Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

እኩይ (ሽርክን፣ቢድዓን) ተግባርን እያዩ ዝም ማለት



እኩይ (ሽርክን፣ቢድዓን) ተግባርን እያዩ ዝም ማለት :-

1) የሙስሊሞችን መንገድ መፃረር ነው
2) ዕውቀትን መደበቅ ነው
3) የደካማ ኢማን ምልክት ነው
4) ሙስሊሞችን መክዳት ነው
5) የኢኽ ዋኖች አካሄድ ነው
6) ያንን እኩይ ተግባር መውደድ ነው
7) የአይሁዶችና የክርስቲያኖች አካሄድ ነው
8) የኒፋቅ ምልክት ነው
ስለዚህም መጥፎን ተግባር ማስጠንቀቅና ሃቅን ግልፅ ማድረግ ግዴታ ነው ፤ በምንም ሁኔታም ይሁን በየትኛውም ቦታ መጥፎ ተግባርን ማውገዝ ይኖርብናል ፤ ስለ ሰው ክብርና ማንነት ትጨነቅ ይሆናል ግን በዛ ሰው ስህተት የሚያልቁት የሺዎቹስ ህይወት? 

1) የሙስሊሞች መንገድን መፃረር ነው
(( በበጎ ነገርና አላህን በመፍራትም ተረዳዱ፤ ግን በኃጢያትና ወሰንን በማለፍ አትረዳዱ አላህንም ፍሩ አላህ ቅጣተ ብርቱ ነውና)) [ማኢዳህ : 2]
እናም..
(( ለሰዎች ከተገለጸች ሕዝብ ሁሉ )በላጭ ሆናችሁ፤ በጽድቅ ነገር ታዛላችሁ ከመጥፎም ነገር ትከለክላላችሁ በአላህም (አንድነት) ታምናላችሁ፤ የመጽሐፉም ሰዎች ባመኑ ኖሮ ለነርሱ የተሻለ በሆነ ነበር፤ ከነርሱ አማኞች አሉ፤ አብዛኞቻቸዉ ግን አመጸኞች ናቸው)) [ዒምራን:110] 
እናም..
(( ከናንተም ወደ በጐ ነገር የሚጠሩ፣ በመልካም ሥራም የሚያዙ፣ ከክፉ ነገርም የሚከለክሉ፣ ህዝቦች ይኑሩ። እነዚያም እነሱ የሚድኑ ናቸዉ)) [ዒምራን::104] 

2) ዕውቀትን መደበቅ ነው
(( እነዚያ ከአንቀጾችና ከቅን መምሪያ ያወረድነውን ለሰዎች በመጽሐፉ ከገለጽነው በኋላ የሚደብቁ፤ እነዚያ አላህ ይረግማቸዋል፤ ረጋሚዎችም ሁሉ ይረግሟቸዋል)) [በቀራህ:159]
ረሱል ሰለላሁአለይሂወሰለም እንዲህ አሉ:-
<< ምንኛውም ሰው ስለሚያውቀው ነገር ተጠይቆ ነገር ግን ያን ነገር ከደበቀ በእሳት በእሳት ልጓም ይለጎማል >>
ቲርሚዚ አልባኒ ሰሂህ ብለውታል

3) የደካማ ኢማን ምልክት ነው
ረሱል ሰለላሁአለይሂወሰለም እንዲህ አሉ:-
<< መጥፎን ነገር ያየ በእጁ ይከልክል ካልቻለ በምላሱ ካልቻለ በልቡ ይጥላ ይሄ የኢማን ደካማው ነው >> 
ሰሂህ ሙስሊም 

