Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የምርጦች ምርጥ «ሙሐመድ» ﷺ


«ሙሐመድ» ﷺ
""""""""""""""""""""""""""""""""""""""

የአላህ ሰላምና ሠላት በርሳቸው ላይ ይሁን
“ሙሐመድ ﷺ” የታላቅ ሰው ስም የታላቅ ስብዕና መጠሪያ ነው:: ስለ ሙሐመድ ﷺ ብዙ ማወቅ ይጠበቅብሀል፡፡ የሚከተለው ፁሁፍ ስለ ማንነታቸው መሠረታዊ ዕውቀት ሊያስጨብጥህ ይሞክራል፡፡
“ሙሐመድ ﷺ” ማን ናቸው?
አላህ እንዲህ ብሏል፦ “አላህንና የመጨረሻውን ቀን የሚከጅል ለሆነ ሰው፣ አላህንም በብዙ ለሚያወሳ፤ ለእናንተ በአላህ መልዕክተኛ መልካም መከተል (አርአያነት) አላችሁ” (ሱረቱል አህዘብ 21)
“ሙሐመድ ﷺ” አላህ የሠው ልጆች እርሱን ብቻ እንዲያመልኩና ለህዝቦቻቸው ጥሪ እንዲያቀርቡ ከላካቸው ተከታታይ ነቢያት የመጨረሻው ነብይ መሆናቸውን እኛ ሙስሊሞች እናምናለን፡፡ አደም፣ ኑህ፣ ኢብራሒም፣ ኢስማኢል፣ ኢስሐቅ፣ ያዕቆብ፣ ዩሱፍ፣ ሙሳ፣ ዳውድ፣ ሱለይማን፣ ዒሳ (በሁሉም ላይ የአላህ ሰላምና እና ሠላት ይሁን) አንድ አይነት ሰማያዊ መልዕክት ያነገቡ ተከታታይ ነቢያቶች ናቸው፡፡
አላህ ለሙሳ ተውራትን አውርዶለታል፡፡ የሰዎች እጅ ገብቶበት ከመበረዙ በፊት የነበረው ኦሪት ከአላህ የወረደ መልዕክት መሆኑን እናምናለን፡፡ እንደዚሁ አላህ ለዒሳ የኢንጂል መልዕክት አውርዶለታል፡፡ ወንጌልም ከመበረዙ በፊት ከአላህ የወረደ መልዕክት መሆኑን እናምናለን፡፡ ቁርዓን በነብዩ ሙሐመድ ﷺ ላይ ወርዷል። ነገር ግን የመጨረሻ መልዕክት ነውና ከመበረዝ የተጠበቀ ነው፡፡ ቁርአን ቀድመው ከአላህ ለሠው ልጆች የወረዱ መልዕክቶችን የሚያብራራ ሆኖ ወርዷል፡፡ እኛ ሙስሊሞች በዚህ እናምናለን!!
