Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ነብዩን የሚወድ ባልደረቦቻቸውን አይጠላም - አል-ሀበሺ ሲጋለጥ


ነብዩን የሚወድ ባልደረቦቻቸውን አይጠላም - አል-ሀበሺ ሲጋለጥBy Salah Ahmed  የነብዩን ع ባልደረቦች መውደድ፣ መልካም ባህሪያቸውን እና ደጋግ ስራዎቻቸውን መጥቀስና ማውሳት፣ በመካከላቸው ስለተፈጠረው ልዩነት ካለዕውቀት አለመዘባረቅን ግዴታ ያደርጋል።
አላህ እንዲህ ይላል፤
وَالسَّابِقُونَ الْأَوَّلُونَ مِنَ الْمُهَاجِرِينَ وَالْأَنْصَارِ وَالَّذِينَ اتَّبَعُوهُمْ بِإِحْسَانٍ رَضِيَ اللَّهُ عَنْهُمْ وَرَضُوا عَنْهُ وَأَعَدَّ لَهُمْ جَنَّاتٍ تَجْرِي تَحْتَهَا الْأَنْهَارُ خَالِدِينَ فِيهَا أَبَدًا ذَلِكَ الْفَوْزُ الْعَظِيمُ التوبة 100
«ከስደተኞቹና ከረዳቶቹም ሲኾኑ የመጀመሪያዎቹ ቀዳሚዎች እነዚያም በበጎ ሥራ የተከተሏቸው አላህ ከእነሱ ወዷል ከእርሱም ወደዋል፡፡ በሥሮቻቸውም ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች በውስጣቸው ዘለዓለም ነዋሪዎች ሲኾኑ ለእነርሱ አዘጋጅቶላቸዋል፡፡ ይህ ታላቅ ዕድል ነው፡፡» አል-ተዉባ 100
ይህ አንቀጽ ሰሀቦች ታማኝ “አድል” መሆናቸውን በግልጽ ያሳያል። አላህ ለትማኝነታቸው ምስክርነቱን ገልጿል። በልባቸው ያለውንም ውዴታ እና ንጹህነት መስክሮላቸዋል። አላህ ስራዉን እና ማንነቱን በውዴታ የተቀበለው ሰው በክህደት ላይ ሊሞት አይችልም። ምክኒያቱም ዋናው የስኬት ሚስጥር ሙስሊም ሆኖ መሞት ነውና አላህ ሙስሊም ሆኖ ለማይሞት ሰው ዘልዓለማዊ ምስክርነት አይሰጥም። መውደድ “ሪዳ” መጀመሪያ የሌለው ጥንታዊ የአላህ ባህሪ ነውና የእርሱን “ሪዷ” ያገኘን ሰው አላህ መልሶ አይቆጣበትም። የአላህን ውዴታ በሚያስገኝ ሁኔታ ላይ እንደሚሞት ያወቀውን እንጂ ዘልዓለማዊ ውዴታውን አያጎናፅፍም።[1] በሰሂህ ሙስሊም ከጃቢር ኢብኑ ዓብዲላህ የተዘገበው ሀዲስ ይህንን ያጠናክራል። ነብዩع እንዲህ ብለዋል፤
روى مسلم عن جابر ابن عبدالله أن النبي -صلى الله عليه وسلم- قال: ((لا يدخل النار أحد بايع تحت الشجرة)) صحيح مسلم 2496.«በዛፍዋ ስር ለኔ ቃል ኪዳን ከገቡ ሰዎች መካከል እሳት የሚገባ የለም»[2] ጃቢር ኢብኑ አብዲላህ “አንድ ሺህ አራት መቶ ሰዎች ነበርን” ብለዋል።
ይህ አጠቃላይ ባልደረቦቻቸውን የተመለከተ ሲሆን አንሷሮችን (ረዳቶችን) ስለመውደድ ነብያችን عእንዲህ ብለዋል፤
حديث أنس عن النبي صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلِّم أنه قال : « آية الإيمان حب الأنصار وآية النفاق بغض الأنصار » صحيح البخاري برقم 17
ከአነስ ኢብኑ ማሊክ የተዝገበው ሀዲስም እንዲህ ይላል «አንሷሮችን መውደድ የኢማን ምልክት ነው፤ አንሷሮችን መጥላት ደግሞ የንፍቅና ምልክት ነው»[3]
“እነሱን ሙእሚን እንጂ አይወዳቸውም፤ ሙናፊቅ እንጅ አይጠላቸውም፤ እነሱን የወደዳቸውን አላህ ወደደው፤ እነሱን የጠላቸውን ደግሞ አላህ ጠላው”[4]
የነብዩን ع ባልደረቦች መውደድ በዱንያ ህይወት ስኬታማ ያደርጋል። አላህ እንዲህ ይላል፦
قال تعالى: {وَمَنْ يَتَوَلَّ اللَّهَ وَرَسُولَهُ وَالَّذِينَ آمَنُوا فَإِنَّ حِزْبَ اللَّهِ هُمُ الْغَالِبُونَ } (المائدة : 56)«አላህንና መልክተኛውን እነዚያንም ያመኑትን የሚወዳጅ ሰው (ከአላህ ጭፍሮች ይኾናል)፡፡ የአላህም ጭፍሮች እነርሱ አሸናፊዎች ናቸው፡፡» አል-ማዒዳህ 56
ታላቁ የቁርዓን ተንታኝ ኢብኑ ከሲር «አላህን፣ መልዕክተኛዉን ع እና ምዕመናንን ወዳጅ የሚያደርግ ሁሉ በዱንያም ይሁን በአኼራ ስኬታማ ነው! የአላህንም እርዳታ ያገኛል» ብለዋል፡፡ ሰሀቦችን የሚወድ ሰው በወዲያኛው አለም ከነሱ ጋር የመሆን እድል አለው።
عن عبد الله بن مسعود رضي الله عنه قال : «جاء رجل إلى رسول الله صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلِّم فقال : يا رسول الله كيف تقول في رجل أحب قومًا ولم يلحق بهم، فقال رسول الله ع: (المرء مع من أحب)» رواه مسلم برقم 6168አብዱላህ ኢብኑ መስዑድ ባስተላለፉትት ሀዲስ የአላህ መልዕክተኛ ع ዘንድ አንድ ሰው ይመጣና እንዲህ ይላቸዋል፤«የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! አንድ ሰው ሰዎችን እየወደዳቸው ነገር ግን (በደረጃው) እነርሱ ጋር ካልደረሰ እንዴት ነው?» የአላህ መልዕክተኛም ع የአላህ «ማንኛዉም ሰው (በአኼራ ዱንያ ላይ) ከወደደው ጋር ነው» አሉት።[5]

