Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የሰላም ዋጋ




እርሱ የሚወስናቸውና የሚፈፅማቸው ድርጊቶች ሁሌም ቢሆን በጥበብ የታጀቡ ናቸው። ታዲያ ነገሮች ሲቀያየሩ ሁኔታዎች ሲፈራረቁ ሙስሊሞች ሁል ጊዜም ቢሆን አዳዲስ ክስተቶችንና ሁኔታዎችን የሚያስተናግዱባቸው መርሆዎች አሏቸው።
ግን ብዙዎች ምናልባት ነገሮችን በምን መልኩ ማስተናገድ እንዳለባቸው፤ ችግሮችን ወይም ፈተናዎችን በምን መልኩ መጋፈጥ እንደሚገባቸው ላይረዱ ይችላሉ። ያም ሆነ ይህ ኢስላም ለሁሉም ችግር መፍትሄ ያለው ሁለንተናዊ የሕይወት መንገድ ነው። ታዲያ ሁሉንም ህዝብ የሚመለከቱ አስፈላጊ እና አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ሰዎች በስሜት እየተነዱ የሚወስዷቸው እርምጃዎች ብዙ ዋጋዎችን ሊያስከፍሏቸው ይችላሉ። ስለዚህ ነገሮችን ረጋ ብሎ ማጤን ፤ ሳይቸኩሉ አመሳክሮና አስተውሎ መንቀሳቀስ ተገቢ ነው።
ከዚህ አንፃር አሁን ባለንበት ጊዜ በአገራችን እየተከሰቱ ያሉ በርካታ ክስተቶች አሉ፤ እና ሰዎች ደግሞ እነዚህን ክስተቶች የሚጋፈጡባቸው ስሜቶች እና ግንዛቤዎች የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም ሁላችንንም ሊያስማሙ የሚችሉ በርካታ ጉዳዮች አሉ፤ ከነዚህ ነጥቦችን ውስጥ አብዛኛዎቹ ወይም ሁሉም ነጥቦች ሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኙ የሚችሉ፤ ሰዎች ሙስሊም ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ሙስሊም ባይሆኑ እንኳን ሊስማሙባቸው የሚገቡ ርእሶች ናቸው። እናም ከአብዛኃኛዎቹ ወንድሞች እና እህቶች የተሰወሩ ሁነው ሳይሆን መታዋወስ ጠቃሚነት አለውና ለመመካከር ያህል ነው ማለት ነው።
የመጀመሪያው ነጥብ የሰላም ዋጋን እና አስፈላጊነትን የተመለከተ ነው ፤ አንዳንድ ሰዎች ዘንድ ስለሰላም አስፈላጊነት መናገር የተወሰኑ ፖለቲከኞችና ካድሬዎች ድርሻ ይመስላቸዋል፤ ይህ ስሕተት ነው። ሰላም እና መረጋጋት አላህ ለህዝቦች ከሚሰጣቸው በርካታ ፀጋዎች መካከል ከዋነኞቹ የሚመደብ ነው።
ለዚህም ነው አላህ - ሱብሓነሁ ወተዓላ - በተለያዩ የቁርአን አንቀጾች ላይ የሰላምን አስፈላጊነት እና የዋጋውን ትልቅነት ብሎም በተለያዩ ህዝቦች ላይ የዋለው ትልቅ ፀጋ እና ውለታ መሆኑንም የሚገልፀው፤ ስለዚህ ይህ ምስጋና የሚያስፈልገው ትልቅ ከአላህ ዘንድ የተሰጠን ፀጋ ነው ማለት ነው።
ለምሳሌ ፡
{ فَلْيَعْبُدُوا رَبَّ هَٰذَا الْبَيْتِ الَّذِي أَطْعَمَهُم مِّن جُوعٍ وَآمَنَهُم مِّنْ خَوْفٍ }
ይላል [|የዚህን ቤት ጌታ ይግገዙ ያምልኩ |] ካለ በኋላ [| ያ! ከረኃብ በኋላ ያበላቸው , ከፍርሃትም በኋላ ሰላምን የሰጣቸው ጌታ |] ይላል (ቁረይሽ ፥ 3-4)
ልብ ሊባል የሚገው አላህ - ሱብሓነሁ ወተዓላ - ምግብ ማጣትን እና ሰላም ማጣትን አንድ ላይ አቆራኝቶ ጠቅሷቸዋል። ይህ ደግሞ በዚህ አንቀጽ ላይ ብቻ አይደለም። በሱረቱ-ነሕል      ፥ 112 ላይ ፦
