Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ጣፋጭ መርዝ/ሊነበብ ተጻፈ!


ጣፋጭ መርዝ/ሊነበብ ተጻፈ! እስቲ ደግሞ ስለ መርዝ ጥፍጥና ሳይሆን ስለ ጣፋጭ መርዝነት አልቀን እናውጋ:: ብንደብቀው የማይደበቅ፥ ብንሸፍነው የማይሸፈን፥ ብናለብሰው የሚገለጥ፥ በድን ሬሳ መስሎ ውስጥ ውስጡን የሚኖር፥ ውስጥ ውስጡን የሚገድል የሆነ አንድ ጉዳይ ማንሳት ፈልጌ ነው:: አዎን የብዙሀኖችን አንደበት የ’እፍረት’ ሸረሪት ድር ካደራበት ወዲህ ይሄን መርዝ ያላጣጣመ ጎበዝ በከተማው ይኖራል ማለት ከንቱ ነው:: በርግጥ እፍረት ልክ አለው፥ ልኩ ካልተጠበቀለት ግን ለከት ያጡ ውጤቶች ይጠብቁታል:: መጨማለቅን ፍራቻ መጨማለቅን መውለድ ይሆናል:: ምናልባትም እኮ የዚህ መርዝ ጥፍጥና ተካፋይ ከሆኑት መካከል አንባቢው ሊካተት ይመቻል፥ ኸረ እንዲያውም ወደ እርግጠኝነት በጣም ተጠግቼ የውጤቱን ገፈት አብሳይ ባይሆን እንኳ ቀማሽ ነው እላለሁ::ስማኝማ! በአንድ ሰከንድ ስለ አንድ ጉዳይ በአማካኝ ከሀያ ዘጠኝ ሺህ 29,000 ጥያቄዎች በላይ የሚጥጠየቅ በነገሩ ላይም ጥልቅ አዋቂ የሆነ አንድ ቡድን አለ:: እንዴት? እንዴት ማለት ጥሩ፥ ባይሆን ከርእሴ ጋር በቀጥታ ለመፋጠጥ ይረዳኝ ዘንድ “በሰከንድ የሀያ ዘጠኝ ሺህ ሰውን ተመሳሳይ ጥያቄ ምን አመሳሰለው?” የሚል ሀሳብ ቢጤ ጭሬ ልነሳ:: እነሆ አዲስ መስመር ገባ ብዬ ተደጋግሞ ስለሚነሳው ጥያቄ ያቅሜን ያህል አትታለሁ ——– ያነበብኩትን ተመርኩዤ ማለቴ ነው::ወጣት ነህ፥ ወጣትነትህ ብዙ ነገር የሚጠብቅብህ ወጣት:: ከሚጥጠበቅብህ ነገር ዋነኛው ደግሞ ስሜት ነው:: ስሜት እራሱ በብዙ ይከፈላል፥ ቢከፈልም ግን ሁሉም ክፍሉ አንተን ይመለከትሀል:: ስፖርታዊ ስሜት፣ ጾታዊ ስሜት፣ ህዋሳዊ ስሜት፣ የገለፍተኝነት ስሜት፣ የትኩሳትና የሆድ ቁርጠት ስሜት እና ሌሎችም ብዙ ስሜቶች:: እዚች ቦታ ላይ ግን እኔም ስሜቴን ልገድብና በጣም ተፈጥሮአዊ የሆነውን ጾታዊ ስሜት ከእለት ተእለት ተግባሮችህ ተነስቼ አንዳንድ ቁምነገሮችን ልጠቁምህ:: በፌስ ቡክ የደንበኝነት ዘመንህ ቢያንስ አንድ ቀን እንኳ ማንነቷን የማታውቃትን ልጅ ዝርዝር መረጃ (Profile) ገብተህ ተመልክተህ ይሆናል:: ፎቶዎቿን ስታየውም ከእናቷ ጋር፣ ከጓደኞቿ ጋር፣ ከአሻንጉሊቷ ጋር (የፎቶ ቤቱ ቢሆንም)፣ እንደ ንብ አበባ ስትቀስም፣ በትምህርቷ ስትመረቅ፣ ስትስቅ፣ ሲደብራት፣ ሲደክማት እንደገና አሁንም