روى الإمام البخاري من حديث أنس بن مالك رضي الله عنه « أن رجلا سأل النبي صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلِّم عن الساعة فقال : متى الساعة ؟ فقال النبي صلى الله عليه وسلم : (وماذا أعددت لها) . قال : لا شيء إلا أني أحب الله ورسوله ، فقَال النبي صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلِّم : (أنت مع من أحببت) ، فقال أنس : فما فرحنا بشيء فرحنا بقول النبي صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلِّم أنت مع من أحببت . قال أنس : (فأنا أحب النبي صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلِّم وأبا بكر وعمر وأرجو أن أكون معهم بحبي إياهم وإن لم أعمل بمثل أعمالهم »ከአነስ ኢብኑ ማሊክ እንደተዘገበው አንድ ሰው ነብዩን ع ስለ ትንሳኤ እለት “ቂያማህ” ይጠይቃቸዋል። እርሳቸውም፤ «ለዛ እለት ምን አዘጋጅተሀል?» በማለት ጠየቁት። ሰውየውም፤ «ምንም ያዘጋጀሁት ነገር የለም፤ ነገር ግን አላህን እና መልዕክተኛውን ع እወዳለሁ።» አላቸው። እርሳቸውም፤ «አንተ ከወደድከው ጋር ነህ» በማለት አበሰሩት። አነስ እንዲህ አሉ፤ «አንተ ከወደድከው ጋር ነህ» የሚለው የነብዩ ع ንግግር ካስደሰተን በበለጠ በምንም ተደስተን አናውቅም። እኔ ነብዩን ع እወዳለሁ፤ አቡበከር እና ዑመርንም እንዲሁ፤ የነሱ ያክል ስራ ባልሰራም እነርሱን በመውደዴ ምክኒያት ከነሱ ጋር እንደምሆን ተስፋ አደርጋለሁ»[6]