  وَضَرَبَ اللَّهُ مَثَلًا قَرْيَةً كَانَتْ آمِنَةً مُّطْمَئِنَّةً يَأْتِيهَا رِزْقُهَا رَغَدًا مِّن كُلِّ مَكَانٍ فَكَفَرَتْ بِأَنْعُمِ اللَّهِ فَأَذَاقَهَا اللَّهُ لِبَاسَ الْجُوعِ وَالْخَوْفِ بِمَا كَانُوا يَصْنَعُونَ
ሰላም እና መረጋጋት ሰፍኖባት የነበረችን አንዲትን መንደር ወይም አካባቢ እንደምሳሌ ጠቀሰ፤ የዚህ መንደር ሲሳይ ከሁሉም ቦታ በምቾት ወደ እነሱ ይመጣላቸው ይፈስላቸው ነበረ እና በድሎትና በፍሰኃ እየኖሩ ነበር ማለት ነው። ታዲያ እነሱ የአላህን ፀጋ አላመሰገኑም { فَكَفَرَتْ بِأَنْعُمِ اللَّهِ } [| በአላህ ፀጋዎች ካዱ |] በምስጋና ፋንታ ክህደትን አስከተሉ፤ እናም ውጤቱ ምን እንደሆነ ሲያወሳ { فَأَذَاقَهَا اللَّهُ لِبَاسَ الْجُوعِ وَالْخَوْفِ بِمَا كَانُوا يَصْنَعُونَ } [| የረኃብ እና የፍርሃት ልባስን አለበሳቸው |] ለምን? { بِمَا كَانُوا يَصْنَعُونَ } [| ይሰሩት በነበሩት ስራ የተነሳ |] ማለት ነው።


አንዳንድ ሰዎች ዘንድ ስለ ሰላም አስፈላጊነት መናገር የተወሰኑ ፖለቲከኞችና ካድሬዎች ድርሻ ይመስላቸዋል፤


እናም ሰላምን ማጣት ምግብን ከማጣት ጋር የተቆራኘው ምናልባት የሰላም ዋጋ ከምግብ ዋጋ ጋራ ግንኙነት ስላለው ይሆናል። ማለትም ሰዎች ልክ ምግብ እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ ሰላምም ያስፈጋቸዋል ማለት ነው።
እንዲሁም አላህ - ሱብሓነሁ ወተዓላ - ምን ይላል ፦
 أَوَلَمْ يَرَوْا أَنَّا جَعَلْنَا حَرَمًا آمِنًا وَيُتَخَطَّفُ النَّاسُ مِنْ حَوْلِهِمْ ۚ 
(ዐንከቡት ፥ 67).
[| "ሐረም"ን ጸጥተኛ እንዳደረግንላቸው አይመለከቱም ወይ? |]  ሐረም ማለት ፡ በመካ እና በመዲና ክልል ውስጥ የሚገኝ በሌሎች ቦታዎች የተፈቀዱ አንዳንድ ተግባራት የሚከለከሉበት የተከበረ የፀጥታ ክልል እንደማለት ነው። እናም ይህንን የፀጥታ ክልል አላደረግንላቸውም ወይ? ማለት በፊት ከኢብራሒም - ዐለይሂ ሰላም - ዘመን ጀምሮ የተደነገገ ፀጥታን የሚያሰፍን ህግ በመኖሩ የተነሳ በሰላም መኖር ችለው የለ ወይ? እንደማለት ነው።
ነገር ግን በዙሪያቸው ያለውን ሲመለከቱ ደግሞ { وَيُتَخَطَّفُ النَّاسُ مِنْ حَوْلِهِمْ } ሰዎች በግድ ከሃገራቸው እየተጠለፉ እየተወሰዱ ባሉበት ሁኔታ ላይ እነሱ ግን ሰላም መሆናቸውን አይመለከቱም ወይ ማለት ነው። ይህ ትልቅ ትምህርት ነው።
ሰዎች የሰላምን ዋጋ ለማወቅ ችግር በራሳቸው ላይ እስኪደርስ መጠበቅ የለባቸውም። ብልጥ ሰው ከሌሎች ችግር ትምህርት ይወስዳል፤ ሞኝ ደግሞ እንደሚታወቀው በራሱ ላይ ከደረሰ በኋላ ብቻ ነው ትምህርት የሚወስደው፤ በጣም ደግሞ የለየለት  ከሆነ በራሱ ላይ ችግር ቢደርስ ራሱ ይህ ትምህርት ሊሆነው አይችልም ማለት ነው። አላህን ከዚህ ሰላም እንዲያደርገን እንጠይቀዋለን!
