Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ለምን ተፈጠርክ?



ለምን ተፈጠርክ?
""""""""""""""""""""""""""""""""""""""

ለምን?
ለምን ወደዚህ ዓለም መጣህ? ለምን ተገኘህ? ለምን ተወለድክ? ለምን ተፈጠርክ?
ለምን? ራስህን ጠይቀው እስኪ?
ለምን እዚህ ምድር? ምን ላደርግ? ምን ልፈይድ መጣሁ?
"ለምግብ ለመጠጥ? ወይስ ላገባ ልወልድ? ነው ወይ ሀብት ንብረት ላከማች? ወይንስ ስልጣን ዙፋን ልይዝ? አሊያ ታዋቂ ተደናቂ ልሆን?"
አስተውል! ይህን ጥያቄ አንተም ሆንክ ሌላ - ማንም አይመልሰውም! ከፈጠረህ ጌታ በስተቀር!
እርሱ ግን ለምን እንደፈጠረህ ያውቃል፣ እርሱው ይነግርሀል? …
["ጋኔንንና ሰውን ሊገዙኝ (ሊያመልኩኝ) እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም ۞ ከነሱም ምንም ሲሳይ አልፈልግም፤ ሊመግቡኝም አልሻም"] ሱረቱ 'ዛሪያት 56-57
የተፈጠርከው ለዚህ ነው!
ፈጣሪህን ጌታህን አላህን፦ ልታውቀው ልታልቀው ልታከብረው ልትወደው፤ ያለ ተጋሪ በብቸኝነት ልታመልከው - ልትገዛው ነው!
ከእርሱ ሌላ ካለ የሀሰት ተመላኪ ልትርቅ ነው። ወደ እርሱ ልትመለስ፣ ልትሰግድ፣ ልትፆም ... ልትታዘዘው ነው!
እየውልህ! ተድላህ፣ ሀዘንህ፣ ኑሮህ፣ ሞትህ ለዛው ለፈጠረህ አላህ ለተፈጠርክበት አላማ ነው። ሌላ ግብ የለህም! …
["«ስግደቴ፣ መገዛቴም፣ ሕይወቴም፣ ሞቴም ለዓለማት ጌታ ለአላህ ነው» በል ۞ «ለእርሱ ተጋሪ የለውም፡፡ በዚህም (በማጥራት) ታዘዝኩ ... » (በል)"] አል -አንዓም 162-163
የምትኖረውም የምትሞተውም ለአምልኮ ነው! አላህን ብቻ እና ብቻ ለማምለክ!
ዓላማህ ላይ በስኬት ከተገኘህ ታላቅ ሽልማት አለህ። በዚህ ጭንቀት ሐሳብ ሩጫ ልፋት በማያቋርጥበት ዓለም፦ አንተ መልካም አስደሳችና ሰላማዊ ህይወትን ታጣጥማለህ።
በዛ ደግሞ ሰዎች እንደ ወንጀላቸው ወደ ገሀነም በሚነዱበት ዓለም ላንተ የማይሰፈር የማይመዘን፤ ያላየኸው ያልሰማኸው፣ በልብህም ውል ብሎብህ እንኳ የማያውቅ የፀጋ የተድላ የምቾት ሀገር ይጠብቅሀል። እንዳሻህ የምትምነሸነሽበት የጀነት ዓለም!
["ከወንድ ወይም ከሴት እርሱ አማኝ ሆኖ በጎን የሠራ መልካም ኑሮን በእርግጥ እናኖረዋለን፤ ይሠሩትም በነበሩት ነገር (በቀጣዩ ዓለም) ምንዳቸውን በተሻለ እንመነዳቸዋለን"] አል-ነህል 97
የምትኖርበት ዕድሜ ምንም አጭር ቢሆንም የተፈጠርክበትን አላማ ለማሳካት ከበቂ በላይ ነው። ግና መንገዱን ማወቅ አለብህ! ለዚህ ደግሞ አላህ አንተን ፈጥሮ አልተወህምና ይህን የሚያስተምሩህ አዛኝ እና ሩህሩህ ነብይ ልኮልሀል። መከተል ያንተ ፋንታ ነው!
["ከናንተው የሆነ ችግራችሁ በርሱ ላይ ጥኑ የሆነ፣ በናንተ (እምነት) ላይ የሚጓጓ፣ በምእምናን ላይ ርኅሩህ አዛኝ የሆነ መልክተኛ በእርግጥ መጣላችሁ"] ሱረቱ ተውባ 128
አስተውል! አላማህን መለየት ትልቅ ነገር ነው፤ እርሱን አሳክተህ ደግሞ ለተደገሰልህ ሽልማት መጓጓት ተገቢ ነው። ሆኖም አንድ ጥያቄ ሊኖርህ ይገባል፤ እንዴት አድርጌ ላሳካው? እንዴት አድርጌ አላህን ልገዛው?
ያዝ!
ከምንም ነገር እውቀት ይቀድማል። በቅድሚያ ፈጣሪህን፣ የምትገዛውን አላህን ፈጣሪነቱን፣ ንግስናውን፣ አስተናባሪነቱን ሌላውንም የጌትነት ስልጣኑን ልታውቅ! እንዲሁም በብቸኛ ተመላኪነቱ እሱን ብቻ ልትለምነው፣ ልትታገዝበት፣ ልትጠበቅበት፣ ለጭንቅህ ደራሽህ ልታደርገው የሚገባ መሆኑን ልትረዳ! በተጨማሪም የእርሱን መልካም ስምና ባህርያቱን አጥንተህ የጌታህን ብቸኛ ተመላኪነት (ተውሒድ) በትክክለኛው መልኩ ማወቅና ማመን ይጠበቅብሀል።