ቁርዓን የህይወት መንገድ ነው፡፡ የመልዕክተኛው ባለቤት የምዕመናን እናት አዒሻ ስለ ባህሪያቸው ተጠይቃ የሠጠችው መልስ "በመሬት ላይ የሚራመድ ቁርዓን ነበሩ" የሚል ነበር። ይህ ማለት በዕለታዊ የህይወት ውጣ ውረዶች ውስጥ የቁርዓንን አስተምህሮት ተግባራዊ ያደርጉ ነበር ማለት ነው፡፡ መልዕክተኛው (ሠላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) የቁርዓንን የላቁ አስተምህሮቶች ወደ ተግባር እንዴት እንደቀየሩ ከብዙ በጥቂቱ ለመመልከት እንሞክር፡፡
አዛኙ ነብይ
አላህ እንዲህ ብሏል፦ “(ሙሐመድ ﷺ ሆይ!) ለዓለማትም እዝነት አድርገን እንጅ አልላክንህም፡፡” ሱረቱል አንቢያ 107
የአላህ መልዕክተኛ ለሰዎች ጥሪ ሲያደርጉ ወደ ሰላት፣ ጾምና ምጽዋት ብቻ አልነበረም፡፡ መልካም ስነ ምግባርም የጥሪያቸው አንድ አካል ነበር፡፡ አንድ ሰው ከሌሎች ሠዎች ጋር ያለውን ግንኙነት መልካም ማድረጉ ስለ አላህ ባለው እምነት ላይ ትጽዕኖ እንደሚኖረው አስተምረዋል፡፡ «ከእናንተ ውስጥ በላጩ የተሻለ ስነ-ምግባር ያለው ሰው ነው» በማለት ሙስሊሞችን አስተምረዋል።
እምነት የአንደበት ምስክርነት ብቻ አይደለም፡፡ በልብ የሰፈረው እምነት በተግባርም መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በርካታ የመልዕከተኛው ምክሮች እምነት ከተግባር ጋር ያለውን ትስስር ግልጽ አድርገው አስቀምጠዋል፡፡ «በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ ጎረቤቱን አያስቸግር፤ በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ እንግዳውን ያክበር፤ በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ መልካምን ይናገር ወይንም ዝም ይበል፡፡» ይህን ሀዲስ ቡኻሪ በሐዲስ ስብስቦቹ ቁጥር 6018 ላይ አስፍሮታል፡፡
እኝህ የመጨረሻ መልዕክተኛ በሠው ልጆች መካከል መተዛዘን እና መከባበር እንዲኖር በጽኑ አስተምረዋል፡፡ ቡኻሪ በቁጥር 5997 በዘገቡት ሐዲስ «(ለሌሎች) የማያዝን አላህ አያዝንለትም» በማለት የተናገሩትን እዚህ ላይ መጥቀስ ይቻላል፡፡
በሌላ ነብያዊ ሐዲስ፤ አንዳንድ ባለደረቦቻቸው አላህ በጣኦታዊያን ላይ ቅጣቱን እንዲያወርድ ዱዓ ያደርጉ ዘንድ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተወስቷል፡፡ መልዕክተኛው ይህን ጥያቄ ለመቀበል ፍቃደኛ አልነበሩም፡፡ የሰጡት ምላሽ «ተራጋሚ ሆኜ አልተላኩም፤የተላኩት ለእዝነት ነው » የሚል ነበር፡፡ ሀዲሱን ሙስሊም በቁጥር 2599 ዘግበውታል።
ይቅር ባዩ ነብይ
አላህ እንዲህ ብሏል፦
“ይቅርታም ያድርጉ፡፡ (ጥፋተኞቹን) ይለፉም፡፡ አላህ ለእናንተ ሊምር አትወዱምን አላህም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡” ሡረቱል ኑር 22
የአላህ መልዕክተኛ በጣም ይቅር ባይ ነበሩ፡፡ ልባቸው ንፁህ ነበር። በርግጥስ ቁርዓን ከወረደበት ከዚያ ድንቅ ልብ እንዴት ገር አይሁን? ሠዎች ለሚፈጽሙባቸው መጥፎና አስቸጋሪ ድርጊቶች ይቅርታን ይለግሱ ነበር፡፡ ሰዎች በርሳቸው ላይ የሚፈጽሙት ክፋት በጠነከረና በጨመረ ቁጥር ትዕግስትና ይቅር ባይነታቸው ይጨምር ነበር። በተለይም የሀይል ሚዛኑ ወደርሳቸው አድልቶ ጠላቶች በቁጥጥራቸው ስር ከሆኑ በኋላ ቻይ እና ይቅር ባይ መሆናቸው በገሀድ ታይቷል፡፡
የረሡል ይቅር ባይነት የአንድ ሰሞን ግዜያዊ መገለጫ አልነበረም፡፡ በሁሉም አስቸጋሪ እና ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ አብሯቸው ዘልቋል፡፡ ብዙ በደሎች ቢፈራረሩቁባቸውም ይቅርታ አድራጊነታቸውን የሚፈታተኑ አልነበረም። በተከበረው ቁርዓን ላይ የሰፈረውን መልዕክት በተጨባጭ ተግብረዋል፡፡
“ገር ፀባይን ያዝ፡፡ በመልካምም እዘዝ፡፡ ባለጌዎቹንም ተዋቸው፡፡” (አዕራፍ 199) ...
