነ ደጋፊዎቹ በሀረም ክልል በግፍ ተገድለዋል፣ እነ አነስ ኢብን ማሊክ፣ ሰዒድ ኢብን ጁበይር ሀጃጅ ፊት ዟሊም መሪ መሆኑን በድፍረት ተናግረዋል))
መልስ፡- ወንድሜ ጉዳዩ እኮ አጭርና ግልፅ ነው፡፡ ከዚህም የበዛ ብትዘረዝር ጉዳዩ ላይ የሚጨምረው ነገር የለም፡፡ እነዚህ ሰዎች ሰልፍ አላደረጉምና!! ርእሳችን “ከዟሊም መሪ ፊት በድፍረት መናገር ይቻላል ወይስ አይቻልም?” የሚል አይደለም፡፡ እስኪ በሐጃጅ ላይ የተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎችን ዘርዝርልን፡፡ በየትስ ሀገር?
8. ((ዛሬ ዛሬ በአፍ ብቻ እንከተላችኋለን የምትሏቸው በተግባር ግን ፍፁም የራቃችኋቸው ኢማም አህመድና ኢብን ተይሚያህ ለጨቋኝ መሪዎች ሳይንበረከኩ እስርን ተቀብለዋል እናተ ግን አቂዳ ሲበከል፣ ሂጃብ ሲከለከል፣ መሳጂዶች ሲታሸጉ አንዲት ቃል እንኳ ተንፍሳችሁ አታውቁም ለመቃወምም አልወደዳችሁም፣ አቧራ እንዳይነካችሁ ዳር ሆናችሁ አያችሁ ኧረ እንደው ድጋፋችሁ ቀርቶብን ሸራችሁን እንኳ ይዛችሁ በተቀመጣችሁ…))
መልስ፡- መልካም እናንተ በተግባር እነ ኢማሙ አሕመድን ትከተላላችሁ እንበል፡፡ ነገር በሙግት ካለመሆኑም ጋር፡፡ እስኪ ንገረን ኢማሙ አሕመድና ኢብኑ ተይሚያስ ሰልፍ ቀስቅሰዋል? በጊዜያቸውስ ሰልፍ ተደርጓል? ያ አኺ ከስሜት ራቅ ብለህ አውራ እንጂ!! (አንዲት ቃል ተንፍሳችሁ አታውቁም ለመቃወምም አልወደዳችሁም) ስትል ሰልፉን ከሆነ እውነት ብለሃል፡፡ ሰልፉን እየተቃወምን እንዴትስ እንገባበታለን? የአሕባሽን ብልሹ ዐቂዳ በማጋለጥ በኩል ከሆነ እንዳቅሚቲ እንሰራለንና ባትዋሽ መልካም ነው፡፡ ለማንም ግን ሪፖርት ማድረግ አይጠበቅብንምና ባታውቅም አይግረምህ፡፡ ግን ያ አኺ አንዲት ቃል እንኳን ተንፍሰን እንደማናውቅ ምን አሳወቀህ? እራስህን ምን አድርገህ ብትስል ነው? ቆይ አንተ የሩቅ ሚስጥር ታውቃለህ እንዴ? ነው ወይስ ሰው ሁሉ የሚሰራውን ላንተ ሪፖርት ሲያቀርብ እኛ ቀረን? እውነት የዐቂዳ መበከል ቆርቁሯችሁ ከሆነ አብዛሃኛው ህዝብ የአሕባሽን ብልሹ ዐቂዳ ስለማያውቅ ቢያንስ ለሰልፍ የምትቀሰቅሱትን ያክል ስለዐቂዳ አስተምሩ፡፡ አብሬት፣ አልከሶ፣ ዳንግላ … በተለያዩ የመውሊድ ቦታዎች የሚፈፀመውን ሺርክ ሰልፍ በምትቀሰቅሱባቸው