Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

“ካህያ ቆዳ የተሰራ ቤት ይበታተናል ጂብ የጮኸለት”

“ካህያ ቆዳ የተሰራ ቤትይበታተናል ጂብ የጮኸለት”በተውሒድ ሒሳብ በተውሒድ ኪሳራ የሚቋቋም አንድነት ለሐቅ ሳይሆን ለስሜት፣ በፅናት ሳይሆን በምርቃና... የኢማን የሱናን ጣእም በማጣጣም ሳይሆን ጠላትን በመፍራት በእልህ ላይ የተመሰረተ “አንድነት” ነው፡፡ አዎ አንድነት ሃይል ነው፡፡ ነገር ግን መሰረቱ ተውሒድና ሱና ላይ መጣል አለበት፡፡ ያለበለዚያ አንዱ አንዱን የሚበላ፣ የጎሪጥ የሚተያይ፣ ልብ ለልብ የተራራቀ ሆኖ ሳለ በአካል ብቻ ተሰባስቦ “አንድ ነን” ቢባል አንድነቱ ከመፈክር አያልፍም፡፡ እርግጥ ነው አንድነት ከታዘዝንባቸው ታላላቅ ነገሮች ውስጥ ነው፡፡ ከተውሒድ በላይ ግን አይደለም፡፡ አዎ አንድነት የሙስሊሞች ታላቅ እሴት ነው፡፡ ነገር ግን በመልካም የማዘዝና ከመጥፎ የመከልከል ድንቅ የኢስላም እሴት ክርችም ተደርጎ የሚዘጋበት አይደለም፡፡ ዛሬ ግን እየሆነ ያለው በተለያዩ ጥፋቶች ላይ የተዘፈቁ ወገኖችን “እንዳናርቅ” በሚል ማመካኛ በሰፊው የተንሰራፉ ጥፋቶችን ማስጠንቀቅ አልተቻለም፡፡ ከህዝቡ ዘንድ ያሉ ጥፋቶችን ገሸሽ አድርጎ ብዙሃኑን የሚያስደስቱ ርእሶችን እየመረጡ ሁሌ መደጋገም የዛሬ “ዱዓቶች” ልዩ መገለጫ ሆኗል፡፡
ቃሚዎች ጫት ሲነካ ከተቆጡ፣ ሙዚቃ የሚያዳምጡት ሙዚቃ ሲነካ “ጃሎ” ካሉ፣ ቢድዐ ላይ የወደቁት ቢድዐ ሲነካ ቢንዘፈዘፉ፣ ልብሳቸውን የሚጎትቱ ወንዶች ይሄ ርእስ ሲነሳ ካበዱ፣ የኢኽዋን ቫይረስ ያለባቸው ሰዎች ይቆጣሉ ብለን ኢኽዋን ሲፈነጭ ዝም ካልን፣ ተብሊጎች እንዳያኮርፉ ቢድዐና ሺርካቸውን እንዳላየን ከዘለልን፣ ... ስለምን እናውራ? ባል ሚስቱን ከጭቃ የጠፈጠፋት ይመስል እንዳሰኘው እየሰራት ዘወትር ስለባል ሐቅ ብቻ መስማት ካማረው፣ ሚስት የሴቶች “መብት” ሽውታ መትቷት ወንዱም እንደሴቷ አርግዞ ይውለድ አይነት ቅጥ ያጣ ትርምስ ውስጥ ከገባች ስለምን እናውራ? በምናስተምረው ጉዳይ፣ በማስተማር ዘያችን ላይ የዲኑን መመሪያ ሳይሆን የሰዎችን ስሜት ተከትለን የምንፈስ ከሆነ ስለምን ማውራት ይቻላል? ህዝቡ ላይ ያለውን ችግር ጥለን ታሪክ እያወራን ብናስደምማቸው እውን በዚህ መልኩ አንድነት ይጠበቃልን? እውን በዚህ መልኩ የህዝባችንን ክብር ማስመለስ ይቻላልን?