የሰሀቦችን ታላቅነት እና ብልጫ፣ አላህ ዘንድ ጀነት ቃል እንደተገባላቸው የሚገልጹና መልካም ባህሪያቸውን የሚዘክሩ መረጃዎች ብዙ ናቸው። ከፊሎቹ ሁሉንም ሰሀቦች የሚመለከቱ ሲሆን ከፊሎቹ ደግሞ የተወሰኑትን ይመለከታሉ። ስለዚህም ማንኛውም ሙስሊም ሰሀቦችን መውደድ፣ታማኝነታቸውን አለመጠራጠር፣ መልካም ስራቸውን ማውሳት እና ፈለጋቸውን መከተል ይጠበቅበታል። ታላቁ የሀዲስ ሊቅ ኢብኑ ሀጀር አልዓስቀላኒይ እንዲህ ብለዋል፤
قال ابن حجر "اتفق أهل السنة على أن الجميع عدول، ولم يخالف في ذلك إلا شذوذ من المبتدعة" الإصابة في تمييز الصحابة(1/17)«ሁሉም ታማኝ መሆናቸውን አህሉሱና ሁሉም ተስማምተዋል።አንዳንድ ያፈነገጡ የቢድዓ አራማጆች እንጂ በዚህ ላይ ውዝግብ የፈጠረ የለም»[7]
በተወሰኑ ሰሀቦች መካከል የተፈጠሩ ግጭቶችን በተመለከተ አስተያየት እና ብይን ከመስጠት መቆጠብ ያስፈልጋል። ሰሀቦች ከስህተት የተጠበቁ “ማዕሱም” አይደሉም፤ ነገር ግን አላህ በመሀከላቸው የሚከሰተዉን ግጭት ከማወቁ ጋር ውዴታዉን አሳርፎባቸዋል። የጀነት ሰዎች መሆናቸውንም ነግሮናል። ስለተፈጠረው አለመግባባት፤ ከመነሻው ጀምሮ የመናፍቃን እና የሰርጎ ገቦች እጅ ከፍተኛውን ሚና እንደተጫወተ ግልጽ ነው። በመካከላቸው የተከሰተው አለመግባባት ምክኒያቱ የስልጣን ወይም የዱንያ ሽኩቻ አልነበረም። ክስተቱን እነርሱ ከነበሩበት ሁኔታ እና ከፊትና ባህሪ አንጻር በመመልከት ለሁሉም ኡዝር መስጠት ይገባል። ሁሉም ወገኖች ለወሰዱት እርምጃ መልካም ጥርጣሬን በማስቀደም ልባችንን ከበሽታ ልንከላከል ይገባል። ለሁሉም የአላህን ማርታ መለመን፣ ሁሉም መልካም አሳቢዎች መሆናቸውን አለመዘንጋት ይገባል። መካከል ስህተት የፈጸመ በኢጅቲሀድ ስለፈሰመው ምንዳ ‘አጅር’ ያገኝበታል። ትክክል የነበረው ወገን ደግሞ ሁለት አጅር ያገኛል። የአህሉሱናን መንገድ ልዩ የሚያደርገው ይህ አቋማቸው ነው።
قال عمر بن عبد العزيز رحمه الله : (أولئك قوم طهر الله أيدينا من دمائهم، فلنطهر ألسنتنا من أعراضهم) . رواه الخلال في السنة (717)አላህ ስራቸውን ይውደድላቸውና፤ በፍትህ እና በቅንነት የታወቁት ኡመር ኢብኑ ዓብዲልዓዚዝ እንዲህ ብለዋል፤«አላህ እጃችንን ከእነዚህ ህዝቦች ደም አጥርቶልናል፤ እና ክብራቸውን ከመንካት ምላሳችንን እናጥራ»[8]

