Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ቁርአን የአላህ ንግግር ነው (የአህሉሱና አቋም)



http://www.facebook.com/asmaewesifat
ከአላህ የመናገር ባህሪ ጋር ተያይዞ የሚወሳው ቁርአን የአላህ ንግግር መሆኑ እና ፍጡር አለመሆኑ ነው፡፡ አህሉሱና ወልጀማዓህ ቁርአንን አስመልክቶ፤ “ከአላህ የተወረደና ፍጡር ያልሆነ፤ መነሻው ከአላህ የሆነ መመለሻውም ወደ አላህ የሆነ የአላህ ንግግር” መሆኑን ያምናሉ።
ይህ እምነት የሙስሊም ምሁራን የሚስማሙበትና የፈላስፋዎችንና አህሉልከላምን ማጭበርበሪያ ያልሰማ ማንኛውም ሙስሊም ህብረተሰብ የሚያምነው ነው። አይነ ስውር የፀሐይን ጮራ ማየት እንደማይችለው ሁሉ አጉል ፍልስፍናቸው የቁርአንን ብርሃን ያጨለመባቸው እነዚህ ሰዎች “ቁርአን ሙሉ በሙሉ የተፈጠረ የአላህ ፍጡር እንጂ የእርሱ ንግግር አይደለም” ይላሉ። አላህ አይናገርም ብለው ስለሚያምኑ ቁርዓን የአላህ ንግግር ነው ካሉ እምነታቸውን ስለሚያፈርስባቸው፤ ቁርዓን የአላህ ንግግር መሆኑን አስተባበሉ። ከእነርሱ መካከል ከፊሎቹ ደግሞ “ቁርዓን፤ የአላህ ነፍሳዊ(ውስጣዊ) ንግግር ነው” ይላሉ። ይህንንም ሲያብራሩት፤ ሀሳቡ የአላህ ሆኖ ቃሉ እና ገለጻው ግን የጅብሪል ወይም የነብዩه ንግግር ነው ይላሉ።ቁርዓን የአላህ ንግግር ነው። የአላህ ንግግር ደግሞ ባህሪው ነው እንጂ ፍጡር አይደለም። ይህ እኛ ዘንድ ያለው ከፋቲሃ እስከ ሱረቱ ናስ ያለው ቃል ፍጡር ነው የሚለው ፈተና በኢማም አህመድ ዘመን የቢድዓ አራማጆች ዋነኛ ሰው መፈተኛ አድርገዉት፤ ከወቅቱ ኸሊፋም ጋር ተባብረው ለአህሉሱና ከባድ ፈተናን ፈጥረው ነበር፤ ኢማሙ አህመድም በፈተናው በመጽናታቸው ለእስር ድብደባ እና እንግልት ተዳርገዋል። ቁርዓን ፍጡር ነው የሚለው ፍልስፍና ከተሳሳተ ግንዛቤ የመጣ ነው። ከበስተጀርባው የሚያስከተለው አደጋም የከፋ ነው፡፡ የአላህን ንግግር ፍጡር ነው ማለት፤ ከፍጡራን ንግግሮች ተለይቶ ለሰዎች መመሪያ የሚሆንበትን ምክንያትን ማሳጣት ነው፡፡ ይህንን ስንል ደግሞ ቃል እና መልዕክቱን እንጂ ወረቀት እና ቀለሙን አለመሆኑ ግልፅ ነው።

ቁርአን ላይ ያለው ትክክለኛው የቀደምት ኡለማዎች እምነት እንደሚከተለው ይገለፃል፦ “ቁርአን ከአላህ የተወረደ የአላህ ንግግር እንጂ ፍጡር አይደለም መነሻው ከእሱ ነው መመለሻውም ወደርሱ ነው”

ይህ የቀደምት ዑለማዎች ንግግር ሲሆን ጠንካራ ቁርዓናዊና ሀዲሳዊ መረጃዎችን መሰረት አድርገው ስለ ቁርአን የሚነገሩ የተሳሳቱ እምነቶች ብቅ ሲሉ የመከቱበት ቃል ነው፡፡ ቁርአን የአላህ ንግግር ስለመሆኑ አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَإِنْ أَحَدٌ مِّنَ الْمُشْرِكِينَ اسْتَجَارَكَ فَأَجِرْهُ حَتَّى يَسْمَعَ كَلَامَ اللَّهِ

“ከአጋሪዎችም አንዱ ጥገኝነትን ቢጠይቅ የአላህን ንግግር ይሰማ ዘንድ አስጠጋው” (ተውባህ 6)

ከአላህ የተወረደ ነው፤ ለሚለው ከሚጠቀሱ ማስረጃዎች መካከል፤ አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَإِنَّهُ لَتَنزِيلُ رَبِّ الْعَالَمِينَ

“እርሱም (ቁርአን) በእርግጥ ከዓለማት ጌታ የተወረደ ነው” (አሽ ሹዐራ 192)

ፍጡር አይደለም፤ ለሚለው ከላይ የተጠቀሱት አንቀፆች ሁሉ ማስረጃ ይሆናሉ። ምከንያቱም ንግግር ከተናጋሪ ተነጥሎ ለብቻው የሚታይ ሳይሆን የተናጋሪው አካል የሚገለፅበትና ከእሱ የማይለይ ነገር ነው፡፡ ይህም ቁርዓን ፍጡር ነው ለሚሉ ሰዎች ምላሽ ይሰጣል።
መነሻው ከእሱ ነው፤ ማለት የመጀመሪያው ቁርአንን የተናገረው አላህ ነው ማለት ነው። በዚህ ንግግር የተፈለገው ቁርአን የጅብሪል ወይም የነብዩ ንግግር ነው ለሚሉት ወገኖች ምላሽ መስጠት ነው፡፡ ቁርአንን ጅብሪል ወደ ነብዩ ለማድረስ ቢናገረውና ነብዩም ለህዝቡ ለማድረስ ቢናግሩትም የመጀመሪያ ተናጋሪው አላህ በመሆኑ የንግግሩ ባለቤት የሚባለው እርሱ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ፤ ዘይድ አንድ ስንኝ ቢቋጥር እና ቢያነብ አህመድ ደግሞ ከእርሱ ሰምቶ ይህን የግጥም ስንኝ ቢያነብ ይህ ግጥም የዘይድድ እንጂ የአህመድ እንደማይባል ግልፅ ነው፡፡

ወደርሱም ተመላሽ ነው፤ የሚለው አባባል የሚጠቁመው ከሰለፎች ቁርአን በመጨረሻው ዘመን ከሰዎች ተነስቶ ወደላይ እንደሚጓዝ የተነገረውን ነብያዊ ትንቢት ነው፡፡

Post a Comment

0 Comments