Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ዱዐ


ዱዐ
ሁሉም ፍጡር ከአላህ ከጃይ ነው። አላህ ዘንድ ያለው ያስፈልገዋል። እርሱ(አላህ) ደግሞ ከፍጡራኑ የተብቃቃና ሀብታም ነው። አላህ የሚለምነውን ይወዳል። እሱን በመለመን ችክ ባዮቹንም ባሮች ይወዳል። ለዚህም ነው ሶሀቦች ለትንሽ ነገር ቢሆን እንኳን አላህን ከመለመን የማይቦዝኑት።
የዱዐዕ ደረጃ፡- ዱዐ አላህ ዘንድ ትልቅ ደረጃ አለው፤ የአላህን ቀደር ሊመልስ/ሊቋቋም/ ይችላል። ዱዐ ከእንቅፋቶች ከፀዳና ቅድመ ሁኔታው ከተሟላ ተቀባይነት አላው። አላህ(ሱ.ወ) እንዲህ ይላል
«ጌታችሁም አለ ለምኑኝ እቀበላኋለው፤እነዛ እኔን ከመገዛት የሚኮሩት ተዋራጆች ሆነው ጀሀነም ይገባሉ» 46፡60
«ባሮቼ በጠየቁህ ጊዜ እኔ ቅርብ ነኝ፣ የለማኝን ፀሎት በለመነኝ ጊዜ እቀበለዋለሁ…»02
ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ «ዱዐ እርሱ እራሱ አምልኮ ነው» ቲርሚዚና ሌሎችም ዘግበውታል
በሌላ ቦታ ነቢዩ አህመድ በዘገቡት ሀዲስ «ዱዐ የኢባዳ መቅኒ ነው» ብለዋል።
ዱዐ በኢስላም ቁርዐንን ከማንበብና ከዚክር በመቀጠል በላጭ የሆነ ኢባዳ ነው።
የዱዐ አይነቶች፡- ሁለት ሲሆኑ አምልኮታዊ(ሶላት፣ፆም…) ዱዐና የልመና(ጥያቄ) ዱዐ ይባላሉ።
ለዱዐ ተቀባይነት የሚረዱ መስፈርቶች፡- 1. ግልፅ ምክንያቶች፡- ሰደቃ፣ውዱዕ፣ ሶላት፣ ወደ ቂብላ መዞር እጅን ማንሳት፣ አላህን በተገቢው ሁኔታ ማወደስ፣በነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) ላይ ሶለዋት ማውረድ፣ ወንጀሉን ማመን፣ የአላህ ስሞችን እያነሱ መለመን… የመሳሰሉትን መጠቀም ናቸው።
2. ድብቅ ምክንያቶች፡- እውነተኛ ተውበትን ማስቀደም፣ በበደል የወሰዱትን ነገር መመለስ፣ምግብን መጠጥን መኖሪያን ማሳመርና ከሀላል ማድረግ፣ ወንጀልና ከአጠራጣሪ ነገሮች መራቅ፣ ዱዐን ከልብ ማድረግ፣ በኣለህ መተማመን፣ የጠስፋ ስሜት ማዳበር፣ ወደ አላህ መጠጋት፣ ራስን ማስተናነስ፣ ችክማለት፣ ወደ አላህ መጠጋት፣ ሁሉን ነገር ወደርሱ ማስጠጋትና ከሌላው ተስፋ መቁረጥ ናቸው።
የዱዐ ወቅቶች፡- በለሊቱ የመጨረሻ ሲሶ ላይ፣ በአዛንና በኢቃማ መካከል፣ ከውዱዕ በኋላ፣ በሱጁድ ውስጥ፣ ከሶላት ማሰላመት በፊት፣ ከሶላቶች በኋላ፣ በቁርዐን ማኽተሚያ ወቅት፣ ዶሮ ሲጮህ፣ ሙሳፊር ሰው፣ የተቸገረ ሰው፣ የአባት ዱዐ ለልጅ፣ ሙስሊም ወንድሙ በርቀት የሚያደርግለት፣ ከጠላት ጋር ሲገናኙ፣ በጁሙዐ ኩጥባ ሶላቱ እስኪያልቅና ከአሱር በኋላ፣ በተመዳን በፊጥርና በሱሁር ወቅት፣ ለይለተል ቀድር፣ የአረፋ ቀን ናቸው።