እንደዚሁም በሌላ አንቀጽ ላይ አላህ - ሱብሓነሁ ወተዓላ - ፦
أَوَلَمْ نُمَكِّن لَّهُمْ حَرَمًا آمِنًا يُجْبَىٰ إِلَيْهِ ثَمَرَاتُ كُلِّ شَيْءٍ رِّزْقًا مِّن لَّدُنَّا .. 
(ቀሰስ ፥ 57).
[| ፀጥተኛ የሆነ ሰላም የሰፈነበት የ"ሐረም" ክልል አላመቻቸንላቸውም ወይ? የሁሉም ነገር ፍሬዎች ወደሱ የሚወሰዱበት የሚጋዙበት ሃገር አልሰጥናቸውም ወይ? |] ይለናል። ስለዚህ አላህ - ሱብሓነሁ ወተዓላ - ይህንን የሰላም ትልቅ ፀጋ ለከሀዲያኑ የሚያስታውሰው ያለምክንያት አይደለም፤ ዋጋው በጣም ከፍ ያለ ስለሆነ ነው።
በዚህም የተነሳ ኢስላም ይህንን ሰላም ሊያናጋ ሁከትን ሊያስነሳ የሚችልን ሰበብ ሁሉ ከመጀመሪያዉኑ ከልክሏል። የሰዎችን ነፍስ ያለአግባብ መግደል፣ የሰዎችን ንብረት ያለአግባብ መቀማት ብሎም እንኳን የሰዎችን አይደለም የራስንም ነፍስ ማጥፋትን እጅግ አድርጎ ኮንኗል፤ የራስንም ንብረትም ያለአግባብ ማጥፋትንም እንደዚሁ ከልክሏል። እንኳን ማውደም ይቅር እና ያለአግባብ ማባከን ራሱ ተከልክሏል።
 በጥቅሉ ስለሰላም በብዛት የሚወሳበት እና የሚዘከርበት ምክንያት ሰዎች ሰላም ከሌለ ሕይወታቸው ውጥንቅጥ ውስጥ ይገባል፤ ሕይወታቸው ሲባል ደግሞ እምነታቸውም እዚህ ውስጥ ይካተታል። ስለዚህ ለዲኑ የሚጨነቅ ሰው ለሰላምም መጨነቅ ይገባዋል። ሰላም በሌለበት ሁኔታ መስጂዶች ውስጥ ተገናኝተው ሙስሊሞች ዲናቸውን መማማር ይከብዳቸዋል፤ የሰዎች ሁሉ ትኩረት ወደ ሌላ ነገር ነው የሚያዘነብለው ፤ ሌላው ቀርቶ ሰዎች እውነታን እንዲረዱ፣ ኢስላምን እራሱ በተገቢው መልኩ እንዲገነዘቡ ሰላም አንድ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው። ለዚህም ደግሞ ማሳያ እንዲሆን አንድ የታወቀ ክስተት አለ፤ መልእክተኛው ሙሐመድ - ዐለይሂ ሶላቱ ወሰላም - ነብይ ሆነው ከተላኩበት ጊዜ አንስቶ ሰዎችን ወደ አላህ - ሱብሓነሁ ወተዓላ - ሲጣሩ ነበረ ፤ እናም የተወሰኑ ሰዎች በዚህ ጥሪያቸው ተማርከው ኢስላምን ተቀብለዋል።
ከዚያ በኋላ በ6ኛው አመተ ሂጅራ መልእክተኛው - ዐለይሂ ሶላቱ ወሰላም - ከሶሓቦቻቸው ጋራ ከመዲና ተነስተው ወደ መካ ዑምራ ለማድረግ ተጉዘው ነበረ እና እነዚያ በመካ የነበሩ ከሀዲያን ሙስሊሞቹ ወደ መካ ዘልቀው የዑምራ ስርአት እንዲያከናውኑ አልፈቀዱላቸውም። እናም በዚያው ሁኔታ ላይ በሁለቱ ወገኖች መካከል የሰላም ስምምነት ተፈፅሞ ነበረ፤ ይህ | صلح الحديبية | "ሱልሑል ሑደይቢያ" ተብሎ ይታወቃል።
እናም በስምምነቱ ውስጥ ከተካተቱት ቁም-ነገሮች መካከል አንዱ፦ ሁለቱም ወገኖች ለ10 አመታት ያክል ውጊያን እንዲያቆሙ ልክ ያው የተኩስ አቁም ስምምነት ፈፀሙ ማለት ነው። ታዲያ ከዚህ ስምምነት በኋላ ወደ አገራቸው ወደመዲና እየተመለሱ እያሉ አላህ - ሱብሓነሁ ወተዓላ - በመልእክተኛው ላይ አንድን የቁርአን ምዕራፍ አወረደ።
