Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ዚክር፣ የዘነጋነው ሃብት

 

ዚክር፣ የዘነጋነው ሃብት
~~~~~~~~~~~~~~
መቼም ሰው ነንና ፈራሽ እንደሆንን እናውቃለን። እንደ ሙስሊም ከሞት በኋላ ህይወት እንዳለ እናምናለን። ስለሆነም የአኺራችን ጉዳይ ያስጨንቀናል። ለዚህም ሲባል በጌታችን ህግ ለመኖር፣ ትእዛዛቱን ለመፈፀም ክልከላውን ለመራቅ፣ ስለ ድክመታችን ተውበት ለማድረግ እንሞክራለን። ሆኖም ግን አንድ በቀላል ጥረት ብዙ ትርፍ የምንሸምትበትን ነገር ስንዘነጋ እንስተዋላለን።
አዎ ስራሽን እየሰራሽ፣ መኪናህን እየሾፈርክ፣ ወረፋ እየጠበቃችሁ፣ በመኪና እየተጓዝክ፣ ሰው እየጠበቅሽ፣ በእግራችን እየተንቀሳቀስን፣… ዚክር ቢደረግ በየእለቱ ስንትና ስንት አጅር በሰበሰብን ነበር። ዚክር ከምናስበው እጅግ የላቀ ፋይዳ አለው። ነብዩ ሶለ፞ላ፞ሁ ዐለይሂ ወሰለ፞ም እንዲህ ብለዋል:–

"أَلَا أُنَبِّئُكُمْ بِخَيْرِ أَعْمَالِكُمْ، وَأَزْكَاهَا عِنْدَ مَلِيكِكُمْ، وَأَرْفَعِهَا فِي دَرَجَاتِكُمْ، وَخَيْرٌ لَكُمْ مِنْ إِنْفَاقِ الذَّهَبِ وَالْوَرِقِ، وَخَيْرٌ لَكُمْ مِنْ أَنْ تَلْقَوْا عَدُوَّكُمْ، فَتَضْرِبُوا أَعْنَاقَهُمْ، وَيَضْرِبُوا أَعْنَاقَكُمْ ".
قَالُوا : بَلَى.
قَالَ : " ذِكْرُ اللَّهِ تَعَالَى".
* "ከ(መልካም) ስራዎቻችሁ በላጭ፣
* ከንጉሳችሁ ዘንድ የጠራ፣
* ደረጃዎቻችሁን ከፍ የሚያደርግ፣
* ወርቅና ብር ከመለገስ የሚሻላችሁ፣
* ጠላቶቻችሁን አግኝታችሁ አንገቶቻቸውን ከምትመቱና አንገቶቻችሁን ከሚመቱ (ከጂሃድ) የሚበልጥባችሁን አልነግራችሁምን?"
√ (ሶሐቦች):– "እንዴታ! (ይንገሩን) የአላህ መልእክተኛ ሆይ" አሉ።
* "አሸናፊና የላቀውን አላህ ማውሳት" አሉ።
[ቲርሚዚ ዘግበውታል: 3377]
ትልልቅ ምንዳ ያላቸው አጫጭር ዚክሮች
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
① ነብዩ ሶለ፞ላ፞ሁ ዐለይሂ ወሰለ፞ም እንዲህ ብለዋል:–
(مَن قال: سبحان الله وبحمده، في يوم مائة مرة، حُطَّت خطاياه وإن كانت مثل زبد البحر)؛
"በቀን ውስጥ መቶ ጊዜ ‘ሱብሓነላ፞ሂ ወቢሐምዲሂ’ ያለ ሰው ወንጀሎቹ እንደ ባህር አረፋ ቢሆኑ እንኳን ይረግፉለታል።" [ቡኻሪ]
② እናታችን ጁወይሪያህ ቢንቲል ሓሪሥ ረዲየላ፞ሁ ዐንሃ ባስተላለፈችው በአንድ ወቅት ነብዩ ሶለ፞ላ፞ሁ ዐለይሂ ወሰለ፞ም ሱብሕን ከሰገዱ በኋላ ማለዳ ላይ ከሷ ዘንድ ወጡ። እሷ መስገጃዋ ላይ ተቀምጣ ዚክር ላይ ነች። እዚያው እንደተቀመጠች ረፋድ ላይ ተመለሱ።
"ካንቺ ከተለየሁ ጊዜ አንስቶ እስካሁን በተለየሁብሽ ሁኔታ ላይ ከመሆን አልተወገድሽም?" አሏት።
"አዎ" አለች።
በዚህን ጊዜ እንዲህ አሉ:–
" لَقَدْ قُلْتُ بَعْدَكِ أَرْبَعَ كَلِمَاتٍ ثَلَاثَ مَرَّاتٍ، لَوْ وُزِنَتْ بِمَا قُلْتِ مُنْذُ الْيَوْمِ لَوَزَنَتْهُنَّ : سُبْحَانَ اللَّهِ وَبِحَمْدِهِ عَدَدَ خَلْقِهِ، وَرِضَا نَفْسِهِ، وَزِنَةَ عَرْشِهِ، وَمِدَادَ كَلِمَاتِهِ ".