በጥቅሉ፤ አህሉሱና ሁሉንም ሶሀቦችን ይወዳሉ፤ መረጃዎችን፣ፍትህንና ሚዛናዊነትን መሰረት አድርገው ለሰሀቦች የሚገባቸውን ክብር ይሰጣሉ፤ ድንበር ማለፍ የተከለከለ ነውና ከስሜታዊነት እና ከጭፍን ወገንተኝነት የራቁ ናቸው።

F ማንኛውም ሙስሊም ሰሀቦች ላይ ነውርን ከመፈለግ እና ልቡን በነሱ ላይ ከማጠልሸት ፍጹም ሊጠነቀቅ ይገባዋል፤ ይህ አይነቱ ጥመት ውስጥ የገባ ከአላህ እዝነት እንደሚርቅ ጥርጥር የለዉም። ቀዳሚ ሙስሊሞች፣ መልካም አርዓያዎች፣ ምስጉን ባሪያዎች፣ ጠንካራ የኢስላም የቁርጥ ቀን ልጆች ነበሩ። ከሰሀቦች የማንንም ክብር የነካ መንገድ የሳተ የሸይጣን ወታደር ነው። ምክኒያቱም የዚህ ዲን ምሶሶ የሆኑትን የመረጃ ምንጮች፤ ቁርዓን እና ሀዲስን ያስተላለፉት እነሱ በመሆናቸው፤ እነርሱን በመጥፎ የሚያነሳ፣ ታማኝነታቸውን ጥያቄ ውስጥ ለመክተት የሚፍጨረጨረው ኢስላምን ኢላማ ያደረገ የከሀዲያንን ተልዕኮ የሚያስፈጽም የውስጥ ጠላት ብቻ ነው።