["እነሆ ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚገዙት አምላክ አለመኖሩን ዕወቅ ..."] ሙሐመድ 19
እንዲሁም እርሱ ወዳንተ የላከውን ነቢይ ሙሐመድ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ማንነት፣ ታሪክ፣ አስተምህሮ፣ የሳቸውንና እና የሶሐቦቻቸውን ፈለግ(ሱና) ልታውቅ ልትማር ይገባሀል።
በሌላ በኩል እንድትገዛው የፈጠረህ አላህ እርሱን በምን መልኩ መገዛት እንዳለብህ ያወረደውን የተሟላ እና ገር የሆነውን እስልምና ከመሰረቱ ጀምረህ ልትማር ይገባሀል።
ይህ የተፈጠርክበትን አላማ አሳክተህ ዘላለማዊ ደስታን የምትጎናፀፍበትን መንገድ የምታውቅበት ሂደት ነውና ከምንም ነገር በላይ ትኩረት ሰጥተህ መወጣት አለብህ!
ይህን የተማርከውን ያወቅከውን ደግሞ ወደ ተግባር በማምጣት የስኬት መንገድህን ለመጀመር የምታባክነው ግዜ ሊኖር አይገባም። ጠላትህ ከአላማህ አዘናግቶ በአላፊ ማታለያ ሊያደናቅፍህ ከመንገድህ ተሰይሟልና ለሸይጧን እድል መስጠት የለብህም!
["እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ወደ ኢስላም ጥቅልል ብላችሁ ግቡ፡፡ የሰይጣንንም እርምጃዎች አትከተሉ፤ እርሱ ለእናንተ ግልጽ ጠላት ነውና"] አል-በቀራ 208
ያወቅከውን እና በቻልከው ልክ በተግባር ላይ የምታውለውን የፅድቅ መንገድ ታዲያ ለሌላውም በማጋራት ያ ሰው ቅኑን መንገድ ቢከተል የሚያገኘውን ምንዳ ከርሱ ሳይቀነስ መቋደስን አትርሳ። ያወቅከውን ማሳወቅ ግዴታህም ጭምር ነውና በጥሩ ሁኔታ ማድረሱን አትዘንጋ!
ይሁንና የስኬት ጎዳና አልጋ ባልጋ አይደለም። ዘላለማዊ ደስታ ያለፈተና አይገኝም። በዚህች ምድር እስካለህ በተለያየ አቅጣጫ አቋምህን የሚፈታተን ተግዳሮት ይመጣብሀል፤ ይህኔ የትእግስትን ጋሻ አንግበህ ወደ ፊት መቀጠል እንጂ ፍፁም ወደኋላ ማለት የለብህም፤ ዓላማህን ጥለህ ወዴት ትመለሳለህ? ወደ ጀሀነም?
["ሰዎቹ አምነናል በማለታቸው ብቻ እነሱ ሳይፈተኑ የሚትተዉ መሆናቸውን ጠረጠሩን? ۞ እነዚያንም ከነሱ በፊት የነበሩትን በእርግጥ ፈትነናል፤ እነዚያንም እውነተኛዎቹን አላህ በእርግጥ ያውቃል፤ ውሸታሞችንም ያውቃል"] አል-ዓንከቡት2-3
በዓላማህ ፀንተህ ስትጓዝ አለማዊ ጥቅሞችህን ትተዋለህ ማለት አይደለም። ከዚህ መብቃቃት አይቻልህም! ይሁንና ለመኖር ስትል መብላት ይኖርብሀል እንጂ ለመብላት ስትል አትኖርም። ፈተናው እዚህ ላይ ነው፤ ጠላትህ ግን ተቃራኒውን ይሰብክሀል። እንዳትሸነፍ!
አላማህን በማሳካት ከዛ አስፈሪ ቅጣት ለመዳን እና ያንን የሚያስጎመዥ ሽልማት ለማግኘት መንገዱን ዛሬ ነገ ሳትል ጀምረው። ሞት መች መጥቶ እንደሚቀድምህ አታውቅምና!
["ከጌታችሁ ወደ ኾነችም ምሕረትና ስፋትዋ እንደ ሰማያትና ምድር ወደ ሆነች ገነት፥ አላህን ለሚፈሩ የተዘጋጀች ስትሆን ተቻኮሉ"] አሉ-ዒምራን 133
አላህ ባነበብነው የምንጠቀም ያድርገን!!
 አቡ ኢብራሂም ሙሐመድ ኢብራሂም
∞∞∞∞≅≅≅≅∞∞∞∞

๏| ነሲሓ መጽሔት ቅጽ Vol1 ቁጥር 1 |๏
መደብ | ነሲሓ ብዕር
http://nesiha.com/blog
https://telegram.me/nesihablog

Post a Comment

2 Comments