ከእናቷ ጋር (አንድ ዙር አየኸው ብዬ ነው)፥ ከዛም የትውልድ ዘመኗን ቼክ ስታደርገው ከአንተ ዘመን ጋር ልክክ ያለ ነው:: ቀጥሎም ፈራ ተባ እያልክ “Single” የሚለውን የብቸኝነት ታፔላ ፍለጋህን ታጧጡፈዋለህ:: የአጋጣሚ ነገር ሆኖ የምትፈልጋቸው መረጃዎች በሙሉ ለትዳር እንኳ ባያደፋፍሩህ ለቻት ግን ከበቂ በላይ ሳይሆኑ አይቀሩም:: በቅንፍ ውስጥ: በፌስ ቡክ አውግቶ ለትዳር የታደለ ያለ አይመስለኝም፥ ምናልባት ተጋብተው የተጣሉ ጥንዶች ደግመው ታርቀውበት ካልሆነ በቀር:: እናም ቅንፉን ዘግተህ ስትመለስ በፍጹም የማይዘጋ የቻት መስኮት ላይ ለረጅም ሰአታት እንቶ ፈንቶ እያወራህ ታስመሻታለህ፥ እንቶ ፈንቶ ልጥጠፋዎቿን (Post) ሁሉ በመውደድ (Like) ትጠመዳለህ:: በአጠቃላይ እንቶ ፈንቶ ሆነህ ትቀራለህ:: ከጥቂት መግባባቶች በኋላም (መጋባቶች አላልኩም ልብ አ’ርግ) እርሷን ስታወራት ሰው እንዲያይህ አትጋብዝም፥ ትሸሸጋለህ፥ ትደበቃለህ፥ ትሰወራለህ:: ለማንኛውም ከዚህ ቀጥሎ በዚህ ገባ በዚህ ወጣ ማለት አስፈላጊ አልመሰለኝም፥ የአንባቢውን ግዜና ማገዶ ይቆጥባልና::አየህ! ስሜት የሚባለው ነገር ከየት እንደሚጀምር ጥርት ብሎ አያስታውቅም:: ማስታወቅ የሚጀምረው ለመውጣት አስቸጋሪው ቦታ ላይ ስትደርስ ብቻ ነው፥ ያኔ ብታውቀው ምንም አታመጣም፥ ብታመጣም አይበጅህም፥ ወድቀሀል:: አንድ ወሳኝ ምሳሌ ልጥቀስልህ:- ጾታዊ ፍላጎትን ግልጽ በማድረግ በኩል ከወንድና ከሴት የበለጠ ማን ይደፍራል? ወንድ! በትዳርም ይሁን ከትዳር ውጪ የሚደረጉ ጥያቄዎችን ማን ቀድሞ ያቀርባል? ወንድ! እምቢታ ቢያጋጥም ማን አብዝቶ ይለማመጣል? ወንድ! ንግግሮች ውጤት ማምጣት ሲሳናቸው ማን ለትግል ይጋበዛል? ወንድ! ወንድ! ወንድ! ሁሉንም ነገር ወንድ! መልካም: በተቃራኒው ቢያጋጥምህ ምን የምትሆን ይመስልሀል? እንጃ: ለማንኛውም ግን ተከተለኝ! ቆንጆ የሆነች ሴት በሩን ዘጋችበት፥ በክፍሉ ውስጥ ሁለቱ ወጣቶች ብቻ ቀሩ፥ እርሷም ብቻቸውን መሆናቸውንና ለእርሱም ብላ እንደተቆነጀች አበሰረችው፥ እፍረቷ ከዳትና ‘ጠ..የ..ቀ..ች..