በ (264 ዓ.ሒ) ያለፉት የኢማም ሙስሊም ሸይኽ የሆኑት አቡ ዙርዓህ አራዚይ እንዲህ ብለዋል፤
قال أبو زرعة الرازي: إذا رأيت الرجل ينتقص أحدا من أصحاب رسول الله ع فاعلم أنه زنديق، وذلك أن الرسول ع حق ، والقرآن حق ، وما جاء به حق ، وإنما أدى إلينا ذلك كله الصحابة ، وهؤلاء يريدون أن يجرحوا شهودنا ، ليبطلوا الكتاب والسنة ، والجرح بهم أولى ، وهم زنادقة«አንድ ሰው ከሰሀቦች መካከል አንዱንም ቢሆን ሲተች ካየኸው “ዚንዲቅ”[9] መሆኑን እወቅ። ምክኒያቱም፤ የአላህ መልዕክተኛ ع ሀቅ ናቸው፣ ቁርዓንም ሀቅ ነው፣ ይዘውት የመጡትም ሀቅ ነው፣ ይህንን ሁሉ ግን ያስተላለፉልን ሰሀቦች ናቸው። እንዲህ አይነት ሰዎች ቁርዓን እና ሱናን ውድቅ ለማድረግ ምስክሮቻችንን ሊኮንኑ ይሞክራሉ። ዚንዲቆች ናቸውና ሊኮነኑ የሚገባቸው እነርሱ ናቸው።»[10]
አል ኢማም አህመድ ለ“ሙሰደድ ኢብኑ ሙሰርሀድ” በጻፉት ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብለው ነበር፤
»الكف عن ذكر مساويهم والخلاف الذي شجر بينهم فمن سب أصحاب رسول الله - صلى الله عليه وسلم - أو أحدا منهم أو تنقصه أو طعن عليهم أو عرض بعيبهم أو عاب أحدا منهم فهو مبتدع رافضي خبيث مخالف لا يقبل الله منه صرفا ولا عدلا بل حبهم سنة والدعاء لهم قربة والاقتداء بهم وسيلة والأخذ بآثارهم فضيلة « طبقات الحنابلة (1/344)«የነብዩ ع ባልደረቦችን በመጥፎ ከማንሳት ተቆጠቡ። መልካም ገድላቸውን አውሱ፤ በመሀከላቸው ስለተፈጠረው ውዝግብ ከመናገር ምላሳችሁን ተቆጥቡ፤ ከሰሀቦች አንዳቸውንም ቢሆን የተሳደበ፣ ክብሩን የነካ ወይም የተቸ መጥፎ የሆነ ራፊዲይ “ሺዓ” ነው። ተጻራሪ ነዉና አላህ ምንም አይነት መልካም ስራ አይቀበለውም፤ እነርሱን መውደድ ሱና ነው፤ ለነሱ ዱዓ ማድረግ ወደ አላህ መቅረብ ነው፤ እነርሱን መከተል ወደ አላህ መቃረቢያ ነው፤ የነሱን ፋና መከተልም ግዴታ ነው»[11]
»من انتقص أحدا من أصحاب رسول الله صلى الله عليه و سلم أو أبغضه لحدث كان منه أو ذكر مساويه كان مبتدعا حتى يترحم عليهم جميعا ويكون قلبه لهم سليما« رسالة أصول السنة«ከሰሀቦች መካከል የአንዱንም ቢሆን ክብር የነካ ወይም በሆነ ክስተት ምክኒያት የጠላው ወይም በመጥፎ ያነሳው ሰው ልቡን ለሁሉም ሰላም ካላደረገና ለሁሉም ማርታን ካለመነ በቀር “ሙብተዲዕ” (የፈጠራ ሰው) ነው።»[12]
አቢ ሰዒድ አልኹድሪይ ባስተላለፉት ሀዲስ ነብያችንع እንዲህ ብለዋል፦
عن أبي سعيد الخدري رضي الله عنه قال: قال النبي صلى الله عليه وسلم «لا تسبوا أصحابي فلو أن أحدكم أنفق مثل أحد ذهبا ما بلغ مد أحدهم ولا نصيفه» رواه البخاري (3470) ومسلم (2540)«ባልደረቦቼን አትሳደቡ! ከናንተ አንዳችሁ የእሁድ ተራራን የሚያክል ወርቅ ቢመፀውት የባልደረቦቼን የአንድ እፍኝ ወይም ግማሽ እፍኝ ምፅወታ አይደርስም፡፡»[13]
ለታላላቅ ሰሀቦች በተለይም ለአቡበክር እና ለዑመር ባላቸው ጥላቻ የሚታወቁ የሺዓ አንጃዎችን ህዝበ ሙስሊሙ ከጥንት ጀምሮ ሲያወግዛቸው እና ሲጠነቀቃቸው ኖሯል። ኸዋሪጆችም ሰሀቦችን ከመጥላት አልፈው ኢማም አሊይ ላይ ሰይፍ መዘዋል። ይሁንና ሁሉም አንጃዎች በየጊዜው አመለካከታቸውን ወርሶ አህሉሱናን እየተዋጋ ባንዲራቸውን ከፍ ሊያደርግላቸው የሚሞክር ጭፍን ተከታይ አያጡም። በዘመናችን ካሉ ታላላቅ የቢድዓ አራማጆች አንዱ የሆነው አብዱላህ አልሀረሪይ «አልሀበሺይ»[14] ሰሀቦችን ከመሳደብ የሚከለክሉ እና የሰሀቦችን ታማኝነት ‘ዓዳላህ’ የሚገልጹ እነዚህ እና መሰል ሀዲሶችን አስመልክቶ እንዲህ ጽፏል “ይህ ስለ ሰሀቦች በጥቅሉ ሊባል ይችላል ነገር ግን በዝርዝር ስለግለሰቦች እንደዚህ አይባልም። ይህ ሀዲስ ከነሱ መካከል አንድም ግለሰብ በመልካም እንጂ መወሳት የለበትም የሚል መልዕክት የለዉም፤ ሸሪዓዊ ብይን መስጠት እና ማስጠንቀቅ የግድ ነው።”[15] በሌላ ‘ሰሪሁል በያን’ በተባለ መጽሁፉም ተመሳሳይ ይዘት ባለው ገለጻ “ሰሀቦቼን አትሳደቡ” የሚለው ሀዲስ ሁሉንም ሰሀቦች እንደማይመለከት ከተናገረ በኋላ ይህ አይነት ክብር እና ደረጃ ከማይገባቸው መካከል እንደምሳሌ ኻሊድ ኢብኑ ወሊድ እና ሙዓዊያህ ኢብኑ አቢ ሱፍያንን ይጠቅሳል።[16]