 إِنَّا فَتَحْنَا لَكَ فَتْحًا مُّبِينًا  (ፈትሕ ፥ 1}
[| ግልፅ የሆነ መክፈትን ከፍተንልሃል |] ይላቸዋል  "ፈትሕ" የሚለው ቃል በዚህ አገባብ ድልን የሚያበስር ነው ፤ እናም አብዛኃኛዎቹ የኢስላም ሊቃውንት , አብዛኃኛዎቹ የተፍሲር አዋቂዎች ይህንን "ፈትሕ" በዚህ አንቀጽ ላይ "ፈትሕ" ተብሎ የተሰየመው "ሱልሕ ሑደይቢያ" ያ! በሑደይቢያ ያደረጉት ስምምነት ራሱ እንደሆነ ይናገራሉ።
ኢብኑ መሥዑድ እና ሌሎችም ሶሓቦች ይህን አስመልክቶ ምን ይላሉ ፦
||" إنكم تعدون الفتح فتح مكة، ونحن نعد الفتح صلح الحديبية "||
እናንተ እንደ ድል ወይም አገርን መቆጣጠር የምትቆጥሩት | فتح مكة | "ፈትሕ መካ" ወይም የመካ መከፈት ነው መካ በሙስሊሞች እጅ ተመልሳ መሆኗን ነው ፤ ነገር ግን እኛ እንደፈትሕ የምንቆጥረው "ሱልሑል ሑደይቢያ"ን ነው ይለናል፤ የሑደይቢያን ስምምነት ነው።
ነገር ግን እኛ እንደ "ፈትህ" የምንቆጥረው "ሱልሕ አልሑደይቢያ"ን ነው - የሑደይቢያን ስምምነት። እንደዚሁም ጃቢር -ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሁ- ምን ይላሉ
 ||"ما كنا نعد الفتح إلا يوم الحديبية"||
"ፈትህ" ብለን የምንቆጥረው "የውመል ሁደይቢያ" የሁደይቢያን ቀን እንጂ ሌላን አልነበረም ይላሉ። ልክ እንደዚሁ አነስ ኢብን ማሊክ - ረዲየላሁ ተዓላ ዓንሁ -
إِنّا فَتَحنا لَكَ فَتحًا مُبينًاَ
አልፈትህ:1] የሚለውን አንቀፅ ሲያብራሩ ምን አሉ ... "አልሑደይቢያህ" ይህ "ፈትህ" የተባለው ሑደይቢያ ነው፤ የሑደይቢያ ስምምነት ማለታቸው ነው። ይህንን አልቡኻሪ እና ሌሎች ዘግበውታል።

ንግግራችን የሚያመጣውን ተፅእኖ ሳናስብ እንዲሁ ያለገደብ ድጋፍን ወይም ተቃውሞን እንሰነዝራለን። ይህ ደግሞ ከተጠያቂነት አያድነንም።

ታዲያ መልእክተኛው - ዓለይሂ ሶላቱ ወሰላም - ከዚህ በፊት እንደ በድር ዘመቻ ያሉ ድልን የተቀናጁባቸው ክስተቶች ነበሩ። ግን ከነዚህ በተለየ መልኩ አላህ - ሱብሐነሁ ወተዐላ - ይህን የሰላም ስምምነት "ፈትህ" ብሎ የጠራበት ምክንያት ምን ይሆን? ይህም ግልፅ በሆነ ምክንያት ነው፤ ዑለማዎች በተለያዩ ኪታቦቻቸው ላይ አስፍረውታል።
ነገር ግን ከቀደምት የኢስላም ሊቃውንት ንግግሮች መካከል አንዱን ለመጥቀስ ያህል አልኢማም አ'ዙህሪይ - ሙሐመድ ኢብኑ ሺሀብ አዙህሪይ ታላቁ ታቢዒይ - ይህን አስመልክቶ ኢብኑ ኢስሀቅ እንደሚያስተላልፉት እና ኢብኑ ሂሻም በታወቀው የሲራ መፅሀፋቸው ላይ እንዳሰፈሩት (አ'ዙህሪይ) ምን ይላሉ ...