በዚያን ሰሞን ነው፣ አንድ ወጣት “ለምንድ ነው ተውሒድ ቅድሚያ ተሰጥቶት ትኩረት የማይደረግበት መቼስ ተውሒድ በኢስላም ያለው ቦታ፣ ሺርክ ያለው አደጋ ከባድ እንደሆነ ይታወቃል” የሚል ጥያቄ ቢነሳ ወጣቱ
“በአሁኑ ሰዐት ሺርክ አያሰጋንም፡፡ ስንት ምእራብ ወለድ ርእዮተ አለሞች እየሰረጉ በፈጣሪ መኖር ላይ ብዥታ እየፈጠሩ፣ “አላህ አለ ወይስ የለም” እያሉ በርካቶች በሚወላውሉበት በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን እንዴትስ ሺርክ ህልውና ይኖረዋል? እንዴትስ በዚህ ዘመን ፍጡር የሚያመልክ ይኖራል?” በማለት የዋሆችን የሚያስተኛ ግን እጅጉን ከእውነታ የራቀ ድምዳሜ ይሰራል፡፡ አልቆየም “ሃጂ” ታምራት ነው ቄስ ታምራት መጣና መሀል አዲስ አበባ ላይ “የነቃውን” የአዲስ አበባ ህዝብ በሺርክ እያጨማለቀ፣ ለመግለፅ በሚሰቀጥጡ ርካሽ ምግባሮች እየተጫወተበት በቴሌቪዥን ታዬ፡፡ አገር ተደመመ፡፡ ብዙዎቹን ያስደነቀው የተፈፀመው ሺርክ ሳይሆን ብልግናዎቹና ሽወዳዎቹ ነበሩ፡፡ ብዙዎቹ ያዘኑት ስለሰለባዎቹ ሞራል፣ አላግባብ ስለተመዘበሩት ንብረታቸው ነበር፡፡ የሺርክን አስከፊ ገፅታ ካልተረዳ ወገን ከዚህ የተሻለ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ ጌታችን “በአላህ የሚያጋራ ልክ ከሰማይ እንደወደቀ ነው፣...” ፤ “የሚያጋራበትን አይምርም” ይላል፡፡ እነ “ሙሐመድን” እና “ፋጢማን” ያስደመማቸው ግን ሺርኩ ሳይሆን ሌላው ነበር፡፡ ከታምራት እኩይ ምግባር የከፋው መርዶ ግን “የንቁዎቹ” እንቅልፍ ነበር፡፡
ያኔ አስተዋይ ቢኖር አስደንጋጭ ደወል ነበር የተደወለው፡፡ ህዝባችን ገና በሺርክ አሮንቃ ውስጥ እንደተዘፈቀ የሚያረዳ አሳዛኝ እውነታ ነበር፡፡ ዛሬም በየጓዳው ያደፈጡ በርካታ ታምራቶች አሉ፡፡ ዛሬም በርካታ ህዝብ ወደ ሺርክ ፋብሪካዎች ይመላለሳል፡፡ ዛሬም ግን በርካታ ሰፍተው ሰፍተው የተንቦረቀቁ ወጣቶች አሉ፡፡ ተውሒድን ችላ ማለታቸው አልበቃ ብሎ፣ ሺርክን አለማስጠንቀቃቸው አንሶ የዘወትር ህልማቸው፣ የሁልጊዜ ሩጫቸው ወደ ተውሒድ የሚጣሩ ሰዎችን ስም ማጥፋት ነው፣ ለተውሒድና ለሱና ደዕዋ ደንቃራ መሆን፡፡ ታዲያ ይህን መሰሪ ስራቸውን ይህን አደገኛ መርዛቸውን በማር ጠቅልለው ነው ወደ ህዝብ የሚያቀርቡት፡፡ ያለበለዚያማ ገበያው አይደራም፡፡ እናም “አንድነት” “አንድነት” ሲሉ ነጋ ጠባ ያስተጋባሉ፡፡ ወደ ተውሒድ የሚጣሩትን ለኡማው አንድነት አስጊ እንደሆኑ ሌት ከቀን ይወተውታሉ፡፡ በየመውሊዱ፣ በየመሳጂዱ፣ በየመቃብሩ፣ በየዛፉ፣ ... የሚታዩት ሺርካሺርኮች ግን “የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ” ካልተባለ በቀር ታሪክ አይደሉም ዛሬም በገሃድ ይታያሉና፡፡ ከኢስላማዊ ድርሳናት መረዳት እንደሚቻለው ነብያት ሲላኩ የነበረው ከሚላኩበት ህዝብ ውስጥ ምርጥ ከሆነው ክፍል ነበር፡፡ ከዚያም በላይ ከነብይነታቸውም በፊት በመልካም ስብእና የታወቁ ለሌሎች ምሳሌ መሆን የሚችሉ ነበሩ፡፡ ያም ሆኖ ግን ትምህርታቸውን ህዝባቸው ዘንድ ከተንሰራፋው ሺርክ በመጀመራቸው ምክኒያት ተደብድበዋል፣ ተባረዋል፣ ተገድለዋል፡፡ አስር እንኳን የሞላ ተከታይ ያላገኙ ሁሉ አሉ፡፡ ኧረ አንድም ሰው እንኳን ያልተከተላቸው አሉ፡፡ “ሒክማ” ስላልነበራቸው ግን አልነበረም፡፡ አንድነት ስላላሳሰባቸውም አልነበረም፡፡ ሁሉን በሚደላው ቢያናግሩት ኖሮ ሁሉ ቢቀር አብዛሃኛውን መያዝ አያቅታቸውም ነበር፡፡ ግና ሁሉን ለመያዝ በሚል የተጣለባቸውን መሰረታዊ የተውሒድ ተልእኮ ገሸሽ ሊያደርጉት አልተቻላቸውም፣ አላደርጉትምም፡፡
ሺርክን፣ ቢድዐንና የህዝባችንን ሞራል አንኮታኩተው የሚያጠፉ በሰፊው የተንሰራፉ አደገኛ ወንጀሎችን እያለፉ “አንድነትን እንገነባለን” ማለት በከንቱ መባዘን ነው፡፡ አይቻልም እንጂ አንድነቱ ለጊዜው ቢገነባ እንኳን እንዲህ አይነቱ አንድነት ካህያ ቆዳ የተሰራ ቤት ማለት ነው፡፡ ይሄ ነው የሚባል እርባና የሌለው፡፡ “ካህያ ቆዳ የተሰራ ቤት ይበታተናል ጂብ የጮኸለት!!” ይባላል፡፡