Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ከሙሐመድ ኢብኑ ዐብዲል ወሃብ በፊት የነበሩ “ወሃቢዮች”

ከሙሐመድ ኢብኑ ዐብዲል ወሃብ በፊት የነበሩ “ወሃቢዮች”
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
ሱፍያ ለኢስላም እንግዳ የሆነ አስተሳሰብ ነው። ይህንን ከግሪክ፣ ከህንድ፣ ከፋርስና ከክርስትና ፍልስፍናዎች የተውጣጣ ወፍ ዘራሽ አስተሳሰብ አንዳንዶች “ነባሩ እስልምና” እያሉ በሃሰት ሲያሞካሹት ቢታይም በቂ የሆነ ብዥታ የመግለጥ ስራ አልተሰራም። እንዲያውም ሱፍያን መቃወም ከሸይኽ ሙሐመድ ኢብኑ ዐብዲል ወሃብ የተሃድሶ ንቅናቄ በኋላ የመጣ ጠርዘኛ መስመር እንደሆነ የሚያስቡት ቀላል አይደሉም። እውነታው ግን ወዲህ ነው። ለዚህም እማኝ ይሆን ዘንድ ከሸይኽ ሙሐመድ ኢብኑ ዐብዲል ወሃብ መምጣት በጣም ቀድሞ ሱፍያ ላይ የሰላ ትችት የሰነዘሩ ታዋቂ ዑለማዎችን ለአብነት ያክል እጠቅሳለሁ።
1. ኢማሙ ማሊክ (179 ሂ.)፡- “እኛ ዘንድ ሱፍያ የሚባሉ ሰዎች አሉ። በብዛት ይበሉና ከዚያ ያንጎራጉራሉ። ከዚያም ተነስተው ይጨፍራሉ” ሲሏቸው “ህፃናት ናቸው?” ብለው ጠየቁ። “አይደሉም” አሏቸው። “እብዶች ናቸው?” ሲሉ “አይደሉም። ሸይኾች ናቸው” አሏቸው። “እኔ ከኢስላም ሰዎች ይህን የሚሰራ አንድም አልሰማሁም” አሉ። [ተርቲቡል መዳሪክ፡ 2/53]
2. ኢማሙ ሻፊዒይ (204 ሂ.)፡ “ተሶውፍ የተገነባው ስንፍና ላይ ነው።” “አንድ ሰው ሱፊያን አርባ ቀን ይዞ በፍፁም አእምሮው ወደሱ አይመለስም” ብለዋል። [ተልቢሱ ኢብሊስ፡ 320፣ 327] በተጨማሪም “አንድ ሰው ጧት ሱፊ ከሆነ ዙህር በሱ ላይ አይደርስም ቂል ሆኖ የምታገኘው ቢሆን እንጂ!!” ብለዋል። [መናቂቡ ሻፊዒይ፣ ነይሀቂ፡ 2/207]
3. መርዋን ኢብኑ ሙሐመድ አዲመሽቂ (210 ሂ.) (ከኢማሙ ማሊክ ባልደረቦች ናቸው) እንዲህ ይላሉ፡- “ሶስት ሰዎች አይታመኑም። ሱፊ፣ ተራኪና በሙብቲደዕ ላይ መልስ የሚሰጥ ሙብተዲዕ። ” [ተርቲቡል መዳሪክ፡ 2/53]
4. ኢብኑ በጧህ አልዑክበሪ (387 ሂ.)፡- “ዘፈንን ማዳመጥ ዑለማዎች የሚጠሉት ግና ቂሎች የሚወዱት ነገር ነው። ይህንን የሚሰሩት ሱፍያ የሚባሉ ቡድኖች ናቸው። … የዘቀጡ አላማዎችና የፈጠራ ሃይማኖት ባለቤቶች ናቸው። … ልጆችንና ሴቶችን በማሰማት ይዘፍናሉ፣ ይጮሃሉ፣ እራሳቸውን ስተው ይወድቃሉ፣ የሞቱ መስለው ለሰዎች ይታያሉ። ይህ ሁሉ የሚሆነው ለጌታቸው ካላቸው ብርቱ ውዴታና ናፍቆት የተነሳ እንደሆነ ይሞግታሉ። እነዚህ መሀይሞች ከሚሉት ነገር አላህ ከፍ ያለ መላቅን ላቀ።” [ተልቢሱ ኢብሊስ፡ 211]
5. አልቃዲ አቡ ጦይብ አጥጦበሪ (450 ሂ.)፡- “ይህቺ ቡድን (ሱፍያ) ለሙስሊም ጀማዐ ተፃራሪ ነች። ምክንያቱም ዘፈንን ዲንና መቃረቢያ አድርገዋልና። በመስጂዶች ውስጥና በሌሎችም ክቡር ቦታዎች በግልፅ ሲያንፀባርቁት አይቻለሁ።” [አስሰማዕ ሊብኒል ቀይዪም፡ 262]
6. አቡበክር አጦርጡሺ (451 ሂ.)፡- “የሱፍያ አካሄድ ቦዘኔነት፣ መሀይምነትና ጥመት ነው። ኢስላም ማለት የአላህ ቁርኣንና የመልእክተኛው ሱና እንጂ ሌላ አይደለም።” [ተፍሲሩል ቁርጡቢ፡ 11/238]
7. ኢብኑ ዐቂል (513 ሂ.)፡- “ሱፍዮች ስራን ያበላሻሉ። የእምነት መሰረቶችን ያናጋሉ። ቦዘኔነትንና ዜማ ማዳመጥን ይወዳሉ።…” “በሸሪዐ ላይ እንደ ዒልመል ከላም ሰዎች እና እንደ ሱፍያ ያለ አደጋ የለም።” [ተልቢሱ ኢብሊስ፡ 375]