 ||"ما فتح في الاسلام فتح قبله كان أعظم منه"||
"በኢስላም ከሱ ማለትም ከ"ሱልሕ አልሁደይቢያ" የበለጠ ድል ኖሮ አያውቅም" ትልቁ ድል ይህ ነው ይላሉ።
በመቀጠልም (አ'ዙህሪይ) ከዛ በፊት ሰዎች የነበሩበትን ሁኔታ ሲያወሱ ...
||"إنما كان القتال حيث التقى الناس"||
ከዛ በፊት ግን "ሰዎች እንደጠላት ሲገናኙ ውጊያ መከሰቱ አይቀርም ነበረ"
||"فلما كانت الهدنة وضعت الحرب وأمن الناس كلهم بعضهم بعضا, فالتقَوا فتفاوضوا في الحديث والمنازعة, فلم يكلم أحد بالإسلام يعقل شيئا إلا دخل فيه"||
"ነገር ግን ይህ የሰላም ስምምነት ሲፀድቅ ጦርነትም ሲቀር እንደዚሁም ሰዎች ከፊሎች ለከፊሎች ሰላምን ሲሰጡ ማለት እርስ በርስ መተማመን በመካከላቸው ሲሰፍን እና ተገናኝተው በንግግር አንድ ሁለት መባባል ሲጀምሩ - በመረጃ መወያየት ሲጀምሩ -" ምን ሆነ ይሉናል "አዕምሮው ክፍት የሆነ ግንዛቤ ያለው ሰው ሁሉ ስለኢስላም ሲነገረው ቀጥታ ወደ ኢስላም መግባት እንጂ ሌላ አማራጭ አልነበረውም"
ስለዚህ ይህ ዲንን ለማሰራጨት ይበልጥ የተመቸ ነበረ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ኢስላም ባብዛኛው በምን እንደተስፋፋ የሚያሳይ ነው። ቀጥሎ (አ'ዙህሪይ) ምን ይላሉ ...
||"فلقد دخل في تينك السنتين في الإسلام مثل من كان في الإسلام قبل ذلك وأكثر"||
"በርግጥም በነዚህ ሁለት አመታት ውስጥ" ማለትም ነብዩ - ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም - ሁደይቢያ ስምምነት ከፈፀሙበት አንስቶ መካን እስኪቆጣጠሩ ባሉት "ሁለት አመታት ውስጥ" ይላሉ።
እንዲያውም ሁለት አመት እራሱ አይሞላም ምክንያቱም የሁደይቢያ ስምምነት በ6ኛው አመተ ሂጅራ በዙልቂዕዳ ወር ነበር ከዛ መልእክተኛው - ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም - መካን የተቆጣጠሩት በ8ኛው አመተ ሂጅራ በረመዳን ወር ነበር።
ይህም የሆነበት ምክንያት እነዚያ በመካ የነበሩ የአጋርያኑ መሪዎች እና ባላባቶች የአስር አመቱን የሰላም ስምምነት በማፍረሳቸው እና ካፈረሱ ሌሎች ወገኖች ጋር አብረው በመተባበራቸው ነው።
ያም ሆነ ይህ አ'ዙህሪ ንግግራቸውን ሲቀጥሉ ...