ሚዲያዎቻችሁ አስተምሩ፡፡ “ዐቂዳ ሲበከል” ማለትህ ግን ፍርደ-ገምድልነትህነ ነው የሚያሳየው፡፡ ማነው ዐቂዳ የሚበክለው? አሕባሽ? የሚሊኒየሙ ስምምነት ምን አይነት ዐቂዳ ካላቸው ጋር ነው የተደረገው? ቻግኒ ላይ ከማን ጋር ነው ስምምነት የተደረገው? ከቲጃኒያ ጋር!! ቲጃኒያ ከአሕባሽ ይሻላሉ? “ኢትዮጵያ ውስጥ የዐቂዳ ልዩነት የለም” ያለው ማነው? “መውሊድ አይለያየንም” ያለው ማነው? “ሱፍያ እና ሱኒ እያላችሁ አትበጥብጡ፡፡ ሁሉም አንድ ነው፡፡ ልዩነቱ የነጭ ሸሚዝና የጥቁር ሸሚዝ አይነት ነው” ሲል የነበረው ማነው? እኛ ነን? “ኢትዮጵየዊ እስልምና ኢትዮጵያዊ ወዙን እንደያዘ መቆየት አለበት” የሚለው ማነው? “አሽዐሪ በመሆኔ እኮራለሁ” የሚለውስ ማነው? “ኢትዮጵያ ውስጥ እንጨትና ድንጋይ የሚያመልክ የለም” እያለ ወደተውሒድ የሚጣሩ ሰዎችን የሚያሳጣው ማነው? ይልቅ ልንገርህ አንድ መስጂድ ያጋጠመውን፡፡ “የከፋ አደጋ ስለመጣብን በጋራ እንስራ” ተባለና “በእከሌ መስጂድ ደዕዋ ማድረግ ትችላላችሁ” አሉ፡፡ በጄ፡፡ “ባይሆን ተውሒድ እንዳታደርጉ ሰው እንዳይበተን” ብለው አረፉ፡፡ አሁን ይሄ ህብረታችሁ በተውሒድ ላይ እንዳልሆነ አያሳይም? አሁን እነዚህ ናቸው የተበከለ ዐቂዳ የሚያስተካክሉት? ተውሒድ ካልተናገርንማ መጅሊሱስ መቼ ይከለክለናል? እኔ እራሱ ያጋጠመኝን ልንገርህ፡፡ ሶስት የተለያዩ የደዕዋ ቦታዎች ላይ አሕባሽን በመቃወም ስንት ጊዜ ሰልፍ የወጡ ሰዎችን “እስኪ የአሕባሽን ብልሹ ዐቂዳዎች ንገሩኝ” ብየ ጠይቄ በጣት የሚቆጠሩ ናቸው ጥቂት ትክክለኛ መልስ የሰጡኝ፡፡ እንዳውም ያንዳንዶቹ መልስ አስደንጋጭ ነበር፡፡ የአሕባሹን የአህሉሱና የሱናውን የአሕባሽ አቋም አድርገው የሚናገሩ ሁሉ አጋጥመውኛል፡፡
9. ((በጉዳዪ ላይ የዑለማዎችን አስተያየት መጠየቅ እንኳ ካለብን ተጨባጩን የሚያውቁ የሀገራችን ዑለሞች በቂ መልስ አላቸው ወይስ ከባህር ማዶ ካሉ ዐሊሞች በቀር ፈትዋን አንቀበልም ነው (የሱዑዲ ዑለሞች ወህይ አይወርድላቸውም እኮ ) …)