8. ኢብኑል ጀውዚ (597 ሂ.)፡- ሱፍዮች አደገኛ ቦዘኔዎች መሆናቸውን ደጋግመው ገልፀዋል። ጥቂት ንግግሮቻቸውን ላጣቅስ፡-
- “አቡ ኑዐይም አልአስፈሃኒ መጣና ‘አልሒልያ’ ኪታብን (ለሱፍዮች) አዘጋጀላቸው። መጥፎና አስቀያሚ ነገሮችን በሱፍያ ውስጥ አሰፈረ። እነ አቡበክር፣ ዑመር፣ ዑሥማን፣ ዐልይና ክቡራን ሶሐቦችን  በሱፍያ ውስጥ ሲጠቅስ አላፈረም።” [ተልቢሱ ኢብሊስ፡ 148]
- “እነዚህ ሰዎች የነብያቸው የሙሐመድን ሃይማኖት በመተው ‘ተሶውፍ’ የሚሉት አዲስ ሃይማኖት የጀመሩ  ይመስላሉ!!” [ተልቢሱ ኢብሊስ፡ 275]
- “አቡ ሓሚድ (አልገዛሊ) ፊቅህን በተሶውፍ የሸጠበት ዋጋ ምንኛ የረከሰ ነው?!” [ተልቢሱ ኢብሊስ፡ 312]
- “ሱፍዮች እስከሚመጡ ድረስ አፈንጋጮች (ዘናዲቃ) ሸሪዐን ለመተው አልተዳፈሩም ነበር!!” [ተልቢሱ ኢብሊስ፡ 329]
- “አብዛኛው ቂላቂል ከነሱ (ከሱፍያ) ጋር ነው። አላህ ምድርን ከነሱ ያጥራትና።” [ሶይዱል ኻጢር፡ 238]
9. አልቁርጡቢ (671 ሂ.)፡- “ሱፍዮች የፈጠሩትን (ዜማ) በተመለከተ በክልክልነቱ ላይ ውዝግብ ከማይነሳበት ነገሮች ነው። ነገር ግን ብዙ በመልካም የሚታሰቡ ሰዎችን ስሜት አሸንፏቸዋል። ብዙዎቹ ላይ የእብዶችና የህፃናት ስራዎች እስከሚታዩባቸውና በተጠና መልኩ እስከሚደንሱ ደርሰዋል። ከዚያም ከፊል ሰዎች መቃረቢያና መልካም ስራ እስከማድረግ ደረሱ።…” [ተፍሲሩል ቁርጡቢ፡ 14/54]
10. ከማሉዲን አልአድፈውይ (748 ሂ.)፡- “ማንቀላፋትና መሀይምነት ሱፍዮች መሀል የተንሰራፋ ነው። አንዳንዶቻቸው ድንቁርናቸው ልክ በማለፉ ግልፅ የሆኑ ህሊናዊ እውነታዎችን ይክዳሉ። ሁለት ተቃራኒ ነገሮችን በአንዴ ሰብስበው ያምናሉ።” [አጥጧሊዑ አስሰዒድ፡ 133]
እነዚህ በሙሉ በ1115 ሂ. ከተወለዱት ሸይኽ ሙሐመድ ኢብኑ ዐብዲል ወሃብ እጅግ ቀድመው ያለፉ ናቸው። የሱፍያ አድናቂዎች ግን “ተሶውፍ ነባሩ እስልምና ሲሆን፤ እሱን የሚተቹት ደግሞ በዘመናዊቷ ሳዑዲ ፔትሮ ዶላር የሚደገፉ ወሃብዮች ናቸው” ይሉናል። በርግጠኝነት ይህንን ድንቁርና የሚያስተጋቡ አካላት ከሁለት ምርጫ አይወጡም።
- ወይ ከኢስላማዊ እውቀትም፣ ከታሪክ ትምህርትም የረባ እርሾ የሌላቸው መድረክ ያገነናቸው ጥራዝ ነጠቆች ናቸው።
- ካልሆነ ግን ለኢስላምምም ለሙስሊሞችምም የተዳፈነ ጥላቻ ያረገዙ ሲሆኑ ኢስላምን ለማዳከም፣ ሙስሊሞችን ለመምታት ይመቻቸው ዘንድ ተሶውፍ ሁነኛ መሳሪያ ስለሚሆናቸው ነው። ተሶውፍ ሙስሊሞችን በጫቱ፣ በኹራፋቱ፣ በእንቶ ፈንቶው አፍዝዞ እግር ከወርች ተብትቦ የሚያስር ስለሆነ አላማቸውን ለማሳካት ሁነኛ ምርጫ ነው። አይሁዳዊው ፕሮፌሰር ሃጋር ኤርሊች አዲስ አበባ መጥቶ “ለኢትዮጵያ የሚበጀው እስልምና አሕባሽ ነው” ማለቱን አስታውሱ። የወያኔ ስርኣት አሕባሽን አቅፎ ሙስሊሞችን ማሳደዱ የቅርብ ትዝታ ነው።
በዚህ ረገድ ብዙ ምሳሌዎች ስለሚኖሩ በአላህ ፈቃድ ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ። ለጊዜው መጠቆም የፈለግኩት ግን ተሶውፍ የቁርኣንና የሐዲሥ መሰረት የሌለው ወፍ ዘራሽ አስተሳሰብ እንደሆነና በዚህ ባይተዋር አካሄዱ የተነሳ ከ “ወሃብያ” መምጣት በጣም ቀድሞ በዑለማዎች የሰላ ሂስ ሲሰነዘርበት እንደነበር መጠቆም ነው።

(ኢብኑ ሙነወር፣ ጥቅምት፡ 27/2012)

Post a Comment

0 Comments