 ||"فلقد دخل في تينك السنتين في الإسلام مثل من كان في الإسلام قبل ذلك وأكثر"||
"በነዚህ በሁለት አመታት ብቻ ከዛ በፊት ከሰለመው ወይም ኢስላምን ከተቀበለው ሰው የማይተናነስ ወይም የሚበልጥ ሰው ኢስላምን ተቀብሏል" ይሉናል።
 ምን ማለት ነው መልእክተኛው -ዓለይሂ ሶላቱ ወሰላም - ጥሪያቸውን ከጀመሩበት ግዜ አንስቶ እስከ "ሱልህ አልሑደይቢያ" ድረስ 19 አመታት አልፈዋል፤ ማለትም ከሒጅራ ስድስተኛ አመት ላይ እንደሆነ አውቀናል፣ ከዛ በፊት ደግሞ በመካ ያሳለፏቸው 13 አመታት አሉ፤ እና እነዚህን አንድ ላይ ስንደምር 19 አመታት አሉ ማለት ነው። እና በ19 አመታት ከሰለመው ህዝብ በሁለት አመቱ የሰላም ግዜ የሰለመው ህዝብ ቁጥር ያየለ ነው ማለት ነው።
ይህንን ኢብን ሒሻም በሲራ መፅሀፋቸው ሲያብራሩ ምን ይላሉ ...
||"والدليل على قول الزهري أن رسول الله خرج إلى الحديبية في ألف وأربع مائة"||
"ይህንን የአልኢማም አዙህሪን ንግግርን ትክክለኝነት የሚያሳየው ነገር መልእክተኛው - ዓለይሂ ሰላቱ ወሰላም - ወደ ሁደይቢያ ሲሄዱ 1400 ያክል ተከታዮችን ይዘው ነው የተጓዙት"
ይህ እንግዲህ አልቡኻሪ እና ሙስሊም ላይ ጭምር ያለ ትክክለኛ ዘገባ ነው። አንዳንድ ዘገባዎች ላይ አንዳንድ ሶሐቦች "1500 ነበሩ" ይላሉ። ያም ሆነ ይህ በ1400 እና በ1500 መካከል ነበረ ቁጥራቸው። እናም "||خرج إلى الحديبية في ألف وأربع مائة"|| ጃቢር ኢብን ዓብዲላህ በሚያስተላልፉት ዘገባ ላይ "1400 ያክል" እንደነበሩ ተነግሯል።
||"ثم خرج فى عام فتح مكة بعد ذلك بسنتين فى عشرة آلاف"||
"ከዛ በኋላ ከሁለት አመት በኋላ ብቻ መካን ለመቆጣጠር ባደረጉት ጉዞ ላይ አስር ሺህ ተዋጊ ይዘው ነው የገቡት"
ስለዚህ በሁደይቢያ ስምምነት ላይ ከፍ አድርገን 1500 ነበሩ ብንል እንኳ ሁለት አመት ባልሞላች የሰላም ግዜ 8500 ያክል አዲስ ተከታይ አፍርተው ነበር። ከዛ በፊት ግን 1500 ብቻ ያክል ነበሩ። ልብ በሉ ይሄ በጦርነት እና መሰል ክስተቶች ላይ የማይሳተፉትን ሴቶችን፣ ህፃናትንና ትላልቅ ሰዎችን ወይም በሆነ አጋጣሚ ሳይመቻቸው የቀሩትን የሚያካትት አይደለም። ነገር ግን (ይህ) የለውጡ ማሳያ ነው። ሁለት አመት ባልሞላ ግዜ ውስጥ ያገኙት ትርፍ በ19 አመታት ውስጥ ካገኙት ትርፍ የላቀ ነው። ያውም በብዙ እጥፍ!