አል ኢማም አጠሀዊይ እንዲህ ብለዋል፤
«ونحب أصحاب رسول الله صلى الله عليه وسلم، ولا نفرط في حب أحد منهم، ولا نتبرأ من أحد منهم. ونبغض من يبغضهم، وبغير الخير يذكرهم. ولا نذكرهم إلا بخير. وحبهم دين وإيمان وإحسان، وبغضهم كفر ونفاق وطغيان»“የነብዩን ባልደረቦች በመልካም እናወሳለን፣ ከሰሀቦች መካከል ከአንዳቸውም አንጥራራም፣ የሚጠላቸውን እና በመጥፎ የሚያነሳቸውን ሁሉ እንጠላለን፣ በመልካም እንጂ አንዳቸውንም አናወሳም፣ እነርሱን መውደድ ዲን፣ኢማን እና ኢህሳን ነው፣ እነርሱን መጥላትም ኩፍር፣ ኒፋቅ እና ድንበር ማለፍ ነው።”[17]አልሀበሺይ ይህንን ያብራራው በዚህ መልኩ ነበር “ይህ ማለት ከነርሱ መካከል ማንም አይወገዝም ማለት አይደለም፤ አንድ ነገር የተረጋገጠበት ሰው ይወገዛል” [18] እንደዚሁ ሙዓዊያህ ኢብኑ አቢ ሱፍያን እና ዓምር ኢብኑልዓስን መውቀስ እና ማውገዝ እንደሚገባ ከተናገረ በኋላ ጠሀዊ ለማለት የፈለገው ሁሉንም ሰሀቦች በጥቅል በመጥፎ ማውሳትን እንጂ ግለሰቦችን ማውገዝን እንዳልሆነ በመናገር ደምድሞታል።[19] ይህ ሁሉ መንደርደር ለምን ሆነና፤ አልሀበሺይ በዚህ አላቆመም በብዙ ጽሁፎቹ ሙዓዊያ እና አምር ኢብኑልዓስ ላይ ሲንጠራራ ይታያል። አልሀበሺይ በአራተኛው ኸሊፋ ዓሊይ ኢብኑ አቢ ጣሊብ እና በሙዓዊያህ መካከል ስለተከሰቱ አለመግባባቶች እና ግጭቶች አስተያየት መስጠት እና ለመዳኘት መሞከር ስህተት መሆኑን ከጥንት ጀምሮ የኖሩ ታላላቅ የሱና ሊቃዉንት ተስማምተው ያጸደቁትን ‘ኢጅማዕ’ ይጻረራል። ይህንን አስመልክቶ የተነገሩ ሀዲሶችን በራሱ ግንዛቤ በመተንተን ሙዓዊያ ድንበር አላፊ እና የእሳት ተጣሪ እንደሆነ ይናገራል።[20] የሺዓዎችን ማደናገሪያዎች አንድ በአንድ ተከታትሎ በማቅረብ ሙዓዊያ የጃሂሊያ ሞት እንደሞተ ተናግሯል።[21] ከዚህም አልፎ ሙዓዊያን አስመልክቶ ስለኸዋሪጆች የተነገሩ ሀዲሶችን ይደረድራል። የዱንያ ጥቅማጥቅም እንደሚያሳድ እና የስልጣን ጥማት እንደነበረበት በግልጽ ጽፏል።[22] የሙዓዊያን ታላቅነት የሚዘክሩ ሀዲሶችን ሁሉ በማስተባበል “ስለሙዓዊያህ ከተጠቀሱ ሀዲሶች ትክክለኛ እና ተቀባይነት ያለው የለም” ብሏል።[23]
የሙዓዊያህ መልካም ገድሎቹ ብዙ ናቸው። የነብዩ ع የወህይ ጸሀፊ መሆኑ ይበቃዋል፣ ብዙ ታላላቅ ዘመቻዎችን ተካፍሏል። የሰሀቦችን ደረጃ የሚያወሱ አንቀጾች ሁሉ ይመለከቱታል። ሰሀቦችን በተለይም የወህይ ጸሀፍትን በመጥፎ መጠርጠር እና መወንጀል የአላህ መልዕክት የሆነውን ቁርዓን ጥርጥር ዉስጥ ለማስገባት የሚደረግ የከሀዲያን ደባ መሆኑ ግልጽ ነው። የሙዓዊያን ታላቅ ደረጃ የሚያወሱ ሰሂህ በሆነ ሰነድ የተዘገቡ በርካታ ሀዲሶችን እናገኛለን። ኢማም አህመድ በዘገቡት ሀዲስ የአላህ መልዕክተኛ ع ሙዓዊያን አውስተው “አላህ ሆይ! የተመራ ቅን መሪ አድርገው፣ ለሰዎችም መቃናት ሰበብ አድርገው”አሉ።[24] ይህ ሀዲስ የሀበሺን ቅጥፈት ውድቅ ለማድረግ በቂ ነው። ቢሆንም ግን አንድ ሌላ ሀዲስ እንጨምር። ቡኻሪ በአነስ ኢብኑ ማሊክ በኩል ከአክስቱ ኡሙ ሀራም ቢንት ሚልሀን በተዘገበ ሀዲስ «የአላህ መልዕክተኛع «ከኔ ኡመቶች ለመጀመሪያ ጊዜ በባህር የሚዘምቱት ጀነት መግባታቸዉን የግድ የሚያደርግ ስራ ሰርተዋ» ሲሉ ኡሙ ሀራም «የአላህ መልዕክተኛع፤ እኔ ከእነርሱ ነኝ?» አለቻቸው። እርሳቸውም «አንቺ ከነርሱ መካከል ነሽ» አሏት። አስከትለዉም «ከኡመቴ የመጀመሪያዎቹ የቆስጠንጢንያ ዘማቾች አላህ ወንጀላቸውን ምሮላቸዋል» አሉ። እርሷም እኔ ከእነርሱ ነኝ? ስትላቸው። አይደለሽም አሏት።[25]
ቡኻሪ በዘገቧቸው ሌሎች ሁለት ሀዲሶች[26]፤ ኡሙ ሀራም ከባለቤቷ ኡባዳህ ኢብኑ ሷሚት ጋር የመጀመሪያው የሙስሊሞች የባህር ጦር በሙዓዊያህ መሪነት ሲዘምት አብራ ሄዳ እንደነበር እና ጦሩ ሲመለስ በሶሪያ ልትሳፈረው የቀረበላት ፈረስ አፈናጥሯት በመውደቋ ህይወቷ አልፏል። አላህ ስራዋን ይውደድላት። በእነዚህ ሀዲሶች የአላህ መልዕክተኛع ከመሰከሩላቸው ሰዎች መካከል የጦሩ መሪ ሙዓዊያህ በግምባር ቀደምነት የሚጠቀሰው መሆኑ ግልጽ ነው።