ው’:: በሚገርም ሁኔታ አጭር የእምቢተኝነት መልስ ሰጣት፥ እምቢታውንም በጉልበት ለመቀልበስ ሞከረች፥ ጉልበት የበዛበት ትግል አደረገች፥ ታግላ ታግላ ታግላ ልብሱን ቀደደችው:: አላህ ያሳይህ እስቲ አንዲት ቆንጆ ሴት ልጅ ደርሳህ ስታበቃ ዚና ካልፈጸምን ብላ ግብግብ ስትይዝህ:: እንዴት አይነት የስሜት ጥም ውስጥ ብትሰጥም ነው ልብስ እስከመቅደድ ድረስ ያደባደባት? በዛ ላይ ባለትዳር ስትሆንስ የበለጠ አይደንቅህም? ብቻ የሆነው ሆኖ የዚህን ወጣት ከሀራም የመብቃቃቱን ልዩ ሽልማት በሱረቱ ዩሱፍ ማብቂያ አካባቢ ፈልገው::ስሜት እጅግ በጣም አደገኛ ነው:: አደገኝነቱ ደግሞ በዱንያም ይሁን በአኼራ አስቸጋሪ ሊባል የሚችል አዘቅት ውስጥ መዶሉ ነው:: እዚህ ጋር “የምን አዘቅት?” የሚል ጥሩ ጥያቄ ተነስቷል:: የግድም መነሳት ነበረበት፥ ለማንኛውም ከተከታዩ ማስታወቂያ በኋላ በድጋሚ እንገናኛለን:: ማስታወቂያ:- አንባቢ ሆይ! ከላይ ለመንደርደሪያነት ከጻፍኳቸው አንቀጾች የበለጠ ቀጥለው የተቀመጡት ሀሳቦች የተሻለ ቁምነገር ስለጨበጡ እባክህን የዘወትር ጥሞናህ እታች ድረስ ይዝለቅ፥ አመሰግናለሁ:: ከአፍታ ቆይታ በኋላ ስንመለስ የምንዳስሰው ነጥብ በሶስት አበይት ክፍሎች መታየት ይችላል:: “ስሜት ላይ ምን ጣለን?”፣ “አዘቅት ብለን ያካበድነው ጉዳይ ምንድነው?” እና “ምን ተሻለን ታዲያ?”:: መልካም ንባብ!“ስሜት ላይ ምን ጣለን”? መውደቂያ አንድ: “Idle man’s mind is devil’s workshop” የሚል ቆንጆ አባባል አለ:: ሙስሊም በመሰረቱ ትርፍ ሰአት ሊኖረው አይችልም፥ ግን በአጋጣሚ ተረፈበት:: ለጀነት የሚያበቃውን ሚኒማ ካሟላ በኋላም ተጨማሪ ትርፍ ሰአት አገኘ ቢባል ይሄ እኔና አንተ አእምሮ ዘንድ ከእውነት ይቆጠራል? በፍጹም! አንድ ሙስሊም ሰአት ተረፈኝ ካለ እጅ ላይ የሚጠለቀውን የሰአት መቁጠሪያ እየጠቆመ መሆን አለበት (ሰአት መቁጠርያው ሰፋኝ ማለቱ ነው):: አለያ ግን ከባድ ክስረት ላይ መሆኑን አስረዳው:: በጠቃሚ ጉዳዮች ላይ በስራ መወጠር ግዜን በአግባቡ ከመጠቀም ባሻገር የወንጀል መስሪያ አጋጣሚዎችን ይቀንሳል:: በተለይ ደግሞ Internet ላይ ስትሆን አላማ ሳይኖርህ፥ እንዳው ዝም ብለህ “እከሌ ምን አለ”፣ “እከሊት ምን ሆነች” የሚለውን ለማየት ከሆነ ቀድሞውኑ የገባኸው፥ መውጫህ የሚሆነው አላህም ሰውም ባያየኝ የምትልበትን በርካታ አስቀያሚ መስኮቶችን ከከፈትክ በኋላ ነው::መውደቂያ ሁለት: ብቸኝነት፥ በተለይም በምኝታ ክፍልህ ውስጥ ያለምንም ስራ ብቻህን መቀመጥ:: እያወራህ ወይንም እየሰራህ ካልሆነ እያሰብክ ነው ማለት ነው፥ በተዘጋ ክፍል ውስጥ ሆነህ ስታስብ ስታስብ ስታስብ አሁንም በጣም ስታስብ “በሩን ቆልፍ ቆልፍ” የሚል ነገር ልብህ ላይ ይመጣል:: አንተም ትቆልፈዋለህ፥ የማትወጣበት የስሜት ገደል ውስጥ ወርውሮህ ይሮጣል:: ማን አባቱ ነው? አሁን ነው “ማን አባቱ” እያልህ “ዘራፍ” የምትለው? በቃ ተወው አንድ ግዜ ሮጧል::መውደቂያ ሶስት: ሙዚቃና ክሊፕ፥ ማንም ሰው በውል የማይረዳው የሙዚቃ ድብቅ ሀይል ስሜት ቀስቃሽነቱን ነው:: ቡና ቤቶች፥ መጠጥ ቤቶች፥ መሸታ ቤቶች ሌሎችም ዚና የሚበረክትባቸው ቤቶችን ካስተዋልክ ሞቅታውን የሚወልዱት በሙዚቃ ነው:: እዚህ ሙቀት ላይ ትንሽ አልኮሆል ቢጤ ቸለስ ስታደርግበት ይበልጥ ይግላል፥ ይበልጥ ይፍማል:: ይሄን ግለት ይዘህ፣ ይሄን ፍም ጨብጠህ ከአንዲት ክፍል ውጪ የት ሄደህ ትሰክናለህ?“አዘቅቶች”አዘቅት አንድ: መጥፎ ፍጻሜ፥ “እድሜውን በሙሉ የጀነት ሰዎችን ስራ ሲሰራ ይቆይና በእርሱና በጀነት መሀል የስንዝር ርቀት ስትቀረው የአዛብ ሰዎችን ስራ ሰርቶ ወደዛው ያመራል” የሚለው ሀዲስ ትዝ ይለኛል:: በፊት ላይ መጥፎ እና ጥሩ ፍጻሜ የሚባለው ነገር እድል ወይንም ሎተሪ ነገር ነበር የሚመስለኝ:: ነገር ግን ማናቸውም በድብቅ የሚሰሩ ወንጀሎች የማታ ማታ ፈልገኸቸው ሳይሆን ፈልገውህ በግልጽ ይታያሉ፥ በግልጽ ይሰማሉ:: አስበው እስቲ እራስህ፥ ዛሬ ላይ ማንም ሳያይህ ባለጌ የሆኑ ዌብሳይቶች ላይ ሰአታትን ታሳልፋለህ፣ በተዘጉ ክፍሎች ውስጥም ደፍሬ የማልጽፈውን ነገር ትሰራለህ፣ የኋላ ኋላም ሞት የሚባለው ነገር መጣህና ቤተሰብ ክብብ ብሎ ሸሀዳ ሲያስይዝህ “www.የማልጠቅሰው ሳይት.com” እያልክ ብትዘላብድ የቱ ጉድጓድ ይውጥሀል፥ የቱስ ቀብር ይሰፋሀል? ይታይህ: ገና ነገ ደግሞ አሊምነትህን፣ ጥሩነትህን በሚያውቁልህና በሚያደንቁህ ሰዎች መሀል “ዝሙተኛውን አሳልፉት፥ ና ወደዚህ” እየተባልክ ዛሬ ላይ ያጣኻውን እፍረት እጥፍ ድርቡን ስትከናነበው……ትንሽ እንኳ ደንገጥ አትልም?አዘቅት ሁለት: የልብ መታሸግ፥ ምንም መፍትሄ የሌለው ከባድ በሽታ! ትንሽ ወንጀል ከዛም ትንሽ ወንጀል ከዛም ትንሽ ወንጀል ከዛም ትልቅ ወንጀል ከዛም ከባድ ወንጀል ከዛም ቀላል ወንጀል (ልብህ ቀላልና ከባድ ወንጀልን መለየት አቁሟልና ነው ቀላል ወንጀልን በስተመጨረሻ የደገምኩት):: ቢያሳዩህ አታይም፥ ቢነግሩህ አትሰማም፥ ከሚያማክሩህ ቢተዉህ ትመርጣለህ፥ ከሚያጫውቱህ ቢርቁህ ትመኛለህ፥ ብቻህን ሆነህ በጥማት ላይ ጨዋማ ውሀን ትጎነጫለህ፥ እንደማስታገስ ታብሰዋለህ፥ በተጓዝክ ቁጥር መንገዱ እየራቀ እየራቀ እየራቀ ይወስድሀል:: ልብህ ልክ እንደ ኩባያ ይገለበጥና የአላህን