እኩልነትና የዘር መድሎ
አላህ እንዲህ ብሏል፦ “አላህ ዘንድ በላጫችሁ በጣም አላህን ፈሪያችሁ ነው” ሠረቱል ሁጅራት 13
ስለ ሰው ልጆች ክብርና እኩልነት ከሙሐመድ ﷺ (ሰላምና ሰላት በርሳቸው ላይ ይሁን) የተሻለ ያስተማረ ማን አለ? በአላህ ዕይታ የሰው ልጆች ሁሉ እኩል እንደሆኑ አስተምረዋል፡፡ ለዚህም ተከታዮቹን ሀዲሶች ማስተዋል በቂ ነው።
"የሁላችሁም አባት አደም ነው፡፡ አደም (የተፈጠረው) ከአፈር ነው፡፡ በዘሩ ወይንም በቆዳው ቀለም ምክንያት፤ ዓረብ የሆነው ዓረብ ባልሆነው ላይ፣ ጥቁሩ በነጩ ላይ ብልጫ የለውም፡፡ ማንኛውም ሰው የተለየ በላጭነትና ክብር የሚያገኘው አላህን በመፍራት ብቻ ነው፡፡" አህመድ በሀዲስ ቁጥር 23489 ዘግበውታል፡፡ የሰው ልጆች በዘራቸውና በቆዳቸው ቀለም ምክንያት መናቅና መገለል እንዳይደርስባቸው እኩልነትን የሰበከ መልዕክት ነው፡፡
በሌላ ሐዲስ ረሱል የሚከተለውን ብለው አስተምረዋል፤ «አላህ ወደ መልካችሁ እና ገንዘቦቻችሁ አይመለከትም፡፡ ነገር ግን ወደ ልባችሁና ተግባራችሁ ይመለከታል» ሙስሊም በሐዲስ በቁጥር 2564 ዘግበውታል።
ቡኻሪ በዘገቡት ሌላ ሐዲስ፤ ከባልደረቦቻቸው መካከል አንዱ ‹‹የጥቁር ሴት ልጅ» በማለት ተገቢ ባለሆነ መልኩ ሌላውን ሰው ሲጠራ ተሠማ፡፡ የአላህ መልዕክተኛ በጣም ተቆጡ፡፡ "በእናቱ (የቆዳ ቀለም) ልታነውረው ሞከርክን? አንተ በርግጥ መሐይምነት በውስጥህ ያለብህ ሰው ነህ" በማለት ወረፉት፡፡
መጥፎን በመልካም የሚመልስ ነብይ
አላህ እንዲህ ብሏል፦ “መልካሚቱና ክፉይቱም (ጸባይ) አይስተካከሉም፡፡ በዚያች እርሷ መልካም በኾነችው ጸባይ (መጥፎይቱን) ገፍትር፡፡ ያን ጊዜ ያ ባንተና በእርሱ መካከል ጠብ ያለው ሰው እርሱ ልክ እንደ አዛኝ ዘመድ ይኾናል፡፡”
ሱረቱል ፉሲለት 34
መጥፎን ተግባር በመጥፎ አለመመለስ የመልዕክተኛው መገለጫ ነበር።«የአላህ መልዕክተኛ መጥፎን በመጥፎ፣ ክፋትን በክፋት አይመልሱም ነበር፡፡ ይልቁንም ይቅር ባይ ነበሩ» ቡኻሪ በሀዲስ ቁጥር 4838 ዘግበውታል
ኢስላማዊ የታሪክ ድርሳናት፤ ታላቁ ነብይ ሙሐመድ ﷺ የበደሏቸውን ሊበቀሉ የሚችሉባቸው ብዙ አጋጣሚዎች እንደነበሩና ሆኖም መበቀል እየቻሉ ይቅር ማለታቸውን በሚያስረዱ በርካታ ክስተቶች ታጭቀዋል፡፡