አላህ ልባችንን በሰሀቦች ፍቅር የተሞላ ያድርገው። አላህ ሙስሊሙን ኡማህ ሰሀቦችን ከሚጠሉ እና በጠላትነት ከሚፈርጁ ሁሉ እፎይታ ይስጠው።
===========================
[1] አሷሪም አልመስሉል (ኢብኑ ተይሚያህ) ገጽ 572

[2] ሙስሊም በቁጥር 2496 ዘግበውታል

[3] ቡኻሪ በቁጥር 17 ዘግበዉታል

[4] ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል

[5] ሙስሊም በቁጥር 6168 ዘግበውታል

[6] ቡኻሪ ከአነስ ኢብኑ ማሊክ ዘግበውታል

[7] አል ኢሷባህ ቅጽ 1 ገጽ 17

[8] ኸላል “አሱናህ” በተባለው ጥንቅራቸው 717 ላይ ዘግበዉታል

[9] ዚንዲቅ የሚለው ቃል መሰረቱ ከፋርስ የተወሰደ ቃል ሲሆን፤ በአረብኛ መሰረት የምናገኝለት “ዘንደቂይ” ለሚለውን ቃል ሲሆን “በጣም ስስታም” ማለት ነው። ከጥንት ጀምሮ ሰዎች ዚንዲቅ የሚለውን ቃል ሚጠቀሙት ሀይማኖትን ለማይከተል እና በተፈጥሮ ለሚያምን “atheist” ነው። ሊሳኑልዓረብ ቅጽ 1 ገጽ 51 እና ሚስባሁል ሙኒር ቅጽ 1 ገጽ 256 ይመልከቱ። ቀደምት የሱና ኪታቦች ላይ ቀንደኛ ለሆኑ የቢድዓ አራማጆች መገለጫ ሆኖ ሲያገለግል ይስተዋላል።