መልስ፡- ትርፍ ቃል ባትናገር መልካም ነበር፡፡ ጉዳዩ ግን እግር ኳስ አይደለም፡፡ የኛ ሲሆኑ መደገፍ የሌላ ሲሆኑ መንቀፍ አይደለም ነገሩ፡፡ ሐቁ ከምንጠላውም ቢመጣ እንቀበላለን፡፡ ባጢሉ ከምንወደውም ቢመጣ እንቃወማለን፡፡ አንተ የምታጣቅሰው ሙፍቲ ከቲጃኒያ ጋር “ታረቁ” ቢል፣ ከሱፍያ ጋር እርቅ ቢፈፅም የፈለገ ቢቀርበን ዋጋ አንሰጠውም፡፡ የባህር ማዶ ስለሆነ ስላልሆነ አይደለም፡፡ ከጠቀስካቸው ውስጥ በግልፅ “ኢትዮጵያ ውስጥ የዐቂዳ ልዩነት የለም” የሚሉ አሉ፡፡ እንቀበላቸው? እንግዲያው አሕባሽ ምን አረጋቸው? ከጠቀስካቸው ውስጥ በሃሳብ ስላልተጋራናቸው ብቻ ሲያሻቸው “ተክፊር” ሲላቸው መዳኺላ” የሚሉን አሉ፡፡ ወላሂ ሺ ጊዜ ቢያስተጋቡ እኛ አንድም ሙስሊም አላከፈርንም!! የመድኸሊ ተከታዮችም አይደለንም!! “ስም አትለጥፉ” ትላላችሁ እናንተ ግን ትለጥፋላችሁ፡፡ ለፈትዋ ካጨሃቸው ውስጥ አወልያን መንግስት እንዲረከበው ያመቻቸ፣ ተቃውሞውን ለማርገብ ውጭ ድረስ ሄዶ በጥፊ የተመታ አለ፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው? “በሬ ካራጁ ይውላል፡፡” ግን እኔ እምልህ እሺ “ሰልፉ ይፈቀዳል” ብለን እንስማማ፡፡ በሰላት መጫወቱንስ ምን እንበለው? ሰልፉ ሲኖራችሁ ጣሃን ተከትላችሁ ትሰግዳላችሁ፡፡ ሌላ ጊዜ አድማ ትመቱና “ኮማንደር ብቻውን ይስገድ” ብላችሁ ትቀራላችሁ፡፡ ጣሃ ትላንትም ዛሬም ጣሃ ነው፡፡ አሕባሽ ከመምጣቱም በፊት በግልፅ ለሺርክ የሚሟገት ነው፡፡ በመላው ኢትዮጵያ የሰላት አድማ ካረጋችሁ እሄው ስንት ጊዜያችሁ? ጀማዐ የለ ጁሙዐ የለ!! “አሕባሽን ተከትሎ መስገድ አይቻልም” ካላችሁ ለምን የሰልፉ እለት ተከትላችሁ ትሰግዳላችሁ? መስገድ ከተቻለስ ይሄ ሁሉ በሰላት መጫወት ለምን? በተረፈ የተቃውሞ ቀን “5 ጊዜ አላሁ አክበር” “ስንት ደቂቃ ለታሰሩት ዱዓ” የምትሉት ቢድዐ አይደለም? ሸሪዐው ያልገደበውን በቁጥርና በመጠን መገደብ ቢድዐ አይሆንም?
10. (በመጨረሻም ኢሊያስ አህመድ በሚላት ወርቃማ ንግግር እቋጫለሁ፡፡ … “ሰዎችን ከሱና ማውጣት ከባድ ነው”) ብለሃል፡፡
መልስ፡- ኧረ ይሄ የኢማሙ አሕመድ እንጂ የዳዒ ኢሊያስ ንግግር አይደለም! ስታዳምጥም ስታነብም ስትፅፍም ከልብ ሁን እንጂ!! ሳያረጋግጡ ወሬ ለምን? “የጂብ ችኩል ቀንድ ይነክሳለ” ይባላል፡፡ የኢማሙ አሕመድ ንግግር ደግሞ ጥንቃቄና ማጣራት እንደሚገባ ለማሳሰብ እንጂ ጭራሽ እንደማይቻል አያመላክትም፡፡ እራሳቸው ኢማሙ አሕመድ እኮ በስም የሚጠቅሷቸው ሙብተዲዖች አሉ!!