"በእርግጥም ካንቺ በኋላ አራት ንግግሮችን ሶስት ጊዜ ተናግሬያለሁ። ከንጋት ጀምሮ አንቺ ካልሺው ጋር ቢመዘኑ (እኔ ያልኳቸው) ይመዝናሉ።
* ሱብሓነላ፞ሂ ወቢ ሐምዲሁ ዐደደ ኸልቂሁ፣
* ወሪዷ ነፍሲሂ፣
* ወዚነተ ዐርሺሂ፣
* ወሚዳደ ከሊማቲሂ።" [ሙስሊም የዘገቡት]
③ ነብዩ ሶለ፞ላ፞ሁ ዐለይሂ ወሰለ፞ም እንዲህ ብለዋል:–
(كلمتان خفيفَتان على اللسان، ثقيلَتان في الميزان، حبيبَتان إلى الرحمن: سُبحان الله وبحمده، سبحان الله العظيم)؛
"ምላስ ላይ የቀለሉ፣ ሚዛን ላይ የከበዱ እና አረ፞ሕማን ዘንድ የተወደዱ ሁለት ንግግሮች አሉ። ‘ሱብሓነላ፞ሂ ወቢሐምዲሂ፣ ሱብሓነላ፞ሂል ዐዚም።" [ቡኻሪና ሙስሊም]
④ ነብዩ ሶለ፞ላ፞ሁ ዐለይሂ ወሰለ፞ም ከጀነት ድልብ ሃብቶች ውስጥ እንደሆነ የገለፁት የዚክር አይነት
(لا حول ولا قوة إلا بالله)؛
"ላ ሐውለ ወላ ቁወ፞ተ ኢላ፞ ቢላ፞ህ" [ኢብኑ ሒባ፞ን]
⑤ ነብዩ ሶለ፞ላ፞ሁ ዐለይሂ ወሰለ፞ም እንዲህ ብለዋል:–
(مَن قال: لا إله إلا الله وحده لا شريك له، له الملك وله الحمد وهو على كل شيء قدير - عشر مرات - كان كمَن أعتق أربعة أنفُسٍ مِن ولد إسماعيل)
"አስር ጊዜ ’ላ ኢላሀ ኢለ፞ላ፞ህ ወሕደሁ ላ ሸሪከ ለህ። ለሁል ሙልኩ ወለሁል ሐምዱ። ወሁወ ዐላ ኩሊ፞ ሸይኢን ቀዲር’ ያለ ሰው ከኢስማዒል ልጆች አራት ነፍሶችን ነፃ እንዳወጣ ነው።" [ሙስሊም]
⑥ ነብዩ ሶለ፞ላ፞ሁ ዐለይሂ ወሰለ፞ም እንዲህ ብለዋል:–
(سيِّد الاستغفار أن تقول: (اللهمَّ أنت ربي، لا إله إلا أنت، خلقتَني وأنا عبدُك، وأنا على عهدك ووعدك ما استطعتُ، أعوذ بك من شرِّ ما صنعتُ، أبوء لك بنعمتك عليَّ، وأبوء لك بذنبي، فاغفر لي، فإنه لا يغفر الذنوب إلا أنت، قال: ومَن قالها من النهار موقنًا بها، فمات من يومه قبل أن يُمسي فهو مِن أهل الجنَّة، ومَن قالها من الليل وهو مُوقن بها، فماتَ قبْل أن يُصبح، فهو مِن أهل الجنَّة)؛
"የኢስቲግፋር ሁሉ አለቃ ‘አላ፞ሁመ፞ አንተ ረቢ፞ ላ ኢላሀ ኢላ፞ አንተ። ኸለቅተኒ። ወአነ ዐብዱከ። ወአነ ዐላ ዐህዲከ ወወዕዲከ መ’ስተጦዕቱ። አዑዙ ቢከ ሚን ሸሪ፞ ማ ሶነዕቱ። አቡኡ ለከ ቢኒዕመቲከ ዐለየ፞። ወአቡኡ ለከ ቢዘንቢ። ፈግፊር ሊ። ፈኢነ፞ሁ ላ የግፊሩ ዙ፞ኑበ ኢላ፞ አንተ’ የሚለው ነው።
በሷ አረጋግጦ በቀኑ ካላት በኋላ ሳያመሽ በእለቱ የሞተ ሰው እርሱ ከጀነት ሰዎች ነው። በሷ አረጋግጦ በሌሊት ካላት በኋላ ሳያነጋ የሞተ ሰው እርሱ ከጀነት ሰዎች ነው።" [ቡኻሪ]
እነዚህ ምሳሌዎች ብቻ ናቸው። ሌሎችም ብዙ አሉ። ከነዚህ በተጓዳኝ ከውዱእ በኋላ፣ ከአዛን በኋላ፣ መስጂድ ስትገባ፣ ከመስጂድ ስትወጣ፣ ከሶላት በኋላ፣ ከምግብ በኋላ፣ ስትተኛ፣ ስትነሳ፣ ወዘተ ያሉትን ብትል ቆጥረህ የማትዘልቀው አክተር አለህ።
በጥቅሉ ጊዜህን መድበህ ዚክርን የህይወትህ አካል አድርገው። ለዚህ ከተቸገርክ እየሰራህ፣ እየተጓዝክ ዚክር ትኩረት እንጂ የረባ ጥረት አይጠይቅህም። መልእክተኛው ሶለ፞ላ፞ሁ ዐለይሂ ወሰለ፞ም እንዳሉት "ምላስህ አላህን በማውሳት ከመርጠብ አይወገድ።"

Ibnu Munewor

አድራሻዎቻችን ይቀላቀሉ

ፌስቡክ           ቴሌግራም         ዩቲዩብ

Post a Comment

0 Comments