አስቸጋሪና አስጨናቂ የህይወት ምዕራፎችን በጠንካራ ትዕግስት መጋፈጥ እንደሚያስፈልግ አስተምረዋል፡፡ «ጠንካራ ሠው በትግል የሚያሸንፍ አይደለም፡፡ ጠንካራ ሰው በቁጣ ወቅት እራሱን የሚቆጣጠር ነው» በማለት ምክር ሰጥተዋል፡፡(ቡኻሪ 6114)
እርግጥ ነው ትዕግስትና መቻቻል እንዲሁም መጥፎን በመልካም መመለስ አንድ ሙስሊም ለራሱ የሚሠጠውን ግምትና ክብር አሉታዊ አያደርገውም፡፡ ጥቃትና የመብት ጥሰት ቢፈፀምበትም በዝምታ ይመልከት ማለትም አይደለም፡፡ በደልን ከራስ ላይ የመከላከል መብትን ኢስላም ያከብራል፡፡ በይቅርታ ማለፍን ግን ያበረታታል፡፡
ድርቅና የማያውቀው ጸባየ ለስላሳ
አላህ እንዲህ ብሏል፦ “ከአላህም በኾነች ችሮታ ለዘብክላቸው፡፡ ዐመለ መጥፎ ልበ ደረቅም በኾንክ ኖሮ ከዙሪያህ በተበተኑ ነበር” አል ዒምራን 159
አነስ ኢብን ማሊክ ለ10 ዓመታት ከመልዕክተኛው ጋር በቅርብ አብሮነት ያገለገለ እድለኛ ወጣት ነበር፡፡ አነስ ስለ ባህሪያቸው እንዲህ ሲል ይናገራል፡፡ «በፍፁም አንድ ነገር ካደረግኩ በኋላ ለምን ይህን አደረግክ ብለው ወቀሳ ሰንዝረውብኝ አያውቁም፤ ያልሰራሁት ነገር ኖሮም (በወቀሳ) ለምን ይህን ነገር አልሠራህም ብለውኝ አያውቁም፡፡» አህመድ 12784 ዘግበውታል
አንድ ሰው የመልዕክተኛውን ክብር ዝቅ ለማድረግ ሞከረ፡፡ ባለቤታቸው አዒሻ ተቆጣች፡እርሳቸው ግን እንድታረጋጋ መከሯት፡፡ “አዒሻ ሆይ ተረጋጊ! አላህ ሩህሩህ ነው፤ በሁሉም ነገሮች ላይ ለስላሳነትን ይወዳል” ሲሉ ገሠጿት። ቡኻሪ በቁጥር 6024 ዘግበውታል
በሌላ ዘገባ ደግሞ «ማንኛውንም ነገር ውስጥ እዝነትና ልስላሴ ሲኖሩ ውበትን ያላብሱታል። ከምንም ነገር ላይ ሲጎድሉ ደግሞ ያጠለሹታል» በማለት መናገራቸውን ሙስሊም በቁጥር 2594 ዘግበውታል
ከኩራት የራቀ ለሰዎች ተናናሽ
አላህ እንዲህ ብሏል፦ “የአልረሕማንም ባሮች እነዚያ በምድር ላይ በዝግታ የሚኼዱት፣ ባለጌዎችም (በክፉ) ባነጋገሩዋቸው ጊዜ ሰላም የሚሉት ናቸው፡፡” ፉርቃን ፡ 63
የአላህ መልዕክተኛ ከኩራት የፀዳ ስብዕና ነበራቸው፡፡ ሲገቡ በደረሱበት ክፍት ቦታ ይቀመጣሉ፡ሰዎች ለርሳቸው ክብር ከመቀመጫቸው እንዳይነሱ ዘወትር ይከለክላሉ፡፡ ከባልደረቦቻቸው ለየት ያለ ልብስ አያደርጉም፡፡ ከችግረኛ ድሆች እንዲሁም እድሜያቸው ከገፋ ሽማግሌዎች ጋር ቆይታ ያደርጋሉ፡፡ ባሎቻቸው የሞቱባቸው ረዳት አልባ ሴቶች ድጋፍ እንዲያገኙ ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ ከሌሎች ተለይተው መታየትን ስለማይፈልጉ በሰዎች ምካከል ሲሆኑ እንግዳ ሰው አይለያቸዉም ነበር፡፡
