Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

በ ሼኽ ሙሀመድ ቢን ሷሊህ አል-ዑሠይሚን ኢኽላስ


በ ሼኽ ሙሀመድ ቢን ሷሊህ አል-ዑሠይሚን
ኢኽላስ

ኢህላስ ማለት ምን ማለት ነው? አንድ ሰው በሚያደርገው ዒባዳ ሌላ ነገር ከፈለገበት ሑክማ (ብያኔው) ምንድነው?
ኢኽላስ ማለት ሰውየው በሚያደርገው ዒባዳ ወደ አላህ መቃረብንና የክብሩ መጎናፀፊያ ቤት ወደ ሆነው ጀነት ለመድረስ መፈለጉ ነው፡፡
ሰውየው በሚያደርገው ዒባዳ ከዚህ ውጪ የሆነ ሌላ ነገር ከፈለገበት ምን እንደሚሆን እንደሚከተለው ከፍለን ማየት እንችላለን፡-
አንደኛው፡-በሚያደርግው ዒባዳ ከአላህ ወጪ ወዳለ ነገር መቃረብን ከፍጡራን ዘንድ ምስጋናን ለማትረፍ መፈለግቸነው፡፡ይህ ስራን ያበላሻል ፡፡ከሽርክ ተግባርም ነው፡፡አቡ ሑረይራ የሚከተለውን ሐዲስ ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) አስተላልፈውልናል፡-
«አላህ እንዲህ ብሏል፡- ‹እኔ ከሸሪኮች ሁሉ ይበልጥ ከሽርክ የተብቃቃሁ ነኝ፡፡ከኔ ጋር ሌላን አካል አጋርቶበት አንድን ስራ የሰራ ሰው እርሱንም ያጋራውንም ነገር ትቸዋለሁ››፡፡› . (ሙስሊም)
ሁለተኛው፡-በሚያደርገው ዒባዳ ወደ አላህ መቃረብን ሳይሆን እንደ ስልጣን ክብር ገንዘብ ያሉ አለማዊ ጥቅሞችን ይፈልጋል ፡፡ ይህ ስራው ከንቱ ነው፡፡ወደ አላህ አያቃርበውም፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-
‹‹ቅርቢቱን ሕይወትና ጌጧን የሚሹ የሆኑትን ሰዎች ስራዎቻቸውን (ምንዳዋን) በርሧ ውስጥ ምንም አይጎድልባቸውም፡፡እነዚያ እነሱ በመጨረሻይቱ ዓለም ለነርሱ ከእሳት በቀር የሌላቸው ናቸው፣የሰሩትም ስራ በርሧ ውስጥ ተበላሸ፣(በቅርቢቱ ዓለም)ይሰሩት የነበሩትም (በጎ ስራ) ብልሹ ነው፡፡) (ሁድ 11፡15-16)
በዚህኛውና መጀመሪያ ባልነው መካከል ያለው ልዩነት የመጀመሪያው ለአላህ ዒባዳ የሚያደርግ (ዓቢድ) በመሆኑ እንዲመሰገንና እንዲወደስ አይፈልግም፡፡ይህ ያሳስበውም፡፡
ሶስተኛው፡- በሚያደርገው ዒባዳ ወደ አላህ መቃረብንና ከዒባዳዎች የሚገኙትን ዱኒያዊ ጥቅሞችም ይፈልጋል፡፡ ለምሳሌ በሚያደርገው ‹‹ጠሃራ›› (ውዱእ/ትጥበት) ወደ አላህ ለመቃረብ ካለው ኒያ ጋር ሰውነቱን የማነቃቃትና የማንፃት ፍላጎት ይኖረዋል፡፡ የሚሰግደውን ሰላትም ከዒባዳነቱ በተጨማሪ ለአካላዊ ወይም ስፖርታዊ እንቅስቃሴው ይፈልጋል፡፡ፆሙንም ከዒባዳነቱ በተጨማሪ ውፍረት ለመቀነስ ይፆማል፡፡ ይህ ፍላጎቱ የኢኽላስን አጅር (ምንዳ) ይቀንስበታል፡፡ ነገር ግን ወንጀል እንደሰራ አይቆጠርበትም፡፡አላህ ሑጃጆችን አስመልክቶ እንዲህ ይላል፡-
‹‹(በሐጅ ጊዜ በንግድ ስራ) ከጌታቸሁ ትርፍን በመፈለጋቸሁ በናንተ ላይ ሀጢአት የለባችሁም… ›› -(አል-በቀራህ 2፡198) 1