ንግግር የሚያስተናግድበት ቀዳዳ አይኖረውም፥ ነገ ደግሞ አላህም በተራው ያንተን ልብ የሚያስተናግድበት ቦታ ይነሳሃል::አዘቅት ሶስት: ብቸኝነትን መሻት፣ ውስጣዊ ስቃይ እና ያቺ ያልኩህን ስራ ለት ተለት መደጋገም:: የምታውቀው ወይንም የምታምንበት እሴትና የምታደርገው ተግባር ሰማይና ምድር ሲራራቁ ግዜ ተስፋ ወደመቁረጥ ትጓዛለህ:: ማንም የማያውቅልህን ከባድ ህመም በውስጥህ ትታመማለህ:: መጥፎ ሱስ፣ መጥፎ ጓደኝነት፣ መጥፎ ልማድ ስታገኘውም ስታጣውም ያው ነው፥ ብታገኘውም መለየትን ፍራቻ ትጨነቃለህ፣ ብታጣውም ደግሞ እየናፈቀህ ታነባለህ:: በልተኸው አትጠግብም፥ ርቦህም አትለምድም፥ እየሰጠኸው “አምጣ አምጣ” ነው ጥያቄው::                      فما في الأرض أشقى من محب               وإن وجد الهوى حلو المذاق                          تراه باكيا في كل حين                                   مخافة فرقة أو لاشتياق                       فيبكي إن نأوا شوقا إليهم                          ويبكي إن دنوا حذر الفراق                     فتسخن عينه عند الفراق                              وتسخن عينه عند التلاقሌሎች በርካታ አዘቅቶች ተራቸውን እየጠበቁ ነበር:: ነገርግን አንድ ሰው ውስጡን ክፉኛ ተጎድቶ፥ ልቡን በገዛ እጁ አሳሽጎ፥ ኻቲማውን አበላሽቶ ሌላ ምን ጉዳት ቢደርስበት ይበልጥ ይሰቃያል? አንኳር ነጥቦቹን ለማንሳት ያክል ነው እንጂ እጄ ላይ ባለ አርባ ሰባት ገጽ ጥናታዊ ጽሁፍ ይዜ ነበር:: ለማንኛውም ፈጠን ብለን ወደ መፍትሄ ሀሳቦች እንሻገር::“ምን ተሻለን ታዲያ?” ምን ተሻለን አንድ: መቼም ማግባትን የሚስተካከል መፍትሄ አይኖርም፥ ባይሆን ጸሀፊው በዚህ ጉዳይ ላይ ጠልቆ መዘላበድ አልሆነለትም::ምን ተሻለን ሁለት: ሱና የሆኑ ጾሞችን ማብዛት፣ ወደ አላህ መመለስ፣ ከሌሊቱ ክፍል ጥቂት ግዜ በመውሰድ አላህን ማማከር:: ከዚና ጋር ተያያዥነት ያላቸው ማናቸውም ጥፋቶች በይዘታቸው “ድገሙኝ ድገሙኝ” የሚሉ እንጂ አንድ ግዜ ተከስተው የሚጠፉ አይደሉም:: በመሆኑም እንዳው አላህ ያንሳልህና በመደጋገም ብትቸገር እንኳ በደጋገምክ ቁጥር ወደ አላህ ከመመለስ እንዳትደክም፥ እንዳትሰለች! ከሌሊቱም ክፍል ለቅሶህን