ለሶሀቦቻቸው ከኩራት ስለመጽዳትና ራስን ዝቅ ስለማድረግ አስተምረዋል፡፡ የአላህ መልዕክተኛ «ከኩራት በመራቅ ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ አንዳችሁ በሌላው ላይ ራሱን የበላይ ለማድረግ ትምክህት አይግባው፤ አንዳችሁ በሌላው ላይ ወሰን አይለፍ የሚል መልዕክት አላህ አውርዶልኛል» ብለው መናገራቸውን ሙስሊም በሐዲስ ቁጥር 2865 ዘግቧል፡፡
የአላህ መልዕክተኛ ሰላም በርሳቸው ላይ ይሁንና ከአላህ ውጭ ለእርሳቸው አምልኮ እንዳይፈጸም በመስጋት ውዳሴንና ሙገሳን አይፈልጉም ነበር፡፡
« ክርስቲያኖች የመርየም ልጅ ዒሳን ከፍ ከፍ በማድረግ (ወሰን እንዳለፉት) እኔንም ከፍ በማድረግ (ወሰን አትለፉ) እኔ የአላህ ባሪያ ነኝና “የአላህ ባሪያና መልዕክተኛ” ስትሉ ጥሩኝ» በማለት ተናግረዋል፡፡ ይህን ሐዲስ ቡኻሪ የሐዲስ ስብስብ ስራው ላይ በቁጥር 3445 አስፍሮት ይገኛል፡፡
ተምሳሌታዊ የትዳር አጋር
አላህ እንዲህ ብሏል፦ «“ሴቶችን”…በመልካምም ተኗኗሩዋቸው» ኒሳእ ፡ 19
ለዓለማት እዝነት የተላኩት ነብይ ለትዳር አጋራቸው ተገቢውን ውዴታ፤ ክብርና እንክብካቤ የሚለግሱ ተምሳሌታዊ የትዳር አጋር ነበሩ። አጅግ የሚወዷት ውዷ ባለቤታቸው የሙዕሚኖች እናት አዒሻ ይህን ምስክርነት ሰጥታለች፡፡ «የአላህ መልዕክተኛ በቤት ውስጥ የትዳር አጋራቸውን (በስራ) ያግዙ ነበር፡፡ ልብሳቸውን ይሰፉና ጫማቸውን ይጠግኑ ነበር፡፡ እንደማንኛውም ሰው የቤት ውስጥ ስራዎችን ያከናዉኑ ነበር፡፡» አህመድ በቁጥር 25341 ዘግበውታል
ሙሐመድ ﷺ ሙስሊሞች ሁሉ የእርሳቸውን ፈለግ እንዲከተሉና ለትዳር አጋራቸው መልካም የህይወት ጓደኛ እንዲሆኑ ምክር ሰጥተዋል፡፡ «የተሟላ እምነት ያለው አማኝ የተሻለ ስነ ምግባር ያለውና ለትዳር አጋሩ በተሻለ ጥሩ የሆውነ ነው» አህመድ በቁጥር 24204 ዘግበውታል
ፈለጉን ሊከተሉለት የሚገባ ድንቅ አርአያ
አላህ እንዲህ ብሏል፦ “አንተም በታላቅ ጠባይ ላይ ነህ!” ሡረቱል ቀለም 4