11. በመጨረሻ ስናስተምር መሳደብ እንደማይገባን መክረኸናል፡፡ ምክርህን እንቀበልሃለን፡፡ ግን 3 ነገሮችን ማንሳት እወዳለሁ፡፡
A. ስድብ ስትል ምን ማለትህ ነው? ተብሊጉን “ተብሊግ” ሱፍዩን “ሱፊ” ኢኽዋኑን “ኢኽዋን” ማለታችንም ከዚህ ይገባል? ከሆነ በዚህ ስሌት መሰረት አሕባሹን “አሕባሽ” ማለት ይቻላል? እያስተዋላችሁ ተናገሩ! ከዚያ ባለፈ ፀረ-ተውሒድነታቸው በገሃድ የሚታይ የማይታበል ሐቅ ነው!!
B. ሌሎች እኛን የሚሳደቡትን በውስጥ መልእክት እንደምትመክር ነግረኸናል፡፡ እነሱን በጓዳ እኛን ባደባባይ አቶ ሙሐመድ? ህሊናህ አይታዘብህም? ሚዛናዊ ለመመስል ያደረግከውን ጥረት እርቃን አላስቀረብህም?
C. ደግሞስ ያንተንስ ስድብ ምን እንበለው? እስኪ ይቺን አጭር ንግግርህን ላስታውስህ፡፡ (ዛሬ ዛሬ በአፍ ብቻ እንከተላችኋለን የምትሏቸው በተግባር ግን ፍፁም የራቃችኋቸው ኢማም አህመድና ኢብን ተይሚያህ… እናተ ግን አቂዳ ሲበከል፣ ሂጃብ ሲከለከል፣ መሳጂዶች ሲታሸጉ አንዲት ቃል እንኳ ተንፍሳችሁ አታውቁም ለመቃወምም አልወደዳችሁም ፣ #አቧራ_እንዳይነካችሁ ዳር ሆናችሁ አያችሁ ኧረ እንዳው ድጋፋችሁ ቀርቶብን#ሸራችሁን_እንኳ_ይዛችሁ_በተቀመጣችሁ_መልካም_ነበር፡፡#የፌይዝ_ቡክ_ፈዲለተ_ሸይኾችን እንጂ ሌሎችን አይመለከትም) “የፌይዝ ቡክ ፈዲለተ ሸይኾች” እያሉ መሳለቅ ስድብ አይደለም? “ከኛ በላይ ነፋስ ብላችሁ የምትፎክሩበት” እያልክ ማንጓጠጥህስ ምን ይሆን ስሙ? ስድብ አታውቅም ወይስ “እኛ እንስደባችሁ እናንተ ዝም በሉ” ነው ነገሩ? እራስህን እንዴት ብትስልስ ነው #ሰላማዊ_ተቃውሞ_በሸሪዐ_መነፅር !” ብለህ የፃፍከው? እስኪ ማነው እራሱን እየኮፈሰ ያለው?
12. (በሀገራችን ኢኽዋን ያላችሁት እንጂ ኢኽዋን ነኝ ያለ አንድም ዐሊም ወይም ዳዒ የለም) ብለሃል፡፡
መልስ፡- ወንድሜ መላው ኢትዮጵያ ያጠናህ ይመስል እንዲህ በድፍረት ባትናገር መልካም ነው፡፡ “እኔ እንደሌሎቹ ኢኽዋኖች የምፈራ እንዳይመስልህ! ኢኽዋን እንደሆንኩ በግልፅ እነግርሃለሁ” የሚል አለ፡፡ ከራሱ ባለፈ እያስተላለፈ ያለው መልእክት ግልፅ ነው፡፡ አሁን ካለበት ሁኔታ ስሙን ማንሳቱ ጥሩ ስላልሆነ ነው የተውኩት፡፡
ሳጠቃልል ይህን በሁለት እግሩ የሚቆም ጠንካራ ማስረጃ የሌለው ሰልፍ በመቃወማችን ሲያሻቸው እንደ ቅጥረኛ ሲላቸው እንደ አይሁድ ከሚገልፁን ችኩሎች በንፅፅር የተሻለ አቀራረብ ስላየሁ ሳላመሰግን አላልፍም፡፡ አንዳንድ ነጥቦችን በተመለከተ ፅሁፌ ስለረዘመ በሌላ ጊዜ እመልሳለሁ ኢንሻአላህ፡፡