አሰማው፥ “ቢያየኝም ምንም አያመጣም’ ብለህ በግዛቱ ቆመህ ወንጀል ስትፈጽም እንዳልቸኮለብህ ሁሉ “እያየኝ ነው” ብለህ ከልብህ ስትጠራውም የበለጠ አዛኝ ነው ያንተ ጌታ::                       ألا يا عين ويحك أسعديني                    بغزر الدمع في ظلم الليالي                         لعلك في القيامة أن تفوزي                  بخير الدار في تلك العلاليምን ተሻለን ሶስት: ቁርአንን በተመስጦ መቅራት፣ ሙታንን መጎብኘት፣ በሽተኞችን መጠየቅ እንዲሁም እይታን መገደብ:: ቅድም እንደ ኩባያ የተገለበጠ ያልኩት ልብህን ወደ ቦታው ለመመለስ ነገን ማስታወስ ይገባሀል:: አላህ በቁርአን ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች “እኔን ፍሩኝ” እያለ ያስጠነቅቃል:: አንዲት አያ ላይ ግን እንደወትሮው አንድ ግዜ ብቻ “እኔን ፍሩኝ” ብሎ አላለፈም:: ይታይህ እንግዲህ በአንዲት አያ ላይ ሁለት ግዜ “እኔን ፍሩኝ” ካለ በኋላ በመካከላቸውም “ማንኛይቱም ነፍስ ለነገ ያስቀደመችውን ትመልከት” የሚል ተጨማሪ ከባድ ማስፈራሪያ ሀሳብ አኖረ:: ወዳጄ ሆይ! ነገ እኮ ከዛሬ ቀጥሎ ነው፥ ዛሬ ደግሞ የስሜት ባህር ውስጥ ነው ያለኸው፥ ለነገ የሚያዘጋጅ የተረፈ ግዜ ይኖርህ ይሆን? ሌላው እይታን መገደብ ከማይጨበጥ አለም ለመውጣት አይነተኛ መፍትሄ ይሆንሀል:: ልታገኛት የማትችላትን አይነት የተገላለጠች ሴት በየመስኮቱ ከምታሳድ “ጌታዬ ሆይ የተሻለችውን ለግሰኝ” ብለህ አንገትህን ብትደፋ ነገ አንገቶች በሚደፉበት ቀን የአንተን አንገት ቀና የሚያደርግ ስራ ሊሆንህ ይችላል::ወሬ አበዛህ ባትለኝ ኖሮ ሌሎች ነጥቦችን ባነሳሁ ደስ ይለኝ ነበር:: ለማንኛውም ግን በተነጋገርነው ሀሳብ ላይ እራስህን አጥብቀህ የማታምነው ከሆነ በተቻለ መጠን ብቸኝነትን አስወግድ:: ኢንተርኔት ስትጠቀምም ሰዎች በቀላሉ ስክሪንህን (Screen) በሚመለከቱበት ቦታ ላይ አኑረው፥ ያለ አላማም ወደ ኢንተርኔት አለም አትግባ፥ ያለ አላማ ከገባህ በአላማም አትወጣም:: ፌስቡክ ላይም እንደለመድከው “ማንም አያየኝም” ብለህ የምታያቸው ጸያፍ ምስሎችና ፊልሞች “እከሌ ይሄንን አየ” እያለ እየነገረን ስለሆነ ጥንቃቄ አድርግ፥ ያንተ ወንጀል እኛንም የሚያጠቃ በላእ እያወረደብን ሊሆን ይችላልና——-ጠንቀቅ ነው::አላህ ይርዳህ::