በጥቂቱ የነብዩ ሙሐመድ ﷺን ማንነት ለመጥቀስ ተሞክሯል። ስለ ኢስላምና ሰለዚህ ታላቅ ስብዕና አንዳንድ መገናኛ ብዙሀን የሚነዙትን መሠረተ-ቢስ አሉባልታዎች መሰረት በማድረግ እይታቸውን ለገነቡ ሰዎች እነዚህ በእዝነት የተሞሉ እውነታዎች እንግዳ ሊሆኑባው ይችላሉ፡፡
ኢስላምን ለመረዳት ካሰብን የኢስላም መሠረታዊ ምንጮች የሆኑትን ቁርዓንንና እና የመልክተኛውን አስተምህሮ መሰረት ማድረግ ግድ ይለናል፡፡ ከአንዳንድ ሙሰሊሞች የተዛነፉ ተግባራት በመነሳት ኢስላም ላይ አሉታዊ አቋም መያዝ ከፍትሀዊነት የራቀ ይሆናል፡፡

ሙስሊም ያልሆኑት ታዋቂ ሰዎች ስለነብያችን ምን አሉ?
የህንድ ነጻነት እንቅስቃሴ የፖለቲካ መሪ ማህተመ ጋንዲ እንዲህ ብሏል፤ “መልዕክተኛው እራሱን አለማካበዱ፣ ለገባው ቃል እውነተኛነቱ፣ ለጓደኞቹና ለምዕመናን ታማኝነቱ፣ በአምላኩና በያዘው ተልዕኮ ያሳየው ሙሉ መተማመን እና መሰል ባህሪያቱ እንጂ ችግሮችን ለመወጣት የበቃው በሰይፍ አልነበረም!!”
ታዋቂው እንግሊዛዊ ደራሲ ጆርጅ በረናርድ ሾው ስለሳቸው እንዲህ ብሏል፤ «ዛሬ ላይ ዓለም ችግሮቹን የሚፈታለት እንደ ሙሐመድ ﷺ አይነት ስብዕና በእጅጉ ያስፈልገዋል፡፡ በመሐከለኛው ዘመን የኖሩ የሀይማኖት አባቶች በዕውቀት ማነሰ ወይም በጭፍን ጥላቻቸው ምክንያት ስለ ሙሐመድ ﷺ ሃይማኖት የተዛባ ጨለምተኛ ምስል ለማስቀመጥ ሞክረዋል፡፡ የክርስትና ጠላት አድርገው ስለውታል፡፡ በግሌ ስለዚህ ሰው ማንነት ባደረግኩት ጥናት የድንቅ ተዐምራዊ ስብዕና ባለቤት ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በጭራሽ የክርስትና ጠላት እንዳልሆነ ድምዳሜ ላይ ደርሻለሁ፡፡ እንዲያውም የሠው ልጆች መድህን ተብሎ ሊሠየም ይገባዋል፡፡ በግል አስቴያየቴ ዛሬ የዓለም ጉዳዩችን ሙሐመድ ﷺ ቢመራቸው የሰው ልጆች የሚናፍቁትን ሠላምና ደስታ በማረጋገጥ ችግሮቻቸውን እንደሚቀረፍ አምናለሁ፡፡ የአውሮፓን ግዛት እንደ ሙሐመድ ﷺ አይነት ሰው ቢመራው ከህመሞቹ ሁሉ እንደሚፈውሰው አምናለው።አዎን! ሙሐመድ ﷺ የሰው ልጆች መድህን ተብሎ ሊጠራ ይገባል!»
∞∞∞∞≅≅≅≅∞∞∞∞

๏| ነሲሓ መጽሔት ቅጽ Vol1 ቁጥር 1 |๏
መደብ | ነሲሓ የዕውቀት ማዕድ
 
 
 

Post a Comment

0 Comments