4) ሙስሊሞችን መክዳት ነው
ረሱል ሰለላሁአለይሂወሰለም እንዲህ አሉ:-

<< የአላህን ትዕዛዛት የሚያከብርና የሚፈፅም እና አመፀኛውና መጥፎ ሰሪ ምሳሌያቸው ልክ አንድ መርከብ ላይ እንደተሳፈሩ ሰዎች ናቸው..
ግማሻቸው በላይኛው የመርከቡ ክፍል ሲቀመጡ ቀሪዎቹ በመርከቧ ስረኛው ክፍል ተቀመጡ ፤ የታችኞቹ ሰዎች ውሃን ፍለጋ ወደላይ ይወጣሉ እናም ያስቸግሯቸዋል ፤ ከታችኞቹ ሰዎች ውስጥ አንደኛው መፍለጫውን አንስቶ የመርከቡን እንጨት መብሳት ያዘ ፤ ከዚያም የላይኞቹ ሰዎች 'ምንድነው ችግርክ ለምን እንዲ ታደርጋለክ?' ብለው ጠየቁት እሱም 'እላይ እየተመላለስኩ እናንተን ከማስቸግር እንዲህ ባደርግ ይሻላል ብዬ ነው' አላቸው ፤ እናም እሱን ከዚህ ተግባሩ ቢከለክሉት እሱም እነሱም ይድናሉ (መርከቧ ከመስመጥ) ፤ ነገር ግን ዝም ካሉት እነርሱም እሱም ይጠፋሉ 
ሰሂህ ቡኻሪ

5) የኢኽዋኖች አካሄድ ነው
የዘወትር መፈክራቸውን ማየት በቂ ነው
በተስማማንበት ነገር አንድ እንሆናለን ባልተስማማንበት ዝም እንባባላለን 
(ልብ ይበሉ እንተራረማለን ሳይሆን ዝም እንባባላለን ነው) ..አላህ ግን እንዲህ ብሏል

((በማንኛውም ነገር ብትከራከሩ በመጨረሻው ቀን የምታምኑ ብትሆኑ (የተከራከራችሁበትን ነገር) ወደ አላህና ወደ መልክተኛው መልሱት ይህ የተሻለ መጨረሻውም ያማረ ነው))
[ኒሳእ: 59]

6) ያንን እኩይ ተግባር መውደድ ነው (ወይንም ከርሱ አለመራቅ ነው)

(( በእናንተም ላይ በመጽሐፉ ውስጥ የአላህን አንቀጾች በርሷ ሲካድባትና በርሷም ሲላገጥባት በሰማችሁ ጊዜ፣ በሌላ ወሬ ውስጥ እስከሚገቡ ድረስ ከነርሱ ጋር አትቀመጡ ማለትን በእርግጥ አወረደ፤ እናንተ ያን ጊዜ ቢጤያቸው ናችሁና አላህ መናፍቃንን እና ከሐዲዎችን በሙሉ በገሀነም ውስጥ ሰብሳቢ ነውና)) [ኒሳእ:140]

7) የአይሁዶችና የክርስቲያኖች አካሄድ ነው 
(( አላህ የነዚያን መጽሐፉን የተሰጡትን (አይሁዶችና የክርስቲያኖች) ቃል ኪዳን ለሰዎች በእርግጥ ታብራሩታላችሁ፥ አትደብቁትምም፥ በማለት የያዘባቸዉን (አስታዉሱ)፤ በጀርባዎቻቸዉም ኋላ ጣሉት፤ በርሱም ጥቂቱን ዋጋ ገዙ፤ የሚገዙትም ነገር ከፋ))
[ዒምራን: 187]
(( እነዚያ መጽሐፍን የሰጠናቸው ወንዶች ልጆቻቸውን እንደሚያውቁ (ሙሐመድን) ያውቁታል፡፡ ከነሱም የተለዩ ክፍሎች እነርሱ የሚያወቁ ሲኾኑ እውነቱን በእርግጥ ይደብቃሉ)) [በቀራህ: 146]

8) የንፍቅና ምልክት ነው
((መናፍቃንና መናፍቃት ከፊሎቻቸው ከከፊሉ ናቸው፤ በመጥፎ ነገር ያዛሉ፤ ከደግም ነገር ይከለከላሉ፤ እጆቻቸዉንም (ከልግስና) ይሰበስባሉ፤ አላህን ረሱ ስለዚህ (እርሱ) ተዋቸዉ፤ መናፍቃን አመጠኖቹ እነሱ ናቸዉ)) [ተውባህ : 67]
______________
አላህ ሁሌም በጥሩ ከሚያዙና ከመጥፎ ከሚከለክሉ ባሮቹ ያድርገን