ስለዚህ ሰላም እና መረጋጋት ለዲን፣ ለዳዕዋ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ እጅግ በጣም ከፍ ያለ ነው። ነገር ግን ይህንን ብዙዎች ባለመገንዘብ ምናልባት ሰላምን የሚያደፈርሱ ክስተቶች ላይ በቀጥታ ባይሳተፉ ራሱ በተዘዋዋሪ የሚሳተፉባቸው አጋጣሚዎች አሉ።
ቀጥታ ተሳትፈው ሰዎችን የሚገድሉ ወይ ንብረትን የሚያወድሙትን - እንዲያው ስለነሱ ብዙ ማለት የሚያስፈልግ አይመስለኝም። ሆኖም ግን ከኋላ ሆነን በንግግር እና በመሰል ድጋፎች ሰዎች እርስ በርስ እንዲባሉ፣ ሰላም እንዲጠፋ፣ ሁከት እንዲጎለብት አስተዋፅኦ የምናደርግ ብዙ ልንንኖር እንችላለን።
ንግግራችን የሚያመጣውን ተፅእኖ ሳናስብ እንዲሁ ያለገደብ ድጋፍን ወይም ተቃውሞን እንሰነዝራለን። ይህ ደግሞ ከተጠያቂነት አያድነንም። ሀላፊነት የጎደላቸውን ቃላት እንዲሁ መሰንዘር ማብቃት ይጠበቅበታል። አንዳንድ ግዜኮ የትላልቅ እልቂቶች መነሻ ንግግር ሊሆን ይችላል። ጦር ያልፈታውን ወሬ ይፈታዋል ነው ነገሩ።
ችግሮች በተፈጠሩ ቁጥር ገና ሳይባባሱ የማረጋጋት ስራ መስራት የሁሉም ሀላፊነት ሊሆን ይገባዋል። ትንሽ እሳት ደግሞ ቶሎ አስፈላጊውን እርምጃ ካልተወሰደ አገር ልታጠፋ ትችላለች። ለሁከትና ለአላስፈላጊ እልቂት የሚያበቁ ክስተቶችን ባጠቃላይ ገና ሳያድጉ በፊት ቶሎ የማርገብና የማረጋጋት ስራን መስራት ልማዳችን ሊሆን ይገባል።
ብዙዎች ባለመገንዘብ ምናልባት ሰላምን የሚያደፈርሱ ክስተቶች ላይ በቀጥታ ባይሳተፉ ራሱ በተዘዋዋሪ የሚሳተፉባቸው አጋጣሚዎች አሉ።

አንዳንድ ግዜ ደግሞ ቃል ባንናገር እንኳ የሆነ ቦታ መገኘታችን ብቻ የአንድ ወገን ደጋፊ ተደርገን እንታሰብና ያ ወገን የሚፈፅመውን ጥፋት ሁሉ የምንደግፍ ሊመስል ይችላል። በተለይ ተሰሚነት ያለን ሰዎች ከሆንን!! ይህንን የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ከታሪክ ልጥቀስ ...
አዩብ አ'ሲኽቲያኒ - ረሂመሁላህ - በኢብን አሽዓስ የፈተና ወቅት የተከሰተን አንድ ክስተት ሲያወሳልን የሚከተለውን ይላል። የኢብን አሽዕስ ፈተና ማለት - ዓብደረህማን ኢብን አሽዓስ በተባለው ግለሰብ መሪነት የተነሳ አንድ ፈተና ነበር።
ይህም አልሐጃጅ ኢብኑ ዩሱፍ በነበረው የበደል አቋም የተነሳ እሱ ላይ አምፀው የወጡ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ እና እነዚህ አማፅያን በተቻላቸው አቅም የሰዎችን ልብ ለመማረክ ከነሱ ጋር የተወሰኑ ዓሊሞችን ለመቀላቀል ይሞክሩ ነበር። 
አዩብ አሲኽቲያኒ እንደሚለው ...