የዱዐ ቦታዎችን፡- በተመለከተ በሁሉም መስጂዶች በተለይ ከካዕባ አጠገብ፣መቃሙ ኢብራሂም ዘንድ፣ ሶፋና መርዋ ላይ፣ በሐጅ ጊዜ(በዐረፋ፣በሙዝደሊፋና፣በሚና) ላይ፣ ዘምዘምን በሚጠጡበት ጊዜ ናቸው።
ዱዐን ተቀባይነት የሚያሳጡ ነገሮች፡- በዱዐው ከአላህ ጋር ሌሎችን መለመን(ሽርክ)፣ በልመናው ውስጥ ዝርዝር ነገሮችን መጥቀስ፣ በራሱ ላይ ወይም በሌላው ላይ ዱዐ ማድረግ(በግፍ)፣ ለወንጀልና ዝምድናን ለመቁረጥ ዱዐ ማድረግ፣ ከፈለክ አድርግልኝ ስትፈልግ ማረኝ ማለት፣ መሰላቸት፣ በተዘናጋ ልብ ዱዐ ማድረግ፣ አላህ ፊት ተገቢውን ስርዐት አላመያዝ፣ በነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) ላይ ሶለዋት አለማውረድ፣ በግድ በግጥም መልክ ለማድረግ መልፋት፣ ድምፅን ከመጠን በላይ ማጉላት… የመሳሰሉት ናቸው።
ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) ቲርሚዚይ በዘገቡት ሀዲስ እንዲህ ብለዋል« ማንም ሙስሊም በወንጀልና ዝምድናን በመቁረጥ ባልተቀላቀለበት ዱዐ ካደረገ ከሶስት ነገሮች አንዱ ይሰጠዋል- የለመነውን ነገር በቀጥታ፣ ወይም ወደ አኺራ ተላልፎ ሊቀመጥለት፣ ወይም እንደ አቅሟ ሊያገኘው የነበረውን ክፉ ነገር በመከላከል ነው»
ከዱዐ መኩራራት፡- አላህ በርሱ ላይ የሚኩራሩትንና ተብቃቂ ለመሆን የሚሹትን በተለያዩ ቦታዎች ያስጠነቅቃል። ለምሳሌ፡-
«…እነዛ እኔን ከመገዛት የሚኮሩት ተዋራጆች ሆነው ጀሀነም ይገባሉ» 46፡60
ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) ኢብኑ ማጃህ በዘገቡት ሀዲስ «አላህ ልመናውን የተወን ሰው ይቆጣበታል» ብለዋል።
በዱዐ ድንበርማለፍ፡- በመጨረሻው ዘመን ሰዎች በዱዐ ላይ ድንበር እንደሚያልፉ ነቢዩ አስ ጠንቅ ቀዋል ይኸውም በአሁንዘመን በመታየት ላይ ይገኛል። ለምሳሌ፡- ድምፅን ከፍ አድርጎ መለመን፣ በጋራ ዱዐ ማድረግ፣ ቦታና ጊዜውን መወሰን… የመሳሰሉት ይገኙበታል ከሁሉ የከፋው ደግሞ ከአላህ ውጪ ያሉ አካለትን መለመን ሲሆን ነቢዩ እንዲህ ሲሉ ያስጠነቅቃሉ፡-
«መለመን ስትፈልግ አላህን ብቻለምን፣ እርዳታ ብትፈልግ በአላህ ብቻ ተረዳ» ቲርሚዚ ዘግበውታል
አላህን በስርዐት ከሚገዙት ዱዐቸውንም ከሚቀበላቸው ባሮች ያድርገን። አሚን!