[10] አልኪፋያህ (አልኸጢብ አልበግዳዲይ) ገጽ 97 / አልኢሷባህ (ኢብኑ ሐጀር ቅጽ 1 ገጽ 10)

[11] ጠበቃቱል ሀናቢላህ ቅጽ 1 ገጽ 344

[12] ለዓብዶስ አኢብኑ ዓጣር በጻፉት ‘ኡሱሉሱናህ’ በተባለው ኪታብ የተጠቀሰ ነው። ጠበቃቱል ሀናቢላህ ቅጽ 1 ገጽ 245

[13] ቡኻሪ እና ሙስሊም ዘግበውታል

[14] የአብዱላህ አልሀረሪ ተከታዮች ዘወትር የነብዩን ع ዉዴታ እንሰብካለን ይላሉ፤ ውዴታቸውንም ለመግለጽ የተለያዩ የቢድዓ ተግባራትን ያስፋፋሉ። የእርሳቸው ለመሆኑ ምንም አይነት መረጃ የማያቀርቡበትን ጸጉር ከሀገር ሀገር እያዘዋወሩ ይሳለማሉ። እውነት ለነብዩ ع ውዴታ ካላቸው ባልደረቦቻቸውን ሊያከብሩ እና ክብራቸውን ከመንካት ምላሳቸውን ሊሰበስቡ ይገባል። የሸይኻቸውን ተከታታይ ትችቶች ያስተዋለ በጭፍን ሊከተለው አይችልም። የነብዩን ع ውዴታ የሚገልጹት ለባልደረቦቻቸው ባለቸው ክብር ነው።

[15] “ኢዝሀሩል ዓቂደቲ ሱኒያህ” በተባለው መጽሀፉ ገጽ 297

[16] ‘ሰሪሁል በያን’ ገጽ 245

[17] ታዋቂው የጠሀዊይ አቂዳ “አቂደቱ ጣሀዊያህ”

[18] “ኢዝሀሩል ዓቂደቲ ሱኒያህ” ገጽ 297

[19] “ኢዝሀሩል ዓቂደቲ ሱኒያህ” ገጽ 300

[20] “ሰሪሁል በያን” ገጽ 225 መናሩል ሁዳ በተባለው መጽሄታቸው ቁጥር 21

[21] “ሰሪሁል በያን” ገጽ 225-244 እንዲሁም አልመቃላት ገጽ 189 ላይ ያሰፈራቸዉን አሳፋሪ ጽሁፎች መመልከት በቂ ነው

[22] ‘ሰሪሁል በያን’ ገጽ 232

[23] ‘ሰሪሁል በያን’ ገጽ 240

[24] ይህንን ሀዲስ ብዙዎች ዘግበዉታል፤ ቡኻሪ አታሪኽ አልከቢር ቅጽ5 ገጽ 240፣ ቲርሚዚይ በሀዲስ ቁጥር 3842፣ ኸላል “አሱናህ” በተባለው ጥራዛቸው ቁጥር 699፣ አል አጁሪይ “ሸሪዓህ” 1914፣ ኢብኑ አቢ ዓሲም “አል አሀድ ወልመሳኒ” 1129፣ ጠበራኒይ “አላውሰጥ” 660 ሌሎችም ዘግበዉታል። ታላቁ የዘመናችን ሙሀዲስ አልባኒ እንዲህ ብለዋል “በጥቅሉ ሀዲሱ ሰሂህ ነው። በእነዚህ ሁሉ መንገዶች መዘገቡ ደግሞ በጥንካሬ ላይ ጥንካሬን ይጨምርለታል” አሲልሲለቱ ሰሂሃህ ቅጽ 16 ገጽ 615 የሰነዱን ዝርዝር ሁኔታ ከ ገጽ 615-618 አብራርተውታል።

[25] ቡኻሪ በቁር 2924 ዘግበዉታል።

[26] ቡኻሪ በቁጥር 2799 እና በቁጥር 2800 የዘገቧቸው ሀዲሶች