 ||"قيل لابن الأشعث إن أردت أن يقتلوا حولك كما قتلوا يوم الجمل حول جمل عائشة فأخرج معك مسلم بن يسار فأخرجه مكرها"||
 ለኢብኑል አሽዓስ ምን ተባለ "ሰዎች ልክ በአዒሻ ግመል ዙሪያ ሁነው ህይወታቸውን ሰውተው ለመከላከል እንደተዋጉት በአንተም ዙሪያ ሁነው ህይወታቸውን እየሰው እንዲዋጉልህ ከፈለክ ሙስሊም ኢብን የሳርን ይዘህ ውጣ" ማለት ሰዎች ይህን ሰው ስለሚወዱት እሱ ከነርሱ ጋር በሚሆንበት አጋጣሚ ለመከላከል ብለው ትልቅ መስዋአትነት ይከፍላሉ ለማለት ፈልገው ነው። እናም ይህን ሲሰማ ሳይፈልግ በግድ ከነርሱ ጋር እንዲቀላቀል ብሎ ይዞት ሄደ።
አዩብ (አ'ሲኽቲያኒ) ከአቡ ቂላባ በሚያስተላልፈው ምን ይላል አቡ ቂላባ ለሙስሊም ቢን የሳር እንዲህ አለው - ይህ እንግዲህ ያ ክስተት ካለፈ በኋላ ነው - ...
 ||"قال أيوب عن أبي قلابة قال لي مسلم بن يسار أحمد الله إليك أني لم أرم بسهم ولم أضرب فيها بسيف"||
"እኔ አላህን አወድሳለሁ - አመሰግናለሁ - ምክንያቱም አንድም ቀስት አልወረወርኩም በሰይፍም አንድም ቢሆን አልተማታሁም" አሉ፤ ያው ይዘውኝ ወጡ እንጂ አልተዋጋሁም ማለታቸው ነው። በዚህ ግዜ አቡቂላባ ምን አልኩት አለ ...
 ||"قلت له فكيف بمن رآك بين الصفين فقال هذا مسلم بن يسار لن يقاتل إلا على حق فقاتل حتى قتل"||
"ታዲያ መዋጋቱንስ አልተዋጋህም ይባል አንተን በሁለቱ የጦር ሰልፎች መካከል ላይ ያየ 'ይህኮ ሙስሊም ኢብኑ የሳር ነው እሱ የሚዋጋው ሀቅ ላይ ቢሆን እንጂ ለሌላ አይደለም' ብሎ አንተን ተከትሎ ተጋድሎ የሞተ ሰውንስ አስመልክቶ እንዴት ታደርጋለህ?" አላቸው።
ይህን ሲላቸው ሙስሊም ኢብኑ የሳር አለቀሱ ...
||"فبكى والله حتى وددت أن الأرض انشقت فدخلت فيها"||
"በጣም አለቀሰ፤ ከማልቀሱ የተነሳ ምድር ተሰንጥቃ ውስጥ ብገባ ወይም ብትውጠኝ ተመኘሁኝ" አለ። ማለት ሙስሊም ኢብኑ የሳር - ረሂመሁላህ - በጣም ከመፀፀታቸው የተነሳ በዚህ መልኩ ሲያለቅሱ ለምን ይህን ተናገርኩኝ ብዬ ተቆጨሁኝ ማለቱ ነው። ይህ ክስተት አልቡኻሪ 'ታሪኹል ከቢር' በተሰኘው መፅሀፋቸው እንዲሁም ኢብኑ ዓሳኪር እና አልፈሰዊ "ፊል ኪታብ አልመእሪፈቲ ወታሪኽ" ያሰፈሩት ነው። ]]]
∞∞∞∞≅≅≅≅∞∞∞∞

ድምጽ ፋይሉን ለማውረድ 

መጠን 5 Mb - ርዝመት 20 ደቂቃ - ፎርማት mp3
Download Link
↓↓↓
  አውርድ(Download)
ወይም
  አውርድ (Download)

መፍቻ፦
[[[ ]]] ...... የሸይኽ ኢልያስ ንግግር መነሻና ማብቂያ
{ }    .... የቁርአን አንቀጽ በዐረበኛ
[| |]   .... የቁርአን አንቀፅ አማርኛ ትርጉም
| |     .... ዓረብኛ ቃል በዓረበኛ ሲፃፍ
" "    .... ዓረብኛ ቃል በአማርኛ ሲፃፍ
||"  "||  .... የሶሓቦች ንግግር
( )  ..... ወደ ፅሁፍ የገለበጠው ሰው ጭማሪ
===========================
 ? ድምጹን ወደ ጽሁፍ የገለበጠው :- ወንድም አሕመድ የሕያ

Post a Comment

0 Comments