በኒያው ላይ አመዛኙ ዒባዳው ሳይሆን ዱኒያዊው ጥቅም ከሆነ በአኺራ ሰዋብ (ምንዳ) የለውም፡፡ ሰዋቡ በዚህ አዱኒያ ያገኘው ጥቅም ብቻ ይሆናል፡፡በዚህ ድርጊቱ ወንጀለኛ እንዳይሆን እሰጋለሁ፡፡ምክንያቱም ትልቅ ዓላማና ግብ ያለውን የአላህን ኢባዳ ለተናቀችው ምንም ለማትጠቅመው አዱኒያው ጥቅም ማግኛ አውሏልና፡፡ስለነዚህ ሰዎች አላህ እንዲህ ይላል፡-
‹‹ከነሱም ውስጥ በምፅዋቶች የሚዘልፉህ ሰዎች አሉ፡፡ከርሧም (የሚሹትን) ቢስሰጡ ይደሰታሉ ከርሧ ባይሰጡ ግን እነርሱ ያን ጊዜ ይጠላሉ፡፡››(አል-ተውባ 9፡58)
አቡ ዳውድ አቡ ሑረይራን አጣቅሰው እንደዘገቡት አንድ ሰው ለነብዩ (ሰ.አ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹ሰውየውጂሀድን ይፈልጋል በጂሃዱ አዱኒያዊ ጥቅምም ይፈልግበታል፡፡››አላቸው ፡፡ነቢዩ(ሰአወ) ‹‹አጅር የለውም››አሉት ሰውየው ሶስት ጊዜ መላልሶ ሲጠይቃቸው ነብዩ (ሰአወ) የመለሱለት መልስ ‹‹አጅር የለውም››የሚል ብቻ ነበር
ዑመር ቢን አል-ኸጣብም (ረ.ዐ) የሚከተለውን ሀዲስ ከነብዩ (ሰ.አ.ወ) አስተላልፈዋል፡-
‹‹የሂጅራው (የስደቱ ዓላማ ዓለማዊ ጥቅም የሆነ ሰው ጥቅሟን ያገኛታል፣ለሴትም ከሆነ ያገባታል ፣ የተሰደደለት ዓላማ ያገኛል፡፡››(ቡኸሪና ሙስሊም)
ሁለቱም ኒያቸው እኩል ሆነው ከመጡ ማለትም ለዒባዳ ያለው ኒያና ከዒባዳ ውጪ ለሌላ ነግር ያለው ሳይበላለጡ በአንድ ድርጊት ላይ እኩል ሆንው ከተገኙ ይሕ የሚታይ ጉዳይ ይሆናል ፡፡ ይሁን እንጂ ይበልጥ የሚያመዝነው በዚያ ድርጊት ሰዋብ (ምንዳ) ሊያገኝበት የማይችል መሆኑ ነው፡፡ለአላህም ከአላህ ውጪ ነገር እንደሰራ ማለት ነው፡፡
በዚህኛው ክፍልና ከዚኅ በፊት ባላው መካከል ያለው ልዩነት ከዚኅ በፊት ባለው ክፍል ውስጥ ያለው ከዒባዳ ውጪ ያለው ዓላማ የተከተለው ለአለማዊ ኑሮው አስፈላጊ የሆነ ስራ በመስራቱ ነው፡፡ ድርጊቱን የሚፈፅመው ከድርጊቱ የሚገኘውን ዓለማዊ ጥቅም በመሻት ነው፡፡
በዚህ ክፍል ውስጥ የሰውየውን ዓላማ (ኒያ) ዒባዳ መሆኑ ይበልጥ በምን ይታወቃል? መለኪያው ምንድ ነው? ከተባለ፡- የሚከተለው መልስ ዕንሰጣለን፡-
ከዒባዳ ውጭ ያለው ነገር ተገኘም አልተገኘም ትኩረት ካልሰጠው ይህ በርግጥ የሚያመለክተው የሚበልጠው ለዒባዳ ያለው ዓላማ መሆኑ ነው፡፡በአንፃሩ ደግሞ ከዒባዳ ውጭ ላለው ነገር ትኩረት የሚሰጥ ከሆነ የርሱ ዓላማ ይበልጥ ማለት ነው፡፡
ያም ሆነ ይሕ የልብ ልሳን የሆነውን ኒያ ጉዳይ ከባድና አደገኛ ነው፡፡ ኒያ ሰውየውን ወደ ላቀ የእውነተኞች (አል-ሲዲቂን) ደረጃ ከፍ ሊያደርገው ይችላል፡፡በተቃራኒውደግሞ ወደ ዘቀጠ ደረጃ ሊያወርደው ይችላል፡፡ከሰለፎች አንዱ የሚከተለውን ተናግሯል፡-
‹‹ነፍሴን ኢኽላስ እንዲኖራት የታገልኳትን ያክል በምንም ነገር ላይ አልታገልኳትም ፡፡ ›› «አላህ በኒያችን ኢኽላስ በስራችን ጥራትን እንዲሰጠን እንለምናለን!!!»